1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 17 2006

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በጃፓን መዲና በሴቶችና በወንዶች የማራቶን ሩጫ ድል ተቀዳጅተዋል። 22ኛው የሶቺ የክረምት ኦሎምፒክ በደማቅ ሁናቴ ተጠናቋል። የአውሮጳ ኅብረት የእግር ኳስ ማኅበር ድልድል ይፋ ሆኗል። የእግር ኳስ ቡድኖች ጨዋታ ውጤቶችንም እንዳስሳለን።

https://p.dw.com/p/1BEh1
ምስል picture-alliance/dpa

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሴቶች እና በወንዶች የማራቶን ሩጫ ፉክክር ትናንት ጃፓን ዋና ከተማ ቶክዮ ውስጥ ድል ተቀዳጅተዋል። የትናንቱ የማራቶን ውድድር በኢትዮጵያውያን፣ ኬንያውያን እና ጃፓናውያን ብቻ የተደረገ እስኪመስል ድረስ የሶስቱ ሃገራት ሯጮች ከአንድ እስከ አስረኛ ደረጃን ተቆጣጥረዋል። ሩስያዊቷ አትሌት አልቢና ማዮሮባ ብቻ ስድስተኛ በመሆን ከመሀል ልትቀላቀል ችላለች።

በጃፓኑ ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ቲርፊ ፀጋዬ በየነ የራሷን ሠዓት በማሻሻል በ2 ሠዓት ከ 22 ደቂቃ ከ23 ሠከንድ አንደኛ ወጥታለች። ብርሐኔ ዲባባ ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ከቲርፊ ጋር ልዩነቷ የ7 ሠከንድ ነበር። ኬኒያዊቷ ሉሲ ካቡ በ2 ሠዓት ከ24 ደቂቃ ከ16 ሠከንድ ሶስተኛ ደረጃን አግኝታለች። ሌሎች ሁለት የሀገሯ ልጆችም ተከታትለዋት ገብተዋል። ስድስተኛ የወጣችው ሩስያዊቷን አስቀድመው አራት ጃፓናውያን እስከ አስረኛ ደረጃ ይዘዋል።

በወንዶች ማራቶን ኬኒያዊው ዲክሰን ቹምባም የራሱን ሠዓት በማሻሻል በ2 ሠዓት ከ 5 ደቂቃ ከ42 ሠከንድ በማጠናቀቅ አንደኛ ወጥቷል። ኢትዮጵያዊው ታደሰ ቶላ አራት ኬንያውያንን ከኋላው አስከትሎ ከዲክሰን 15 ሠከንድ በመዘግየት በሁለተኛነት አጠናቋል። ታደሰ 2 ሠዓት ከ 5 ደቂቃ ከ57 ሠከንድ ነው ያስመዘገበው። ሌላኛው የሀገሩ ልጅ ዴሬሳ ጪምሳ ሰባተኛ ወጥቷል። ሶስት ጃፓኖች ተከትለውት እስከ አስረኛ ደረጃ ለመያዝ ችለዋል።

የ27 ዓመቱ ኬንያዊ ሯጭ ዲክሰን ቹምባ ትናንት የጃፓኑን ማራቶን በድል ሲያጠናቅቅ ከ2 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው። ዲክሰን ለመጨረሻ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድል የተቀዳጀው እጎአ በ2012 ዓም የኤንድሆቨን ማራቶን ላይ ነበር። ከእዚያን ጊዜ በኋላ በተደረጉ የሩጫ ውድድሮች አንዱንም ጊዜ ሳይቀናው ቀይቷል። ሲማን ቻይና ውስጥ ሰባተኛ፣ ቦስተን እና አምስተርዳም ላይ ደግሞ ስምንተኛ በመሆን ነበር ያጠናቀቀው። በትናንቱ የቶኪዮ ማራቶን ግን ከሁለት ዓመታት በፊት ኤንድሆቨን ላይ ያስመዘገበውን ሠዓት በ 4 ሠከንድ በማሻሻል ለማሸነፍ ችሏል።

Berlin Marathon Männer
ምስል AP
Wladimir Putin und IOC-Chef Thomas Bach
ምስል Reuters

ጀርመን ፍራንክፉርት ውስጥ ትናንት እና ከትናንት በስተያ በተደረገ የአጭር ርቀት ውድድር ሆሚዩ ተስፋዬ በ1550 ሜ እና በ3000ሜ አሸናፊ ለመሆን ችሏል። ሆሚዩ ኢትዮጵያ የተወለደ ሲሆን፤ ነዋሪነቱ ጀርመን ፍራንክፉርት ውስጥ መሆኑ ተዘግቧል።

የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውድድር በደማቅ የመዝጊያ ስነስርዓት ሩስያ ሶቺ ውስጥ ትናንት ተጠናቋል። አርብ ጥር 30 ቀን 2006 ዓም ተጀምሮ ትናንት እሁድ የካቲት 16 ቀን፣ 2006 ዓም በተጠናቀቀው የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች አዘጋጇ ሩስያ 33 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በሠላማዊ ፍልሚያ ኃያልነቷን አመስክራለች። ኖርዌይ 26፣ ካናዳ 25፣ USA 28 እንዲሁም ኔዘርላን 24፣ ጀርመን 19 ሜዳልያዎችን በማግኘት እስከ ስድስተኛ ደረጃ ይዘዋል።

የጀርመን ቡድን 30 ሜዳሊያዎችን ለማግኘት አቅዶ የተነሳ ቢሆንም፤ ዕቅዱ ሳይሰምርለት ቀርቷል። የጀርመን ኦሎምፒክ ስፖርት ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ሚካኤል ቬስፐር ZDF ለተሰኘው የጀርመን የቴሌቪዥን ጣቢያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በቡድናቸው ውጤት መከፋታቸውን ገልፀዋል። «ለእኔ አንድ ቡድን ኳስ ጨዋታ ሲመራ ቆይቶ የማታ ማታ አራት እኩል ሆኖ እንደመለያየት» ነው ብለዋል በመግለጫቸው። የጀርመን ቡድን በሶቺ ኦሎምፒክ የመጀመሪያ ሳምንት ውውድድር በሜዳልያ ብዛት አንደኛ እንደነበር ይታወሳል።

ሩስያ ባሰናዳችው የክረምት ኦሎምፒክ ገናና ሆና በመውጣት ስታሸንፍ ይህ ከ20 ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። የሩስያ የኦሎምፒክ ቡድን 13 የወርቅ፣ 11 የብር እንዲሁም 9 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ነው አሸናፊነትን የተጎናፀፈው።

በኦሎምፒክ ስፖርት ውድድሩ የተከለከሉ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገሮችን የተጠቀሙ ስፖርተኞችን በመመርመሩ ሂደት ላይ ቅሬታ ሲንፀባረቅም ተስተውሎዋል። አንዳንድ ሃገራት በቸልታ ታልፈዋል በሚልም ወቀሳ ቀርቧል። ለአብነት ያህል ለወራት የተቃውሞ ሰልፍ የናጣት ዩክሬይን ስፖርተኞች የተከለከሉ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገሮችን ሳይጠቀሙ እንዳልቀሩ ሆኖም ችላ እንደተባሉ ተዘግቧል። የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባሕ የዩክሬይን አትሌቶች ሀገራቸው ምስቅልቅል ሁናቴ ተከስቶባትም ቢሆን ድል ለመቀዳጀት ችለዋል፤ ያ የሚደነቅ ነው ሲሉ የሰጡት አስተያየት አነጋግሯል።

ትናንት በደማቅ ሁናቴ በተቋጨው የሶቺ ኦሎምፒክ የመዝጊያ ስነስርዓት ላይ የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባሕ ተገኝተዋል።


አሁን እግር ኳስ ነክ ዘገባዎችን ነው የምናቀርብላችሁ። የአውሮጳ ኅብረት የእግር ኳስ ማኅበር ተወዳዳሪ ሃገራት ድልድል ታወቀ። ትናንት ፈረንሳይ ኒስ ውስጥ ይፋ በሆነው ድልድል በማኅበሩ ውድድር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የምትካፈለው ንዑሷ ጂብራልትር የሶስት ጊዚ ዋንጫ ባለድል የሆነው የጀርመን ቡድን ከሚገኝበት ምድብ ውስጥ ተደልድላለች። አየርላንድ፣ ፖላንድ፣ ስኮትላንድ እና ጆርጂያ በእዚህ ምድብ ውስጥ ይገኛሉ።

አጠቃላይ የቆዳ ስፋቷ ከ6 ኪሎ ሜትር ስኩዌር የማይልቀውና የአነስተኛ መንደር መጠን ያላት ጂብራልትር በመጀመሪያ ላይ ዕጣው ሲወጣ የተደለደለችው ስፔን ከምትገኝበት ምድብ ውስጥ ነበር። ሆኖም ወዲያውኑ ወደ ሌላ ምድብ እንድትዛወር የተደረገው። የብሪታንያ የሩቅ ግዛት የሆነችው ጂብራልትር የሜዲትራኒያ ባሕርን በመሀከሏ በጠባቡ ዘርግታ አውሮጳን ከአፍሪቃ የምታገናኝ አነስተኛ ወሽመጥ ናት። ይህች የሕዝብ ብዛቷ 30,000 ገደማ የሆነው አነስተኛ ምድር ስፔን እና ብሪታንያን ለዘመናት በይገባኛል ስታጨቃጭቅ የቆየች ንዑስ ሀገር ናት።

