1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 21 2002

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር የመክፈቻው ዙር ተጋጣሚ ምድቦች ዕጣ የሚወጣው በፊታችን አርብ ነው።

https://p.dw.com/p/Kl3p
የደቡብ አፍሪቃ ብሄራዊ ቡድን
የደቡብ አፍሪቃ ብሄራዊ ቡድንምስል AP

ደቡብ አፍሪቃ፣ የዓለም ዋንጫውና የምድቦች ዕጣ

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር የሚሳተፉት 32 አገሮች በስምንት ምድቦች ተደልድለው የጨዋታውን የመጀመሪያ ዙር የሚጀምሩበት ዕጣ በፊታችን አርብ ይወጣል። በመሆኑም በሣምንቱ መጨረሻ የዓለም ዓይን የሚያተኩረው በደቡብ አፍሪቃ ላይ ነው። አፍሪቃ በውድድሩ ደቡብ አፍሪቃ በአስተናጋጅነት ያለ ማጣሪያ በመታከሏ በስድሥት አገሮች የምትወከል ሲሆን በገዛ ክፍለ-ዓለሟ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው ውድድር ዕድሏ ምን ሊሆን ይችላል፤ ማነጋገር የያዘ ጉዳይ ነው። ቢቀር አፍሪቃውያን ከመቼውም የበለጠ ከፍተኛ ውጤት ይጠብቃሉ። ግን ለአፍሪቃ ቡድኖች ከፍተኛ ግምት የሚሰጡት ዓለምአቀፍ ታዛቢዎችም ጭምር ናቸው።
ውድድሩ በአፍሪቃ መካሄዱና የአየሩ ሁኔታ ተስማሚነት አንዱ ምክንያት ሲሆን እርግጥ በሌላ በኩል ክፍለ-ዓለሚቱ ዓለምአቀፍ ከዋክብትን ማፍራቷም የጥንካሬ ምልክት ሆኖ ነው የሚታየው። በአውሮፓ ሊጋዎች ውስጥ ለቁንጮነት የበቁት ዲዲየር ድሮግባ፣ ሣሙዔል ኤቶ፣ ማይክል ኤሢየንና መሰሎቻቸው ዛሬ የዚህ ዕርምጃ መለያዎች በመሆን ይጠቀሳሉ። ከዚሁ ሌላ አብዛኞቹ የሚሳተፉት ቡድኖቹም እንዲሁ የዓለም ዋንጫ ውድድር ልምድ ያፈሩ ናቸው። ካሜሩን በአፍሪቃ አቻ ባልታየለት ሁኔታ በዓለም ዋንጫ ለስድሥተኛ ጊዜ የምትሳተፍ ሲሆን ለናይጄሪያም መጪው አራተኛው ነው። አልጄሪያና ደቡብ አፍሪቃም ሁለት ሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫን አየር ተንፍሰዋል። ቀጣዩ ሶሥተኛቸው ይሆናል ማለት ነው። ሆኖም በወቅቱ ብዙዎች የላቀ ተሥፋ የሚጥሉት ለሁለተኛ ጊዜ በሚሳተፉት በጋናና በአይቮሪ ኮስት ላይ ነው።
የብራዚሉ ታላቅ ኮከብ ፔሌ አፍሪቃ በሃኛው ምዕተ-ዓመት መጨረሻ ላይ የዋንጫ ባለቤት የምትሆን አገር እንደምታፈራ አንዴ መተንበዩ ይታወሣል። ግን እስካሁን ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰ እንኳ የለም። የአፍሪቃን እግር ኳስ እስካሁን ይህም ሆኖ በጥቂቱም ለኩራት ያበቁት ካሜሩንና ሤኔጋል ነበሩ። ካሜሩን ኢጣሊያ ውስጥ ከ 18 ዓመታት በፊት በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር በአስደናቂ ሁኔታ ለሩብ ፍጻሜ ደርሳ በመጨረሻም በሰዓት ጭማሪ በእንግሊዝ ስትገታ ሤኔጋልም ከ 12 ዓመታት በኋላ ተመሳሳይ ደረጃ ላይ መድረሷ ይታወሣል። ባለፈው የጀርመን የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ በአንጻሩ ከአፍሪቃ ጋና ብቻ የመጀመሪያውን የምድብ ዙር ስታልፍ ለዚያውም በመጀመሪያው ጥሎ ማለፍ ግጥሚያ በብራዚል ተሸንፋ ቀድማ ነበር የወጣችው።
በወቅቱ ተሥፋን የሚያዳብር ነገር ቢኖር የአፍሪቃ አገሮች በወጣቶች የዓለም ዋንጫ በተከታታይ የድል ባለቤት ለመሆን መቻላቸው ነው። ለምሳሌ ጋና በቅርቡ ብራዚልን በማሸነፍ ከሃያ ዓመት በታች ወጣቶች የዓለም ዋንጫ ባለቤት ለመሆን መብቃቷ አይዘነጋም። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ባለፈው ሰኔ ወር በተካሄደው የኮን-ፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ደግሞ ግብጽ ኢጣሊያን አሸንፋ ማሰናበቷም ለአፍሪቃ ተሳታፊዎች ይበልጥ በራስ መተማመንን የሚያዳብር ነው። ለማንኛውም በፊታችን አርብ የሚወጣው ዕጣ ይዘት ለአንዱ ወይም ለሌላው የአፍሪቃ ቡድን ወደፊት መራመድ በመጠኑም ቢሆን ወሣኝነት ይኖረዋል። አንድ ወር የሚፈጀው ውድድር የሚካሄደው ከመጪው ሰኔ 4 እስከ ሐምሌ 3 ድረስ ነው።

የምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪቃ ዋንጫ

በዚያው በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም በወቅቱ ኬንያ ውስጥ በሚካሄደው የምሥራቅና ማዕከላዊ አፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ትናንት ሩዋንዳና ሶማሊያ 1-0 ሲለያዩ፤ ኡጋንዳ ታንዛኒያን 2-0፤ እንዲሁም ዛምቢያ ኬንያን በተመሳሳይ 2-0 ውጤት አሸንፈዋል። በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያ ከጂቡቲ፣ ነገ ደግሞ ኤርትራ ከዚምባብዌና ታንዛኒያ ከዛንዚባር ይጋጠማሉ። ወደ ሩብ ፍጻሜው የሚያልፉት የሶሥቱ ምድብ አሸናፊዎች፤ ሁለተኞችና ሁለት ከፍተኛ ነጥብ ያስቆጠሩ ሶሥተኛ ቡድኖች ይሆናሉ።

የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች

በዚሁ ወደ አውሮፓ እንመለስና በስፓኝ ላ-ሊጋ በቀደምቱ ክለቦች በባርሤሎናና በሬያል ማድሪድ መካከል በተካሄደው ግጥሚያ ባርሣ 1-0 በማሸነፍ አመራሩን መልሶ ሊነጥቅ በቅቷል። የግጥሚያውን ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው የስዊድኑ አጥቂ ዝላታን ኢብራሂሞቪች ነበር። የባርሣ ተከላካዮች የሬያሉን ኮከብ ተጫዋች ክሪስቲያኖ ሮናልዶን መላወሻ ሲያሳጡ ቡድኑ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የበላይ ሆኖ ታይቷል። ሬያል በሁለት ነጥብ ልዩነት ዝቅ ብሎ አመራሩን ሲያስረክብ ሤቪያ ሶሥተኛ፤ ቫሌንሢያ አራተኛ፤ ዴፖርቲቮ-ላ-ኮሩኛ አምሥተኛ በመሆን ይከተላሉ።

