1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 1 2004

በአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን የቀደምቱ ክለብ የሬያል ማድሪድ ከቫሌንሢያ 0-0 መለያየት የሻምፒዮናውን ፉክክር እንደገና ጠባብ አድርጎታል።

https://p.dw.com/p/14Zv0
ምስል AP

በአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን የቀደምቱ ክለብ የሬያል ማድሪድ ከቫሌንሢያ 0-0 መለያየት የሻምፒዮናውን ፉክክር እንደገና ጠባብ አድርጎታል። ሁለተኛው ባርሤሎና በበኩሉ ግጥሚያ ሣራጎሣን 4-1 ሲያሸንፍ ሬያል አሁን የሚመራው በአራት ነጥቦች ልዩነት ብቻ ነው። ሬያል ማድሪድ በገዛ ሜዳው በቤርናቤው ስታዲዮም ጠቃሚ ነጥቦቹን ያጣው በተለይ በቫሌንሢያው በረኛ በቪቼንቴ ጋኢታ አልበገር ባይነት ነበር።                                                                                              

 የማድሪዱ ክለብ ከጥቂት ሣምንታት በፊት በአሥር ነጥብ ሲመራ ለብዙዎች ሻምፒዮናው ያለቀለት መስሎ ታይቶ ነበር። ይሁንና ሬያል በቀሪዎቹ ግጥሚያዎች ያለፉት ሶሥት ዓመታት ሻምፒዮን ባርሣ አልፎት እንዳይሄድ በጣሙን መጠንቀቅ ይኖርበታል። ሬያል ማድሪድ ከባርሣ ጋር በኑው ካምፕ ስታዲዮም በዚህ በያዝነው ወር ሂደት ጠንካራ የመልስ ግጥሚያ ነው የሚጠብቀው። ምናልባትም የዚያ ግጥሚያ ውጤት በሻምፒዮናው ላይ ዓቢይ ተጽዕኖ ይኖረው ይሆናል።                                                                                      

 በሌላ በኩል ባርሤሎና ሳይቆይ በነገው ምሽት ግጥሚያው ካሸነፈ ሬያልን ከወዲሁ በአንዲት ነጥብ ልዩነት በቻ ሊቃረብም ይችላል። ይህ ከሆነ የሬያልን ኮከቦች ጥቂትም ቢሆን የሚያስደነግጥ እንደሚሆን ግልጽ ነው።  ለማንኛውም ውድድሩ ሊያበቃ ሰባት ጨዋታዎች ብቻ ቀርተው ሳለ ሬያል ማድሪድ በወቅቱ በ 79 ነጥቦች አንደኛ ሲሆን ባርሤሎና ደግሞ 75 ነጥቦች አሉት። የሁለቱን ክለቦች ከዋክብት የጎል ፉክክር በተመለከተ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በቫሌንሢያ በረኛ በጋኢታ ሲገታ ሊዮኔል ሜሢ በአንጻሩ ሁለቱንም የባርሣ ጎሎች በማስቆጠር ቀደምቱ ነበር።

የዓለም ድንቅ ተጫዋች የሆነው የአርጄንቲና ኮከብ በአንድ የውድድር ወቅት 60 ጎሎችን በማስቆጠር ከአርባ ዓመታት ወዲህ በአውሮፓ የመጀመሪያው ተጫዋች ሆኗል። ከርሱ በፊት በጎርጎሮሳውያኑ 1972/73 የውድድር ውቅት ለዚህ ክብር የበቃው የባየርን ሚዩኒኩ አጥቂ ጌርድ ሙለር ነበር። የዘንድሮው የስፓኝ ሻምፒዮና በሮናልዶና በሜሢ የጎል ፌስታ የደመቀ ሆኖ ሲቆይ የሁለቱ ተጫዋቾች ቀጣይ ሁኔታ ወሣኝነት የሚኖረውም ይመስላል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ሢቲይ በአርስናል 1-0 ሲረታ የሻምፒዮንነት ተሥፋው ይበልጥ እየመነመነ መሄድ ይዟል። የከተማ ተፎካካሪው ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ ኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስን 2-0 ሲያሸንፍ አመራሩን ወደ ስምንት ነጥቦች ማስፋቱ ሰምሮለታል። አርስናል ሢቲይን በማሸነፉ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ሲል እርግጥ ከሁለተኛው የአሥር ነጥቦች ልዩነት አለው። በጎል አግቢነት የአርሰናሉ ሆላንዳዊ አጥቂ ሮቢን-ፋን-ፕርሢ በ 26 የሚመራ ሲሆን ዌይን ሩኒይ ከማንቼስተር ዩናይትድ  በ 22 ሁለተኛ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋም ሁለቱ የሻምፒዮና ተፎካካሪዎች ዶርትሙንድና ባየርን የየበኩላቸውን ጨዋታ በማሸነፍ ሲወጡ በፊታችን ረቡዕ እርስበርስ የሚያደርጉት ግጥሚያ ወሣኝነት እንደሚኖረው ይጠበቃል። ዶርትሙንድ ቮልፍስቡርግን 3-1 ሲረታ በተለይም ለክለቡ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው አጥቂው ሌቫንዶቭስኪ የዕለቱ ድንቅ ተጫዋች ነበር። ዶርትሙንድ እስካሁን በተከታታይ ከሃያ በሚበልጡ ግጥሚያዎች ያልተሸነፈ ሲሆን አሠላጣኙ ዩርገን ክሎፕ እንደሚለው ይህም የቡድኑ ጥንካሬ ምልክት ነው።

