1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 3 2003

በአውሮፓ የቀደምቱ የእግር ኳስ ዲቪዚዮኖች ውድድር በዚህ ሰንበትም በደመቀ ሁኔታ ሲቀጥል ነገና ከነገ በስቲያ ደግሞ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የመጀመሪያ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ።

https://p.dw.com/p/PB1k
የባየርን አጥቂ ቶማስ ሙለርምስል AP

ቱርክ-ኢስታምቡል ላይ ሲካሄድ በሰነበተው የዓለም የቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ዩ.ኤስ.አሜሪካ ከዓመታት ቆይታ በኋላ እንደገና ለፍጻሜ ድል በቅታለች። አትሌቲክስ፣ ቴኒስ፣ ቡጢና የፎርሙላ አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድምም በሣምንቱ ትኩረት የተሰጣቸው የስፖርት ዓይነቶች ነበሩ።

በሣምንቱ የአውሮፓ ሊጋዎች ውድድር ባርሤሎናንና ኤ.ሢሚላንን የመሳሰሉት ታላላቅ ክለቦች በትናንሽ ተጋጣሚዎች ለዚያውም በገዛ ሜዳቸው መሸነፋቸው ለደጋፊዎቻቸው አስደንጋጭ ነው የሆነው። ባርሤሎና በሄርኩለስ 2-0 ሲረታ ሚላንም እንዲሁ ከሁለተኛ ዲቪዚዮን በወጣው በቼሴና በተመሳሳይ ውጤት ተሸንፏል። ሁለቱ ክለቦች ነገና ከነገ በስቲያ ለሚካሄደው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የመጀመሪያ የምድብ ዙር ግጥሚያ የሚቀርቡት ምናልባትም በራስ መተማመን ሊጎለው በሚችል ሁኔታ ነው። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በአንጻሩ ቀደምቱ የለንደን ክለቦች ቼልሢይና አርሰናል በቀላሉ በማሸነፍ በስኬት ቀጥለዋል።

ወደ ስፓን ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ እንመለስና ባርሣ በሰንበቱ ክሽፈት ወደ ሰባተኛው ቦታ ሲያቆለቁል አትሌቲኮ ማድሪድና ቫሌንሢያ በሁለተኛ ግጥሚያቸውም በማሽነፍ ሊጋውን በስድሥት ነጥቦች ይመራሉ። አትሌቲኮ ማድሪድ ቢልባዎን 2-1 ሲረታ ቫሌንሢያ ደግሞ ሣንታንዴርን 1-0 ሸኝቷል። በነገራችን ላይ ባርሤሎና በሜዳው ሲሸነፍ ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ ወዲህ ለመጀመሪያ መሆኑ ነው። ሤቪያ ከዴፖርቲቮ-ላ-ኮሩኛ ባዶ-ለባዶ በመለያየት ሶሥተኛ ሲሆን ሬያል ማድሪድም ኦሣሱናን 1-0 በማሸነፍ አራተኝነቱን ይዟል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ያለ ኮከብ አጥቂው ያለ ዌይን ሩኒይ ለማሸነፍ ቀርቦ መታየቱ የሣምንቱ ዓቢይ ዜና የሚሆን መስሎ ነበር። ግን አልሆነም፤ አስተናጋጁ ኤቨርተን ሁለቴ ባለቀ ሰዓት ጎል በማስቆጠር ውጤቱን በመጨረሻ 3-3 ሊያደርግ በቅቷል። ያለፈው የውድድር ወቅት ሻምፒዮን ቼልሢይ በአንጻሩ ዌስት-ሃም-ዩናይትድን 3-1 በመርታት ለፊታችን ረቡዕ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚያ ራሱን አማሙቋል። የጋናው ኮከብ ማይክል ኤሢየን ሁለቱን ጎሎች ሲያስቆጥር ለቼልሢይ የሰንበቱ ድል በአራት ግጥሚያዎች አራተኛው መሆኑ ነው። አርሰናልም ቦልተን ዎንደረርስን 4-1 በማሸነፍ ሁለት ነጥቦች ዝቅ ብሎ በቅርብ ይከተለዋል። በሌላ በኩል ማንቼስተር ሢቲይ፣ ሆትስፐርና ሊቨርፑል በሙሉ በእኩል-ለእኩል ውጤት ነው የተወሰኑት። ሶሥተኛው ማንቼስተር ዩናይትድ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ዘንድሮ ኢንተርን ከአምሥት ዓመት ተከታታይ ሻምፒዮንነት በኋላ ከዙፋኑ ያወርዳል ተብሎ ተሥፋ የተጣለበት ኤ.ሢ.ሚላን ባልተጠበቀ ሁኔታ በቼሴና ተቀጥቶ ተሸማቋል። ስዊድናዊ አጥቂው ዝላታን ኢብራሂሞቪች ዘግይታ የተገኘች ፍጹም ቅጣት ምትን እንኳ ለማስገባት አልቻለም። ኢንተር በአንጻሩ በሣን-ሢሮ ስታዲዮሙ ኡዲኔሰን 2-1 ሲያሸንፍ የድሏን ጎል ያስቆጠረው ካሜሩናዊው ሣሙዔል ኤቶ ነበር። ሮማ ደግሞ ባልተጠበቀ ሁኔታ ባካልጋሪይ 5-1 ተቀጥቶ ተመልሷል። የለየለት ሽንፈቱ የረቡዕ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተጋጣሚውን ባየርን ሙንሺንን የሚያደፋፍር እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። በአጠቃላይ ሁለት ግጥሚያዎቹን በሙሉ በማሸነፍ ሊጋውን የሚመራው ቺዬቮ ቬሮና ነው።