BdT Spanien La Liga Fußball Madrid gegen Barcelona 29. November 2009
ምስል AP

በእንግሊዝ ፕሬሚየር-ሊግም ሰንበቱ ሁለቱ ሃያል የለንደን ክለቦች ቼልሢይና አርሰናል እርስበርስ የተገናኙበት ነበር። በዚሁ ግጥሚያ ይሁንና ቼልሢይ በለየለት 3-0 ውጤት በማሽነፍ ዘንድሮ በቀላሉ የማይበገር መሆኑን እንደገና አስመስክሯል። ሁለቱን ጎሎች ዲዲየር ድሮግባ ሲያስቆጥር ሶሥተኛዋን ከራሱ ጎል የከተተው የአርሰናል ተጫዋች ቶማስ ፈርሜለን ነበር። ቼልሢይ ከትናንቱ ድል ወዲህ በአምሥት ነጥቦች ልዩነት የሚመራ ሲሆን ፖርትማውዝን 4-1 ያሸነፈው ማንቼስተር ዩናይትድ ፈንጠር ብሎ በሁለተኝነት ይከተለዋል። ቶተንሃም-ሆትስፐር ደግሞ ከኤስተን-ቪላ 1-1 ቢለያይም በሶሥተኝነቱ እንደቀጠለ ነው። አርሰናል አራተኛ፤ ሊቨርፑል አምሥተኛ!

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኢንተር ሚላን ፊዮሬንቲናን ወደ መጨረሻው ባስቆጠራት ጎል 1-0 በመርታት አመራሩን አጠናክሮ ቀጥሏል። በሰባት ነጥቦች ልዩነት እየመራ ነው። በሌላ በኩል ጁቬንቱስ በካልጋሪ 2-0 ተሸንፎ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ሲያቆለቁል ኤ-ሢ.ሚላን በፊናው ካታኛን በተመሳሳይ ውጤት በመርታት ወደ ሁለተኛው ስፍራ ከፍ ብሏል። በውድድሩ መጀመሪያ የሊጋው ቁንጮ በመሆን ብዙዎችን ያስደነቀው ሣምፕዶሪያ በአንጻሩ በጌናዋ ሲሽነፍ በማቆልቆል ሂደቱ እንደቀጠለ ነው። በወቅቱ አራተኛ ነው። በኢጣሊያ ሤሪያ-አ በፊታችን ቅዳሜ ጁቬንቱስና ኢንተር የሚገናኙ ሲሆን ይሄው እጅግ ጠንካራ ግጥሚያ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቀደምቱ ባየር ሌቨርኩዘን የቅርብ ተፎካካሪዎቹን ድክመት በመጠቀም አመራሩን በሶሥት ነጥቦች ልዩነት ለማስፋት በቅቷል። ሌቨርኩዝን ትናንት ግሩም በሆነ ጨዋታ ሽቱትጋርትን 4-0 ሲሸኝ ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው ድንቅ አጥቂው ሽቴፋን ኪስሊንግ ነበር። ቡድኑ እንደ ትናንት አጨዋወቱ ከ 31 ዓመታት የቡንደስሊጋ ተሳትፎ በኋላ ሻምፒዮን ለመሆን ከመቼውም ይልቅ የተቃረበ ነው የሚመስለው። አሠልጣኙ ዩፕ ሃይንከስም ቢሆን ቆጠብ ይበል እንጂ ይህንኑ ማሰቡ አልቀረም።

“የሊጋውን አመራር ያዝን አልያዝን ዛሬ በአብዛኛው ግሩም ጨዋታ ነው የተጫወትነው። ተጋጣሚያችን ደግሞ ተቃሎ መታየት የለበትም። የሽቱትጋርት ቡድን ውጤቱ የሚናገረውን ያህል መጥፎ አይደለም”

እርግጥ ሌቨርኩዝን በሻምፒዮንነት አቅጣጫ መገስገስ መቻሉ በቅርቡ ከክረምቱ እረፍት መልስ በሚጀምረው ሁለተኛ ዙር ውድድር በሚኖረው ጥንካሬ የሚወሰን ይሆናል። ልምድ እንዳሳየው ከሆነ የኋላ ኋላ የሚጠነክሩት በአብዛኛው የሻምፒዮንነት ልምድ ያላቸው ባየርን ሙንሺንን የመሳሰሉ ቡድኖች ናቸው። ያም ሆነ ይህ ሌቨርኩዝንን በሁለተኝነት የሚከተለው ብሬመን ከቮልፍስቡርግ 2-2 ሲለያይ ሻልከ ደግሞ በግላድባህ 1-0 በመሽነፍ በሶሥተኝነት መወሰኑ ግድ ሆኖበታል። ሃምቡርግ ከማይንስ 1-1 ተለያይቶ ወደ አምሥተኛው ቦታ ሲያቆለቁል የሣምንቱ ተጠቃሚ ሃኖቨርን 3-0 አሸንፎ ከስምንት ወደ አራት ከፍ ያለው ባየርን ሙንሺን ነው።

