1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 18 2001

በርሊን ላይ ለአንድ ሣምንት ሲካሄድ የሰነበተው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር በውጤቱም ሆነ በዝግጅቱ አድናቆትን በማትረፍ ባለፈው ምሽት ተፈጽሟል። ውድድሩ በተለይ በአጭር ርቀት ሩጫ የጃማይካ አትሌቶች ልዕልና የሰመረበት ሆኖ ነው ያለፈው።

https://p.dw.com/p/JHOH
ድንቁ የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮን ቀነኒሣ
ድንቁ የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮን ቀነኒሣምስል AP

በ 12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ላይ ሲሳተፉ የሰነበቱት ከ 201 ሃገራት የመጡ 1,984 ስፖርተኞች ባለፈው ምሽት ከበርሊን ስንብት አድርገዋል። ውድድሩ ሶሥት አስደናቂ ክብረ-ወሰኖች የተመዘገቡበት፤ በዝግጅት ብቃት ረገድም ለአስተናጋጇ አገር አኩሪ ሆኖ ነው የተጠናቀቀው። ጀርመን በመጨረሻ ስድሥተኛ ስትወጣ የብሄራዊው የአትሌቲክስ ማሕበር ፕሬዚደንት ክሌመንስ ፕሮኮፕ አጠቃላዩን የውድድሩን ሂደትና የአገራቸውን ስፖርተኞች ውጤትም አኩሪ ነው ብለውታል።
“አስደናቂ የስፖርት ውጤቶችን ያስከተለው በስታዲዮሙ የታየው መንፈስ ልዩ ነበር። በውድድሩ ሶሥት የዓለም ክብረ-ወሰኖች ተመዝግበዋል። ይህ የሚያሳየው ውድድሩ በአጠቃላይ ከፍተኛ ደረጃ የነበረው እንደሆነ ነው። ከጀርመን አንጻርም ብዙ አስደሳች ውጤቶችን አይተናል። እርግጥም በጠቅላላው ዘጠኝ ሜዳሊያዎች ማግኘታችን ለኛ ግሩም ውጤት ነው”

የመጨረሻው ዕለት ውድድር ትናንት የጀመረው በሴቶች የማራቶን ሩጫ ነበር። በዚሁ ውድድር የቻይና የሃያ ዓመት ወጣት ተሳታፊ ቹዌ ባይ ጃፓናዊቱን ዮሺሚ ኦዛኪንና አሰለፈች መርጊያን ከኋላዋ በማስቀረት አሸናፊ ሆናለች። ቹዌ በማራቶን ስትወዳደር ገና ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ያሳዝናል አሰለፈች መርጊያን ድሉ ያመለጠው ለጥቂት ነው። ቢሆንም በወንዶች ማራቶን እንደሆነው ሁሉ በሶሥተኝነት የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆኗ ራሱ የሚያኮራ ውጤት ነው፤ እንኳን ደስ ያለሽ በርቺ እንላለን።

በሴቶች 1,500 ሜትር ሩጫ የባሕሬይኗ ማርያም-ዩሱፍ-ጃማል አንደኛ ስትወጣ በወንዶች 800 ሜትር ማንም ያልጠበቀው የደቡብ አፍሪቃ ተወዳዳሪ እምቡላኒ ሙላውጂ አሸናፊ ሆኗል። በጦር ውርወራ እንደተጠበቀው የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው የኖርዌዩ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን አንድሬያስ ቶርኪልድሰን ነበር። በሴቶች የርዝመት ዝላይ ደግሞ አሜሪካዊቱ ብሪትኒይ ሪስ የዓለም ሻምፒዮን ሆናለች። በበርሊኑ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ማጠቃለያ ዕለት እርግጥ ታላቁ የወንዶች 5000 ሜትር ሩጫ ነበር።

