1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ፤ ሚያዝያ 5 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሚያዝያ 5 2007

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎች የደረሰው ድልድል ከ30ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ አንፃር ጠንካራ የማይባል ነው። ኢትዮጵያውያን ሯጮች ከረዥምና መካከለኛ ርቀት ወደ ማራቶን ውድድሮች ማተኮራቸው ለምን? ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የውድድር መድረኮች በማራቶን የሩጫ ውድድር ተደጋጋሚ አመርቂ ውጤቶችን እያገኙ ነው።

https://p.dw.com/p/1F7Il
Paris, Marathon
ምስል H. Tiruneh

በሣምንቱ መገባደጃ ላይ ብቻ በፓሪስ፣ ሮተርዳም እና ቪዬና የማራቶን ሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያኑ ኃያል ተፎካካሪ ከመሆንም በላይ ተደራራቢ ድሎችን አስመዝግበዋል። ለመሆኑ አትሌቶቻችን ከረዥም እና መካከለኛ ርቀት ወደ ማራቶን ሩጫ ማተኮራቸው ምክንያቱ ምንድን ነው? በሌሎቹ የሩጫ ዘርፎችስ ምን አይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል? በአትሌቲክስ ዙሪያ የሚያተኩር የስፖርት ጋዜጠኛ አነጋግረናል። ኢትዮጵያ ለአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ማጣሪያ ዘንድሮ የተደለደለችበት ምድብ ቀላል በመሆኑ የግድ ማለፍ አለብን የሚል ታዋቂ የስፖርት ተንታኝንም አነጋግረናል። በሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ፍልሚያ ነገ ሪያል ማድሪድ ጠንካራ ተፎካካሪ ይገጥመዋል። የጣሊያኑ ጁቬንቱስ ከፈረንሣይ ቡድን ጋር ይገናኛል። ሊቨርፑል ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ አለው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር በ2017 ጋቦን እንድታሰናዳው ዕቅድ በተያዘለት 31ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ የተደለደለበት ምድብ ይፋ ሆኗል። ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ አልጀሪያ ጠንካራ ቡድን ስትሆን ሌሎቹ ሁለት ቡድኖች ግን በእግር ኳሱ ዓለም ከኢትዮጵያ ያነሰ ልምድ እና ደረጃ ያላቸው ናቸው። ኹለቱ ቡድኖች ንዑሳኑ ሌሶቶ እና ሲሸልስ ናቸው።

ደቡብ አፍሪቃዊቷ ንዑስ ሀገር ሌሶቶ
ደቡብ አፍሪቃዊቷ ንዑስ ሀገር ሌሶቶ

ሀገር ውስጥ ብቻ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ማሰለፍ በሚፈቀድበት ቻን በተሰኘው ሌላኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ግጥሚያ ማጣሪያ ኢትዮጵያ የደረሳት ከጎረቤት ኬንያ ጋር ነው። በእነዚህ ድልድሎች መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ዕድል ምን ይመስላል?በአዲስ ጉዳይ ጋዜጣ በምክትል ዋና አዘጋጅ እንዲሁም በተለያዩ የሬዲዮ ዝግጅቶች በዋና አዘጋጅነት እና አዘጋጅነት ያገለግል የነበረው ጋዜጠኛ ኢብራሒም ሻፊን በስካይፕ አነጋግረነዋል። በ31ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ጥሩ ኹለተኛ ሆነን ለማለፍ ካቀድን የመሳካት ዕድሉ ከፍተኛ ነው ሲል ተናግሯሏል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የወደፊት አሠልጣኝ ማንም ይሁን ማን ይኽን ዕድል በመጠቀም ድል የናፈቀውን የስፖርት አፍቃሪ ለማስደሰት 31ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ የተመቻቸ ይመስላል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ሆነ የስፖርት አፍቃሪያን በአጠቃላይ ይኽን ጉዳይ ከወዲሁ ትኩረት ሊሰጡበት ይገባል እንላለን።

እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር በሚቀጥለው ዓመት ማለትም በ2016 ሩዋንዳ በምታሰናዳውናየሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ብቻ እንዲጫወቱ በሚፈቀድበት 4ኛው የ CHAN ውድድር ኢትዮጵያ የምትጋጠመው ከኬንያ ቡድን ጋር ነው። የኬንያ ቡድን ጠንካራነቱ ውጪ ሃገራት ተሰልፈው በሚጫወቱ ተጨዋቾቹ በመሆኑ ኢትዮጵያ በዚህም ውድድር የማሸነፍ ዕድሏ ከፍተኛ መሆኑን ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ገልጧል።

የአልጄሪያ ቡድን እጎአ በ2014 FIFA የዓለም ዋንጫ ወቅት
የአልጄሪያ ቡድን እጎአ በ2014 FIFA የዓለም ዋንጫ ወቅትምስል K. Kudryavtseva/AFP/Getty Images