በዚህ በጀርመን ቡንደስሊጋም ከሶሥት ግጥሚያዎች በኋላ ምንም እንኳ የውድድሩ ወቅት ገና በአፍላ ደረጃው ላይ ቢሆንም አመራሩ በሆፈንሃይምና በማይንስ መያዙ ለብዙዎች ያልተለመደ ነገር መሆኑ አልቀረም። ሁለቱ አነስተኛ ክለቦች ቁንጮነቱን የያዙት የእስካሁን ሶሥት ግጥሚያዎቻቸውን በሙሉ በማሸነፍ ነው። ሆፈንሃይም ባለፈው አርብ ሻልከን 2-0 ሲረታ ማይንስም ትናንት ካይዘርስላውተርንን 2-1 አሸንፏል። ሆኖም የማይንስ በረኛ ክሪስቲያን ቬትክሎ ሁኔታው ተጋኖ መታየት የለበትም ባይ ነው።

“እኛ ሁላችንም የቅደም ተከተሉን ሰንጥረዥ አንመለከትም። ይሄ አሁን ገና ከሶሥት ግጥሚያዎች በኋላ ብዙም ጭብጥ ትርጉም የለውም። እርግጥ ሶሥት ድሎች ማግኘት ትልቅ ነገር ነው። ወደታች ላለመውረድ ለምናደርገው ትግል ጠቃሚ ዘጠኝ ነጥቦች ሰብስበናል ለማለት እወዳለሁ”

ሃምቡርግና ሃኖቨር በሁለት ነጥቦች ዝቅ ብለው በሶሥተኝነትና በአራተኝነት ይከተላሉ። ሻልከን ካነሣን ራውልንና ሃንቴላርን በመሳሰሉት የስፓኝና የኔዘርላንድ ዓለምአቀፍ ከዋክብት ራሱን ያጠናከረው ቀደምት ክለብ እስካሁን ያሰበው አልሰመረለትም። በዜሮ ነጥብ 17ኛ ነው። ሌሎቹም ቀደምት የቡንደርሊጋ ክለቦች ባየርንና ብሬመን በሰንበቱ ግጥሚያቸው ባዶ-ለባዶ ሲለያዩ በወቅቱ 10ኛና 11ኛ ናቸው። ውጤቱ በተለይም ባየርን ሙንሺንን ማስከፋቱ አልቀረም። ተከላካዩ ፊሊፕ ላም እንደሚለው ክለቡ በሜዳው አለማሸነፉ የሚቆጭ ነገር ነው።
“በገዛ ሜዳችን 0-0 ከተለያየን በውጤቱ ልንረካ አንችልም። ከመጀመሪያዎቹ ሶሥት ግጥሚያዎች አራት ነጥቦች ብቻ በማግኘታችንም እንዲሁ። ይህ በጅምሩ የጠበቅነው ነገር አልነበረም። ባለፉት ግጥሚያዎች በመሠረቱ የማያጋጥሙ ብዙ ስህተቶችን ነው የሠራነው”