በዚሁ ሩጫ ድንቁ ቀነኒሣ በቀለ ትግል በተመላበት አስደናቂ ሁኔታ በማሸነፍ በዓለም አትሌቲክስ ውድድር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሥርና የአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ድርብ ድል ባለቤት ለመሆን በቅቷል። ሁለተኛ የአሜሪካው ተወዳዳሪ በርናርድ ላጋት ሲሆን የካታሩ ጀምስ ኩሩዊ ደግሞ ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽሟል። በመካከለኛና ረጅም ርቀት ታላቅ ልዕልና እንዳሳየው እንደ ቀነኒሣ በቀለ ሁሉ የበርሊኑ አትሌቲክስ ውድድር የአጭር ርቀት መንኮራኩርና ድንቅ አትሌት እርግጥ የጃማይካው ዩሤይን ቦልት ነው።

ዩሤይን ቦልት በመቶና በሁለት መቶ ሜትር ሩጫ አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ሲያስመዘግብ በአራት ጊዜ መቶ ሜትር የዱላ ቅብብልም ከአገሩ ቡድን ጋር በማሸነፍ የሶሥት ወርቅ ሜዳሊያዎች ባለቤት ለመሆን በቅቷል። የአትሌቱን ድል ታሪካዊና የማይረሳ የሚያደርገው በተወዳዳሪዎቹ ላይ ያሳየው ፍጹም ልዕልና ነው። መቶ ሜትሩን በ 9,58 ሤኮንድ፤ ሁለት መቶ ሜትሩን ደግሞ በ 19,19 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም በተለይ የመቶ ሜትር ውጤቱን ከርሱ በስተቀር ሊደፍር የሚችል አትሌት ቢቀር በአጭር ጊዜ መገኘቱ ሊያስቡት ያዳግታል።

“ውድድሩ ግሩም ነበር። ሁለት የዓለም ክብረ-ወሰኖች በመሮጤ በራሴ ኮርቻለሁ” ዩሤይን ቦልት!

በዕውነትም የበርሊን አትሌቲክስ ውድድር መድረክ የዩሤይን ቦልት ነበር። ወደ አጠቃላዩ ውጤት እንሻገርና ከ 47 ውድድሮች በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ አሥር ወርቅ፣ ስድሥት ብርና ስድሥት ናስ ሜዳሊያዎች በማግኘት ቀደምት ለመሆን በቅታለች። ጃማይካ በሰባት ወርቅ፣ አራት ብርና ሁለት ናስ በሜዳሊያው ተዋረድ ላይ ሁለተኛውን ስፍራ ስትይዝ ልዕልናዋን ያስመሰከረችው በተለይ በአጭር ርቀት ሩጫ እንደ ቤይጂንጉ ኦሎምፒክ ሁሉ አሜሪካን ከተለመደ የቀደምትነት መድረኳ በማውረድ ነው። አሜሪካ ከሴቶች ሁለት መቶ ሜትር ሩጫ በስተቀር በአጭር ርቀት አንድም የወርቅ ሜዳይ አላገኘችም።

በመካከለኛና ረጅም ርቀት ደግሞ የሃያላኑ አገሮች የኢትዮጵያና የኬንያ ፉክክር በዚህ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኬንያ የበላይነት ለይቶለታል። በተለይም በጥሩነሽ ዲባባ አለመሳተፍ የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ያመለጣቸው የአሥርና የአምሥት ሺህ ሜትር ድል የኬንያ የወንዶች ማራቶን አሸናፊነት ተደምሮበት ለጎረቤቲቱ አገር ምጥቀት በጣሙን ነው የበጀው። ኬንያ በመጨረሻ አራት ወርቅ፣ አምሥት ብርና ሁለት ናስ ሜዳሊያዎች በማግኘት ሩሢያን ዘላ ሶሥተኛ ለመሆን በቅታለች። ይህ ድንቅ ውጤት ለኬንያ ብቻ ሣይሆን በጠቅላላው ለአፍሪቃም አኩሪ ነው።

ኢትዮጵያ ከአስተናጋጇ ከጀርመን ቀጥላ በሁለት ወርቅ፣ ሁለት ብርና አራት ናስ ሰባተኛ ስትወጣ ውጤቱ ምናልባት ከተጠበቀው ይነስ እንጂ የሚያስከፋ አይደለም። ቢቀር ብሪታኒያን፣ ደቡብ አፍሪቃን፣ ኩባንና ቻይናን የመሳሰሉትን አገሮች ከኋላዋ አስቀርታለች። በተለይ ወጣት አትሌቶቿ ለወርቅ ሜዳሊያ ባይበቁም ያሳዩት ግሩም ውጤት ግን ለነገው የተሥፋ ምንጭ የሚሆን ነው። ኢትዮጵያ በዚህም በዚያም በዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ መድረክ ላይ ከቀደምቶቹ አንዷ እንደሆነች ትቀጥላለች።

