1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 15 2002

እንግሊዝ-በርሚንግሃም ላይ ሰንበቱን ተካሂዶ በነበረው የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች በኬንያ ተፎካካሪዎቻቸው ላይ ፍጹም የበላይነት አሳይተዋል። ይህም ዶሃ ላይ ከሶሥት በኋላ ለሚካሄደው የአዳራሽ ውስጥ የዓለም ሻምፒዮና ተሥፋን የሚያጠናክር ነው።

https://p.dw.com/p/M88r
ጥሩነሽ ዲባባ በኦሎምፒክ ድሏ ወቅትምስል picture-alliance/ dpa

የኢትዮጵያ አትሌቶች ልዕልና በበርሚንግሃም

ባለፈው ቅዳሜ እንግሊዝ-በርሚንግሃም ላይ የተካሄደው የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች ልዕልና እጅግ ጎልቶ የታየበት ነበር። በዚሁ ዓለምአቀፍ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር በተለይም ጥሩነሽ ዲባባ አልፎ አልፎ በተለመደው የሁለት ማይል ሩጫ በአስደናቂ ሁኔታ አሸናፊ ሆናለች። ጥሩነሽ ምንም እንኳ የመሠረት ደፋርን የቆየ ክብረ-ወሰን ለማሻሻል ስድሥት ሤኮንዶች ያህል ቦጎሏትም ሩጫውን ለመፈጸም የፈጀባት 9 ደቂቃ ከ 12,23 ሤኮንድ የወቅቱ ፈጣን ጊዜ ነው። የኦሎምፒኳ ሻምፒዮን ጥሩነሽ ኬንያዊት ተፎካካሪዋን ቪቪያን ቼሩዮትን በሁለተኝነት ስታስከትል ስንታየሁ እጅጉ ደግሞ ሶሥተኛ ወጥታለች። በሴቶች የአንድ-ማይል ሩጫ እንዲያውም የኢትዮጵያ አትሌቶች ድል እጥፍ-ድርብ ነበር። ገለቴ ቡርቃ በዓመቱ ፈጣን ጊዜ 4  ደቂቃ ከ 23,53 ሤኮንድ ሩጫውን በአንደኝነት ስትፈጽም ቃልኪዳን ገዛኸኝ’ ሁለተኛ ሆናለች። ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመችው የባሕሬይኗ ተወዳዳሪ ማሪያም ጃማል ነበረች።                                   
የኢትዮጵያን አትሌቶች የበርሚንግሃም ጥንካሬ ካነሣን አይቀር በወንዶች 1,500 ሩጫም እንዲሁ ደረሰ መኮንን የዓመቱን ፈጣን ጊዜ በማስመዝገብ አሸንፏል። ሁለቱ ዋነኛ የኬንያ ተፎካካሪዎቹ አውጉስቲን ቾጌና ጊዴዮን ጋቲምባ የኋላ ተመልካች ከመሆን ሌላ የተሻለ ዕድል አልነበራቸውም። ከኢትዮጵያ አትሌቶች በኩል ሌላው የአዲስ ክብረ-ወሰን ውጥን ግን ገና ከጅምሩ ገቢር ሣይሆን ቀርቷል። ለዚሁም ምክንያት የሆነው ቀነኒሣ በቀለ በእግር ሕመም ምክንያት በሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ለመወዳደር ከነበረው ዕቅድ መቆጠቡ ነው። ቀነኒሣ በዚህ ርቀት 12  ዓመት የሆነውን የኬንያዊውን አትሌት የዳኒዬል ኮሜንን ክብረ-ወሰን ለማሻሻል ወደፊት ሌላ አጋጣሚን መጠበቅ ይኖርበታል። በበርሚንግሃሙ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር በተለይ በአጭር ሩጫ የአሜሪካ አትሌቶች አየል ብለው ሲታዩ በ 60  ሜትር መሰናክል ኩባዊው የዓለም ሻምፒዮን ዴይሮን ሮብልስ እንደገና የበላይነቱን አስመስክሯል። ኬንያ በሣሚ ሙታሂ የ 3000  ሜትር ድል ብቻ መወሰኑ ግድ ነው የሆነባት። ይህም ዶሃ ላይ የሚካሄደው የዓለም የአዳራሽ ውስጥ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና እየተቃረበ ባለበት ሰዓት ተሥፋን የሚያጠነክር አይደለም።

