1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 21 2001

ባለፈው ቅዳሜ ዮርዳኖስ ርዕሰ-ከተማ አማን ላይ የተካሄደው ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር እንደተጠበቀው በኢትዮጵያና በኬንያ ድል ተፈጽሟል። ሰንበቱ ደቡብ አፍሪቃ በመጪው 2010 ዓ.ም. ለምታስተናግደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ለማለፍ በዓለም ዙሪያ በርካታ ማጣሪያ ግጥሚያዎች የተካሄዱበትም ነበር።

https://p.dw.com/p/HMuv
ምስል Benjamin Wüst

አትሌቲክስ

ባለፈው ቅዳሜ አማን ላይ የተካሄደው የዓለም አገር-አቁዋራጭ ሩጫ ውድድር የአፍሪቃ አትሌቶች በተቀረው ዓለም ላይ እንደገና ልዕልናቸውን ያሳዩበት ሆኖ አልፏል። ውድድሩ የተከናወነው እንደተጠበቀው በኢትዮጵያና በኬንያ አትሌቶች ድል ነው። በዚህ ውድድር የብዙ ጊዜው የሜዳሊያ ባለቤት ቀነኒሣ በቀለ ባይሳተፍም ኢትዮጵያ ሌላ ድል መቺ አላጣችም። ገ/እግዚአብሄር ገ/መድሕን በ 12 ኪሎሜትር ሩጫ የወንዶች አሸናፊ ሆኗል። ኡጋንዳዊው ሞሰስ ኪፕሢሮ ሁለተኛ ሲወጣ ሶሥተኛ የሆነው ከሁለት ዓመታት በፊት ሻምፒዮን የነበረው የኤርትራው አትሌት ዘረሰናይ ታደሰ ነው። በቡድን ኬንያ አንደኛ፤ ኢትዮጵያ ሁለተኛ፤ ኤርትራ ሶሥተኛ!
በሌላ በኩል በሴቶች ውድድር ያለፈው ውድድር ሻምፒዮን የጥሩነሽ ዲባባ በአማን አለመገኘት ለኬንያ ጥሩ የሜዳለያ በር ነው የከፈተው። ኬንያዊቱ ፍሎሬንስ ኪፕላጋት ዕድሉን በመጠቀም በስምንት ኪሎሜትር ሩጫ ለማሸነፍ በቅታለች። ለኬንያ ሴቶች ከ 15 ዓመታት በፊት የአገሪቱ ሯጭ ሄለን ቼፕጌኖ ካሸነፈች ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ድል መሆኑ ነበር። በቅዳሜው ሩጫ ያለፈው ዓመት የኤደንቦሮህ የብር ሜዳይ ተሸላሚ ሌላዋ ኬንያዊት ሊኔት ማዋይ ሁለተኛ ስትወጣ መሰለች መልካሙ ሶሥተኛ ሆናለች። በቡድን ውጤት አሁንም ኬንያ አንደኛ፤ ኢትዮጵያ ሁለተኛ፤ ፖርቱጋል ደግሞ ሶሥተኛ ናት።

በተቀረ የኢትዮጵያ ወጣት አትሌቶች በወንዶችም ሆነ በሴቶች ውድድር ቁንጮ ለመሆን በቅተዋል። በወጣት ወንዶች የ 8 ኪሎሜትር ሩጫ አየለ አብሸሮ የኬንያና የኡጋንዳ ተፎካካሪዎቹን ቲቱስ እምኒሼይንና ሞሰስ ኪቤትን በማስከተል አሸንፏል። በቡድን እዚህም ኬንያ አንደኛ ስትሆን ኢትዮጵያና ኤርትራ ሁለተኛና ሶሥተኛ በመሆን ይከተላሉ። በሴት ወጣቶች 6 ኪሎሜትር ደግሞ ገንዘቤ ዲባባ ያለፈ ድሏን ደግማዋለች። ሁለተኛ ሜርሢይ ቼሬኖ፤ ሶሥተኛ ዣክሊን ቼፕኔጎ፤ ሁለቱም ከኬንያ! በወጣት ሴቶች ውድድር ኢትዮጵያ በቡድንም ቀደምቷ ስትሆን ኬንያ ሁለተኛ ናት፤ ሶሥተኛ ጃፓን!

