1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ፥ መስከረም 10 ቀን 2008 ዓ.ም.

ሰኞ፣ መስከረም 10 2008

ማንቸስተር ሲቲ በሜዳውና በደጋፊዎቹ ፊት የመጀመሪያ ሽንፈቱን ቀምሷል። ማንቸስተር ሲቲን ጉድ ያደረጉት አፍሪቃውያን ተጨዋቾች ናቸው። በቅዳሜው ጨዋታ አርሰናል ለዋነኛ ተቀናቃኙ ቸልሲ እጅ ሰጥቷል። ሊቨርፑል ማሸነፍ ተስኖት፤ ዳግም አቻ ወጥቷል።

https://p.dw.com/p/1Ga3b
Fußball Bundesliga SV Darmstadt 98 - FC Bayern München
ምስል Getty Images/D. Roland

የስፖርት ዘገባ፥ መስከረም 10 ቀን 2008 ዓ.ም

በጀርመን ቡንደስሊጋ በዜሮ ነጥብ ከታች የሚዳክረው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ አሠልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬስ የሥራ መልቀቂያ አስገብተዋል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዘንድሮ በአዲሱ አሠልጣኝ አይበገሬነቱን እያስመሰከረ ነው። ሊዮኔል ሜሲ ፍፁም ቅጣት ምት ስቷል። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ለክብር-ወሰን እየገሰገሰ ነው፤ ግን ግብ ሳያስቆጥር ወጥቷል።

ናይጀሪያዊው ቪክቶር ሞስስ እና ሴኔጋላዊው ዲያፍራ ሳክሆ በእርግጥም የማንቸስተር ሲቲ ተጨዋቾችና ደጋፊዎች መስማት የማይፈልጓቸው ስሞች ናቸው። ሁለቱ አፍሪቃውያን ተጨዋቾች በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲን አንገት ያስደፉ የዌስትሐም ዩናይትድ የቁርጥ ቀን ልጆች ተብለዋል።

በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አልበገርም ብሎ ሲገሰግስ የነበረውን ማንቸስተር ሲቲን በስድስተኛ ጨዋታው፤ ስድስተኛ ደቂቃ ላይ ልጓሙን የገታው ናይጀሪያዊው ቪክቶር ሞስስ ነበር። በቀኝ በኩል ያገኛትን ኳስ ሳይጠበቅ መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት ከመረብ ሲያሳርፍ ተጨዋቾቹን ብቻ ሳይሆን ጨዋታውን ሲዘግብ የነበረውን ጋዜጠኛም አስበርግጓል። ማንቸስተር ሲቲዎች ከብርጋጌያቸው ሳይወጡ በ31ኛው ደቂቃ ላይ የሴኔጋሉ ዲያፍራ ሳክሆ ከቀኝ ማዕዘን የተላከለትን ኳስ ሁለተኛ ግብ አድርጎ አደንዝዟቸዋል።

የማንቸስተር ሲቲው ሠርጂዮ አጉዌሮ ግብ ለማስቆጠር ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች መክነው ቀርተዋል። በእርግጥም አርጀንቲናዊው አጥቂ ቀኑ አልነበረም፤ ጭንቅላቱን ከመነቅነቅ ባለፈ ምንም ማድረግ ተስኖት አምሽቷል። ማንቸስተር ሲቲ በባዶ ከመውጣት ያዳነችውን ግብ ያገኘው በ47ኛው ደቂቃ ላይ በ ኬቪን ዴብሬዌይና ነው።

ሌላኛው አፍሪቃዊ የናይጄሪያው ኦዲዮን ኢጋሎ ዋትፎርድ ቅዳሜ ዕለት ኒውካስትልን 2 ለ1 በሸኘበት ጨዋታ ግብ አስቆጥሯል። በተመሳሳይ ቀን ከስቶክ ሲቲ ጋር ተጋጥሞ ሁለት እኩል አቻ የተለያየው ላይስተር ሲቲ የመጀመሪያዋን ግብ በ51ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው በአልጀሪያዊው ሪያድ ማህሬዝ ነበር። የአፍሪቃውያን ሣምንት ማለት ይቻላል።

