1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 7 2004

28ኛው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በፊታችን ቅዳሜ ይጀመራል። እግር ኳስ በዚህ በአውሮፓም እንደተለመደው የሣምንቱ ዓበይት ስፖርት ሆኖ ነው ያለፈው። ባለፈው ሰንበት ከሂዩስተን እስከ ሙምባይ የኢትዮጵያ አትሌቶች በስኬት የተሳተፉባቸው የማራቶን ሩጫ ውድድሮችም ተካሂደው ነበር።

https://p.dw.com/p/13kUN
ምስል dapd

የዘንድሮው የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊጀመር የቀሩት አምሥት ቀናት ብቻ ናቸው። በአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን አማካይነት የሚዘጋጀውን ውድድር በጋራ የሚያስተናግዱት ኤኩዋቶሪይ ጊኒና ጋቡን ሲሆኑ ለዚህ የበቁትም ናይጄሪያን በፉክክር በማሸነፍ ነው። ውድድሩ በአራት አስተናጋጅ ከተሞች በሚገኙ ስታዲዮሞች ውስጥ ሲካሄድ ይሰነብታል። አንጎላ ያለፈውን የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ስታስተናግድ ሊቢያ ደግሞ የመጪው ዓመት አዘጋጅ ናት። የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮኔደሬሺን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሶሥቱን ተከታታይ ውድድሮች አዘጋጆች በአንድ ጊዜ መሰየሙ አይዘነጋም። በየሁለት ዓመቱ ሲካሄድ የቆየው ውድድር በሚቀጥለው ዓመት ቀድሞ የሚደረገውም የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ከዓለም ዋንጫ እንዳይገጥም ለውጥ በማስፈለጉ ነው። ከ 2013 በኋላ ግን በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ይሆናል።

የዘንድሮው ፍጻሜ ውድድር በአራት ምድቦች ተከፍሎ የሚጀምር ሲሆን በምድብ-አንድ ውስጥ በፊታችን ቅዳሜ ከኤኩዋቶሪያል ጊኒ ጋር ውድድሩን የምትከፍተው ሊቢያ ናት። ሤኔጋልና ዛምቢያም የተቀሩት የዚሁ ምድብ ተሳታፊዎች ሲሆኑ ፉክክሩ ለአስተናጋጇ አገር ለኤኩዋቶሪያል ጊኒ ገና ከጅምሩ ቀላል የሚሆን አይመስልም። በምድብ-ሁለት ውስጥ አይቮሪ ኮስት፣ ሱዳን፣ ቡርኪና ፋሶና አንጎላ በአንድ የተሰለፉ ሲሆን ይህም ፈታኝ ምድብ መሆኑ የማይቀር ነው። በስም ከሆነ አይቮሪ ኮስት ዙሩን በልዕልና ለመፈጸም የላቀው ዕድል የሚሰጣት ናት። ግን አንጎላም ሆነች ሌሎቹ በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። ምድብ-ሶሥት ውስጥ ሁለተኛዋ አስተናጋጅ ጋቡን፤ ከኒጀር፣ ከሞሮኮና ከቱኒዚያ ጋር ስትደለደል በዚሁ የማግሬብ ልዕልና ጎልቶ በሚታይበት ክበብ ገና ከጅምሩ ስንብት እንዳታደርግ እጅጉን ያሰጋታል።
የምድብ-አራት ተሳታፊዎች ደግሞ ጋና፣ ቦትሱዋና፣ ማሊና ጊኒ ናቸው። ምንም እንኳ ያለፈው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ተሳታፊ ጋና በምድቡ ውስጥ ቀደምት ሆና ብትታይም ልምድ እንዳሳየው ማሊና ጊኒም ብርቱ ተፎካካሪ ሊሆኑ የማይችሉበት ምክንያት የለም። በሌላ በኩል የብዙ ጊዜዋን የአፍሪቃ ዋንጫ ባለድል ግብጽን፣ ደቡብ አፍሪቃን፣ ካሜሩንና አልጄሪያን የመሳሰሉት ታላላቅ ቡድኖች ለፍጻሜው አለመድረሳቸው አፍሪቃ ውስጥ ፉክክሩ ምን ያህል እየጠነከረ እንደመጣ የሚያመለክት ነው። የነዚሁ አገሮች በዘንድሮው ውድድር አለመሳተፍ ያልተጠበቀ ነገር ካልተፈጠረ ምናልባት የጋናን፣ የሞሮኮን ወይም የቱኒዚያን የዋንጫ ዕድል ከፍ ሊያደርግ ይችላል።
ለማንኛውም ወደ ተከታዩ ሩብ ፍጻሜ ዙር የሚያልፉት የየምድቡ አንደኛና ሁለተኛ ቡድኖች ናቸው። ከዚያ በኋላ በጥሎ-ማለፍ መልክ የሚቀጥለው ውድድር ሩብና ግማሽ ፍጻሜውን አልፎ የዋንጫው ባለቤት የካቲት 4 ቀን በሚካሄድ የፍጻሜ ግጥሚያ ይለይለታል። በነገራችን ላይ ውድድሩን እየተከታተልን በየጊዜው ዘገባ የምናቀርብ ሲሆን በፊታችን ቅዳሜ በተለመደው “ትኩረት’ በአፍሪቃ” ዝግጅታችን ደግሞ ከወዲሁ የሁለቱን አስተናጋጅ ሃገራት የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ የሚመለከት ዘገባ እንደሚኖረን ለማስታወቅ እንወዳለን።