FC Bayern München - Borussia Dortmund Robben Schmelzer
ምስል picture-alliance/dpa

«በ 23 ግጥሚያዎች በተከታታይ ነጥብ ለማግኘት ችለናል። ይህ ያልተለመደ ነገር ነው። እርግጥ ይህን መሰል ውጤት የሚገኘው ከባድ ግጥሚያዎችን በማሸነፍ መሆኑ መዘንጋት የለበትም»

ያም ሆነ ይህ ባየርንም አውግስቡርግን 2-1 ሲያሸንፍ አሁን ከዶርትሙንድ የሚለየው በሶሥት ነጥቦች ብቻ ነው። በፊታችን ረቡዕ ካሸነፈ አመራሩን በጎል ብልጫ ሊይዝ ይችላል። ቢሆንም በመሃል ሜዳ ተጫዋቹ በባስቲያን ሽቫይንሽታይገር ግምት በዶርትሙንድ ሜዳ ለድል መብቃቱ ቀላል ነገር አይሆንም።

«ዶርትሙንድ በዚህ ሰንበት ነጥቦች ያጣል ብለን ተሥፋ አድርገን ነበር። ግን ከሁሉም የሚበልጠው በራሳችን ግጥሚያ ማሸነፋችን ነው። የፊታችን ረቡዕ ግጥሚያ በጣም ከባድ እንደሚሆን እናውቃለን። እናም በመጨረሻ ምን ውጤት እንደሚታይ ነው የምንጠብቀው»

በተረፈ ሻልከ ሃኖቨርን 3-0 በማሸነፍ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ በሚያበቃው ሶሥተኛ ቦታ ላይ ይበልጥ ቶቆናጧል። በግሩም ጨዋታ ከሶሥት ሁለቱን ጎሎች በማስቆጠር ቡድኑን ለድል ያበቃው በተለይም የስፓኙ ኮከብ ራውል ነበር። ግላድባህ በአንጻሩ ከ 17ኛው ከበርሊን ጋር 0-0 ሲለያይ በአረተኛነቱ ቀጥሏል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ፓሌርሞን 2-0 የረታው ጁቬንቱስ በአንዲት ነጥብ ብልጫ ኤሲ ሚላንን ከአንደኛው ቦታ መፈንቀሉ ሰንበቱን ተሳክቶለታል። ኤሲ ሚላን ለሣምንታት ይዞት የቆየውን አመራር የተነጠቀው በገዛ ሜዳው በፊዮሬንቲና 2-0 ከተሸነፈ በኋላ ነው። ላሢዮ ናፖሊን 3-1 አሸንፎ በሶሥተኛነቱ ሲቀጥል ሶሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ አራተኛው ፓርማን በተመሳሳይ ወጤት የረታው ኡዲኔዘ ነው። ናፖሊ በአምሥተኝነት ይከተላል።

በፈረንሣይ ሻምፒዮና ደግሞ ሞንትፔሊየር ሶሾን 2-1 አሸንፎ በአመራሩ ሲቀጥል ፓሪስ-ሣንት-ዠርማንም ኦላምፒክ ማርሤይን በተመሳሳይ ውጤት በመርታት በእኩል ነጥብ እየተከተለ ነው። እርግጥ ሞንትፔሊየር አንድ ጨዋታ ይጎለዋል። በጎል አግቢነት በብቸኝነት ሊጋውን የሚመራው 18 ያስቆጠረው የሞንትፔሊየር አጥቂ ኦሊቪየር ዢሩ ነው።

በፖርቱጋል ሻምፒዮና ውድድሩ ሊጠቃለል አራት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ሳለ ፖርቶ ሶሥተኛውን ብራጋን 1-0 በማሸነፍ በቁንጮነቱ ቀጥሏል። ሁለተኛው ቤንፊካ አሁን በአራት ነጥቦች ልዩነት እየተመራ ሲሆን የዋንጫ ተሥፋው እንዳይመነምን በዛሬው ምሽት ከከተማ ተፎካካሪው ከስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር በሚያደርገው ግጥሚያ ማሸነፉ ግድ ነው።

በኔዘርላንድ ስንበቱ ያለፈው የአገሪቱ ፌደሬሺን ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ የተካሄደበት ሆኖ ነው። በዚሁ ፍጻሜ ግጥሚያም የአንዴው የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊ አይንድሆፈን ሄርኩለስ አልሜሎን 3-0 በመርታት ለዘጠነኛ ጊዜ የኔዘርላንድ ፌደሬሺን ዋንጫ አሸናፊ ለመሆን በቅቷል። ዋንጫው ለክለቡ አዲስ አሠላጣኙ ለፊሊፕ ኮኩ ደግሞ በዚህ ሥልጣን የመጀመሪያው መሆኑ ነው። አይንድሆፍን በሊጋው ሻምፒዮና ውድድር በወቅቱ አምሥተኛ ሲሆን ስድሥትግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ በአራት ነጥበ ብልጫ አያክስ አምስተርዳም ይመራል።

