1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሐምሌ 20 2001

ታላቅ ሽልማት በሚያሰጠው የለንደኑ ግራንድ ፕሪ አትሌቲክስ ውድድር፤ ቅዳሜ ኢትዮጵያውያኑ በአሽናፊነት ግርማ ገነው ወጥተዋል።

https://p.dw.com/p/IyAW
ጥሩነሽ አሁንም አሸናፊ ሆናለችምስል picture-alliance/ dpa

የለንደኗ ዘጋቢያችን አትሌቲክሶቹን በቀጥታ ከለንደን አነጋግራ ያቀናበረችውን ዘገባ ይዘናል። እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ዋና፣ ብስክሌት፣ ዝውውር ነክ ዜናዎችና አጫጭር ዘገባዎች የዛሬው የስፖርት ጥንቅራችን ዋነኛ ትኩረቱ ይሆናል።

------

ታላቅ ሽልማት በሚያሰጠው የለንደኑ ግራንድ ፕሪ አትሌቲክስ ውድድር፤ በአምስት ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ልማደኛዋ ጥሩነሽ ዲባባ አሸናፊ ሆነች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ስንታየሁ እጅጉ በዚሁ ውድድር ሁለተኛ ስትወጣ፤ በሶስት ሺህ ሜትር የመሰናክል ውድድር ደግሞ ነፃነት አቻሞ በሶስኛነት ባለድል ሆናለች። ዝርዝሩን ሀና ደምሴ ከለንደን ልካልናለች።

ዘገባ፥

ትናንት እሁድ በጣሊያን ሮም ከተማ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮን ውድድር በአራት መቶ ሜትር የነፃ ቀዘፋ ዋና ጀርመናዊው ፓውል ቢደርማን አሸናፊ ሆነ። ቢደርማን ውድድሩን አስደናቂ በሆነ ክብርወሰን እንዳሸነፈም ታውቋል። የነፃ ቀዘፋውን ያጠናቀቀበት የሶስት ደቂቃ ከአርባ ነጥብ ዜሮ ሰባት ሰከንድ ጊዜ ቢደርማን ለሁለት መቶ ሜትር ውድድር የተዘጋጀበት እንደነበረም ገልጿል። ሆኖም አራት መቶ ሜትሩን ለሁለት መቶ ሜትር በተዘጋጀበት ሠዓት ለማገባደድ ተሳክቶለታል።

ድምፅ፥

ለአራት መቶ ሜትር እንደተመዘገብኩና ወደ ውድድሩ እንደተጓዝኩ፤ ምናልባት እስከፍፃሜ እንኳን አትደርስም ብዬ ለራሴ አሰብኩ። በኋላ ላይ ግን በፍፃሜው አንደኛ ነበርኩ። በዚያ ላይ ከክብረ ወሰን ጋር የዓለም ሻምፒዮን መሆን ፈፅሞ በአምሮዬ የሌለነ ነገር ነው።

ትናንት እሁድ በዓለም ሻምፒዮን አስረኛ ቀንና በዋና ውድድር መክፈቻ እለት አጠቃላይ የሜዳሊያ ሰንጠረዡን ቻይና በሃያ ሜዳሊያ ስትመራ ሩስያ በአስራ ሶስት ሁለተኛ እንዲሁም ጀርመን በአምስት ሜዳሊያ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት እሽቅድምድም ሰሞኑን ዋነኛውን የብስክሌት ተወዳዳሪ አሜሪካዊው አርምስትሮንግን እየመራ የነበረው ኮንታደር ውድድሩን የዓመቱ አሸናፊ በመሆን በድል አጠናቀቀ። ለሰባት ዓመታት በተከታታይ አሸናፊ የነበረው አሜሪካዊው አርምስትሮንግ በሃያ አራት ዓመቱ አንዲ ሽሌክም ተቀድሞ በአጠቃላዩ ውድድር በሶስተኛነት አጠናቋል።

አርምስትሮንግ ከሶስት ዓመት ተኩል በኋላ ወደ ውድድሩ በድጋሚ ከመመለሱ አስቀድሞ፤ እ.ኤ.አ. ከሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ አንስቶ እስከ ሁለት ሺህ አምስት ዓ.ም. ድረስ በተከታታይ አሸናፊ እንደነበር ይታወቃል። አሁን ኮንታዶር አሸናፊ መሆኑ ተራው ለስፔኖች የተለቀቀ ይመስላል። ኮንታዶርን ጨምሮ ላለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት እሽቅድምድም አሸናፊዎች ስፔናውያኖች ብቻ ሆነዋል።

ጂንግል፥

አሁን ዝውውር ነክና አጫጭር ስፖርታዊ ዘገባዎችን እናስደምጣለን።

የቀድሞው የዓለም የቦክስ ሻምፒዮን ቬርኖን ፎረስት አሜሪካን ውስጥ ከግማሽ ደርዘን በላይ በሆነ የጥይት ውርጅብኝ ጀርባውን ተደብድቦ ተገደለ። ቬርኖን የተገደለው ነዳጅ ማደያ ውስጥ የጃጉዋር መኪናውን ጎማ አየር እየሞላ ባለበት ቅፅበት ቅዳሜ ለት ነበር። ሊዘርፉት ከተጠጉት ነፍሰ ገዳይ ቀማኞች አንዱን ለማሳደድ ባደረገው ሙከራ እንደተገደለም አትላንታ ጆርናል ኮንስቲቲዩሽን ዘግቧል። ቬርኖን የዛሬ አስራ ሰባት ዓመት ዩናይትድ ስቴትስን ወክሎ በኦሎምፒክ መድረክ ተፋላሚ እንደነበረም ታውቋል። የሰላሳ ስምንት ዓመቱ ቬርኖን በህይወት ዘመኑ ለአርባ አንድ ጊዜያት አሸናፊ ሲሆን፤ ሃያ ዘጠኝ ግዜያት በዝረራ ተሸንፏል።