የአፍሪቃ አትሌቶች በዓለም ክሮስ-ካንትሪይ ውድድሮች በአማኑም ሻምፒዮና የማይደፈሩ ሆነው እንደቀጠሉ በሚገባ ነው ያስመሰከሩት። በሴቶችም ሆነ በወንዶች ባለፉት ዓመታት ደጋግሞ እንደታየው ሁሉ አንድም የሌላ ክፍለ ዓለም አትሌት ቀደምቱን የአፍሪቃ ሯጮች ሊፈታተን አልቻለም። እ.ጎ.አ. ከ 1973 ዓ.ም. ወዲህ በዚሁ ውድድር ከተሰጡት ዘጠኝ መቶ ሜዳሊያዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የተካፈሉት ኬንያና ኢትዮጵያ ናቸው። ኬንያ 262፤ ኢትዮጵያ ደግሞ 222 ሜዳሊያዎችን ለማግኘት በቅተዋል። ሰንጥረዦች እንደሚያሣዩት አውሮፓውያን ለመጨረሻ ጊዜ ለድል የበቁበት ጊዜ በጣሙን ሩቅ ነው። እንግሊዝ በ 1980 የወንዶች የቡድን አሸናፊ ስትሆን የፖልቱጋል ሴቶችም በ 1994 ለዚሁ ክብር በቅተው ነበር።
በተናጠልም እስከ 2004 አንዳንድ ድል መታየቱ አልቀርም። ይሁንና ከዚያን ወዲህ በተለይም የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ሁሉንም ከኋላቸው አስቀርተዋል። የሚቀጥሉት ዓመታት ሂደትም ከዚህ የተለየ የሚሆን አይመስልም። በተረፈ ባለፈው ቅዳሜ ፕራግ ላይ ተካሂዶ በነበረ የግማሽ ማራቶን ውድድር የኬንያ አትሌቶች ፍጹም የበላይነት አሳይተዋል። በወንዶች ሁለት የአገሩን አትሌቶች አስከትሎ በአንደኝነት ሩጫውን የፈጸመው ኮች ኪፕሩቶ ነበር። ኒኮላስ ማንዛ ሁለተኛ፤ ማቲው ኪፕቺርቺር ሶሥተኛ! በሴቶች ሮዛ ኮስጋይ በአዲስ ክብረ-ወሰን ስታሸንፍ፤ ኢሬነ ኩዋምባይና ኪፕኮች ቼፕኮሪር ደግሞ ተከትለዋት ገብተዋል።

በኔዘርላንድ ከተማ ብሩንሱም ትናንት በተካሄደ የአሥር ኪሎሜትር የአደባባይ ሩጫም እንዲሁ ኬንያዊው ሚካህ ኮጎ አዲስ ክብረ-ወሰን ሊያስመዘግብ በቅቷል። የ 22 ዓመቱ ወጣት በአንዲት ሤኮንድ ያህል ያሻሻለው ሃይሌ ገብረ ሥላሴ ከሰባት ዓመታት በፊት አስመዝግቦት የነበረውን ፈጣን ጊዜ ነው። ሌላው ኬንያዊ አብራሃም ቼቢም በግሩም ጊዜ ሁለተኛ ሆኗል።

እግር ኳስ

ያለፈው ሰንበት በዓለም ዙሪያ በርካታ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች የተካሄዱበት ነበር። በደቡብ አሜሪካ ምድብ የሰንበቱ ግጥሚያ ከአካባቢው ሃያላን አገሮች ለአርጄንቲና ሲሰምር ለብራዚል ግን ብዙም አስደሳች አልነበረም። የአርጄንቲና ብሄራዊ ቡድን በአሠልጣኙ በዲየጎ ማራዶና እየተመራ ቬኔዙዌላን 4-0 ሲሸኝ ውጤቱ ከነገ በስቲያ ረቡዕ ላፓዝ ላይ ከቦሊቪያ ጋር ለሚያካሂደው ከባድ ግጥሚያ ተሥፋን የሚያዳብር ሆኖለታል። ብራዚል በአንጻሩ የጨዋታ ድክመት በማሣየት ከኤኩዋዶር 1-1 ብቻ ነው የተለያየችው። በፊታችን ረቡዕ ተጋጣሚዋ የምድቡ መጨረሻ ፔሩ ብትሆንም እንዳትንሸራተት መጠንቀቅ ይኖርባታል።
በሌላ በኩል ኡሩጉዋይ የላቲኑን ምድብ መሪ ፓራጉዋይን 2-0 ስታሸንፍ ኮሎምቢያም ከስድስት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች የግብ ጥም በኋላ ቦሊቪያን በተመሳሳይ ውጤት ረትታለች። ፓራጉዋይ ብትሽነፍም አሥር ቡድኖችን ባቀፈው ምድብ ውስጥ ከ 11 ግጥሚያዎች በኋላ በ 23 ነጥቦች ትመራለች። አርጄንቲና አራት ነጥቦች ወረድ ብላ ሁለተኛ ስትሆን፤ ቺሌ በተመሳሳይ ነጥብ ሶሥተኛ፤ ብራዚል ደግሞ አራተኛ ናት። ከምድቡ የመጀመሪያቹ አራት ቡድኖች ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ በቀጥታ የሚያልፉ ሲሆን አምሥተኛው ከሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ ካራይብ አካባቢ አራተኛ ጋር መጋጠሙ ግድ ነው።

በሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ በኮንካካፍ አካባቢ ማጣሪያ ዩ.ኤስ.አሜሪካ ከኤል-ሣልቫዶር 2-2 ስትለያይ ሜክፒኮ ደግሞ ኮስታሪካን 2-0 በመርታት ከመጀመሪያ ሽንፈቷ አገግማለች። የሜክሢኮ ድል ለስዊድናዊው አሠልጣኝ ለስቬን-ጎራን-ኤሪክሶን ዕፎይታ ነው የሆነው። ትሪኒዳድና ቶባጎ ከሆንዱራስ ደግሞ 1-1 ተለያይተዋል። አሜሪካ ስድሥት ቡድኖችን የጠቀለለውን ምድብ በአራት ነጥብ የምትመራ ሲሆን ሜክሲኮና ኮስታሪካ በሶሥት ነጥብ ይከተላሉ። ከዚህ ምድብ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የሚያልፉት የመጀመሪያዎቹ ሶሥት ቡድኖች ይሆናሉ። አራተኛው ቀደም ሲል እንዳልነው ከደቡብ አሜሪካው አምሥተኛ መፈታተን ይኖርበታል።

የዓለም ዋንጫው ማጣሪያ ግጥሚያዎች በዚህ በአውሮፓም የብዙ ተመልካችን ትኩረት የሳቡ ነበሩ። የአውሮፓ ሻምፒዮን ስፓኝ፤ እንዲሁም እንግሊዝና ኔዘርላንድ አንዲት ነጥብ ሳያስነኩ እንደቀጠሉ ሲሆን ሁለቱ የባልካን አገሮች ሰርቢያና ቦስናም ለፍጻሜ ዙር የመድረስ ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግ ጠቃሚ ዕርምጃ ነው ያደረጉት። ምድብ አምሥት ውስጥ ስፓኝ ቱርክን 1-0 ስታሸንፍ በአምሥት ግጥሚያዎች ሙላውን 15 ነጥቦች በመያዝ በአስተማማኝ ሁኔታ ትመራለች። በነገራችን ላይ የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን ባለፉ ሰላሣ ግጥሚያዎቹ አንዴም አልተሽነፈም። ይህም የልዕልናው መለያ ነው።

በዚህ ምድብ ውስጥ አስደናቂ ነገር ቢኖር ቦስና በሁለተኛው ቦታ ላይ መቀመጧ ነው። ቦስና ቤልጂግን ለዚያውም በሜዳው 4-2 ስታሸንፍ ቅዳሜ ሌሊቱን እስከ ዕሑድ ንጋት ድረስ ብሄራዊ ኩራት ያነሳሳው የአደባባይ ፌስታ ቀልጦ ነው ያደረው። ሣራየቮ ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በሰንደቅ ዓላማና በርችት ተኩስ ከተማይቱን ሲያደምቁ የአውቶሞቢል አጀቡም ማለቂያ ያጣ ነበር።, ቦስና ከነገ በስቲያ ከቤልጂግ ጋር በምታደርገው ግጥሚያ ከቀናት በዕወነት ሕልሟን ዕውን ለማድረግ የምትቃረብ ነው የሚሆነው። ስፓኝም በዚያው ምሽት ከሶሥተኛዋ ከቱርክ ጋር ትጋጠማለች።

በምድብ ሰባት ሌላዋ የባልካን ግዛት ሰርቢያ ሩሜኒያን 3-2 ስትረታ በሶሥት ነጥቦች ልዩነት ትመራለች። ወደ ደቡብ አፍሪቃ ፍጻሜ በሚደረገው ጉዞ ጠቃሚ ዕርምጃ ነው ያደረገችው። ሊቱዋኒያ ምንም እንኳ በፈረንሣይ 1-0 ብትሽነፍም በሁለተኝነት እንደቀጠለች ነው። ፈረንሣይ በዚሁ ምድብ ውስጥ ሶሥተኛ ስትሆን እርግጥ አንድ ጨዋታ ይጎላታል። በአጠቃላይ በምድብ አንድ ግጥሚያዎች ዴንማርክ ከማልታ 3-0፤ ሁንጋሪያ ከአልባኒያ 1-0፤ ፖርቱጋል ከስዊድን ባዶ ለባዶ ሲለያዩ ዴንማርክ ትመራለች።