ቴኒስ

Serena Williams Tennis
ምስል dapd

በቴኒስ ዴቪስ-ካፕ  የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ትናንት አርጄንቲና ክሮኤሺያን 4-1 ስታሸንፍ ቼክ ሬፑብሊክም ሰርቢያን በተመሳሳይ ውጤት ረትታለች። ስፓኝም እንዲሁ አውስትሪያን 4-1 ስታሸንፍ አሜሪካ ደግሞ ፈረንሣይን 3-2 አሰናብታለች። በዚሁ ውጤት መሠርት የ 32 ጊዜዋ ሻምፒዮን አሜሪካና የወቅቱ ሻምፒዮን ስፓኝ በፊታችን መስከረም በግማሽ ፍጻሜ  ይገናኛሉ።                                                                   

አሜሪካ ባለፉት ሰባት ዓመታት ለአራተኛ ጊዜ ከግማሽ ፍጻሜ መድረሷም ነው።  ስፓኝም በአገር ውስጥ ያካሄደቻቸውን 23 ግጥሚያዎች በሙሉ ያሸነፈች ናት። እናም ግማሽ ፍጻሜው ጠንካራ እንደሚሆን ይጠበቃል።  ሁለተኛው ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ የሚካሄደው ደግሞ በአርጄንቲናና በቼክ ሬፑብሊክ መካከል ነው።

በተቀረ በደቡብ ካሮላይና የቻርልስተን የዓለም ቴኒስ ማሕበር የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያ  በዓለምአቀፉ የማዕረግ ተዋረድ ላይ አምሥተኛ የሆነችው አሜሪካዊት ሤሬና ዊሊያምስ ትናንት የቼክ ተጋጣሚዋን ሉሢ ሣፋሮቫን በለየለት 6-0,6-1 ውጤት አሸንፋለች። የ 13 ጊዜ ግራንድ-ስላም አሸናፊዋ ሤሬና ሣፎሮቫን ለማሰናበት ከ 58 ደቂቃዎች በላይ ረጅም ጊዜ አላስፈለጋትም።                                                                                

በተረፈ ዛሬ አዲስ በወጣው የዓለም ቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ መሠረት የአመራር ለውጥ የለም። በወንዶች የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪች በ 12670 ነጥቦች ራፋኤል ናዳልንና ሮጀር ፌደረርን በሩቅ አስከትሎ መምራቱን ሲቀጥል በሴቶችም የቤላሩሷ ቪክቶሪያ አዛሬንካ ቁንጮ እንደሆነች ነው። ሩሢያዊቱ ማሪያ ሻራፖቫ ሁለተኛ ስትሆን ፔትራ ክቪቶቫ ቼክ ሬፑብሊክ ሶሥተኛ፤ እንዲሁም አግኔሽካ ራድቫንስካ ከፖላንድ በአራተናነት ትከተላለች።

ከዚሁ ሌላ ዶሃ ላይ በተካሄደ የሞተር ቢስክሌት የዓለም ሻምፒዮና ውድድር የስፓኝ ተወዳዳሪዎች ግንባር ቀደም ሆነው ታይተዋል። በሞቶ-ጂፒ መደብ በተካሄደው  የ 118,36 ኪሎሜትር 22 ዙር እሽቅድድም ሆርሄ ሎሬንሶ ሲያሸንፍ ሌላው የስፓኝ ተወላጅ ዳኒ ፔድሮዛም ሁለተኛ ሆኗል። ሎሬንሶ ከ 18 አንዱ እሽቅድድም ተካሂዶ አሁን ውድድሩን በ 25 ነጥቦች ይመራል። በሞቶ-2 መደብ ሃያ ዙር እሽቅድድም የስፓኙ ማርክ ማርኬዝ ሲያሸንፍ በሞቶ-3 መደብም እንዲሁ ድሉ የስፓኝ ነበር። ማቬሪክ ቪ-አሌስ ቀደምቱ ሆኗል።

Flash-Galerie Sportjahr 2011
ምስል picture-alliance/dpa

አውስትራሊያ ሜልበርን ላይ ሲካሄድ የሰነበተው የዓለም የቢስክሌት ሻምፒዮና ደግሞ ትናንት በአስተናጋጇ አገር የበላይነት ተፈጽሟል። አውስትራሊያ በስድሥት ወርቅ፣ ስድሥት ብርና  ሶሥት ናስ ሜዳሊያዎች አሸናፊ ስትሆን ብሪታኒያ በሁለት የብር ሜዳሊያዎች ብቻ በመበለጥ ሁለተኛ ውጥታለች።  በተረፈ ጀርመን በሁለት ወርቅ፣ ሁለት ብርና አንድ ናስ ሶሥተኛዋ ነበረች።

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