ጂንግል፥

በጎልደን ካፕ የእግር ኳስ ግጥሚያ ሜክሲኮ ዩናይትድ ስቴትስን በሜዳዋ አምስት ለዜሮ አሸነፈች። ግጥሚያው አሜሪካን ውስጥ የተደረገ ቢሆንም፤ ሰባ ዘጠኝ ሺህ ታዳሚያንን ያስተናገደው ግዙፉ ስታዲየም ከጥግ እስከጥግ የሜክሲኮ ደጋፊ እንደነረም ተዘግቧል። የፊታችን ነሐሴ ስድስት ሜክሲኮ ከተማ ላይ ለመልስ ግጥሚያ ቀጠሮ ተይዟል።

የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዲየጎ ማራዶና ቡድኑን ጥሎ በምንም ተአምር ወደ ፖርትስ ማውዝ እንደማያቀና ገለፀ። ማራዶና ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ ሰማያዊና ነጭ ቀለም በደም ስሬ ውስጥ ይዘዋወራል፤ በፍፁም ብሔራዊ ቡድኑን ጥዬ የትም አልሄድም ሲል ገልጿል። አያይዞም ለቀጣይ ሁለት ዓመታት በአሰልጣኝነት የሚያስቆየውን ስምምነት መፈረሙንም አስታውቋል። ማራዶና የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ሰማያዊና ነጭ ቀለም ማሊያን ለብሶ ባንድ ወቅት በእግር ኳስ ሜዳዎች ውስጥ ተዓምር ይሰራ እንደነበር አይዘነጋም።

በሌላ ዜና ደግሞ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አንበል ጆን ቴሪ ቸልሲን ሊለቅ ነው መባሉ አሉባልታ እንደሆነ ተገለፀ። የሃያ ስምንት ዓመቱ ጆን ቴሪ ቸልሲን የተላቀለው ገና የአስራ አራት ዓመት ታዳጊ ሳለ እንደነበር ይታወቃል። ቴሪ እኔ ሁሉ ነገሬን ለቸልሲ የሰጠሁ ነኝ። ሁሌም ለቸልሲ ነኝ፤ ለኔ ቡድኔን መልቀቅ የማይታሰብ ነገር ነው ሲል እቅጩን ተናግሯል።

የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ራፋኤል ቤኒቴዝ፤ ዣቢ አሎንሶ ሊቨርፑልን ጥሎ እንዳይሄድ ጠየቁ። ከሲንጋፖር ጋር ለነበረው የእሁድ ግጥሚያ አርብ በመለማመጃ ሜዳ አካባቢ ሃያ አንድ የሊቨርፑል ደጋፊዎች በለበሱት ካናቲራ ላይ ዣቢ እባክህ ጥለኸን ወደ ስፔን አትሂድ የሚል ፅሁፍ አድርገው ዣቢ አሎንሶን ተማፅነዋል። አሎንሶን ለማስፈረም ዳር ዳር ሲል የነበረው የስፔኑ ሪያል ማድሪድ አርብ ለት የጌታፌውን ሌላኛው አማካይ ኤስቴባን ግራኔሮን ማስፈረሙ ታውቋል። በእሁዱ የሲዝኑ ቅድመ ማሟሟቂያ ግጥሚያ ሊቨርፑል ሲንጋፖርን አምስት ለዜሮ ረቷል። ሶስት ቀሪ ጨዋታዎች ሲቀሩት፤ የፊታችን እሁድ ከኢስፓኞላ ጋር ለሚኖረው ግጥሚያም ቡድኑ ትናንት ወደ እንግሊዝ ተመልሷል።

በተያያዘ ዜና ማንቸስተር ዩናይትድ የቻይናው ሐንግዝሆን ስምንት ለባዶ በሆነ ሰፊ ልዩነት አሸንፏል። ማንቸስተር እስካሁን የነበሩትን የቅድመ ሲዝኑ የእስያ የማሟሟቂያ አራት ግጥሚያዎች በድል አጠናቋል። ቸልሲ በበኩሉ ኤስ ሚላንን ሁለት ለአንድ ረቷል። በድሉ አዲሱ ጣሊያናዊ አሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ከልብ መርካታቸው ተገልጿል፤ ምንም እንኳን ቸልሲ የቀድሞ ቡድናቸውን ቢረታም ማለት ነው።

ጂንግል፥

አድማጮች እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ዋና፣ ብስክሌት፣ ዝውውር ነክ ዜናዎችና አጫጭር ዘገባዎችን ያስቃኘን የዛሬው የስፖርት ዘገባችን በዚህ ይጠናቀቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ/