1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 26 2005

ባለፈው ሰንበት በዩ ኤስ አሜሪካ ኦሬገን ተካሂዶ የነበረው የአትሌቲክስ ዳያመንድ ሊግ ውድድር በተለይም በመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫ የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎችም ጥንካሬ ያሳዩበት ሆኖ አልፏል።

https://p.dw.com/p/18j6I
ምስል Jonathan Ferrey/Getty Images

በወንዶች 800 ሜትር ሩጫ መሐመድ አማን ኬንያዊ ተፎካካሪውን ቲሞቲይ ኪቱምን ከኋላው አስቀርቶ አሸንፏል። ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመው አሜሪካዊው ኒክ ሢመንድስ ነበር። በነገራችን ላይ በዚህ ሩጫ ኬንያዊው የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮን ዴቪድ ሩዲሻ በአካል ጉዳት የተነሣ አልተሳተፈም። ሩዲሻ ከዚህ ቀደም ከመሐመድ አማን በስተቀር በሌላ አትሌት አለመሸነፉ የሚታወስ ነው።

በአንድ መቶ ሜትር ሩጫ አሜሪካዊው ጀስቲን ጋትሊን በ 9,94 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ የአገሩ ልጆች ማይክል ሮጀርስና ራያን ቤሊይ ተከትለውት ገብተዋል። የጃማይካው ኔስቶር ካርተር በአራተኝነት ሲወሰን የባሃማስና የትሪኒዳድ ሯጮች ቀጣዮቹ ነበሩ። በሁለት መቶ ሜትር የጃሜይካው ኒክል አሽሜድ ሲያሸንፍ በአራት መቶ ሜትር ደግሞ የአሜሪካው ላሽዋን ሜሪት ቀዳሚ ሆኗል።

Äthiopien Kenenisa Bekele
ምስል picture-alliance/dpa

በአጭር ርቀት ሩጫ እንግዲህ እንደተለመደው የአሜሪካና የጃሜይካ አትሌቶች በበላይነት ሲፈራረቁ በአካል ጉዳት የተነሣ ለረጅም ጊዜ በረድ ብሎ የቆየው ዝነኛው የረጅም ርቀት የዓለም ሻምፒዮን ቀነኒሣ በቀለ በ 10 ሺህ ሜትር ሩጫ አሸናፊ ሆኗል። ቀነኒሣ ሩጫውን በ 27 ደቂቃ ከ 12,08 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም ኢማነ መርጋና አበራ ኩማም ሁለተኛና ሶሥተኛ በመሆን የኢትዮጵያን ድል የተሟላ አድርገዋል።

ቀነኒሣ በቀለ በወቅቱ አንዳች ህመም እንደማይሰማው ሲገልጽ ሩጫውን ከ 27 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ለመሮጥ አቅዶም እንደነበር አመልክቷል። ይሁንና አያይዞ እንዳስረዳው በውድድሩ ላይ ሩጫውን በሚገባ የማፍጠን ጥረት ባለመታየቱ ይህ አልሆነም። ለማንኛውም የቀነኒሣ መልሶ መጠናከር በፊታችን ነሐሴ ወር ሞስኮ ላይ ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሥፋን የሚያጠናክር ነው። በ 5 ሺህ ሜትር ሩጫ ኬንያዊው ኤድቪን ሶል ሲያሸንፍ የብሪታኒያው የኦሎምፒክ ባለድል ሞ ፋራህ ሁለተኛና የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ የኔው አላምረው ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል።

በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ድሉ ከአንድ እስከ ሶሥት የኬንያውያን ነበር። በማይል ሩጫም እንዲሁ ኬንያውያኑ ሲላስ ኪፕላጋትና አስቤል ኪፕሮፕ ቀዳሚ ሲሆኑ አማን ወትዬ ከኢትዮጵያ ሶሥተኛ ሆኗል። በሴቶች 1,500 ሜትር የኬንያ ሴት አትሌቶች ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል በፍጹም ልዕልና ሲያሸንፉ በአምሥት ሺህ ሜትር ግን ቅድሚያውን ለኢትዮጵያ መተው ተገደዋል። በዚህ ሩጫ ጥሩነሽ ዲባባ ሁለት ኬንያውያትን አስከትላ ለድል ስትበቃ ቡዜ ዲሪባ፣ ገለቴ ቡርካ፣ ሕይወት አያሌውና በላይነሽ ኦልጂራም ከአራት እስከ ሰባት በመከታተል የኢትዮጵያን ጥንካሬ በማስረገጥ ውድድሩን አጠናቀዋል።

Stadien Fußball WM 2014 Brasilien Estádio Nacional de Brasília Modell
ምስል imago/Fotoarena

