1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 7 2005

ብሪታኒያ-ኒውካስል ውስጥ ትናንት የተካሄደው ዓመታዊው ታላቁ የሰሜን ሩጫ «ግሬት-ረን» የአፍሪቃውያን ልዕልና በሰመረበት ተፈጽሟል።

https://p.dw.com/p/16Abq
ምስል Reuters

ብሪታኒያ-ኒውካስል ውስጥ ትናንት የተካሄደው ዓመታዊው ታላቁ የሰሜን ሩጫ «ግሬት-ረን» የአፍሪቃውያን ልዕልና በሰመረበት ተፈጽሟል። በግማሽ ማራቶኑ ሩጫ በወንዶች ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሣንግ ግሩም በሆነ 59,06 ደቂቃ ጊዜ ሲያሸንፍ በሴቶች ደግሞ ጥሩነሽ ዲባባ ቀደምቷ ለመሆን በቅታለች። ኪፕሣንግ ለድል የበቃው የአገሩን ልጅ ሚካ ኮጎን በመጨረሻዎቹ ሜትሮች በፍጥነት አምልጦ ከግቡ በመድረስ ነው።

ኬንያዊው አትሌት የዚህ ዓመቱ የለንደን ማራቶን አሸናፊ እንደነበርና በቅርቡ የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታም በዚሁ ርቀት ሶሥተኛ በመውጣት ናስ ሜዳሊያ መሸለሙ ይታወሳል። የሶሥት ጊዜዋ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ ለድል የበቃችው ኬንያዎቱን ጠንካራ አትሌት ኤድና ኪፕላጋትን በመቅደም ነው። ኤድና ያለፈው 2011 ዓመተ-ምሕረት የማራቶን የዓለም ሻምፒዮን መሆኗ ይታወሳል።

በነገራችን ላይ ጥሩነሽ በዚህ ርቀት ስትወዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነበር። ሩጫውን የፈጸመችውም ግሩም በሆነ የ 67 ደቂቃ ከ 35 ሤኮንድ ጊዜ ነው። ጥሩነሽ ከለንደኑ ኦሎምፒክ በኋላ በማራቶን ላይ እንደምታተኩር መግለጿ ሲታወስ የትናንቱ ውጤት በእርግጥም ለዚሁ እጅግ የሚያበረታታ ነው። በሌላ በኩል ከሶማሊያ የመነጨው የብሪታኒያው የአምሥትና አሥር ሺህ ሜትር የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሞ ፋራህ እረፍት በመፈለጉ እንደተጠበቀው በውድድሩ አልተሳተፈም። በኒውካስሉ ታላቅ ሩጫ ላይ 55 ሺህ ሰዎች ተሳትፈዋል።

Real Madrid besiegt Barcelona im Supercup
ምስል Reuters

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር የስፓኙ ሻምፒዮን ሬያል ማድሪድ በመጥፎ አጀማመሩ እንደቀጠለ ነው። ቡድኑ በሰንበቱ ግጥሚያው በሤቪያ 1-0 ተረትቶ ወደ 11ኛው ቦታ ሲያቆለቁል ፖርቱጋላዊው የቡድኑ አሰልጣኝ ሆሴ ሞሪኞ በተጫዋቾቹ ድክመት በጣሙን ነው የተቆጣው። ሬያል እስካሁን ባካሄዳቸው አራት የሊጋ ግጥሚያዎች በአራት ነጥቦች ብቻ ሲወሰን ከአንደኛው ከባርሤሎና ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ስምንት ከፍ ብሏል። ይህ ደግሞ አሁን በውድድሩ አፍላ ወቅት ከፍተኛና ያልተጠበቀም ነው።