ለማጠቃለል ከበርሊኑ አትሌቲክስ ውድድር አስገራሚና አሳዛኝ ክስተቶች መካከል አንዱ የምርኩዝ ዝላይ ንግሥት የሚል ቅጽል የተሰጣት ሩሢያዊት የዓለም ሻምፒዮን የለና ኢዚምባየቫ አንዲት ሙከራዋን እንኳ ሳታሳካ ከውድድሩ መውጣቷ ነበር። ማንም ያልጠበቀውን ውድቀቷን ራሷ እንኳ ልታምነው አልቻለችም።

“እንዲሀ ነው ብዬ የምገልጸው ነገር የለም። ሁሉም ነገር የተሟላ ነበር። በራስ መተማመን አልጎደለኝም። ሰውነቴንም በሚገባ ለማሟሟቅ ችያለሁ። ግን ከመዝለያው ፍራሽ ላይ ሳርፍ መሽነፌን ማመን ነው ያቃተኝ”

የበርሊኑ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር እንደ ሌሎች ውድድሮች ሁሉ አይብዛ እንጂ ዶፒንግ ጥላውን ሳያሳርፍበትም አላለፈም። ትናንት በመጨረሻው ዕለት የሞሮኮ የ 1,500 ሜትር ሯጭ ማሪየም-አሎዊ-ሤልሱሊ የተከለከለ አጎልባች መድሃኒት መውሰዷ መረጋገጡ ሲገለጽ ቀደም ሲል ሌላው የሞሮኮ መሰናክል ሯጭ ጃማል ቻትቢና የናይጄሪያዋ አትሌት አማካ ኦጎቡናምም በተመሳሳይ ድርጊት ተይዘው ነበር። የደቡብ አፍሪቃ የሴቶች የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ካስተር ሤሜንያ ወንድ ትሁን ሴት የጾታ ክርክር ማስነሳቱና እስከ ምርመራ መደረሱም የዚህ ሻምፒዮና መለያ ሆኖ አልፏል።

