1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 16 2002

አግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ዋና!

https://p.dw.com/p/KFZl
ሻልከ-ሃምቡርግ የሣምንቱ ታላቅ ግጥሚያ
ሻልከ-ሃምቡርግ የሣምንቱ ታላቅ ግጥሚያምስል AP

አትሌቲክስ

በዚህ በጀርመን ሣምንቱን በተካሄደ የፍራንክፈርት የማራቶን ሩጫ ኬንያውያን በወንዶችና በሴቶችም አሸናፊ ሆነዋል። በወንዶች ጂልበርት ኪርዋ በ 2 ሰዓት ከ 6 ደቂቃ 14 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ያለፈው ዓመት ባለድል ሮበርት ቼሩዮት ሁለተኛ፤ እንዲሁም ሌላው ኬንያዊ ዊሊያም ኪፕላጋት በሶሥተኝነት ድሉን የተሟላ አድርጓል። በሴቶች ደግሞ አግነስ ኪፕሮፕና ሄለን ኪሙታይ የኬንያን ልዕልና ሲያስመሰክሩ የፖላንዷ ካሮሊና ያርዢንስካ ሶሥተኛ ሆናለች።

የትናንቱ የናይሮቢ ዓለምአቀፍ ማራቶን ውድድርም ድሉ ሙሉ በሙሉ የኬንያውያን ነበር። በወንዶችም ሆነ በሴቶች ከአንድ እስከ ሶሥት ቀደምቱን ቦታ ለመያዝ ችለዋል። በወንዶች ሞሰስ ኪገን ሲያሸንፍ በሴቶች ለድል የበቃችው ኢሬነ የሮቲች ነበረች። ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ደግሞ የአገሪቱ ታዋቂ አትሌት የ 39 ዓመቱ ሊ-ቦንግ-ጁ ዴይጆን ላይ በተካሄደ ብሄራዊ የማራቶን ሩጫ በግሩም ውጤት ስንብት አድርጓል። ሊ በአትላንታ ኦሎምፒክ በሶሥት ሤኮንዶች ብቻ በመቀደም የብር ሜዳይ ተሸላሚ ለመሆን ሲበቃ የቦስተን ማራቶንና የእሢያ ጨዋታ ባለድልም ነበር። በአገሩ ውስጥ ባለው ታዋቂነት ጋብቻውን በሶውል ኦሎምፒክ ስታዲዮም እንዲፈጽም ክብር የተሰጠው አትሌት መሆኑም ይታወቃል።

ብሄራዊ ክብር ስለሚገባቸው አትሌቶች ከተወራ በኢትዮጵያም ከብዙዎቹ አንዷ የሁለት ጊዜዋ የኦሎምፒክ አሥር ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳይ ባለቤት ደራርቱ ቱሉ ናት። የ 37 ዓመቷን ድንቅ አትሌት ማንሣታችን በፊታችን ቅዳሜ በኒውዮርክ ማራቶን ለመሳተፍ መወሰኗን ምክንያት በማድረግ ነው። ደራርቱ ከብዙ ጠንካራ አትሌቶች ጋር ለመፎካከር ቆርጣ በመነሣቷ ልትደነቅ ይገባታል። ኢትዮጵያዊቱ ግሩም አትሌት ከአራት ዓመታት በፊት በኒውዮርክ ማራቶን ስትሣተፍ ለነገሩ ለስፍራው እንግዳ አይደለችም። ያኔ ሩጫውን በአምሥተኝነት ፈጽማለች። አሁንስ? ከወዲሁ መልካም ዕድል እንመኝላታለን!