ለነገሩ ያለፉ ልምዶች እንዳሳዩት የሊጋው ገጽታ ከሣምንት ሣምንት እየተቀየረ መሄዱና ቀደምቱ ክለቦች አመራሩን መጨበጣቸው የማይቀር ጉዳይ ነው።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮንም ለዓመታት በቀደምትነት የሚታወቁት ክለቦች ማርሤይ፣ ኦላምፒክ ሊዮን ወይም ቦርዶው በወቅቱ ከታች ወደላይ ተመልካች ሆነው ነው የሚገኙት። ቱሉዝ እስካሁን በተካሄዱት አምሥት ግጥሚያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሽነፍም ሊጋውን በ 12 ነጥቦች በብቸኝነት መምራቱን ቀጥሏል። ሬንስ አንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ሲሆን በአሥር ነጥቦች ሶሥተኛው ሣንት-ኤቲየን ነው።

በኔዘርላንድ ሊጋ ቀደምቱ ክለቦች የሰንበት ግጥሚያቸውን በየፊናቸው ሲያሸንፉ የበላይ እንደሆኑ ቀጥለዋል። አይንድሆፈን ኒይሜኸንን 3-1 እንዲሁም አያክስ አምስተርዳም ቲልቡርግን 2-0 በማሸነፍ በእኩል 13 ነጥቦች ሊጋውን ተከታትለው ይመራሉ። በሁለት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሶሥተኛው ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ትዌንቴ-ኤንሼዴ ነው። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ ፖርቶ ጊማሬሽን በአራት ነጥብ ልዩነት በማስከተል አመራሩን እንደያዘ ቀጥሏል።

በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የምድብ ዙር የመጀመሪያዎቹ ግጥሚያዎች በዚህ ሣምንት ይካሄዳሉ። በምድብ-አንድ ነገ ትዌንቴ ኤንሼዴ ከኢንተር ሚላንና ቬርደር ብሬመን ከቶተንሃም ሆትስፐር የሚገናኙ ሲሆን በስምንት ምድቦች በተከፈለው ዙር ከብዙ በጥቂቱ ኦላምፒክ ሊዮን ከሻልከ፤ ማንቼስተር ዩናይትድ ከሬንጀርስ፤ እንዲሁም ያለፈው ሻምፒዮና ባለድል ባርሤሎና ከፓናቴናኢኮስ አቴን ይጋጠማሉ። በማግሥቱ ረቡዕ ደግሞ ሬያል ማድሪድ ከአያክስ አምስተርዳምና ኦላምፒክ ማርሤይ ከስፓርታክ ሞስኮው ጠንከር ብለው የሚታዩት ግጥሚያዎች ናቸው።

Basketball Türkei USA
ምስል AP

የዩ.ኤስ.አሜሪካ የቅርጫት ኳስ ብሄራዊ ቡድን ትናንት ኢስታምቡል ውስጥ ሲካሄድ የሰነበተው የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ባለድል ሆኗል። ቡድኑ ከ 16 ዓመታት ቆይታ በኋላ ለዚህ ክብር መልሶ የበቃው አስተናጋጇን አገር ቱርክን ግሩም በሆነ አጨዋወት 81 ለ 64 በማሸነፍ ነው። በተለይ 28 ነጥቦችን ያስቆጠረው የ 21 ዓመት ወጣት ኬቪን ደራንት ድንቁ ተጫዋችና የአሜሪካ የድል ዋስትና ነበር። በግማሽ ፍጻሜው በአሜሪካ የተረታው የሊቱዋኒያ ቡድን ሰርቢያን 99 ለ 88 አሸንፎ ሶሥተኛ ሲሆን አርጄንቲና ደግሞ ስፓኝን 86 ለ 81 በመርታት አምሥተኛ ወጥታለች።