ምድብ ሁለትን በቀደምትነት የሚመሩት ግሪክና ስዊስ ናቸው። ግሪክ ከእሥራኤል ጋር 1-1 በመለያየቷ እርግጥ በሁለት ነጥብ ልዩነት የመምራት ዕድሏን አጥታለች። በምድብ ሶሥት ፖላንድን 3-2 የረታችው ሰሜን አየርላንድ አመራሩን ስትይዝ በምድብ አራት ጀርመን ቀላል ተጋታሚዋን ሊሽተብሽታይን 4-0 በማሸነፍ በቀደምትነት መገስገስ ቀጥላለች። እንግሊዝም በዓለም ዋንጫው ማጣሪያ እስካሁን ሳትበገር ነው የቆየችው። በአራት ግጥሚያች 12 ነጥቦችን ሰብስባለች። ብሄራዊ ቡድኑ ሰንበቱን በወዳጅነት ጨዋታ ሲያሳልፍ ከነገ በስቲያ የምድብ ስድሥት ተጋጣሚው ኡክራኒያ ትሆናለች።

ኢጣሊያና ኔዘላንድም እንዲሁ በዓለም ዋንጫው ማጣሪያ የቤት ሥራቸውን በስኬት አከናውነዋል። ኢጣሊያ በምድብ ስምንት አምሥተኛ ግጥሚያዋ ሞንቴኔግሮን 2-0 ስትረታ በ 13 ነጥቦች አንደኛ ናት። በዚሁ ምድብ አየርላንድ ከቡልጋሪያ 1-1 ስትለያይ ሁለት ነጥቦች ወረድ ብላ ትከተላለች። ኔዘርላንድም በምድብ ዘጠኝ ስኮትላንድን 3-0 በመሸኘት በሙሉ ነጥብና በሰፊ ልዩነት እየመራች ነው። በተረፈ በእሢያ ማጣሪያ ከብዙ በጥቂቱ ጃፓን ባሕሬይንን 1-0 ስታሽንፍ ሳውዲት አረቢያ ኢራንን 2-1፤ እንዲሁም ሰሜን ኮሪያ አረብ ኤሚሮችን 2-0 ሽኝታለች።
በአፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞው ገና ረጅም ሲሆን ከግጥሚያው ይልቅ የዓለምን ትኩረት ይበልጥ የሳበው ትናንት አቢጃን ውስጥ የስታዲዮም ግምብ ፈርሶ 19 ሰዎች የመሞታቸው አሳዛኝ ዜና ነው። ግምቡ የፈረሰው በተመልካቾች መካከል በተፈጠረ ግብግብ ሳቢያ ሳይሆን አልቀረም። ለማንኛውም 50 ሺህ ተመልካች በታጨቀበት ስታዲዮም ብዙዎች መቁሰላቸውም ሲነገር በአይቮሪ ኮስትና በማላዊ መካከል የተካሄደው ማጣሪያ ግጥሚያም በአስተናጋጇ አገር ድል 5-0 ተፈጽሟል። እርግጥ ሁኔታው አፍሪቃ ውስጥ እንግዳ ነገር አይደለም። የሰው ሕይወት በከንቱ መጥፋት መቀጠሉ ግን ያሳዝናል። አስቆጪ ነው። የዓለምና የአፍሪቃ እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበራት በስታዲዮሞች አስተማማኝ የደህንነት ሁኔታ እንዲረጋገጥ አጥብቀው ግፊት ማድረግ ያለባቸው ነው የሚመስለው።

በመጨረሻም አውስትራሊያ-ሜልበርን ላይ ትናንት በተካሄደው የወቅቱ የመጀመሪያ የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም እንግሊዛዊው ጄንሰን ባተን አሸናፊ ሆኗል። ግጭትና ትርምስ በበዛበት እሽቅድድም ብራዚላዊው ሩበንስ ባሪኬሎ ሁለተኛ ሲወጣ ያለፈው ዓመት ሻምፒዮን ሉዊስ ሃሚልተን ደግሞ በሶሥተኝነት ተወስኗል።

መሥፍን መኮንን
AFP, RTR