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የሣምንቱ ግጥሚያ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቼልሢይ ብላክበርን ሮቨርስን 5-0 በመሸኘት አመራሩን ከማንቼሰተር ዩናይትድ ወስዷል። ማንቼስተር ዩናይትድ አመራሩን የለቀቀው በሊቨርፑል 2-0 በመረታቱ ነው። ኤፍ-ሢ.ሊቨርፑል ከአራት ጊዜ ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ቀደምቱን ክለብ በማሸነፍ እንዲያገግም የረዱት ፌርናንዶ ቶሬስና ዴቪድ ንጎግ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ናቸው። ሊቨርፑል አሁን አምሥተኛ ነው። አርሰናል ደግሞ ዌስት ሃም ዩናይትድን ሁለት-ለባዶ ከመራ በኋላ በመጨረሻ 2-2 ቢለያይም ሶሥተኝነቱን እንደያዘ ቀጥሏል። በአጠቃላይ ከፕሬሚየር ሊጉ አሥር ግጥሚያዎች በኋላ ከሊቨርፑል በስተቀር የተቀሩት ቀደምት ክለቦች ሁሉ እንደተጠበቀው ግንባር-ቀደምቱ ናቸው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ባርሤሎና ሣራጎሣን 6-1 በመቅጣት ከዋና ተፎካካሪው ከሬያል ማድሪድ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶሥት ለማስፋት በቅቷል። የዕለቱ የባርሣ ኮከብ ሶሥት ጎሎች ያስቆጠረው የመሃል ሜዳ ተጫዋች ሰይዱ ኬይታ ነበር። የስዊድኑ አጥቂ ዝላታን ኢብራሂሞቪችም ሁለት ጎሎች አስገብቷል። በአንጻሩ ሬያል ማድሪድ ከስፖርቲንግ ጊዮን ባዶ-ለባዶ ነው የተለያየው። ሤቪያም እንዲሁ ከኤስፓኞል ባርሤሎና ጋር ባዶ-ለባዶ ሲለያይ ከሬያል ሶሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ ባለበት፤ በሶሥተኝነቱ እንደጸና ነው። ቫሌንሢያና ዴፖርቲቮ-ላ-ኮሩኛ አንዲት ነጥብ ዝቅ ብለው ይከተሉታል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኢንተር ሚላን ካታኛን 2-1 በማሽነፍ አመራሩን እንደያዘ ቀጥሏል። ጎሎቹን ያስቆጠሩት ሱሌይ ሙንታሪና ዌስሊይ ስናይደር ነበሩ። የዘንድሮው ያልተጠበቀ አስደናቂ ክለብ ሣምፕዶሪያ ቦሎኛን 4-1 ሲሸኝ ሁለተኝነቱን እንደጠበቀ ነው። ከኢንተር የሚለዩት ሁለት ነጥቦች ብቻ ናቸው። ጁቬንቱስ ሢየናን 1-0 አሸንፎ ሶሥተኛ ነው፤ ኤ-ሢ.ሚላንም ቺየቮን 2-1 በመርታት መልሶ ነፍስ ሲዘራ ስድሥተኛው ቦታ ላይ ተቆናጧል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውስጥ አመራሩን የሚሻሙት ቡድኖች ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ በነጥብ እጅግ ተቀራርበዋል። ለዚሁም ምክንያት የሆነው ቀደምቱ ሌቨርኩዝንና ሃምቡርግ ባለፉት ሁለት ግጥሚያዎች ከእኩል-ለእኩል ውጤት ሊያልፉ አለመቻላቸው ነው። በአንጻሩ ከጥቂት ሣምንታት በፊት ስምንተኛ የነበረው ብሬመን አጋጣሚውን በመጠቀም ቀደምቱን ክለቦች በአንዲት ነጥብ ሊቃረብ በቅቷል። ብሬመን ትናንት ቦሁምን 4-1 ሲያሸንፍ አሁን ሶሥተኛ ነው። በተረፈ ሻልከ ባለፈው ምሽት ጠንካራ ግጥሚያ ከሃምቡርግ 3-3 ሲለያይ ከሶሥት ወደ አራት ሸርተት ብሏል። ሆኖም ከብሬመን የምትለየው አንዲት ነጥብ ብቻ ናት። በሣምንቱ ጠንካራ ግጥሚያ ሃምቡርግ በጥሩ አጨዋወቱ አብዛኛውን ጊዜ ባለድል መስሎ ታይቶ ነበር። ይሁንና ሻልከ መልሶ መላልሶ በመነሣት በመጨረሻይቱ ደቂቃ ላይ የጨዋውን ውጤት ሊያስተካክል በቅቷል። እርግጥ የሃምቡርግ አሠልጣን ብሩኖ ላባዲያ በውጤቱ ቅር መሰኘቱ አልቀረም። ቢሆንም ተጫዋቾቹን ላሣዩት ትግል አወድሷል።

“ጨዋታውን አሸንፈን ቢሆን በተገባን ነበር። ግን አሁን ቡድኑ ሁለት ነጥቦች ጥሎ እንደሄደ ነው የሚቆጠረው። የሆነው ሆኖ በጥቅሉ ሲታይ ቡድኑ ያሳየውን ታላቅ ትግል ከፍ አድርጌ ማወደስ ይኖርብኛል”

