1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 10 2001

ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችና የአውሮፓ እግር ኳስ ሻምፒዮና፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሺን የአመራር ችግር!

https://p.dw.com/p/HsmX
የቮልፍስቡርግ ኮከብ ግራፊትና አሠልጣኙ ፌሊክስ ማጋት
የቮልፍስቡርግ ኮከብ ግራፊትና አሠልጣኙ ፌሊክስ ማጋትምስል AP

አትሌቲክስ

የቤይጂንጉ ኦሎምፒክ የሶሥት ክብረ-ወሰኖች ባለቤት ጃማይካዊው ኡሤይን ቦልት ትናንት በሰሜናዊው እንግሊዝ-ማንቼስተር ላይ በተካሄደ የአትሌቲክስ ውድድር በዓለም ላይ እስካሁን ፈጣን የሆነ የ 150 ሜትር ጊዜ በማስመዝገብ አሸንፏል። ቦልት ለዚህ አስደናቂ ድል የበቃው ለዚያውም አስቸጋሪ በሆነ የአየር ሁኔታ ነው። አዘጋጆቹ በዝናብ ሳቢያ በውሃ የተመላውን መሮጫ ማጥራት ነበረባቸው። ጃማይካዊው አትሌት ይህም ሆኖ ግን ሩጫውን ግሩም በሆነ 14,35 ሤኮንድ ጊዜ በመፈጸም 26 ዓመት ያለፈውን ክብረ-ወሰን ለማሻሻል በቅቷል። የቀድሞው ክብረ-ወሰን ባለቤት ኢጣሊያዊው ፒየትሮ ሜኔያ ነበር። በሴቶች 150 ሜትር ሩጫ ያሸነፈችው ደግሞ የኦሎምፒክ 200 ሜትር የናስ ሜዳይ ተሸላሚ የሆነችው የባሃማስ አትሌት ዴቢይ ማኬንዚይ ነበረች።

በመካከለኛ ርቀት የዓለም የማራቶን ክብረ-ወሰን ባለቤት ሃይሌ ገ/ሥላሴ በመንገድ አሥር ኪሎሜትር ሩጫ አሸናፊ ሆኗል። ሃይሌ በነፋስ ግፊት የተነሣ በዚህ ርቀት የዓለም ክብረ-ወሰኑን ለማስመለስ የነበረው ሕልም ግን ዕውን አልሆነለትም። ኬንያዊው ሚካ ኮጎ ባለፈው መጋቢት ወር ሁለተኛ አጋማሽ ላይ የቀድሞውን የሃይሌን ክብረ-ወሰን ማሻሻሉ አይዘነጋም። ለማንኛውም ሃይሌ ሩጫውን በ 27 ደቂቃ ከ 39 ሤኮንድ ሲፈጽም አሊ ዛይድ ከሊቢያ ሁለተኛ፤ እንዲሁም የኡክራኒያው አንጋፋ አትሌት ሤርጌይ ሌቪድ ሶሥተኛ ወጥቷል። ሃይሌ በዚህ ዓመት ይበልጥ የሚያተኩረው በፊታችን ነሐሴ ወር በርሊን ላይ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ነው። የማራቶን ክብረ-ወሰኑን ማስከበር አለበት። በተቀረ በሴቶች አሥር ኪሎሜትር ሩጫ ኬንያዊቱ ቪቪያን ቼሩዮት አሸናፊ ሆናለች።

ባለፈው ቅዳሜ ካሊፎርኒያ ውስጥ ተካሂዶ በነበረ የአዲዳስ-ትራክ-ክላሢክ ከአዳራሽ ውጭ የአትሌቲክስ ውድድር በተለይ ሶሥቱ የዓለም ሻምፒዮኖች በርናርድ ላጋት፣ አሊይሰን ፌሊክስና ጀረሚይ ዋሪነር ገነን ብለው ታይተዋል። ከኬንያ የመነጨው አሜሪካዊ ላጋት በ 1,500 ሜትር ሩጫ ሲያሸንፍ፤ የሎስ አንጀለሷ ፌሊክስ በ 200ሜትር ባለድል ሆናለች። የሚያስደስት ሆኖ በ 5000 ሜትር ሩጫ ደግሞ ድሉ በሴቶችም ሆነ በወንዶች የኢትዮጵያ ነበር። ደጀን ገ/መስቀልና አሄዛ ኪሮስ በየፊናቸው አሸናፊ ለመሆን በቅተዋል።