የሁለቱን የዓለም የመካከለኛና ረጅም ርቀት ቀደምት አገሮች የኢትዮጵያንና የኬንያን ፉክክር ካነሣን ድንቁ የኬንያ አትሌት ፓውል ቴርጋት የአገሩ አሠልጣኞች ኢትዮጵያ በዓለም አገር አቋራጭ ሩጫ ውድድር ላይ ያላትን የበላይነት ለማብቃት የአሠለጣጠንና የማነቃቃት ዘዴያቸውን ማሻሻል እንዳለባቸው ሰሞኑን አጥብቆ እስከማስገንዘብ ነው የደረሰው። የአምሥት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮን ባለፈው ቅዳሜ የኬንያ የአገር አቋራጭ ሩጫ ብሄራዊ ውድድር አኳያ ናይሮቢ ውስጥ ሲናገር ኢትዮጵያውያን ድንኳናችን ውስጥ ገብተው እንዲቆጣጠሩን እያደረግን ነው ሲል ነበር ጠበቅ ያለ ማስጠንቀቂያ የሰነዘረው። ቴርጋት እንዳለው ኬንያ ሁኔታውን ወይም የሃይል ሚዛኑን ለመለወጥ የተለየ ዕቅድና የተቀናበረ ጥረት ሳያስፈልጋት አይቀርም።                                                                      
ለማንኛውም በኬንያው ብሄራዊ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በወንዶች 12  ኪሎሜትር ሩጫ ፓውል ታኑዊ ሲያሸንፍ በወጣቶች 8  ኪሎሜትር ደግሞ ቻርልስ ቼቤት አንደኛ ሆኗል። ከሴቶቹ መካከል በተመሳሳይ ርቀት አሸናፊ የሆኑት ደግሞ ሊኔት ማሣይና ኔሊይ ቼቤት ናቸው። በተረፈ ሣምንቱ ለኬንያ አትሌቲክስ የሃዘንም ነበር። የቀድሞው የኬንያ የመካከለኛ ርቀት ራጭ ዴቪድ ሌሌይ በመኪና አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ አብሮት የነበረው የአንዴው የአሥር ሺህ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ሞሰስ ታኑዊ ደግሞ ከባድ የመቁሰል ጉዳት ደርሶበታል። አደጋው በደረሰበት ወቅት ሁለቱ አትሌቶች ከናይሮቢ ተነስተው ወደ ኤልዶሬት መኖሪያቸው እያመሩ ነበር።

እግር ኳስ፤ የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች/አፍሪቃ

Bundesliga Werder Bremen - Bayer Leverkusen Flash-Galerie
የቡንደስሊጋ ቁንጮ ሌቨርኩዝንምስል AP

