1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 21 2002

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ዛሬ 18ኛ ቀኑን ሲይዝ ከስምንቱ የሩብ ፍጻሜ ዙር ተሳታፊዎች የአራቱ ማንነት ሰንበቱን ለይቶለታል።

https://p.dw.com/p/O55X
የጀርመን ጋዜጦች በድል ማግሥትምስል AP

ኡሩጉዋይና ጋና ወደ ሩብ ፍጻሜው መሻገራቸውን ባለፈው ቅዳሜ ቀድመው ሲያረጋግጡ ትናንት ደግሞ ጀርመንና አርጄንቲና ተከትለዋል። በእነዚህ በኋለኞቹ ሁለት ግጥሚያዎች ውጤት ላይ በተለይም የዳኞች ስህተት የተወሰነ ተጽዕኖ ማድረጉ አልቀረም።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ውድድር ጎልቶ የሚታየው በአንድ በኩል የቀደምቱ የአውሮፓ አገሮች ድክመት ሲሆን በአንጻሩም የላቲን አሜሪካ ጥንካሬ መጨመር ነው። ኡሩጉዋይ ደቡብ ኮሪያን 2-1 አርጄንቲናም ሜክሢኮን 3-1 በማሽነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜው ዙር ሲያልፉ ዛሬ ከብራዚልና ከቺሌ አንዱ፤ እንዲሁም ነገ ፓራጉዋይ ከተሳካላቸው የላቲን አሜሪካ የሩብ ፍጻሜ ተሳታፊዎች አራት ይሆናሉ። ይህም ትልቅ ልዕልና ነው።

በመጀመሪያው የምድብ ዙር ተወስነው ለቀሩት ለፈረንሣይና ለኢጣሊያም ሆነ ብዙም ላልተሻለችው ለእንግሊዝ ውድቀት ምክንያቱ ገና መጤን ቢኖርበትም የዶቼ ቬለ የስፖርት ፕሮግራም ክፍል ባልደረባ ቮልፍጋንግ-ፋና-ካን እንደሚለው ጭብጥ ሆኖ የሚታየው ሃቅ ባረጁት ቡድኖች ላይ በጊዜው ተሃድሶ አለመደረጉ ነው።

“እርግጥ ምክንያቶቹን በውል ለመለየት የያንዳንዱን የነዚህን ቡድኖች ሁኔታ በትክክል ማጥናት ያስፈልጋል። ግን አንድ ነገር ከወዲሁ በግልጽ ይታያል። ይሄውም የሶሥቱም አገሮች ሁኔታ አንድ ዓይነት መሆኑ ነው። በነዚህ ሶሥት አገሮች ቡድኖቹ ያረጁ በመሆናቸው ድክመት ተፈጥሯል። ተጫዋቾችን በተመለከተ ባለፉት ዓመታት በቂ ለውጥ ወይም ተሃድሶ አልተደረገም። በዓለምአቀፉ እግር ኳስ ላይ ከተደረገው ዘመናዊ ዕርምጃ ጋር ራስን ለማጣጣም በቂ ጥረት አለመደረጉም ሌላው ሃቅ ነው። እነዚህ አገሮች በነዚያው ባሏቸው ሰዎችና የቀድሞ ዝና ብቻ ለመቀጠል ነው የሞከሩት። ሌሎቹ ግን በወጣት ተጫዋቾች ተሃድሶ አድርገዋል። ይህ ነው አሁን ለፈረንሣይ፣ ለኢጣሊያና ለእንግሊዝም ወጥመድ የሆነው”

ወደ ሰንበቱ ግጥሚያዎች መለስ እንበልና ኡሩጉዋይ ደቡብ ኮሪያን 2-1 በመርታት ወደ ሩብ ፍጻሜው ስታልፍ ደቡብ ኮሪያ ስንብት ያደረገችው እርግጥ ግሩም ትግል በማሳየት ነው። የኡሩጉዋይ ቡድን እንደ መጀመሪያ ግጥሚያዎቹ ሁሉ ጠንካራ ጨዋታ ሲያሳይ ሁለቱን ጎሎች በማስቆጠር የድሉ ዋስትና የሆነው ድንቁ አጥቂ ሉዊስ ሱዋሬሽ ነበር። የሱዋሬሽ ደስታ ታዲያ ከጨዋታው በኋላም ገደብ አልነበረውም።

“ሊያምኑት የሚያድግት ነው። የሕልምን ያህል ነው። እንደ አንድ ትንሽ ልጅ በዓለም ዋንጫ ውድድር ተሳትፈህ ጎል ማግባት ትመኛለህ። ሊያምኑት ያስቸግራል። አሁን የማየው ያ ሕልም ዕውን መሆኑን ነው”

