1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ፤ ጳጉሜ 2ቀን፣ 2007 ዓ.ም

ሰኞ፣ ጳጉሜን 2 2007

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከንዑሷ ሲሸልስ ጋር ባደረገው ጨዋታ የተጠበቀውን ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም። ጀርመን ዛሬ ከስኮትላንድ ጋር ትጋጠማለች። የዊሊያምስ ልጆች እህትማማቾቹ ሴሬና ዊሊያምስ እና ቬኑስ ዊሊያምስ በሜዳ ቴኒስ ለሩብ ፍፃሜ ውድድር ቀጠሮ ተይዞላቸዋል። ኔዘርላንድ በቱርክ ከባድ ቅጣት ገጥሟታል።

https://p.dw.com/p/1GSRJ
UEFA Euro 2016 Qualifikation Türkei - Niederlande
ምስል Reuters/U. Bektas

የስፖርት ዘገባ፤ ጳጉሜ 2ቀን፣ 2007 ዓ.ም

የኢትዮጵያ እና የሲሸልስ ጨዋታን በጥንቃቄ የተከታተሉ ኹለት የስፖርት ጋዜጠኞችን አነጋግረናል። የቡድኑን ችግር ጠቁመው መፍትኄ ያመላክታሉ። 11ኛው የመላው አፍሪቃ ጨዋታዎች ፋክክር የዛሬ 50 ዓመት የመጀመሪያዎቹ ውድድሮች በተኪያሄዱበት ሪፐብሊክ ኮንጎ ብራዛቪል ውስጥ ተጀምሯል። በአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ያልተጠበቁ ውጤቶች ተስተናግደዋል። ጀርመን ዛሬ ከስኮትላንድ ጋር ትጋጠማለች። የዊሊያምስ ልጆች እህትማማቾቹ ሴሬና ዊሊያምስ እና ቬኑስ ዊሊያምስ በሜዳ ቴኒስ ለሩብ ፍፃሜ ውድድር ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።

የአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ውጤት እና ሌሎች ዘገባዎችን ከማሰማታችን በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከንዑሷ ሲሸልስ ጋር ነጥብ ተጋርቶ የወጣበትን ጨዋታ ለመቃኘት እንሞክራለን።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዘንድሮ የተደለደለበት ምድብ ውስጥ የሚገኙት ሲሸልስ እና ሌሶቶ የእግር ኳስ ደረጃቸው ከኢትዮጵያ ያነሱ ናቸው። ኢትዮጵያ ደረጃዋ 103 ሲሆን፤ ሲሸልስ 192ኛ ላይ ትገኛለች። ሌሶቶ ደግሞ 128ኛ ነው። ያም በመሆኑ ኢትዮጵያ ኹለቱን ቡድኖች በሜዳዋ እና ከሜዳዋ ውጪ በማሸነፍ በምትሰበስበው ነጥብ ማጣሪያውን የማለፍ እድል እንዳላት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለመግለጥ ተሞክሯል። ጋዜጠኛ ኢብራሒም ሻፊ ቅዳሜ ዕለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በትንሿ ሲሸልስ አንድ ለባዶ ሲመራ ቆይቶ አቻ በመውጣት ነጥብ መጋራቱ የሚያመለክተው ብዙ ነገር አለ ይላል።

የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ዓርማ
የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ዓርማ

በዓለም የእግር ኳስ ደረጃቸው ከፍተኛ ልዩነት ያላቸው ኢትዮጵያ እና ሲሸልስ በህዝብ ብዛትም ልዩነታቸው የሰማይ እና የምድር ነው። ከ90 ሚሊዮን በላይ ነዋሪ ካላት ኢትዮጵያ አንፃር ስትታይ 90ሺህ ነዋሪ ያላት ሲሸልስ ከመላ ነዋሪዋ ሦስት ሺህ ያኽል ተጨዋች እንዳላት ይገመታል። ጋዜጠኛ ማርቆስ ኤሊያስ የሕዝብ ብዛት በአግባቡ ካልተጠቀሙበት ከቁጥር በላይ ፋይዳ የለውም ይላል። በብሥራት 101.1 የስፖርት ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ ነው፤ ውድድሩን በቦታው ተገኝቶ ሲዘግብ ነበር።

ጋዜጠኛ ኢብራሂም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ደካማ ውጤት ከአስተዳደሩ እና ከፌዴሬሽኑ መዋቅር ባሻገር የአሰልጣኙ ብቃት እና ከተጨዋቾች ጋር ያላቸው ግንኙነት ጥያቄ ያስነሳል ይላል።

ጋዜጠኛ ማርቆስ ኤልያስ በበኩሉ «በምንከተለው በጣም የተጣመመ አሠራር ለራሳችን ከፍተኛ ግምት ከመስጠት ባለፈ ተጨባጩ እውነታ ግን እንደዚህ እንድናስብ፤ በጣም ተስፋ እንድናደርግ የሚያደርገን አይደለም» ይላል። ለዚህ ደግሞ መፍትኄ የሚለውን ይተነትናል።

ብሔራዊ ቡድኑ ዘላቂ ለውጥ ለማግኘት የረዥም ጊዜ ሥራ ይጠብቀዋል። ሆኖም ኢትዮጵያ ከሲሸል በቀላሉ ነጥብ ልታገኝ ትችላለች ተብሎ የነበረው ግምት መምከኑን ተከትሎ ለአፍሪቃ ዋንጫ ለማለፍ በአጭር ጊዜ ምን መደረግ አለበት? ኢብራሂም የመፍትኄ ሐሳብ አለው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎችምስል DW/H. Turuneh

እንግዲህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደፊት የማለፍ ዕድሉን ለማስፋት የተሰጡትን ትንታኔዎች እና የመፍትኄ ሐሳቦች የሚመለከታቸው አካላት አጢነው ተግባራዊ እንደሚያደርጉት ተስፋ እናደርጋለን።

የመላው አፍሪቃ ጨዋታዎች ኮንጎ ብራዛቪል ውስጥ ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ላይ ተጀምሯል። አምሳኛ ዓመቱን የያዘው ውድድር የሚከናወነው የመጀመሪያ ዓመት ውድድር በተኪያሄደበት የኮንጎ ሪፐብሊክ ውስጥ ነው። ለኹለት ሳምንት በሚዘልቀው ውድድር 54 የአፍሪቃ ሃገራት በውድድሩ ይሳተፋሉ ተብሏል። የኮንጎ ሪፐብሊክ ይኽን ውድድር ለማከናወን የገነባቸው አዲስ የስፖርት መወዳደሪያስፍራዎቹ 900 ሚሊዮን ዶላር ግድም ያወጣሉ ተብሏል። የመላው አፍሪቃ ጨዋታዎች በኮንጎ ሪፐብሊክ ብራዛቪል ውስጥ የተከፈተው ቅዳሜ እለት ነው። የአህጉሪቱ 8,000 ያኽል አትሌቶች በኹለት የተለያዩ የመወዳደሪያ ስፍራዎች በ20 የተለያዩ የአትሌቲክስ ዘርፎች እንደሚፎካከሩ ተገልጧል።

ስፔን እንግሊዝን ለወዳጅነት ጨዋታ ልትጋብዛት እንደምትችል አስታውቃለች። ስፔን እንግሊዝን ኅዳር 3 ቀን 2008 ዓም ለወዳጅነት ጨዋታ ልትጋብዛት የምትችለው ፈረንሣይ ውስጥ ለሚከናወነው የአውሮጳ ዋንጫ ጨዋታ ማጣሪያውን ካለፈች እንደሆነ ጠቅሳለች። ስፔን የምትገኝበትን ምድብ እየመራች ነው።

ከየምድቡ ከፍተኛ ነጥብ ያላቸው ኹለት ቡድኖች ናቸው ማጣሪያውን አልፈው ለአውሮጳ ዋንጫ መሳተፍ የሚችሉት። እንግሊዝ ቅዳሜ እለት ሳን ማሪኖን 6 ለ0 በመርታት ማጣሪያውን ማለፏን አረጋግጣለች። በእለቱ ዋይኔ ሩኒ በዓለም አቀፍ ውድድር 49ኛ ግቡን ከመረብ አሳርፏል። በዚህ ግቡም እስካሁን ተይዞ ከቆየው የቦቢ ቻርልተን ክብር ወሰን ጋር መስተካከል ችሏል። የእንግሊዝ ቡድን ለፈረንሳዩ የአውሮጳ ዋንጫ ዝግጅት ከፓሪስ 38 ኪሊ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሻንቲል ከተማ በመስፈር ልምምዱን እዛው እንደሚያኪያሂድ አሰልጣኙ ዛሬ ይፋ አድርገዋል።

የብሪታንያው ዋይኔ ሩኒ
የብሪታንያው ዋይኔ ሩኒምስል Reuters/C. Recine

የማንቸስተር ዩናይትዱ አማካይ ሚካኤል ካሪክ ባቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት የተነሳ እንግሊዝ ለአውሮጳ ዋንጫ ማጣሪያ ነገ ከስዊዘርላንድ ጋር በምታደርገው ጨዋታ መሰለፍ እንደማይችል አሰልጣኝ ሮይ ሆድግሰን ዛሬ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ሚካኤል ካሪክ ቡድኑ ማንቸስተር ዩናይትድ የፊታችን ቅዳሜ ከሊቨርፑል ጋር ለሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታም እንደማይደርስ ተገልጧል።