ሌላው የአትሌቲክስ ዜና የምርኩዝ ዝላይ የዓለም ሻምፒዮን የሆነችው ሩሢያዊት የለና ኢዚምባየቫና የቤይጂንጉ ኦሎምፒክ የአምሥትና አሥር ሺህ ሜትር ሩጫ አሸናፊ ቀነኒሣ በቀለ ከፊታችን ሰኔ እስከ መስከረም በስድሥት ከተሞች በሚካሄደው የጎልደን-ሊግ አትሌቲክስ ውድድር የሚሳተፉ መሆናቸው መረጋገጡ ነው። ሁለቱ ቀደምት አትሌቶች አንድ ሚሊዮን ዶላር በተመደበለት ውድድር እንደሚሳተፉ ዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ሰሞኑን ከሞንቴ-ካርሎ ይፋ አድርጓል። ውድድሩ በበርሊን ጀምሮ፣ በኦስሎ፣ በሮማ፣ በፓሪስና በዙሪክ በመቀጠል በብራስልስ የሚጠቃለል ሲሆን ሙሉውን ሽልማት የሚያገኘው ስድሥቱንም ውድድሮች በአሸናፊነት የሚፈጽመው አትሌት ነው።

እግር ኳስ

የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የዘንድሮ ሻምፒዮና ሰንበቱን ከሞላ-ጎደል በአብዛኛው ለይቶለታል። በቅርቡ በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ ግጥሚያ የሚገናኙት ማንቼስተር ዩናይትድና ባርሤሎና በየፊናቸው የብሄራዊ ዋንጫ ባለቤትነታቸውን ሲያረጋግጡ ኢንተር ሚላንም በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ የኢጣሊያ ሻምፒዮን ሆኗል። በጀርመንና በፈረንሣይም ቮልፍስቡርግና ቦርዶው ለድል እየተቃረቡ ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ኤፍ.ሢ.ባርሤሎና ምንም እንኳ ሰንበቱን በሬያል ማዮርካ 2-1 ቢሸነፍም ለ 19ኛ ጊዜ የአገሪቱን ሊጋ ሻምፒዮንነት አረጋግጧል። ባርሣ ሁለት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ድሉን እንዲያረጋግጥ የረዳው በተለይ የቅርብ ተፎካካሪው ሬያል ማድሪድ በቪላርሬያል 3-1 መሽነፉ ነው። ሬያል በዚሁ ከባርሤሎና በስምንት ነጥቦች ዝቅ ብሎ የሻምፒዮንነት ዕድሉን መዝጋቱ ግድ ሆኖበታል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም ማንቼስተር ዩናይትድ ከአርሰናል ጋር ነርቭ በፈጀ ጨዋታ ባዶ-ለባዶ በመለያየት ለ 18ኛ ድሉ በቅቷል። ይህም በተከታታይ ሶሥተኛ ድሉ መሆኑ ነው። ሊቨርፑል የበኩሉን ግጥሚያ 2-0 ቢያሸንፍም በአራት ነጥብ ልዩነት ከወዲሁ በሁለተኝነት መወሰኑ ግድ ሆኖበታል። የእንግሊዙ ሊጋ ውድድር ሊጠናቀቅ የሚቀረው አንድ ግጥሚያ ብቻ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አም ኢንተር ሚላን ትናንት ሢየናን በአስተማማኝ ሁኔታ 3-0 በመርታት በአጠቃላይ ለ 17ኛና በተከታታይም ለአራተኛ ጊዜ የአገሪቱ ሻምፒዮን ሆኗል። የዘንድሮው ሻምፒዮና ገና ሁለት ግጥሚያዎች ቀርተው የለየለት ሁለተኛው ኤ.ሢ.ሚላን በኡዲኔዘ 2-1 በመሸነፉ ነው። ተመልካቾቹ የዘረኝነት ጩኸት በማስተጋባታቸው የተነሣ ወና በሆነ ስታዲዮሙ እንዲጫወት የተገደደው ጁቬንቱስ ደግሞ ከአታላንታ አቻ-ለአቻ ሲለያይ በሶሥተኝነቱ ቀጥሏል።