ጨዋታው በተጀመረ በአምሥተኛው ደቂቃ ላይ የደቡብ ኮሪያ ቡድን ያገኘው ቅጣት ምት የጎሉን ማዕዘን ሲያናጋ ዕለቱ ለኡሩጉዋይ የፈተና መስሎ ነበር። ግን አልሆነም። እንዲያውም በአንጻሩ ኡሩጉዋይ ወዲያው የመጀመሪያ ጎሏን ታስቆጥራለች። የደቡብ ኮሪያ ተጫዋቾች ከእረፍት በኋላ እንደገና ትግላችውን ቢያጠናክሩም ኡሩጉዋይ ግጥሚያው ሊያበቃ አሥር ደቂቃ ሲቀረው ሁለተኛ ጎል አግብታ ሁሉም ይለይለታል።


በፊታችን አርብ የኡሩጉዋይ የሩብ ፍጻሜ ዙር ተጋጣሚ ብችኛዋ የአፍሪቃ ተወካይ ጋና ናት። የጋና ብሄራዊ ቡድን በደመቀ ጨዋታ ዩ.ኤስ.አሜሪካን በተጨማሪ ሰዓት 2-1 ሲረታ በውድድሩ ታሪክ ውስጥ ከካሜሩን ቀጥሎ ለሩብ ፍጻሜው የደረሰው ሁለተኛው የአፍሪቃ ቡድን ሊሆን በቅቷል። ለብላክ-ስታርስ ሁለተኛዋንና ወሣኛን ጎል ያስቆጠረውም አጥቂው አሣሞአህ ጂያን ነበር።

“በዓለም ላይ ደስተኛው ሰው ነኝ። አሜሪካን ካለፈው 2006 ዓ.ም. የዓለም ዋንጫ ወዲህ እንደገና በማሽነፋችን። ግን አሁን አንድ ዙር ለማለፍ ችለናል። እናምደስታዬ ታላቅ ነው”

ኡሩጉዋይና ጋና በፊታችን አርብ በጆሃንስበርግ ሶከር-ሢቲይ ስታዲዮም የሚጋጠሙ ሲሆን የሩብ ፍጻሜው ምሽት የደቡብ አፍሪቃ የኳስ አፍቃሪዎች ጥሩምባ የቩቩዜላ ድምጽ ከመቼውም ልቆ የሚያስተጋባበት እንደሚሆን የሚጠበቅ ነው። ጋና ተሳክቶላት ወደ ግማሽ ፍጻሜው ከዘለቀች በአፍሪቃ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር የመጀመሪያው የአፍሪቃ እግር ኳስ ገናና ታሪክ የሚጻፍበትም ነው የሚሆነው። ማን ያውቃል። አሣሞአህ ጂያን ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ጎሉን አስገብቶ የሚማጸን በሚመስል አይኑ ሰማይ ሰማዩን ሲመለከት ምናልባት ጉዞው ወዴት እንደሆነ ከከዋክብቱ አድምጦ ይሆን? መልሱን አርብ እንደርስበታለን።

በትናንትናው ዕለት ግጥሚያዎች ጀርመን እንግሊዝን በለየለት ሁኔታ 4-1 ስትረታ አርጄንቲና ደግሞ ሜክሢኮን 3-1 አሸንፋለች። ሆኖም በሁለቱም ግጥሚያዎች ላይ ከባድ የዳኞች ስህተት ሲፈጸም ተሸናፊዎቹ ቡድኖች ጎሎቻቸውን ባይከለከሉ ኖሮ ውጤቱ ሌላ መልክ ሊይዝም በቻለ ነበር። በመጀመሪያው ግጥሚያ ጀርመን 2-1 እየመራች እረፍት ስትወጣ ዳኛው ማዕዘን ገጭታ በግልጽ የገባችውን የእንግሊዝ ጎል መስመር አላለፈችም ሲል መሻሩ ብዙዎችን አስገርሟል። የሆነው ሆኖ ቮልፍጋንግ-ፋን-ካን እንደሚለው ጀርመን በዚህም በዚያም ማሽነፉ ባልተሳናት ነበር።

“እርግጥ ነው የዳኛው ስህተት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተጽዕኖ ማድረጉ አልቀረም። ሆኖም ግን በጨዋታው ላይ ይህ ወሣኝ ነበር ብዬ አላምንም። የጀርመን ቡድን በበላይነት ነው የተጫወተው። በአንጻሩ እንግሊዞች በጣም ደካሞች ነበሩ። የጀርመንን ተጫዋቾች ጨርሶ ሊቋቋሙ አልቻሉም። ምናልባት የእንግሊዝ ጎል ተቆጥራ ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ጠባብ ሊሆን በቻለም ነበር። ግን በመጨረሻ ጀርመኖች የተሻሉት ስለነበሩ ማሽነፋቸው የተጠበቀ ነው”


የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን በዚሁ ስንብት ሲያደርግ ጀርመን በፊታችን ቅዳሜ ኬፕ-ታውን ውስጥ የአርጄንቲና ተጋታሚ ናት። አርጄንቲና ትናንት ሜክሢኮን 3-1 ብታሸንፍም የሜክሢኮ ቡድን በመጀመሪያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ያሳየው ቀልጣፋ አጨዋወት ቡድኑን ያስደነገጠ ነበር። ሆኖም አርጄንቲና በባያሻማ ኦፍ-ሣይድ ሁኔታ ድንገት ያስቆጠረቻት የመጀመሪያ ጎል ሁኔታውን ድንገት ይለውጠዋል። የዳኛው ስህተት ሊዋጥላቸው ያልቻለው የሜክሢኮ ተጫዋቾች ከዚያ በኋላ ረግተው ለመጫወት ብዙ ጊዜ ነው የወሰደባቸው። እንደ አጀማመራቸው ጨዋታው ሌላ አቅጣጫን ሊይዝም በቻለ ነበር። ለማንኛውም የአርጄንቲና ቡድን በጣሙን ሃያል ሲሆን ፋ-ካን እንደሚገምተው ጀርመን የማራዶናን ጋውቾዎች አልፋ ለግማሽ ፍጻሜ መድረሷ የማያጠራጥር ነው።

“ከአርጄንቲና ጋር የሚደረገው ግጥሚያ ለጀርመን ከእንግሊዝ ጋር ከታየው ይልቅ በጣም ከባድ ነው የሚሆነው። እዚህ ላይ ምንም ጥርጣሬ የለም። የአርጄንቲና ቡድን እስካሁን ግሩም ጨዋታዎች ነው ያሳየው። በሌላ በኩል በአርጄንቲናና በሜክሢኮ ግጥሚያ በመጀመሪያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ሜክሢኮ በማጥቃትና ግፊት በማድረግ ላይ በነበረበት ጊዜ የአርጄንቲና ተከላካዮች ጥቂት መንገዳገዳቸውን ታዝበናል። የጀርመን ቡድን ይህን ልብ ሊል ይገባል። ቡድኑ በተከላካዮቹ ላይ ግፊቱን በማጠናከር ምናልባት ዕድል ሊያገኝ ይችል ይሆናል”

በተረፈ ፋን-ካንም ሆነ ብዙዎች ታዛቢዎች ወጣቱ የጀርመን ቡድን ለዋንጫ ባለቤትነት ይበቃል የሚል ዕምነት የላቸውም።

“በበኩሌ ይህን ያህል ገፍቼ መሄድ አልፈልግም። ብራዚልንና አርጄንቲናን ነው በጣሙን ጠንካራ አድርጌ የምመለከተው። በዚህም የተነሣ የጀርመን ቡድን ዋንጫዋን ይወስዳል ብዬ አልጠብቅም። ከሆነ በተለየ ሁኔታ ግሩም ጨዋታ ማሳየት መቻል አለበት። አርጄንቲናን ለማሸነፍ ሁሉም ነገር በትክክል መስመር ይኖርበታል። እንደ እኔ አስተሳሰብ ግን አርጄንቲና ለጀርመን ቡድን የመጨረሻዋ ጣቢያ ናት። የጀርመን ቡድን ገና ወጣትና ልምድ የሚጎለው ነው። በተለይ በዚህ ዓይነቱ ውድድር ላይ ደግሞ ልምድ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ለወደፊቱ ግን ለጀርመን እግር ኳስ ወርቃማ ዘመን ነው የሚታየኝ”

ያም ሆነ ይህ የቀሪዎቹ አራት የሩብ ፍጻሜ ተሳታፊ ቡድኖች ማንነት ዛሬና ነገ ይለይለታል። በዚህ ወቅት የኔዘርላንድና የስሎቫኪያ ግጥሚያ የመጀመሪያ አጋማሽ አብቅቶ ሁለተኛው እየተጠበቀ ሲሆን ማምሻውን ደግሞ ብራዚልና ቺሌ ይጋጠማሉ። በነገው ዕለት ፓራጉዋይ ከጃፓኝ፤ እንደሁም ስፓኝ ከፖርቱጋል የሚገናኙ ሲሆን ከዚያም እስከ አርብ ድረስ ጊዜው የዕረፍትና የዝግጅት ነው።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