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር ለሻምፒዮንነት ከሚፎካከሩት ቁንጮ ክለቦች መካከል በዚህ ሰንበት ውጤቱ የሰመረለት ከሁሉም በላይ ቼልሢይ ነበር። በተቀረ ከኢጣሊያ እስከ ጀርመን ሰንበቱ ለመሪዎቹ ክለቦች ብዙም የስኬት ሣይሆን ነው ያለፈው። በስፓኝ ላ-ሊጋ ባርሤሎና ባለፈው ሣምንት በአትሌቲኮ ማድሪድ ደርሶበት ከነበረው ሽንፈት በማገገም ሣንታንዴርን 4-0 አሰናብቷል። ሬያል ማድሪድም ቪላርሬያልን 6-2 አከናንቦ ሲሸኝ ሁለቱ ክለቦች በሁለት ነጥቦች ልዩነት ተከታትለው ሊጋውን መምራታቸውን እንደቀጠሉ ነው። አንድ ግጥሚያ የሚጎለው ቫሌንሢያ ከሬያል 13 ነጥቦች አቆልቁሎ ሶሥተኛ ሲሆን ማዮርካን 3-1 ያሽነፈው ሤቪያ ደግሞ አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ አራተኛ ነው። እንደ ወቅቱ ሂደት የስፓኝ ሻምፒዮና ሊጋውን ከላይ ወደታች በሚመለከቱት ሁለት ክለቦች መካከል የሚለይለት ነው የሚመስለው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የማስቼስተር ዩናይትድ መሽነፍ ለቼልሢይ ጠቃሚ እመርታ ሆኗል። ማኒዩ ኤቨርተንን ለዚያውም ቀድሞ ከመራ በኋላ በመጨረሻ 3-1 ተረትቶ ከሜዳ ሲወጣ ቼልሢይ በአንጻሩ የአይቮሪ ኮስት ኮከቡ ዲዲየር ድሮግባ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ዎልቨትሃምፕተንን 2-0  በማሽነፍ አመራሩን በአራት ነጥቦች ለማስፋት ችሏል። አርሰናል ደግሞ ሰንደርላንድን 2-0 ሲረታ ከማንቼስተር ዩናይትድ ሁለት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሶሥተኛ ነው። 11  ነጥቦች ወረድ ብሎ ቶተንሃም ሆትስፐር አራተኛ፤ ማንቼስተር ሢቲይ አምሥተኛ፤ ሊቨርፑል ስድሥተኛ!

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ድክመት ማሣየት የጀመረው ኢንተር ሚላን ከሣምፕዶሪያ ባዶ-ለባዶ ብቻ በመለያየቱ አመራሩ ወደ አምሥት ነጥቦች ዝቅ ብሏል። በፊታችን ረቡዕ የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ቼልሢይን የመሰለ ሃያል ተጋጣሚ የሚጠብቀው ኢንተር የተሽነፈው እርግጥ በጎዶሎ በመጫወቱም ነው። የመሃል ሜዳ ተጫዋቾቹ ዋልተር ሣሙዔልና ኢቫን ኮርዶባ ቀይ ካርድ ተሰጥቷቸው ከሜዳ የወጡት ገና በመጀመሪያው አጋማሽ ነበር። ውጤቱ ታዲያ ተከታዮቹን ክለቦች መበጀቱ አልቀረም። ቀስ በቀስ ወደ ላይ መውጣት የያዘው ሮማ ካታኛን 1-0 በመርታት ኢንተርን በአምሥት ነጥቦች ልዩነት ሲቃረብ ኤ-ሢ.ሚላንም ባሪን 2-0  በመሸኘት በሶሥተኝነቱ እንደቀጠለ ነው። ኢንተር ልዕልናውን ማጣቱን ከቀጠለ የለየለት መስሎ የታየ አመራሩን እንዳያስረክብ በጣሙን ያሰጋዋል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቀደምቱ ክለቦች ሌቨርኩዝንና ባየርን ሙንሺን ሁለቱም በእኩል-ለእኩል ውጤት በመወሰናቸው በአመራሩ ላይ የተደረገ ለውጥ የለም። ባየርን ሙንሺን ከቀላል ተጋጣሚው ከኑርንበርግ 1-1 ሲለያይ ከተከታታይ 13 ድሎች በኋላ ምጥቀቱ ተገትቷል። ሌቨርኩዝን በአንጻሩ ጠንከር ያለ ተጋጣሚውን ብሬመንን ከሽንፈት አፋፍ ላይ ካደረሰ በኋላ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረችበት ግብ 2-2 ሆኖ ነው ያለቀለት ድሉን ያጣው። በተረፈ ያለፈው የውድድር ወቅት ሻምፒዮን ቮልፍስቡርግ ሻልከን 2-1 በማሸነፍ በ 12 ተከታታይ ጨዋታዎች ያጣውን ድል ለማረጋገጥ ችሏል። ቮልፍስቡርግ ብራዚላዊ አጥቂው ግራፊት ባስቆጠራቸው ጎሎች ነፍስ ሲዘራ ሻልከን ግን ሽንፈቱ ከአመራሩ ነው የነጠለው። ሆኖም ቀደም ሲል የቮልፍስቡርግ አሁን ደግሞ የሻልከ የሆነው አሠልጣኝ ፌሊክስ ማጋት የቡድኑን ሽንፈት “ነገሩ ሁሌ እንደተለመደው ነበር። እኔ እዚህ ስታዲዮም በተገኘሁበት ጊዜ ሁሉ ቮልፍስቡርግ ነው ያሽነፈው” ሲል በቀልድ ነው የተቀበለው።                                                                                               
ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ሌቨርኩዝንና ባየርን እኩል 49 ነጥብ ሲኖራቸው ሌቨርኩዝን የሚመራው በአንዲት ጎል ብልጫ ብቻ ነው። ሻልከ አራት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሶሥተኛ ሲሆን ሃምቡርግና ዶርትሙንድ ይከተሉታል። የቀደምቱ ሊጋዎች ሁኔታ በዚህ ሣምንት ከሞላ-ጎደል ይህን የመሰለ ነበር፤ በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ደግሞ በነገው ምሽት ሽቱትጋርት ከባርሤሎና፤ እንዲሁም ኦሎምፒያኮስ ፒሬውስ ከዢሮንዲን ቦርዶ ይጋጠማሉ። በማግሥቱ ደግሞ ተራው ሲ.ኤስ,ኬ.ኤ ሞስኮ ከሤቪያና ኢንተር ሚላን ከቼልሢይ ነው።                                                                            