ስዋንሲ ሲቲ እና ኤቨርተን ያለግብ ተለያይተዋል። ዘንድሮ ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ያደገው በርንማውስ ሰንደርላንድን 2 ለምንም በመርታት ሦስት ነጥብ አግኝቷል። አስቶን ቪላ በዌስት ብሮሚች አልቢኖ አንድ ለምንም ተሸንፏል። በቸልሲ 2 ለባዶ የተረታው አርሰናል ሦስት ነጥብ ጥሎ በመሪው ማንቸስተር ሲቲ በአምስት ነጥብ ርቀት ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ሲቲ 15 ነጥብ ሰብስቧል። የአርሰናሉ ጋብሪየል ፓውሊስታ በመጀመሪያው አጋማሽ የባከነ ሰአት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ጋብሪየል ከሜዳ የተሰናበተው እግሩን ወደኋላ ሰንዝሮ በመራገጡ ነው። በ79ኛው ደቂቃ ላይ ሌላኛው የአርሰናል ተጨዋች ሳንቲ ክዞላ መሬት ለመሬት በመንሸራተት መጥፎ አገባብ በመግባቱ ከሜዳ በቀይ ተባሯል። ሳንቲ ክዞላ ጥፋቱን አምኖ ሲወጣ ጋብሪየል ፓውሊስታ ግን አላስፈላጊ ንትርክ እና ግብግብ ለመግጠም ሲሞክር ታይቷል።

እሁድ በተደረጉ ጨዋታዎች ቶትንሀም ሆትስፐር ክሪስታል ፓላስ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ማሸነፍ ችሏል። ሊቨርፑል ከኖርዊች ሲቲ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ዳኒ ኢንግስ ለሊቨርፑል እና ለራሱ ብቸኛዋን ግብ በ48ኛው ደቂቃ ላይ ሲያስቆጥር ለኖርዊች በ61ኛው ደቂቃ ላይ ሩሴል ማርቲን አቻ የምታደርገውን ኳስ ከመረብ አሳርፏል።

ማንቸስተር ዩናይትድ በ34ኛው እና 50ኛው ደቂቃ ላይ በአንቶኒ ማርሲያል እንዲሁም በ68ኛው ደቂቃ ላይ በጆን ማታ ባስቆጠራቸው ሦስት ግቦች ሳውዝሐምፕተንን አሸንፏል። ሳውዝሐምፕተን የማታ ማታ ሽንፈትን ቀመሰ እንጂ በ13ኛው ደቂቃ ላይ በጋርሲያኖ ፔሌ ባስቆጠረው ግብ ሲመራ ነበር። በ86ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛዋንም ግብ ያስቆጠረው ጋርሲያኖ ፔሌ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ በትናንቱ ድል ከማንቸስተር ሲቲ ጋር የነጥብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ዝቅ ማድረግ ችሏል፤ 13 ነጥብ አለው። ዌስትሐም ዩናይትድ በ12 ይከተላል። ።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የሳምንቱ ማሳረጊያ ግጥሚያዎች ቦሩስያ ዶርትሙንድ በግስጋሴው ሲቀጥል፤ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ አሠልጣኙን አጥቷል። የቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ አሠልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬስ ትናንት ድንገተኛ የሥራ መልቀቂያ አስገብተዋል። አሠልጣኙ መልቀቂያ ያስገቡት ቡድናቸው በተደጋጋሚ የደረሰበትን ሽንፈት ተከትሎ ነው። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ የውድድር ዘመኑ ከተጀመረ አንስቶ የተከናወኑ አምስቱንም ጨዋታዎች ያጠናቀቁው በሽንፈት ነው። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ትናንት በኮሎኝ 1 ለ0 መሸነፉን ተከትሎ አሰልጣኙ በሰጡት መግለጫ ከአራት ዓመት አገልግሎት በኋላ ማረፍ መፈለጋቸውን ገልጠዋል።

አሠልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬስ ባለፈው የውድድር ዘመን ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በቡንደስ ሊጋው ሦስተኛ ሆኖ እንዲጨርስ በማስቻላቸው ይወደሱ ነበር። ቡድናቸው የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ እንዲሆንም ማድረጉ ተሳክቶላቸዋል። በቡንደስ ሊጋው ግን ዘንድሮ ማሸነፍ ተስኗቸው፥ በዜሮ ነጥብ በደረጃ ሠንጠረዡ 18ኛ ላይ ተንሳፈዋል።

የአሠልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬስ ድንገተኛ ስንብትን ተከትሎ ቡድኑን ማን ያሰልጥነው የሚለው ጥያቄ ደጋፊዎችን አስጨንቋል። በተደጋጋሚ ሽንፈት ራሳቸውን ከአሠልጣኝነት ያሰናበቱት የቀድሞው የቦሩስያ ዶርትሙንድ አሠልጣኝ ዬርገን ክሎፐ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጭምጭምታ እየተሰማ ነው። ሆኖም ዬርገን ክሎፐ የቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ አሠልጣኝ ሊሆኑ ነው መባሉን በወኪላቸው በኩል አስተባብለዋል።

ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር እኩል 15 ነጥብ ይዞ በግብ ልዩነት ብቻ በደረጃ ሠንጠረዡ ሁለተኛ የሆነው ባየር ሙይንሽን ትናንት ዳርምሽታድትን 3 ለዜሮ አሸንፏል። ዳርምሽታድት ዘንድሮ ከታች ወደ ቡንደስሊጋው ያደገ ቡድን ነው። የዳርምሽታድቱ አጥቂ ማርሴል ሔለር በባየርን ሙይንሽን መሸነፋቸው ብዙም እንዳላስቆጨው ተንግሯል።

«ዛሬ ከባየርን ጋር ያደረግነው ጨዋታ ግልጽ ነው፤ ከዓለማችን እጅግ ጠንካራው ቡድን ጋር የተደረገ ጨዋታ ነው። ያን መቋቋም በእርግጥም ይከብዳል። ባየርኖች ኳሷን ምን ያህል በአስተማማኝ መልኩ እንደተቆጣጠሯትና ያገኙትን ዕድል በሚገባ እንደተጠቀሙበት ማየት ይቻላል። ግን እኛም ብንሆን ጨዋታውን ተቋቁመን እንደውም በሁለተኛው አጋማሽ ኳሷን በቁጥጥራችን ስር ማድረግ ተሳክቶልን ነበር። መቼም ብንሸነፍም አያስቆጭም።»

ማርሴል ሔለር ከጨዋታው ቀደም ሲል የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ እንደሚሞክሩ ጠቅሶ ነበር። «የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን፤ እናም የሚሆነውን ማየት ነው። ባናሸንፍ የምንራጨው እንባ አይኖርም» ሲል አስቀድሞ የማፅናኛ ንግግሩን አድርጎ ነበር። በእርግጥም ቡድኑ ዳርምሽታድት እስከ 20ኛው ደቂቃ ድረስ ግብ ሳይቆጠርበት መቆየት ችሎ ነበር። በ20ኛው ደቂቃ ግን አርቱር ቪዳል የመጀመሪያዋን ግብ አስቆጥሮባቸዋል። ከዚያም በ62ኛው ኪንግስሌይ ኮማን እንዲሁም በ63ኛው ደቂቃ ሰባስቲያን ሮደ በተከታታይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል።

እስካሁን ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በሰፋ የግብ ልዩነት ማሸነፍ የቻለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት ባየር ሌቨርኩሰንን 3 ለ0 ድል አድርጓል። ሐኖቨርን በአውስቡርግ 2 ለባዶ ተሸንፏል። ሽቱትጋርትን 1 ለዜሮ ያሸነፈው ቡድን ሻልከ አሠልጣኝ አንድሬ ብራይተንራይተር ባገኙት ድል እጅግ ተደስተዋል።

«የዛሬው ድል እጅግ የሚያስደስት ነው። እጅግ ድንቅ የሆነችዋን ብቸኛዋን ግብ አስቆጥሮ ያስፈነደቀን ራልፍ ፌይርማንን እናመሠግናለን። ሽቱትጋርቶች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የማጥቃት ስልታቸው ጠንካራ እና የሚያዝናና ነበር። ጨዋታቸው እስካሁን አንዳችም ነጥብ መያዝ እንዳልቻለ ቡድን አዓይነት አልነበረም። ዕድላቸውን በሚገባ ቢጠቀሙበት ኖሮ ስኬታማ በሆኑ ነበር።»


ማክሰኞ መስከረም 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ማት ከሚከናወኑ የቡንደስ ሊጋ ጨዋታዎች መካከል ባየር ሙይንሽን ከቮልፍስቡርግ የሚያደርጉት ይጠበቃል።

የጀርመን የሴቶች እግር ኳስ ቡድን የአውሮጳ ማጣሪያ እና የኦሎምፒክ ዝግጅታቸውን በግብ ተንበሽብሸው ነው የጀመሩት። ጀርመኖች ዐርብ እለት የሐንጋሪ ቡድንን የግብ ጎተራ አድርገው ሸኝተዋል። ከዚህ ቀደም 7 ለዜሮ የተሸነፈው የሐንጋሪ ቡድን ደርዘን ግቦች ሲቆጠርበት ማስተዛዘኛ አንዲት ግብ እንኳን ማስቆጠር ተስኖታል። ጀርመን ሐንጋሪን እጅግ አሸማቃቂ በሆነ የ12 ለባዶ ሽንፈት ነው የሸኘችው። ውድድሩን 4500 ግድም ተመልካቾች ታድመው ተከታትለዋል።
በስፔን ላሊጋ አርጀንቲናዊው የኳስ ጠቢብ ሊዮኔል ሜሲ ቡድኑ ባርሴሎና ትናንት ከሌቫንቴ ባደረገው ጨዋታ ፍፁም ቅጣት ምት ስቷል። ሆኖም ባርሴሎና ሌቫንቴን 4 ለ1 ሲረታ ሁለቱን ግቦች ከመረብ ያሳረፈው ይኸው ሊዮኔል ሜሲ ነው። ባርሴሎና አራት ጨዋታዎችን በመደዳ ማሸነፍ ችሏል።