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት ክለቦች ውድድር ያለፈው ዓመት የኢጣሊያ ሻምፒዮን ኢንተር ሚላን ከባሪ ጋር ባካሄደው የመጀመሪያ ግጥሚያው አንድ-ለአንድ ከሆነ ውጤት ሊያለፍ ሳይችል ቀርቷል። በአንጻሩ የከተማ ተፎካካሪው ኤ-ሢ.ሚላን ሢየናን 2-1 በመርታት የተሣካ ጅማሮ አድርጓል፤ ብቻውንም እየመራ ነው። ሁለት ጊዜ ግሩም አቀባበል በማድረግ ለቡድኑ ድል ዋስትና የሆነው ብራዚላዊው ሮናልዲኞ ነበር። ጁቬንቱስ ቱሪንም ቺየቮን 1-0 ሲረታ ፊዮሬንቲናና ቦሎኛ ደግሞ አቻ-ለአቻ ተለያይተዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰንበቱን የአዲሱ ውድድር ወቅት ሶሥተኛ ግጥሚያዎች ሲካሄዱ ቶተንሃም-ሆትስፐር ከ 60ኛዎቹ ዓመታት የድል ዘመን ወዲህ የተሳካ በሆነ አጀማመሩ አንዴም ሳይሸነፍ ከቼልሢይ ጋር አመራሩን እንደያዘ ቀጥሏል። ቼልሢይ ፉልሃምን 2-0 ሲረታ አርሰናልም ፖርትማውዝን 4-1 ሸኝቷል። ሶሥቱ የለንደን ክለቦች አመራሩን ተከታትለው ሲይዙ ማንቼስተር ዩናይትድ ለጊዜው አራተኛ ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሰንበቱ የሊጋው ውድድር ሣይሆን የብሄራዊው ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ነበር። በዚሁ ትናንት በተካሄደው የብሄራዊ ዋንጫ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያም ያለፈው የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑና የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮን ባርሤሎና አትሌቲክ ቢልባዎን 3-0 በማሸነፍ ከሁለቱ ግጥሚያዎች በተገኘው 5-1 አጠቃላይ ውጤት የሱፐር-ካፑ ባለድል ሆኗል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ የሰንበቱ ዋነኛ ተሸናፊ ከሁለተኛ ዲቪዚዮን በወጣው ቡድን በማይንስ 2-1 ተረትቶ ወደ 14ኛ ቦታ ያቆለቆለው የብዙ ጊዜው ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን ነበር። የቡንደስሊጋው ውድድር ሶሥተኛ ግጥሚያው ላይ በመድረስ ገና በአፍላ ሁኔታ ላይ ቢሆንም ቡድኑ እስካሁን ከሁለት እኩል-ለእኩል ውጤትና ሽንፈት አለማለፉ በአዲሱ ሆላንዳዊ አሠልጣኝ በሉዊስ-ፋን-ሃል ላይ ቁጣ እንዳያስነሣ ከወዲሁ አስግቷል።
ሌቨርኩዝን ፍራይቡርግን 5-0 በመቅጣት የሊጋውን አመራር ሲይዝ ሃምቡርግ ደግሞ ያለፈውን ሻምፒዮን ቮልፍስቡርግን 4-2 በማሸነፍ ሁለተኛ ሆኗል። በፈረንሣይ ሊጋ ቦርዶ መላ ሶሥት ግጥሚያዎቹን በማሸነፍ አመራሩን ለብቻው ሲይዝ ኦላምፒክ ሊዮን፣ ፓሪስ-ሣን-ጃርማንና ማርሤይ እያንዳንዳቸው ሰባት ነጥቦች ይዘው ይከተላሉ። በኔዘርላንድ ሻምፒዮና በጎል ብልጫም ቢሆን ፋየኖርድ አመራሩን ከኤንሼዴ ተረክቧል። ያለፈው ሻምፒዮን አልክማር ሶሥተኛ፣ አይንድሆፈን አራተኛ፤ አያክስ አምስተርዳም ስድሥተኛ ናቸው።

የአውቶሞቢል ስፖርት

ስፓኝ-ቫሌንሢያ ላይ ትናንት የተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊ ብራዚላዊው ሩበንስ ባሪቼሎ ሆኗል። ያለፈው ሻምፒዮን የብሪታኒያው ሉዊስ ሃሚልተን ሁለተኛ ሲወጣ ውድድሩን በሶሥተኝነት የፈጸመው የፊንላንዱ ኪሚ ራይኮነን ነው። የጀርመኑ ወጣት ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል በሞተር ብልሽት የተነሣ በ 24ኛው ዙር ላይ ከውድድሩ መውጣቱ ግድ ሆኖበታል። የዓለም ሻምፖዮን ለመሆን ባለው ሕልም ጠቃሚ ነጥቦችን ነው ያጣው። በአጠቃላይ ነጥብ ጄሰን ባተን የሚመራ ሲሆን ባሪቼሎ ሁለተኛ፤ የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር ደግሞ ሶሥተኛ ነው።

ቴኒስ

ትናንት አሜሪካ ውስጥ በተካሄደ የሢንሲናቲ-ማስተርስ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያ የዓለም አንደኛው የስዊስ ተወላጅ ሮጀር ፌደረር አራተኛውን ኖቫክ ጆኮቪችን በሁለት ምድብ ጨዋታ በማሸነፍ በመጪው US-Open ጠንካራው ተወዳዳሪ እንደሚሆን እንደገና አስመስክሯል። ቶሮንቶ ላይ በተካሄደ የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ ሩሢያዊቱ ኤሌና ዴሜንቴቫ የአገሯን ልጅ’ ማሪያ ሻራፖቫን በለየለት ውጤት 6-4, 6-3 በማሸነፍ ለዓመቱ ሶሥተኛ ድሏ በቅታለች።

MM/DW/AFP/dpa

መስፍን መኮንን ፣ ሂሩት መለሰ