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት በአሜሪካ የተካሄደው የሂዩስተን ማራቶን ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች የበላይነት የሰመረበት ሆኖ አልፏል። በወንዶች ታሪኩ ጁፋር ሩጫውን በሁለት ሰዓት ከስድሥት ደቂቃ 51 ሤኮንድ ሲያሸንፍ ይሄውም በካና ዳባ በዚያው ስፍራ ባለፈው ዓመት አስመዝግቦት ከነበረው ጊዜ በ 13 ሤኮንዶች የፈጠነ መሆኑ ነው። የ 27 ዓመቱ ጁፋር በውጤቱ እጅግ መርካቱን በአስተርጓሚ አማካይነት ለጋዜጠኞች ገልጿል። በሴቶች ዓለሚቱ አበራም እንዲሁ በ 2010 ዓ.ም. ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ጠይባ ኤርኬሶ አስመዝግባ የነበረውን ጊዜ በማሻሻል አሸናፊ ሆናለች። በግማሽ ማራቶንም ኢትዮጵያውያኑ ፈይሣ ሌሊሤና በላይነሽ ኦልጂራ በየፊናቸው ለድል በቅተዋል።

የሕንድ-የሙምባይ ማራቶንም ትናንት የኢትዮጵያ አትሌቶች ቀደምት የሆኑበት ነበር። በሴቶች ከአንድ እስከ አሥራ ሁለት በተከታተሉበት ሩጫ ነጻነት አበዮ ስታሸንፍ በወንዶች ደግሞ ራጂ አሰፋ ኬንያዊውን ላባን ሞይቤን ተከትሎ ሁለተኛ ወጥቷል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች ሻምፒዮና

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ቦልተን ወንደረርስን 3-0 በመርታት ለጊዜውም ቢሆን ሊጋውን ከሚመራው የከተማ ተፎካካሪው ከማንቼስተር ሢቲይ ጋር በነጥብ እኩል ሊሆን በቅቷል። እርግጥ ሢቲይ አንድ ጨዋታ የሚጎለው ሲሆን በዚሁ ዛሬ ማምሻውን ከዊጋን አትሌቲክ በሚያደርገው ግጥሚያ ካሽነፈ መልሶ በሶሥት ነጥቦች ብልጫ የሚመራ ነው የሚሆነው። በሌላ በኩል ሶሥተኛው ቶተንሃም ሆትስፐር ከዎልቨርሃምፕተን ወንደረርስ አቻ-ለአቻ 1-1 በመለያየት የማንቼስተሩን ክለቦች ለመቃረብ የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከዚሁ ሌላ ቼልሢይ ሰንደርላንድን 1-0 በመርታት በአራተኝነቱ ሲቀጥል አምሥተኛው አርሰናል በአንጻሩ በዝቅተኛው ክለብ በስዋንሢይ ሢቲይ 3-2 በመሸነፍ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ ከሚያበቃው ቦታ ለመድረስ በያዘው ትግል ክስረት ነው የደረሰበት።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ሬያል ማድሪድ ዘንድሮ ከመቼውም ይልቅ ለሻምፒዮንነት የሰከነ እየመሰለ ነው። ከሣምንት ሣምንት ብዙ ጎሎችን በማስቆጠር ተጋጣሚዎቹን ከንቱ እያደረ የመጣው ንጉሣዊ ክለብ ሰንበቱን ሬያል ማዮርካን 2-1 ሲያሸንፍ በዚሁም አንድ ጨዋታ ቀድሞ የመጀመሪያው ዙር የበልግ ሻምፒዮን ሆኗል። ሬያል በ 18 ግጥሚያዎች 46 ነጥቦችን ሲሰበስብ የቅርብ ተፎካካሪው ባርሤሎና ምንም እንኳ በበኩሉ ግጥሚያ ቤቲስን 4-2 ቢያሽንፍም በአምሥት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው።

ቫሌንሢያ ሶሥተኛ ሲሆን ክለቡ ሰንበቱን በሬያል ሶሢየዳድ 1-0 መረታቱ ከባርሣ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ይበልጥ ወደ ሰባት እንዲሰፋ አድርጓል። እንደ ዕውነቱ ከሆነ ሻምፒዮናው እንደተለመደው በሬያልና በባርሣ መካከል የሚለይለት ነው የሚሆነው። በተረፈ ስለ ስፓኝ ላ-ሊጋ የሚባል ነገር ካለ የባርሤሎናና የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን የመሃል ሜዳ ኮከብ ሻቪ በአራት መቶ የሊጋ ግጥሚያዎች በመሰለፍ የመጀመሪያው የባርሣ ተጫዋች መሆኑ ነው። ለሶሥተኛ ጊዜ በማከታተል የዓለም ድንቅ ተጫዋች ሆኖ የተሰየመው ሊዮኔል ሜሢም በዚሁ ግጥሚያ ሁለት ፍጹም ቅጣቶችን ሲያስቆጥር በጎል አግቢነት ቀደምቱን ክሪስቲያኖ ሮናልዶን እስከ ሁለት ጎሎች ልዩነት መቃረቡ ተሳክቶለታል። ሮናልዶ በወቅቱ በ 21 ጎሎች ሊጋውን በቀደምነት እንደሚመራ የሚታወቅ ነው።

በኢጣሊያ አንደኛ ዲቪዚዮን ሤሪያ-አ የሰንበቱን ትኩረት ከሁሉም በላይ የሳበው የቀደምቱ የከተማ ተፎካካሪዎች የኢንተርና የኤ.ሢ.ሚላን ግጥሚያ ነበር። በዚሁ ግጥሚያ ዘንድሮ ደከም ብሎ የታየው ኢንተር ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ ኤ.ሢ.ሚላንን 1-0 ሲረታ ኤ.ሢሚላን በዚሁ ወደ ሁለተኛው ቦታ ማቆልቆሉ ግድ ሆኖበታል። ብቸኛዋን ጎል ለኢንተር ያስቆጠረው መልሶ መነቃቃት የያዘው ዲየጎ ሚሊቶ ነበር። በበኩሉ ግጥሚያ ከካልጋሪ 1-1 የተለያየው ጁቬንቱስ አንደኝነቱን ሲይዝ ኤ.ሢ.ሚላን አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ፣ ኡዲኔዘ ሶሥተኛ፣ የሮማው ክለብ ላሢዮ አራተኛ፤ እንዲሁም ኢንተር ሚላን አምሥተኛ ነው።
በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ቱሉዝን 3-1 በመርታት በአመራሩ ሲቀጥል ድሉ ለአዲሱ ኢጣሊያዊ አሠልጣኙ ለካርሎ አንሄሎቲም የመጀመሪያው መሆኑ ነበር። በተቀረ ሞንትፔሊየር ሁለተኛ ነው፤ ኦላምፒክ ሊዮን ደግሞ ሶሥተኛ ሆኖ ይከተላል። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ቤንፊካ ሊዝበን በሁለት ነጥቦች ብልጫ ፖርቶን አስከትሎ አመራሩን እንደያዘ ሲሆን ብራጋ ሶሥተኛ ነው።

የዕጅ ኳስ

ሰርቢያ ውስጥ ትናንት በተከፈተው የአውሮፓ የዕጅ ኳስ ሻምፒዮና በምድብ-አንድና በምድብ-ሁለት በተካሄዱት የመክፈቻ ግጥሚያዎች ሰርቢያ ፓላንድን 22-18፤ ዴንማርክ ስሎቫኪያን 30-25፤ ቼክ ሬፑብሊክ ጀርመንን 27-24 ሲያሸንፉ ስዊድንና ማቄዶኒኒያ ደግሞ 26-26 ተለያይተዋል። የምድብ-ሶሥትና አራት የመጀመሪያ ግጥሚያዎች የሚካሄዱት ደግሞ በዛሬው ምሽት ነው። ከያንዳንዱ ምድብ ወደዋናው ተከታይ ዙር የሚሻገሩት ቀደምቱ ሶሥት ሃገራት ናቸው። በተረፈ የሜልበርኑ የአውስትሬሊያን-ኦፕን ቴኒስ ውድድር ዛሬ በመጀመሪያ ዙር ግጥሚያዎች ተጀምሯል። ያለፈውን ዓመት የሴቶች አሸናፊ ኪም ክላይስተርስን ጨምሮ በርካታ ቀደምት ተጫዋቾችም ወደተከታዩ ዙር መሻገሩ ብዙም አልከበዳቸውም።

መሥፍን መኮንን
አርያም ተክሌ

EM Handball Mazedonien gegen Schweden
ምስል Reuters
FC Barcelona Xavi Hernandez Fußballspieler
ምስል picture-alliance/dpa
Marathonläufer beim Kölner Marathon
ምስል DW/N. Karbasova
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