ባርሤሎና በበኩሉ በአዲስ አሰልጣኙ በቲቶ ቪላኖቫ መሪነት በአራተኛ ግጥሚያውም ጌታፌን 4-1 በማሸነፍ ሙሉ 12 ነጥቦቹን እንደያዘ ይመራል። ከአራት ሁለቱን ጎሎች በማስቆጠር እንደተለመደው የቡድኑ የድል ዋስትና የነበረው አሁንም አርጄንቲናዊው የዓለም ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ነበር። ባርሣን በሁለት ነጥቦች ዝቅ ብሎ በሁለተኝነት የሚከተለው ማላጋ ሲሆን ማዮርካና ሤቪያ በ8 ነጥቦች ሶሥተኛና አራተኛውን ቦታ ይዘዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የቼልሢይ የድል ጉዞ በዘንድሮው የውድድር ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ ተገትቷል። ቼልሢይ ባለፈው ቅዳሜ በአራተኛ ግጥሚያው ከኩዊንስ-ፓርክ-ሬንጀርስ 0-0 ሲለያይ አሁን ሊጋውን የሚመራው በአንዲት ነጥብ ብልጫ ብቻ ነው። አሥር ነጥቦች አሉት። ማንቼስተር ዩናይትድ ዊጋን አትሌቲክን 4-0 ሲረታ በዘጠን ነጥቦች ሁለተኛ ሆኖ በቅርብ ይከተላል። ሶሥተኛው ሳውዝሃምፕተንን 6-1 የሸኘው አርሰናል ሲሆን ከስቶክ ሢቲይ 1-1 የተለያየው ማንቼስተር ሢቲይም በተመሳሳይ ነጥብ አራተኛ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ዘንድሮ በአዳዲስ ተጫዋቾች የተጠናከረው ባየርን ሙንሺን ሶሥተኛ ግጥሚያውንም በድል በማሳለፍ ሊጋውን መምራቱን ቀጥሏል። ባየርን ማይንስን 3-1 ሲያሸንፍ በሶሥት ግጥሚያዎች በጠቅላላው 12 ጎሎችን ማስቆጠሩ የማየሉ ምልክት ነው። ዘንድሮ ሻምፒዮንነቱን አያስነካም የሚሉት ታዛቢዎች ከሣምንት ሳምንት እየተበራከቱ በመሄድ ላይ ናቸው። ለማንኛውም ከሁለተኛው ዲቪዚዮን የወጣው ፍራንክፉርት ሶሥቱንም ግጥሚያዎቹን አሸንፎ በእኩል ዘጠን ነጥቦች ከባየርን ጋር ግንባር ቀደም መሆኑን ሲቀጥል ይህ እርግጥ የተጠበቀ አልነበረም። ቡድኑ ትናንት ሃምቡርግን 3-2 ሲያሸንፍ በወቅቱ ጥንካሬው ከገፋ ቢቀር በአንደኛው ዲቪዚዮን ውስጥ ጸንቶ የመቆየት ዕድሉን ከፍ እንደሚያደርግ አያጠራጥርም።

አንዲት ነጥብ እንኳ ሳያገኝ 17ኛ ቦታ ላይ የሚገኘው ሃምቡርግ ግን እያቆለቆለ ሄዶ ወደ ዝቅተኛው ዲቪዚዮን እንዳይከለስ በጣሙን ያሰጋዋል። ሃምቡርግ በዚህ ሰንበትም ትልቅ ድክመት ሲታይበት ጀርመንን ከለቀቀ በኋላ ወደ ክለቡ የተመለሰው የኔዘርላንድ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ራፋኤል ፋን-ደር-ፋርት እንኳ ከሽንፈት ሊያድነው አልቻለም። እንደርሱ አባባል ችግሩ በራስ የመተማመን እጦት ነው።

«በልምድ እንደማውቀው አንድ ክለብ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ላይ በሚገኝበት ጊዜ ተጫዋቾቹ የሚሰማቸው ሁሉም ነገር እነርሱን የሚጻረር እንደሆነ ነው»

በእርግጥም ባለፉት አሠርተ-ዓመታት ከታላላቆቹ የቡንደስሊጋ ክለቦች አንዱ ሆኖ የቆየው ክለብ በቀደምቱ ሊጋ ውስጥ እንዲቀጥል የተጫዋቾቹ የመንፈስ ጥንካሬ በጣሙን ነው አስፈላጊ የሚሆነው። በተቀረ ያለፉት ሁለት የውድድር ወቅቶች ሻምፒዮን ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ሌቨርኩዝንን 3-0 ረትቶ አምሥተኛውን ቦታ ሲይዝ ሃኖቨር ሶሥተኛና ፉርትን 2-0 ያሸነፈው ሻልከ ደግሞ አራተኛ ነው።

Fußball Bundesliga - Hannover 96 - SV Werder Bremen
ምስል picture-alliance/dpa

ሃኖቨር በተጨማሪ ሰዓት ላይ በተገኘች ጎል ብሬመንን በዕድል 3-2 ሲያሸንፍ ግሩም ጨዋታ የሚያሳየው የብሬመን ወጣት ቡድን ግን ያሳዝናል በዚህ ሰንበትም በጥበቡ ሳይካስ ቀርቷል። ሆኖም በዚህ ድንቅ አጨዋወቱ እያደር ከፍ ማለቱ የማይቀር ነው የሚመስለው። የሊጋው መጨረሻ በወቅቱ ያለፉትን ሶሥት ግጥሚያዎች በሙሉ የጎል መቁጠሪያ የሆነው ሆፈንሃይም ነው። ቡድኑ ባለፈው ሰንበት ግጥሚያው ብቻ በፍራይቡርግ አምሥት ጎሎች ተቆጥረውበታል። 5-3 ተሸንፎ ነው ከሜዳ የወጣው።