የትናንቱ ሰንበት በሚቀጥለው 2014 ዓ-ም የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ አስተናጋጅ በሆነችው በብራዚል በአዲስ መልክ የታደሰው ዝነኛው ማራካና ስታዲዮም በወዳጅነት ግጥሚያ የተመረቀበት ነበር። በግጥሚያው ብራዚል ከእንግሊዝ 2-2 ስትለያይ እርግጥ ከጨዋታው ይልቅ የብራዚል ዝግጅት መጓተት የበለጠ ትኩረትን ሳይስብ አልቀረም። በፌሊፔ ስኮላሪ የሚመራው የብራዚል ብሄራዊ ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ ግሩም ጨዋታ ሲያሳይ በሁለተኛው አጋማሽ ግን ትልቅ ድክመት ታይቶበታል። በዚሁ የተነሣም ተመልካቾች «አህያ» «አህያ» እያሉ ሲሳደቡ እስከመሰማት ነበር የደረሰው።

የመሃል ሜዳ ተጫዋቹ ፓውሊኞ በ 82ኛዋ ደቂቃ ላይ ሁለተኛዋን ጎል በማስቆጠር ውጤቱን ባያስተካክል ኖሮ ብራዚል ለሽንፈት በበቃችም ነበር። የተመልካቹ ቁጣ ለብራዚል ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች በፊታችን 2014 የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በራስ ሜዳ የመጫወትን ያህል የሚያዝናና እንደማይሆን ምልክት መሆኑ አልቀረም።

ለሚቀጥለው ዓመት የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ እንደ ማሟሟቂያ ሆኖ የሚታየው የስምንት አህጉራዊ ሻምፒዮን ቡድኖች ውድድር የፊታችን ቅዳሜ ሣምንት በዚያው በብራዚል የሚከፈት ሲሆን ውድድሩ ለአስተናጋጇ አገር የተሻለ ጨዋታ ለማሳየት እንደገና መልካም አጋጣሚ የሚሆን ነው። እርግጥ ይህ እንዲሳካ የትናንቱ ድክመት እንዳይደገም ማድረጉግድ ነው የሚሆነው። በነገራችን ላይ የኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ተሳታፊ ስምንት ሃገራት ከብራዚል ጋር ጃፓን፣ ሜክሢኮ፣ ኢጣሊያ፣ ስፓኝ፣ ኡሩጉዋይ፣ ታሂቲና ናይጄሪያ ይሆናሉ።

Fußball Freundschaftsspiel USA Deutschland
ምስል picture-alliance/dpa

ወደ ወዳጅነቱ ግጥሚያዎች እንመለስና በትናንትናው ምሽት ዩ ኤስ አሜሪካም የጀርመንን ብሄራዊ ቡድን ባልተጠበቀ ሁኔታ 4-3 ለማሸነፍ በቅታለች። የጀርመን ቡድን ምንም እንኳ አንዳንድ መደበኛ ተጫዋቾቹ ቢጎሉትም ከመጠን በላይ ድክመት ታይቶበታል። የአሜሪካ ብሄራዊ ቡድን አጨዋወት በአንጻሩ ቅልጥፍናና ሕይወት የሰመረበት ነበር። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ለቶተንሃም ሆትስፐር የሚጫወተው ዴምፕሴይም ሁለት ጎሎችን በማስቀጠር የቡድኑ ድንቅ አጥቂ ነበር። በጀርመናዊው አሠልጣን በዩርገን ክሊንስማን የሚመራው የዩ ኤስ ቡድን የጀርመኑ ብሄራዊ ቡድን አንገቱን ደፍቶ ወደ በጋ ዕረፍቱ እንዲሰናበት ነው ያደረገው።

በተጨማሪ በትናንትናው ዕለት ተካሂደው በነበሩ ሌሎች የወዳጅነት ግጥሚያዎች አየርላንድ ጆርጂያን 2-0፤ ደቡብ አፍሪቃ ከሌሶቶ 2-0 እና እሥራኤልም እንዲሁ ሆንዱራስን በተመሳሳይ ውጤት ስትረታ ኡክራኒያና ካሜሩን ደግሞ 0-0 ተለያይተዋል። በተቀረ በነገው ዕለት በእሢያ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። እነዚሁም በምድብ-አንድ ካታር ከኢራንና ሊባኖስ ከደቡብ ኮሪያ ሲሆኑ በምድብ-ሁለት የሚገናኙት ኦማን ከኢራቅና ጃፓን ከአውስትራሊያ ናቸው።

ከዚሁ በኋላ ሌሎች ሁለት ግጥሚያዎች የሚከተሉ ሲሆን ሁለቱ አሸናፊ ቡድኖች በቀጥታ ለፍጻሜ የሚያልፉ ናቸው። በአፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያም የሚቀጥሉት ሁለት ሣምንታት ወደ መጨረሻዎቹ አሥር ቡድኖች ዙር ለመሻገር ወሣኝነት አላቸው። የሰሜን አፍሪቃ ሃገራት በቅርቡ የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ለመጀመሪያ ጊዜ እስከ ሩብ ፍጻሜ እንኳ መድረስ ሲሳናቸው አሁን ለዓለም ዋንጫ በመካሄድ ላይ ባለው ማጣሪያ ግን ጥሩ ዕርምጃ እያሳዩ ነው። ቱኒዚያ፣ አልጄሪያና ሊቢያ ዕድላቸውን እንደጠበቁ ሲሆኑ ግብጽም እንደ አይቮሪ ኮስት፣ ካሜሩን ወይም ጋና ሁሉ ወደፊት የመዝለቅ ዕድሏ ከፍተኛ ነው።