በተቀረ በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ዢሮንዲን-ቦርዶው ናንሢይን 3-0 ሲረታ የሊጋውን አመራር በሁለት ነጥብ ልዩነት ከኦላምፒክ ሊዮን መልሶ ነጥቋል። ኦላምፒክ ሊዮን ከሬንስ ጋር ለዚያውም በገዛ ሜዳው ከአንድ-ለአንድ ውጤት ሊያልፍ አልቻለም። በኔዘርላንድ ሊጋ ትዌንቴ-ኤንሼዴ በተከታታይ አሥረኛ ግጥሚያውን በማሸነፍ በሶሥት ነጥብ ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። ሁለተኛው አይንድሆፈን ነው። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ ሁለቱ የሊዝበን ክለቦች ስፖርቲንግና ቤንፊካ ባዶ-ለባዶ ሲለያዩ ቤንፊካ በወቅቱ የሊጋውን አመራር ይዟል። በቅርብ የሚከተሉት ብራጋና ፖርቶ የሚጋጠሙት ገና ዛሬ ማምሻው ላይ ነው።

USA Sport US Open Tennis Mahesh Bhupathi und Lukas Dlouhy
ምስል AP

አትሌቲክስ፣ ቴኒስ

በኢጣሊያ ከተማ በፍሎሬንስ ትናንት የተካሄደው የወንዶች ማራቶን ሩጫ አሸናፊ ኬንያዊው ቤን ቼቤት ሆኗል። ሌላው ክንያዊ ሩበን ኮስጋይ ሁለተኛ ሲሆን ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመው አሰፋ ግርማ ነው። በሴቶች የአውስትሪያ ተወዳዳሪ ኤቫ-ማሪያ ግራድቮል ስታሸንፍ ደስታ ታደሰ ሁለተኛ፤ እንዲሁም የስዊድኗ ሌና ጋቬሊን ሶሥተኛ ወጥታለች። በአውስትራሊያ የ 15 ኪሎሜትር ታላቅ ሩጫ ደግሞ የአውስትሪያው ጉንተር ቫይድሊንገር ሣሚ ዋንጂሩንና ስቴፋኖ ባልዲኒን የመሳሰሉ ታላላቅ አትሌቶችን ከኋላው በማስቀረት አሸናፊ ሆኗል። ሁለተኛና ሶሥተኛ የወጡት የአስተናጋጇ አገር አትሌቶች ናቸው። የቤይጂንግ ኦሎምፒክ የማራቶን ባለድል ኬንያዊው ዋንጂሩ አራተኛ ሲሆን የአቴኑ ኦሎምፒክ ሻምፒዮን ባልዲኒ ደግሞ ሩጫውን በ 11ኝነት ፈጽሟል። ያለፈው ዓመት አሸናፊ ሃይሌ ገ/ሥላሴ እንደነበር የሚታወስ ነው።

የዘንድሮው የለንደን ዓለምአቀፍ የቴኒስ ፍጻሜ ውድድር በኒኮላይ ዳቪዴንኮ አሸናፊነት ተፈጽሟል። ኡክራኒያ ውስጥ የተወለደው የሩሢያ ተወዳዳሪ ለዚህ ክብር የበቃው የአርጄንቲና ተጋጣሚውን ሁዋን-ማርቲን-ዴል-ፖትሮን በለየለት 6-3, 6-4 ውጤት በማሸነፍ ነው። ዳቪዴንኮ ከፍጻሜ የደረሰው በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቱ የሆኑትን ሮጀር ፌደረርንና ራፋኤል ናዳልን ጭምር በማሸነፍ ነበር። በጥንድ ደግሞ የአሜሪካ መንትዮች ቦብና ማርክ ብራያን የቤላሩስና የእሥራኤል ቅይጥ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

መስፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