በነገው እለት ከሚኪያሄዱ ጨዋታዎች መካከል ስፔን ከመቄዶኒያ ጋር የምታደርገው ስዊድን ከኦስትሪያ ጋር የምታከናውነው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ። ዩክሬን ከስሎቫኪያ፣ ቤላሩስ ከሉግዘምቡርግ፣ ሊቱዋንያ ከሳን ማሪኖ፣ ስሎቫኒያ ከኢስቶኒያ፣ ሩስያ ከሊሽተንሽታይን እንዲሁም ማልዶቫ ከሞንቴኔግሮ ጋር ይጋጠማሉ።

ቅዳሜ እለት ስፔን ስሎቫኪያን 2 ለ0 እንዲሁም ዩክሬን ቤላሩስን 3 ለ1 ረትተዋል። ሉክዘምቡርግ መቄዶንያን 1 ለባዶ አሸንፋለች። ትናንት ከተከናወኑ በርካታ የማጣሪያ ጨዋታዎች መካከል ቱርክ ኔዘርላንድን የረታችበት ውጤት አስገራሚው ነበር። ቱርክ ኔዘርላንድን 3 ለ0 ነበር የሸኘችው። ኖርዌይ ክሮሺያን 2 ለባዶ፣ ጣሊያን ቡልጋሪያን 1 ለምንም ረትተዋል። ቤልጂየም ሳይፕረስን 1 ለ0፣ ቼክ ሪፐብሊክ ላቲቪያን 2 ለ1 እንዲሁም ቦስኒያ ሔርዜጎቬንያ አንዶራን 3 ለባዶ ድል በማድረግ ነጥብ ሰብስበዋል። ማልታ ከአዘርባጃን ኹለት እኩል ተለያይተዋል። እንደ ቼክ ሪፐብሊክ ማለፏን ያረጋገጠችው አይስላንድ ከካዛክስታን እንዲሁም ዌልስ ከእስራኤል ያለምንም ግብ ተለያይተዋል።

በሜዳ ቴኒስ ውድድር የዓለማችን ቁጥር አንድ ተጨዋች የሆነችው አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስ በዩናይትድ ስቴትስ የሜዳ ቴኒስ ፉክክር ለሩብ ፍፃሜ ከታላቅ እህቷ ቬኑስ ዊሊያምስ ጋር ነገ ትጋጠማለች። የ33 ዓመቷ ሴሬና እና በኹለት ዓመት የምትበልጣት እህቷ ቬኑስ ነገ ሲገናኙ ለ27ኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በበዩናይትድ ስቴትስ የሜዳ ቴኒስ ለሩብ ፍፃሜ ውድድር ሲገናኙ ደግሞ ለአምስተኛ ጊዜያቸው ነው።

ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ሴሬኔና ዊሊያምስ
ቁጥር አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ሴሬኔና ዊሊያምስምስል Getty Images/A. Goodlett

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2001 ዓም ፍፃሜውን 6:2, እና 6:4ያሸነፈችው በዕድሜም በቁመትም የምትበልጠዋ ቬኑስ ነበረች። ኹለቱ እህትማማቾች አንድ ዓመት ዘግየት ብሎ ባደረጉት ፍልሚያ ታናሺቱ ሴሬና ታላቋን 6:4, እና 6:3. በሆነ ውጤት ልትበቀላት ችላለች። በ2005 በተከናወነው የሩብ ፍፃሜ ዳግም ተገናኝተው ተራው የታላቅዬው የቬኑስ መሆን ችሎ ነበር። 7:6 (7:5) እና 6:2ነበር ሴሬናን ያሸነፈቻት። በ2008 ደግሞ ድሉ ወደ ሴሬና ዞረና ቬኑስን 6:3እና6:4መርታት ችላለች።

1,75 ሜትር ርዝማኔ ያላት ሴሬና ዊሊያምስ በታላቋ ቬኑስ ዊሊያምስ በ10 ሴንቲሜትር ትበለጣለች። በዓለም የሜዳ ቴኒስ ደረጃ ግን የአንደኛነቱን ስፍራ ሴሬና ነው የተቆናጠጠችው። ቬኑስ 23ኛ ናት። ኹለቱም እህትማማቾች በሜዳ ቴኒስ ውድድር በሚሊዮናት የሚቆጠሩ ዶላሮችን መሸለምችለዋል። ሴሬና እስካሁን ባደረገቻቸው ውድድሮች ድልን በመቀዳጀት የ73,3 ሚሊዮን ዶላር ተሸላሚ ልትሆን ችላለች። ቬኑስ በበኩሏ እስካሁን የ31,0 ሚሊዮ ዶላር ተሸላሚ ናት። ነገ የሚከናወነው የዩናይትድ ስቴትስ የሜዳ ቴኒስ የሩብ ፍጻሜ ውድድር በበርካታ የሜዳ ቴኒስ አፍቃሪዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ነው። የነገው ውድድር ከታላላቆቹ የአውስትራሊያ እና የፈረንሳይ እንዲሁም የዊምብልደን የሜዳ ቴኒስ ፍፃሜ ውድድሮች አራተኛው ሲሆን፤ ከሁሉም መጨረሻ ላይ የሚከናወን ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