በዚህ በጀርመን ቡንደስሊጋ ያለፈውም ሰንበት የዘንድሮውን ባለድል ማንነት ቀድሞ አላበሰረም። በመሆኑም ሻምፒዮናው የሚለይለት በፊታችን ቅዳሜ በሚካሄዱት የመጨረሻ ግጥሚያዎች ነው። ቢሆንም ሃኖቨርን በተለየ ልዕልና 5-0 የሸኘው ቮልፍስቡርግ የሣምንቱ ተጠቃሚ ነበር። ቀደም ሲል ከባየርን ሙንሺን ጋር በነጥብ እኩል የነበረው ቮልፍስቡርግ አሁን በሁለት ነጥቦች ብልጫ ለብቻው ይመራል። ሻምፒዮን ለመሆን በመሠረቱ እኩል-ለእኩል ውጤትም ይበቃዋል።
በአንጻሩ ከሆፈንሃይም ጋር 2-2 በሆነ ውጤት ብቻ የተወሰነው ባየርን ሻምፒዮንነቱን በራሱ አቅም ሊያረጋግጥ አይችልም። ሻምፒዮን ሊሆን የሚችለው በመጨረሻው ዕለት በበኩሉ ግጥሚያ ሽቱትጋርትን ካሽነፈና በአንጻሩ ቮልፍስቡርግ በብሬመን ከተረታ ነው። በነጥብ ከባየርን ሙንሺን ጋር እኩል የሆነው ሶሥተኛው ሽቱትጋርትም ተመሳሳይ ዕድል አለው። በነገራችን ላይ ቮልፍስቡርግ በፊታችን ቅዳሜ ከቀናው ሻምፒዮንነቱ በክለቡ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ነው የሚሆነው።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ዢሮንዲን-ቦርዶው ውድድሩ ሊጠቃለል ሁለት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ሌ-ማንስን 3-2 በማሽነፍ በሶሥት ነጥብ ልዩነት ይመራል። የሣምንቱ ተረቺ በገዛ ሜዳው በሊዮን 3-1 የተሸነፈው ኦላምፒክ ማርሤይ ነው። ሆኖም ጨርሶ አላለቀለትም። በአንጻሩ ለስምንተኛ ዓመት በተከታታይ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን ያልም የነበረው የኦላምፒክ ሊዮን የሻምፒዮንነት ዕድል ሰንበቱን አክትሞለታል።
በተረፈ ሻምፒዮናው ከሣምንታት በፊት በለየባት በኔዘርላንድ ሰንበቱ የፌደሬሺን ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ነበር። ተጋጣሚዎቹ ክለቦች ሄረንፌንና ኤንሼዴ በመደበኛው ጊዜ 2-2 ሲለያዩ ጨዋታው የለየለት በፍጹም ቅጣት ምት ነው። በዚሁም ሄረንፌን 5-4 በመርታት ለመጀመሪያ ጊዜ የኔዘርላንድ ፌደሬሺን ዋንጫ ባለቤት ሊሆን በቅቷል። ከዚሁ ሌላ የፖርቱጋል ሊጋ ውድድር በኤፍ.ሢ.ፖርቶ ሻምፒዮንነት በመጪው ሣምንት የሚጠቃለል ሲሆን በክሮኤሺያ ደግሞ ዲናሞ-ዛግሬብ በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ ሻምፒዮንነቱን አረጋግጧል። የአውሮፓ ሻምፒዮና ሁኔታ ከሞላ-ጎደል ይህን የመሰለ ነበር።
በኢትዮጵያ የአገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሺን ፕሬዚደንት አቶ አሸብር ወ/ጊዮርጊስ በዓመኔታ እጦት ሳቢያ ሥልጣን እንደሚለቁ ባለፈው ቅዳሜ አስታውቀው ነበር። ፌደሬሺኑ በደምቡ መሠረት በሰባት ቀናት ውስጥ አንድ የምርጫ ኮሚቴ መሰየምና ቢዘገይ ከ 45 ቀናት በኋላ አዲስ ምርጫ ማካሄድ ይኖርበታል። የዓለም አግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ ብሄራዊው ፌደሬሺን የአመራር ውዝግቡን ለመፍታት መርሁን ባለመከተሉ ባለፈው መስከረም ወር ኢትዮጵያን ለደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ከሚካሄደው ማጣሪያ ውድድር ማስወጣቱ አይዘነጋም። የአዲስ አበባ ወኪላችን ታደሰ እንግዳው የፌደሬሺኑን ሁኔታ ተከታትሏል።!

ለማጠቃለል ከነገ በስቲያ ረቡዕ ምሽት የዘንድሮው የአውሮፓ እግር ኳስ ፌደሪሺኖች ማሕበር የዩኤፋ ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ይካሄዳል። ለፍጻሜ የደረሱት የጀርመኑ ቬርደር ብሬመንና የኡክራኒያው ሻክታር ዶኔትስክ ሲሆኑ ግጥሚያው የሚካሄደው ቱርክ ውስጥ 54 ሺህ ተመልካች በሚይዘው በፌረንባሸ-ኢስታምቡል ሱክሩ-ሣራኮግሉ-ስታዲዮም ነው። በነገራችን ላይ የዩኤፋ ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ በፊታችን ረቡዕ ሲካሄድ ለ 38ኛ ጊዜ ይሆናል።

DW/RTR/TE

መስፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