ለባርሴሎና የመጀመሪያዋን ግብ በ50ኛ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ማርክ ባርትራ ነበር። ስድስት ደቂቃ ዘግየት ብሎ ኔይማር ሁለተኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል። ሊዮኔል ሜሲ በ61ኛው ደቂቃ ሦስተኛዋን ግብ፤ እንዲሁም በ90ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት አራኛዋን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ለሌቫንቴ ቪክቶር ካሳዴስ በ66ኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን የማስተዛዘኛ ግብ አግብቷል።

የሪያል ማድሪዱ ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በራውል ጎንዛሌዝ ብላንኮ ተይዞ የቆየውን 323 ግብ የማስቆጠር ክብርወሰን ለመስበር ቅዳሜ ዕለት ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት ቀርቷል። ቡድኑ ሪያል ማድሪድ ግን በ54ኛው ደቂቃ ላይ ቤንዜማ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ግራናዳን 1 ለባዶ ማሸነፍ ተሳክቶለታል። የቀድሞው የስፔን አጥቂ ራውል ጎንዛሌዝ ብላንኮ በዓለማችን እጅግ ሀብታም ለሆነው ቡድን 741 ጊዜ ተሰልፎ 321 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ተጨዋች ነው። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ከ400 በላይ ጨዋታዎች አድርጎ ራውል ላይ ሊደርስበት የቀረው ሁለት ግቦች ብቻ ናቸው።

በጣሊያን ሴሪኣ ኢንተር ሚላን ቺዬቮን 1 ለምንም ሸኝቷል። የአራት ጊዜ የሴሪኣው ባለድል ጁቬንቱስ በ10 ተጨዋቾች የተወሰነው ጌኖዋን 2 ለምንም አሸንፏል።

በሜዳ ቴኒስ የሴቶች ውድድር እጅግ ታዋቂ የሆነችው ማሪያ ሻራኮቫ ከደረሰባት የእግር አደጋ አገግማ ለሚቀጥለው ሳምንት የውሃን ግጥሚያ ብቁ እንደሆነች ተገልጧል። ማሪያ ሻራኮቫ በደረሰባት ጉዳት የተነሳ ከሴሬና ዊሊያምስ እና ሲሞና ሐሌፕ ቀጥላ ሦስተና ደረጃ ላይ ትገኛለች። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠr በ2014 የቤጂንግ ውድድር አሸናፊ መሆኗም ይታወቃል።

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የፌራሪ አሽከርካሪው ጀርመናዊው ሰባስቲያን ቬትል የሲንጋፖር አሸናፊ ሆኗል። የሬድ ቡሉ አሽከርካሪ ዳኒኤል ሪካርዶ ሁለተኛ ኪም ራይኮነን በፌራሪ ሦስተኛ ወጥተዋል። የዓለም ሻምፒዮናው እና የመርሴዲስ አሽከርካሪው ልዊስ ሀሚልተን በ32ኛው ዙር መኪናው በገጠማት የሞተር ብልሽት ከውድድሩ አቋርጦ መውጣት ተገዶዋል። ሌላው የመርሴዲስ አሽከርካሪው ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ በአራተኛነት አጠናቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

የሲንጋፑር የመኪና ሽቅድምድም አሸናፊ ሠባስቲያን ቬተል
የሲንጋፑር የመኪና ሽቅድምድም አሸናፊ ሠባስቲያን ቬተልምስል Reuters/T. Chong
የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ
የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲምስል K. Kudryavtsev/AFP/Getty Images
Fußball Championsleague Halbfinale Rückspiel FC Bayern München FC Barcelona Symbolbild Barcelona am Ball
ምስል picture-alliance/dpa/MiS
ተሰናባቹ የቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ አሠልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬስ
ተሰናባቹ የቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ አሠልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬስምስል Getty Images
ማንቸስተር ዩናይትድ
ማንቸስተር ዩናይትድምስል Getty Images/D. Mouhtaropoulos
ማንቸስተር ሲቲ
ማንቸስተር ሲቲምስል Reuters/C. Recine Livepic

አርያም ተክሌ