ኢትዮጵያም ቢሆን ምድብ-አንድን በሰባት ነጥቦች ደቡብ አፍሪቃን አስከትላ የምትመራ ሲሆን በፊታችን ሰንበት ከቦትሱዋናና ከዚያም በሣምንቱ ከደቡብ አፍሪቃ በምታደርገው ግጥሚያ ስኬት ካገኘች የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ትሳትፎ ተሥፋዋን ዕውን የማድረግ ዕድሏን ለማጠናከር ትችላለች። የየምድቡ አንደኛ አሥር ሃገራት ለተከታዩ ዙር የሚያልፉ ሲሆን ከነዚሁ የአምሥቱ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ተሳታፊዎች ማንነት በደርሶ መልስ ግጥሚያ የሚለይለት ይሆናል።

FC Bayern München feiert Triple
ምስል picture-alliance/dpa

በዚህ በጀርመን ቀደምቱ ክለብ ባየርን ሙንሺን ባለፈው ቅዳሜ ምሽት የፌደሬሺኑን ዋንጫ በማግኘት በአገሪቱ ሶሥት ሻምፒዮናዎችን በመጠቅለል የመጀመሪያው ሆኗል። ባየርን ዋንጫውን የወሰደው በርሊን ላይ በተካሄደው ፍጻሜ ግጥሚያ ሽቱትጋርትን 3-2 ካሸነፈ በኋላ ነበር። ክለቡ ቀደም ሲል የቡንደስሊጋው ሻምፒዮን ሲሆን ከተል ብሎም በቅርቡ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የዋንጫ ባለቤትነት መብቃቱ የሚታወስ ነው። የሚዩኒኩ ክለብ ሶሥቱንም ሻምፒዮናዎች በመጠቅለል ከኢንተር ሚላን፣ ባርሤሎና፣ ማንቼስተር ዩናይትድ፣ አይንድሆፈን፣ አያክስ አምስተርዳምና ሤልቲክ ቀጥሎ ሰባተኛው የአውሮፓ ክለብ ለመሆን በቅቷል።

በዓለም ላይ ከታላላቆቹ የቴኒስ ውድድሮች አንዱ በሆነው በፓሪስ-ኦፕን በሴቶች ዛሬ የአውስትራሊያ-ኦፕን አሸናፊ ቪክቶሪያ አዛሬንካ የኢጣሊያ ተጋጣሚዋን ፍራንቼስካ ሻቮኔን በፍጹም የበላይነት 6-3, 6-0 በመርታት ወደ ሩብ ፍጻሜው ዙር አልፋለች። የቤላሩሷ አዛሬንካ ቀደም ሲል በሁለተኛው ዙር ጀርመናዊቱን አኒካ ቤክን ስታሸንፍ በፊታችን ረቡዕ የምትገናኘው ከአሜሪካዊቱ ከቤታኒ ማቴክ-ሣንድስ ውይም ከሩሢያዊቱ ከማሪያ ኪሪሌንኮ ይሆናል።

Rafael Nadal French Open 2013
ምስል Reuters

በወንዶች ደግሞ ጀርመናዊው ቶሚይ ሃዝ ሩሢያዊ ተጋጣሚውን ሚሃኢል ዩሽኒን 6-1,6-1,6-3 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ ደርሷል። ቀጣይ ተጋጣሚው የዓለም አንደኛው የኖቫክ ጆኮቪችና የፊሊፕ ኮልሽራይበር አሸናፊ ይሆናል። የሰባት ጊዜው የፓሪስ-ኦፕን አሸናፊ የስፓኙ ራፋኤል ናዳል ቀደም ባለ ግጥሚያው የመረበሽ መንፈስ ሲታይበት ዛሬ ከጃፓናዊው ከካይ ኒሺኮሪ ጋር በሚያደርገው አራተኛ ዙር ግጥሚያ ጥንካሬውን እንደሚያሳይ ይጠበቃል።

ናዳል ዛሬ 27 ዓመት ሲሞላው ወደ ሩብ ፍጻሜው ማለፉ ጠቃሚ የልደት ስጦታው ነው። የስዊሱ ሮጀር ፌደረር ደግሞ በነገው ዕለት ሩብ ፍጻሜ ከፈረንሣዩ ጆ-ዊልፍሪድ-ሶንጋ የሚጋጠም ሲሆን ቀላል ጨዋታ አይጠብቀውም። ፌደረር ለሩብ ፍጻሜ የደረሰው ሌላውን ፈረንሣዊ ጂል ሢሚንን በአምሥት ምድብ ጨወታ በመርታት ነበር። በሴቶች በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቷ የሆነችው አሜሪካዊት ሤሬና ዊሊያምስ የኢጣሊያ ተጋጣሚዋን ሮቤርታ ቪንቺን በአራተኛው ዙር በለየለት ሁለት ምድብ ጨዋታ ስታሸንፍ ቀጣይ የሩብ ፍጻሜ ተጋጣሚዋ ሩሢያዊቱ ስቬትላና ኩዝኔትሶቫ ናት።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