በትናንቱ ሰንበት በዚህ በጀርመን የተካሄደው ዘጠነኛ የሙንስተር ከተማ ዓለምአቀፍ የማራቶን ሩጫ ውድድር ደግሞ የኬንያ አትሌቶች ልዕልና የሰመረበት ሆኖ አልፏል። በወንዶች ኬንያዊው ፓትሪክ ሙሪኡኪ ሁለት የአገሩን ልጆች በማስከተል በሁለት ሰዓት ከአሥር ደቂቃ ከ 25 ሤኮንድ አሸንፏል። በሴቶች የቤላሩሷ ተወዳዳሪ ቮልሃ ሤሌቪች አንደኛ ስትወጣ ኬንያዊቱ ትሩፌና ጄፕቹምባ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ዓለም አሸብር ሶሥተኛ ሆናለች። በውድድሩ ከ 31 አገሮች የመጡ 7,500ሯጮች ሲሳተፉ ይህም ለሙንስተር ማራቶን አዲስ ክብረ-ወሰን መሆኑ ነው።

ኢጣሊያ ሞንሣ ላይ በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም የስፓኙ የፌራሪ ዘዋሪ ፌርናንዶ አሎንሶ ሲያሸንፍ የእንግሊዙ ጄሰን ባተን ሁለተኛ፤ እንዲሁም ብራዚላዊው ፌሊፔ ማሣ ሶሥተኛ ሆነዋል። በአጠቃላይ ነጥብ ትናንት ስድሥተኛ የወጣው የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር በ 187 ነጥቦች መምራቱን እንደቀጠለ ነው። በቡጢ ስፖርት ደግሞ የኡክራኒያው ቭላዲሚር ክሊችኮ የናይጄሪያ ተጋጣሚውን ሣሙዔል ፒተርን በአሥረኛው ዙር በመዘረር ሶሥቱንም የዓለም የከባድ ሚዛን ማዕረጎቹን አስከብሯል። ክሊችኮ ገና በሁለተኛው ዙር አካባቢ ተጋጣሚውን በቁጥጥሩ ስር አውሎ እንደነበር ነው የተናገረው።

በዓለም ላይ ታላላቅ ከሚባሉት አንዱ በሆነው የቴኒስ ሻምፒዮና በኒውዮርኩ የዩ-ኤስ.ኦፕን የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያ በጊዜው ሲጠናቀቅ የወንዶቹ ፍጻሜ ግጥሚያ ግን በዝናብ ሳቢያ ተቋርጦ ለዛሬ ምሽት መሸጋሸጉ ግድ ሆኖበታል። በሴቶች የቤልጂጓ ተወላጅ ኪም ክላይስተርስ የሩሢያ ተጋጣሚዋን ቬራ ዝቮናሬቫን በለየለት 6-2, 6-1 ውጤት ስታሸንፍ ይህም ሶሥተኛው የኒውዮርክ ድሏ መሆኑ ነው። በአንጻሩ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ግንባር ቀደም በሆነው በራፋኤል ናዳልና በኖቫክ ጆኮቪች መካከል ትናንት የተጀመረው የፍጻሜ ግጥሚያ በዝናብ ሳቢያ ወደዛሬው ምሽት ተሸጋግሯል። በወጣቶች ፍጻሜ በሴቶች ሩሢያዊቱ ዳሪያ ጋቭሪሎቫ፤ እንዲሁም በወንዶች የአሜሪካው ጃክ ሶክ ሲያሸንፉ ትናንት የተቋረጡት የጥንድ ግጥሚያዎች የሚካሄዱትም በዛሬው ምሽት ነው።

መሥፍን መኮንን