ከእግር ኳስ ወደ አትሌቲክስ ነው የምንሻገረው። ወደ በኋላ ላይ የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች እና የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ውጤቶችን እናሠማችኋለን። አሁን ወደ አትሌቲክስ ዜና እንሻገር።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሣምንቱ መገባደጃ በሦስት ዓለምአቀፋዊ የማራቶን ሩጫ ውድድሮች አሸናፊ ሆነዋል። በ39ኛውየፓሪስማራቶንትናትት ኢትዮጵያዊቷ መሠረት መንግሥቱ 2:23:26 በመግባት አንደኛ ወጥታለች፤ አማኔ ጎበና በአራት ሠከንዶች ልዩነት ኹለተኛ ወጥታለች። ኬኒያዊው ማርክ ኮሪ አሸናፊ ቦሆነበት የወንዶች ፉክክር ደግሞ ኢትዮጵያዊው ሠቦቃ ቶላ ሦስተኛ ለመውጣት ችሏል። በኦስትሪያ ቪዬና የማራቶን ሩጫ ውድድርም ኢትዮጵያዊው ሲሣይ ለማ፣ ሲራጅ ገናን አስከትሎ በ2:07:31አንደኛ ሆኗል። በሮተርዳም ማራቶንም አበራ ኩማ በ2:06.46 በመግባት በአንደኛነት ድል ተቀዳጅቷል። ለመሆኑ አትሌቶቻችን ከ5 ሺህ እና 10 ሺህ ውድድር እየወጡ ወደ ማራቶን የሩጫ ውድድር ያተኮሩት ለምንድን ነው? የሀትሪክ ጋዜጣ ም/ዋና አዘጋጅ እንዲሁም በሬዲዮ እና በጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እና አዘጋጅ የሆነውጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሠ የውድድር አዘጋጆቹ በማራቶን ላይ ማተኮራቸው እና አትሌቶቹ ከፍተኛ ክፍያ በሚገኝበት ውድድር ላይ ለመሳተፍ መምረጣቸው ወደ ማራቶን እንዲያዘነብሉ እንዳደረጋቸው ጠቅሷል።

የፓሪስ ማራቶን አሸናፊ አትሌት መሠረት መንግሥቱ
የፓሪስ ማራቶን አሸናፊ አትሌት መሠረት መንግሥቱምስል H. Tiruneh

ከቅርብ ጊዜ አንስቶ በማራቶን ያገኘናቸው ተደጋጋሚ ድሎች ባሉበት እንዲቀጥሉ የሚበረታታ ቢሆንም በሌሎች የውድድር ዘርፎች ላይም ከፍተኛ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ሳንጠቁም አናልፍም።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በደረጃ ሠንጠረዡ ሦስተኛነት የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ማንቸስተር ሲቲን 4 ለ2 በሆነ ሰፊ ልዩነት በማሸነፍ ድል ተቀዳጅቷል። ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት ያገኘው 3 ነጥብ ተደምሮለት አሁን 65 ነጥብ በመያዝ ከማንቸስተር ሲቲ በ4 ነጥብ ርቋል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው ከመሪው ቸልሲ ግን በ8 ነጥብ ዝቅ ብሎ ይገኛል። ቸልሲ ትናንት ኩዊንስ ፓርክን 1 ለባዶ በማሸነፍ ነጥቡን 73 አድርሶታል። በ54 ነጥቡ በ6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል 13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ኒውካስል ዩናይትድ ጋር ዛሬ ከጥቂት ሠዓታት በኋላ ይፋለማል። ሊቨርፑል ካሸነፈ 56 ነጥብ ካለው ሳውዝሀምፕተን በአንድ ነጥብ በመብለጥ ማንቸስተር ሲቲን በ4 ነጥብ ርቀት ይጠጋል ማለት ነው።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ትናንት ኮሎኝ ሆፈንሀይምን 3 ለ2 አሸንፏል። ቬርደር ብሬመን በሽቱትጋርት 3 ለ2 ተረትቷል። ከትናት በስትያ ፓዴርቦርን አውስቡርግን 2 ለ1 በማሸነፍ ከወራጅ ቀጣናው ጠርዝ እንደምንም ከፍ ብሏል።

Fußball Bundesliga 22. Spieltag SC Paderborn FC Bayern München
ምስል Lars Baron/Bongarts/Getty Images

ባየር ሙይንሽን እንደተለመደው አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 3 ለዜሮ ሸኝቷል። ቮልስፍስቡርግ ሐምቡርግን 2 ለምንም በማሸነፍ በደረጃ ሠንጠረዡ 60 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። ከመሪው ባየር ሙይንሽን ልዩነቱ የ10 ነጥብ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ አኹንም እዚያው 10ኛ ደረጃ ላይ እየታሸ ነው፤ 33 ነጥብ አለው ከትናንት በስትያ በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ 3 ለ1 ሽንፈት ቀምሷል።

ለሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ፍልሚያ ነገ ኹለቱ የስፔን ኃያሎች አትሌቲኮ ማድሪድ እና ሪያል ማድሪድ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል። ሪያል ማድረድ በስፔን ላሊጋ ከመሪው ባርሴሎና በ2 ነጥብ ዝቅ ብሎ በደረጃ ሠንጠረዡ በኹለተኛነት ነው የሚገኘው። ባርሴሎና 75 ነጥብ አለው። ነገ ለሻምፒዮንስ ሊግ የሚሰለፈው አትሌቲኮ ማድሪድ በላሊጋው በ66 ነጥብ ሦስተኛ ነው። በነገራችን ላይ በደረጃ ሠንጠረዡ 62 ነጥብ ይዞ 4ኛ የሆነው ቫለንሺያ በ28 ነጥብ 18ኛ ደረጃ ላይ የተወሰነው ሌቫንቴን ዛሬ ከሠዓታት በኋላ ያስተናግዳል።

አርሰናልን ከመንገድ ያስቀረው የፈረንሣዩ ሞናኮ እና የጣሊያኑ ጁቬንቱስ የሩብ ፍፃሜ ፍልሚያቸውን የሚያከናውኑት በነገው ዕለት ነው። ከነገ በስተያ የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙይንሽን ከፖርቺጊዙ ፖርቶ ጋር ይገናኛል። የፈረንሣዩ ፓሪስ ሴንጀርማን ከስፔኑ ባርሴሎና ጋር የሚፋለመው ረቡዕ ነው። ጨዋታዎቹ በሙሉ በጉጉት የሚጠበቁ ናቸው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