በኢጣሊያ አንደኛ ዲቪዚዮን ሤሪያ-አ ባለፈው ሰንበት ጁቬንቱስ ከኋላ ተነስቶ ጀኖዋን 3-1 ሲያሸንፍ ላሢዮ ቺየቮንም እንዲሁ 3-1፤ ናፖሊም ፓርማን በተመሳሳይ ውጤት 3-1 ረትቷል። ከዚህ ውጤት በኋላ ላሢዮ፣ ናፖሊ፣ ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን ጁቬንቱስና ሣምፕዶሪያ ሁሉም ሶሥተኛ ግጥሚያቸውን በማሸነፍ ሙሉ ዘጠኝ ነጥብ እንደያዙ ይቀጥላሉ። ቀደምቱ ጁቬንቱስ ሊጋውን የሚመራው በአንዲት ጎል ብልጫ ብቻ ነው። ኢንተር ሚላን በስድሥት ነጥቦች አምሥተኛ ሲሆን ፊዮሬንቲናና ሮማ ወረድ ብለው ይከተሉታል።

በፈረንሣይ ሻምፒዮና ኦላምፒክ ማርሤይ በአምሥተኛ ግጥሚያውም አሸናፊ በመሆን ሙሉ 15 ነጥቦቹን ይዞ ሊጋውን በግንባር-ቀደምነት እየመራ ነው። ማርሢይ ትናንት ናንሢን 1-0 ሲያሸንፍ ሊዮን በ 13 ነጥቦች ሁለተኛ ሆኖ ይከተላል። በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን ትዌንቴ-ኤንሼዴ በአንደኝነቱ ሲቀጥል ቪቴስ-አርንሀይም ሁለተኛ ነው፤ አያክስ አምስተርዳም በሶሥተኝነት ይከተላል። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ ቤንፊካ ሊዝበንና ፖርቶ በእኩል ነጥብ ሊጋውን ይመራሉ።

UEFA Champions League Auslosung
ምስል AP

የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ

የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የምድብ ዙር ውድድር በነገው ምሽት ይከፈታል። በምድብ-አንድ ዲናሞ ዛግሬብ ከፖርቶና ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ከዶናሞ ኪየቭ፤ በምድብ-ሁለት ሞንትፔሊየር ከአርሰናልና ኦሊምፒያኮስ ፒሬውስ ከሻልከ፤ በምድብ-ሶሥት ማላጋ ከዜኒት-ሣንት-ፒተርስበርግና ኤ ሲሚላን ከአንደርሉኽት፤ በምድብ-አራት ዶርትሙንድ ከአያክስ አምስተርዳምና ሬያል ማድሪድ ከማንቼስተር ሢቲይ!እነዚህ በነገው ምሽት የሚካሄዱት ግጥሚያዎች ናቸው።

በማግሥቱ ረቡዕ ምሽትም ከምድብ-አምሥት እስከ ስምንት ማራኪ ግጥሚያዎች ሲኖሩ ከነዚሁ መካከልም ቼልሢይ ከጁቬንቱስ፤ ባርሤሎና ከስፓርታክ ሞስኮ፤ ባየርን ሙንሺን ከቫሌንሢያ፤ እንዲሁም ማንቼስተር ዩናይትድ ከጋላታሳራይ ኢስታምቡል በተለይ ጠንካሮቹ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

Sport Tennis Victoria Azarenka Australian Open
ምስል AP

ቴኒስ

በሴቶች ዓለምአቀፍ ቴኒስ የቤላሩሷ ቪክቶሪያ አዛሬንካ በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቷ ሆና መቀጠሏን የዓለም ቴኒስ ማሕበር ዛሬ ባወጣው ዝርዝር አመልክቷል። አዛሬንካ በ 10,265 ነጥቦች ቀደምቷ ስትሆን ሩሢያዊቱ ማሪያ ሻራፖቫ በ 8,435 ነጥቦች ሁለተኛ ናት። የፖላንዷ አግኔሽካ ራድዋንስካ ሶሥተኛ፤ እንዲሁም አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስ አራተኛ በመሆን ይከተላሉ።

በተቀረ በቻይና ግዋንግሹ ዓለምአቀፍ የሴቶች ቴኒስ ውድድር ዛሬ በተካሄዱ የመጀመሪያ ዙር ነጠላ ግጥሚያዎች ማንዲይ ሚኔላ ከሉክሰምቡርግ ፈረንሣዊቱን ፓውሊን ፓርሜንቲየርን፤ ደቡብ አፍሪቃዊቱ ቻኔል ሺፐርስ ዋንግ ኪያንግን፤ የብሪታኒያ ላውራ ሮብሰን የስፓኟን ማሪያ-ቴሬዛ-ቶሮን፤ እንዲሁም ቦያና ዮባኖቪች ከሰርቢያ የሁንጋሪያን ቲሜያ ባቦስን በማሸነፍ ወደ ተከታዩ ዙር አልፈዋል።

Symbolbild Fahrrad Tour
ምስል Fotolia/lassedesignen

የቢስክሌት እሽቅድድም

በኔዘርላንድ-ፋልከንቡርግ በዛሬው ዕለት በተካሄደ የዓለም ወጣቶች የመንገድ ላይ የሰዓት እሽቅድድም የኖርዌዩ ተወላጅ ኦስካር ስቬንድሰን አሸናፊ ሆኗል። የ 18 ዓመቱ ወጣት በሰባት ሤኮንዶች ልዩነት ቀዳሚ ሲሆን የስሎቬኒያው ማቴይ ሞሆሪች ሁለተኛ፤ እንዲሁም ጀርመናዊው ማክስሚሊያን ሻህማን ሶሥተኛ በመሆን እሽቅድድሙን ፈጽመዋል። ርቀቱ 26,6 ኪሎሜትር ነበር። ያለፈው ጊዜ አሸናፊ የዴንማርኩ ማድስ ሽሚት ስምንተኛ ወጥቷል። በቡድን እሽቅድድም ያሸነፉት ደግሞ በወንዶች የቤልጂግና በሴቶችም የጀርመን ተወዳዳሪዎች ናቸው።

በእግር ኳስ ለማጠቃለል በደቡብ አሜሪካ የመልስ ዙሩ ላይ በሚገኘው የብራዚል ሻምፒዮና ቀደምቱ ፍሉሚኔዘ ትናንት በሜዳው ቢሸነፍም አሁንም ከ 25 ጨዋታዎች በኋላ በ 53 ነጥቦች እየመራ ነው። እርግጥ ገና አንድ ግጥሚያ የሚጎለው አትሌቲኮ ሚኒየሮ በ51 ነጥቦች ይበልጥ ተቃርቦታል። ሚኒየሮ በጎደለው ግጥሚያ 16ኛውን ፍላሜንጎን ካሸነፈ አመራሩን ሊነጥቅ እንደሚችልም ግልጽ ነው። ግሬሚዮም በ 48 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን ለሻምፒዮንነት ገና ዕድል አለው።

እጅግ የሚያስደንቀው በቀድሞው የዓለም ዋንጫ ባለድል የብራዚል ብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ በፌሊፔ ስኮላሪ ሲመራ የቆየው ፓልሚየራስ 17ኛ በመሆን ወደታች እንዳይወርድ እየተንገዳገደ ነው። ስኮላሪ ክለቡን ሲለቁ ክለቡን ከመውረድ አድናለሁ ሲሉ የገቡትን ቃል አፍርሰዋል በሚል ከተጫዋቾች በኩል ወቀሣ እየተሰነዘረባቸው ነው።

ስኮላሪ ብራዚል የምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ውድድር እየተቃረበ ሲሆን ምናልባት ወደ ቀድሞ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ ወሬ መሰማቱም አልቀረም። ይህን ለጊዜው በዚሁ ተወት እናድርገውና በአፍላ ደረጃው ላይ በሚገኘው በአርጄንቲና ሻምፒዮና ደግሞ ቦካ ዩኑዮርስ በሰባተኛ ግጥሚያው ኢንዲፔንዴንቴን 2-1 በማሸነፍ አመራሩን ይዟል። ቦካ 16 ነጥቦች ሲኖሩት በ 15 ነጥቦች ሁለተኛው ሰንበቱን በሽንፈት ያሳለፈው ኒዌል-ኦልድ-ቦይስ ነው።

መሥፍን መኮንን


አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