በሌላ በኩል አንጎላ ላይ የተካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ገና የቅርብ ትውስት ሆኖ ሳለ ከአራት አመታት በኋላ ለሚካሄደው ፍጻሜ የማጣሪያው ዕጣ ባለፈው ቅዳሜ ወጥቷል። ኢትዮጵያ በምድብ-ሁለት ውስጥ ከከጊኒ ከማዳጋስካርና ከናይጄሪያ ጋር ስትደለደል እጅግ ከባድ ምድብ ነው የደረሳት። በተረፈ በምድብ-ሰባት የዋንጫው ባለቤት ግብጽና ደቡብ አፍሪቃ የሚገናኙ ሲሆን ካሜሪን፣ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎና ሤኔጋል የተሰለፉበት ምድብ-አምሥትም ጠንካራ የሚባል ነው። በምድብ-አራትም እንዲሁ አልጄሪያ፣ ሞሮኮና ታንዛኒያ አሉ። ኤኩዋቶሪያል ጊኒና ጋቦን በሚያስተናግዱት ፍጻሜ ላይ ከነዚሁ ሌላ 11  የምድብ አሸናፊዎችና ሶሥት ጠንካራ ሁለተኞች፤ በጠቅላላው 16  አገሮች ተሳታፊ ይሆናሉ።

ዓለምአቀፍ ቴኒስ

በሜምፊስ የቴኒስ ሻምፒዮና ትናንት ለፍጻሜ በደረሱት ሁለት አሜሪካውያን መካከል በተካሄደው ግጥሚያ ሣም ኩዌሬይ ጆን ኢስነርን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1  በማሸነፍ ባለድል ሆኗል። ብዌኖስ አይረስ ላይ ደግሞ የቀድሞው የዓለም አንደኛ የስፓኙ ሁዋን-ካርሎስ-ፌሬሮ የአገሩን ልጅ ዴቪድ ፌሬርን በተመሳሳይ ውጤት በመርታት ለሁለተኛ የደቡብ አሜሪካ ድሉ በቅቷል። ፌሬሮ ባለፈው ሣምንት የብራዚል-ኦፕን አሸናፊ እንደነበር ይታወሣል። በዚያው በላቲን አሜሪካ ኮሉምቢያ ውስጥ በተካሄደ የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ ፈረንሣዊቱ ማሪያና ኩኬ ጀርመናዊቱን አንጌሊክ ኬርበርን በማሸነፍ ለመጀመሪያ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ውድድር ድሏ በቅታለች።

MM HM/AFP/RTR