ከሰንበቱ የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች በኋላ ፍራንክፈርትን፤ እንበል በዕድል 2-1 ያሽነፈው ባየርን ሙንሺን አምሥተኛ ነው። ሆፈንሃይም በቅርብ ይከተለዋል። በተረፈ በፈረንሣይ ሊጋ ቦርዶው ሌ-ማንስን 3-0 በማሸነፍ አመራሩን መልሶ ሲይዝ ሞናኮ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሁለተኛ ቦታ ከፍ ሊል በቅቷል። የኦላምፒክ ማርሤይና የፓሪስ-ሣን-ዣርማን ታላቅ ግጥሚያ በኋለኛው ክለብ ውስጥ በተላላፊው የአሣማ ኢንፍሉዌንዛ የተለከፉ ተጫዋቾች በመገኘታቸው ሳቢያ አልተካሄደም። በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን ደግሞ ቀደምቱ ኤንሼዴና አይንድሆፈን የተመካከሩ ይመስል የየራሳቸውን ግጥሚያዎች 4-0 በማሸነፍ ባሉበት ቀጥለዋል። ሶሥተኛው አያክስ አምስተርዳም ነው።

በደቡብ አሜሪካ አገሮች ሻምፒዮና የብራዚል አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር ከ 31 ግጥሚያዎች በኋላ ለፍጻሜው እየተቃረበ ሲሆን ፉክክሩ እስትንፋስ የሚያሳጣ እየሆነ ሄዷል። ፓልሜይራስ በአንዲት ነጥብ ብልጫ አመራሩን ይዞ እንደቀጠለ ቢሆንም ከአምሥተኛው ክለብ ጋር ያለው የሶሥት ነጥቦች ልዩነት ብቻ ነው። አትሌቲኮ ሚኔይሮ ሁለተኛ፤ ሶሥተኛ ኢንተርናሺናል፣ አራተኛ ደግሞ ሣኦ ፓውሎ ነው። በተለይ ሣኦ ፓውሎ ትናንት በብራዚል ሻምፒዮና ከሣንቶስ ጋር ያካሄደው ግጥሚያ በሰንበቱ ከሁሉም ልብ የሚሰውር ነበር። ሣኦ ፓውሎ 4-3 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ጨዋታው በጎል ፌስታ ተመልካቹን ያስፈነደቀ ሆኖ አልፏል። የሣኦ ፓውሎ በረኛ አንድ ጎል በቅጣት ምት ማስቆጠሩም አዲስ ነገር አይሁን እንጂ አንዱ የግጥሚያው አስደናቂ ገጽታ ነው።

ብራዚልን ካነሣን አይቀር የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ደቡብ አፍሪቃ ለብሄራዊ ቡድኗ ዝግጅት በምታደርገው አሠልጣኝ ፍለጋ ብራዚላዊው ካርሎስ አልቤርቶ ፓሬይራ ከሶሥት ዓመት በፊት በጀመሩበት ሥራቸው እንዲቀጥሉ ልታደርግ ነው። ፓሬይራ የሚተኩት ባለፈው ሰኞ ብሄራዊው ቡድን ስምንት ጉዜ በደረሰበት ሽንፈት የተነሣ ያሰናበታቸውን የአገራቸውን ልጅ ጁዌል ሣንታናን ነው። ፓሬይራ ከብራዚል ጋር አንዴ የዋንጫ ባለቤት ሲሆኑ ኩዌይትን፣ አረብ ኤሚሮችንና ሳውዲያ አረቢያን ጭምር በማሰልጠን ስድሥት ጊዜ በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የተሳተፉ ናቸው። መጪው ዓላማቸው ደቡብ አፍሪቃን ቢቀር ለሁለተኛው ዙር ማብቃት ነው። ከዚያ ወዲያ ያለው ሎተሪ ነው ብለዋል ፓሬይራ!

ዘገባችንን በዋና ለማጠቃለል በዚህ በጀርመን የአገሪቱ የወደፊት ተሥፋ እንደሆነ የሚነገርለት ወጣት ዋናተኛ ሽቴፈን ዳይብለር በ 50 ሜትር በተርፍላይ ስልት ሰንበቱን አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ለማስመዝገብ በቅቷል። ወጣቱ ስፖርተኛ በሌሎች በተለያዩ ስልቶችም ብሄራዊ ሬኮርዶቹን አሻሽሏል።

MM/DW/AFP/RTR/AA