ጅብራልትር በምትገንበት ምድብ የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የአውሮጳ ኅብረት የእግር ኳስ ማኅበር ዋንጫን ለሶስት ጊዜያት የወሰደ በመሆኑ ጠንካራው እንደሆነ ተነግሮለታል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮኣሒም ሎቭ ድልድሉን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ ቡድናቸው በምድቡ አሸናፊ በመሆን እንደሚያልፍ ገልፀዋል።

«በስፖርት አይን ሲታይ በጣም አጓጊ ነው፤ ድባቡና ስሜቱም እንደዛው። አየርላንድ እና ስኮትላንድ፤ እነዚህ ሃገራት ላይ ስትጫወት ምን አይነት ድባብ እንዳለው ይታወቃል። እና ምድቡ ለእኛ በጣም አጓጊ ነው። እኛ ምንጊዜም ቢሆን ምድቡን አሸንፈን እንደምናልፍ ጥርጥር የለውም።»

የአውሮጳ ኅብረት የእግር ኳስ ማኅበር ውድድር እያንዳንዳቸው ስድስት ሃገራትን የያዙ ስምንት ምድቦች እና አምስት ሃገራትን ያቀፈ አንድ ቡድን ይገኝበታል።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት ሊቨርፑል ስዋንሲን 1 ለ 3 አሸንፏል። የሊቨርፑል አሰልጣኝ የኳስ ጥበብ እያሳየን በማጥቃት ስልት መጫወታችንን እንቀጥልበታለን ብለዋል። ኒውካስል አስቶን ቪላን፤ ኖርዊች ቶትንሐምን 1, ለባዶ ረትተዋል። ቅዳሜ ዕለት አርሰናል ሰንደርላንድን 4 ለ1 አርበትብቷል፤ ሁል ሲቲ ካርዲፍን 4 ለ ባዶ አንገት አስደፍቷል ። ቸልሲ ኤቨርተንን፣ ማንቸስተር ሲቲ ስቶክ ሲቲን 1 ለ ዜሮ አሸንፈዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ ክሪስታል ፓላስን 2 ለ ባዶ ሲሸኝ ዌስትሐም ሳውዝ ሐምፕተንን 3 ለ 1 ቀጥቷል። ፉልሐም ከዌስት ብሮሚች አንድ ለአንድ አቻ ወጥተዋል።

የደረጃ ሰንጠረዡን ቸልሲ በ60 ነጥብ ይመራል፤ አርሰናል አንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተላል። ማንቸስተር ሲቲ በ57 ነጥብ ሶስተኛ ሊቨርፑል በ56 አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ማንቸስተር ዩናይትድ ከቶትንሐም በአምስት ነጥቦች ዝቅ ብሎ 45 ነጥብ በመያዝ 6 ደረጃን ተቆናጧል።

በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ባየር ሙንሽን ሐኖቨርን ትናንት በሜዳው ሐኖቨር አሬና ስታዲየም ውስጥ 4 ለባዶ ጉድ አድርጎታል። አይንትራኅት ፍታንክፉርት ከቬርደር ብሬመን ጋር ተገናኝቶ ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ከትናንት በስትያ ሌላኛ ው ኃያል ቡድን ባየር ሌቨርኩሰን በዎልፍስቡርግ ሽንፈትን ቀምሷል።

የደረጃ ሰንጠረዡን ባየር ሙንሽን በ62 ነጥብ በመምራት እየገሰገሰ ነው። ባየር ሌቨርኩሰን በ19 ነጥቦች ርቆ በሁለተኛ ደረጃ ይከተላል። ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በ42 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ፤ ሻልካ በ42 አራተና ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በስፔይን ላሊጋ ትናንት ኦሳሱና አትሌቲኮ ማድሪድን 3 ለ ባዶ፤ ባሌንሺያ ግራንዳን 2 ለ1፤ አትሌቲኮ ቢልባዎ ሪያል ቤቲስን 2 ለ ዜሮ እንዲሁም ሴልቪያ ራዮ ቫሌካኖን 1 ለባዶ አሸንፈዋል። ቅዳሜ ኃያሉ ሪያል ማድሪድ ኤልቼን 3 ለ ምንም ሸኝቷል። ጌታፌ ከሴልታቪጎ አንድ እኩል ተለያይቷል።



ማንተጋፍቶት ስለሺ

Auslosung EM-Qualifikation 2016 Gruppe Deutschland
ምስል picture-alliance/dpa
Auslosung EM-Qualifikation 2016 Gruppe Deutschland Löw
ምስል picture-alliance/dpa
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