1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ማክሰኞ፣ መስከረም 25 2003

የጋራ ብልጽግናው መንግሥታት የኮመንዌልዝ ሃገራት 19ኛ ጨዋታ በሕንድ የዝግጅት መጓተት ሳቢያ ከተነሣ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ አሁን በይፋ ተከፍቶ እየተካሄደ ነው።

https://p.dw.com/p/PVVJ
ምስል AP

ዝግጅቱን በተመለከተ እንደ ዋዜማው ሁሉ አሁን በሂደቱም የሚያነጋግር ነገር አልጠፋም፤ በዚያው የሚቀጥልም ነው የሚመስለው። ይሄው የኮመንዌልዙ ጨዋታና የአውሮፓ ቀደምት ክለቦች የእግር ኳስ ሻምፒዮና ዛሬ ዋና ማተኮሪያዎቻችን ናቸው።

የኮመንዌልዝ ጨዋታ በኒው ዴልሂ

ሕንድ ውስጥ የሚካሄደው 12 ቀናት የሚፈጅ የኮመንዌልዝ ሃገራት ጨዋታ ሰንበቱን ሶሥት ሰዓታት በፈጀ የደመቀ ትርዒት ኒው ዴልሂ ላይ ተከፍቷል። የቀድሞ የብሪታኒያ ቅኝ ግዛቶች በዋነኝነት የሚሳተፉበት 19ኛው የኮመንዌልዝ ጨዋታ በሕንድ የዝግጅት ውጣ ውረድ ስጋት የተነሣ ሲያከራክር ነበር የቆየው። ብዙዎች አትሌቶችም እስከመጨረሻው ደቂቃ በደህንነትና በጤና ስጋት የተነሣ ከውድድሩ ወደ ኋላ ማለታቸው ይታወቃል። ያም ሆነ ይህ ውድድሩ ዛሬ ተጀምሮ እየተካሄደ ነው።

በውድድሩ በርካታ የአፍሪቃ የኮመንዌልዝ ዓባል መንግሥታትም የሚካፈሉ ሲሆን ከነዚሁ መካከል ኬንያም ትገኝበታለች። በተለይም በመካከለኛና ረጅም ርቀት ሯጮቿ ሃያልነት የታወቀችው ኬንያ እ.ጎ.አ. በ 1963 ዓ.ም. ነጻነቷን ከተጎናጸፈች አንስቶ በውድድሩ የምትሳተፍ ሲሆን ዘንድሮ ወደ ኒው ዴልሂ የላከቻቸው ስፖርተኞች 240 ይጠጋሉ። ይህም የስፖርት ሚኒስትሩ ፓውል ኦቶማ እንደሚሉት ለአገሪቱ አኩሪ ነገር ነው።

"የኮመንዌልዙ ጨዋታ ለኛ ፍጹም የተለየ ክብደት አለው። ራሳችንን የምንመለከተው እንደ አንድ ቤተሰብ፣ ክለብ አድርገን ነው። ምክንያቱም ከኮመንዌልዝ ጋር ከተሳሰሩት ሃገራት ጋር አንድ ዓይነት ምንጭና ታሪካዊ ቅርስ ነው ያለን። ዝግጅቱንና ተሳትፎውን በተመለከተ ደግሞ ጨዋታው ምናልባት ከኦሎምፒክ ቀጥሎ ሁለተኛው ታላቅ ውድድር ነው"

ችግሩ የዝግጅቱ ሁኔታ ብዙ ጉድለት የተመላበት ሆኖ መገኘቱ ላይ ነው። በውድድሩ መክፈቻ ዋዜማ የስፖርተኞች ማረፊያዎችን ይዞታ፣ ጸጥታን፣ ምግብንና በሽታን ወዘተ. በተመለከተ እንደገና ብዙ መወራቱና መተችቱ አልቀረም። አንዳንድ የብሪታኒያና የአውስትራሊያ ስፖርተኞችም ተሳትፏቸውን በመሰረዝ አገር መቅረቱን መርጠዋል። ወደ ውድድሩ ሻገር እንበልና በዛሬው ዕለት ውድድር ለቀኑ በተመደቡት የወርቅ ሜዳሊያዎች ላይ መተኮሩ የሕንድን የዝና ጉድፈት ጥቂትም ቢሆን ችላ የሚያሰኝ ነው የሚመስለው።

ዛሬ ለሜዳሊያዎች ከሚታገሉት ስፖርተኞች መካከል ዋናተኞችና ክብደት አንሺዎችም ተረኞች ሲሆኑ ዕለቱ እንደታሰበው በተለይም ለእንግሊዟ የዋና ድርብ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ለሬቤካ አድሊንግተን የቀና አልነበረም። እስካሁን በደረሱን መረጃዎች መሠረት ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪቃ ወዘተ. ለመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያዎቻቸው በቅተዋል።

ከ 71 ሃገራት የተውጣጡት 4,300 አትሌቶች በሚቀጥሉት 11 ቀናት በ 272 የስፖርት ዓይነቶች የሚሳተፉ ሲሆን አንዱ ወይም ሌላው አስደናቂ ውጤት መገኘቱ የሚጠበቅ ነው። የውድድሩ በስኬት መካሄድ በተፋጠነ ዕድገት ላይ በምትገኘው በሕንድ የወደፊት የኦሎምፒክ አዘጋጅነት ተሥፋ ላይ ወሣኝ እንደሚሆንም ጨርሶ አያጠራጥርም።

የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ሻምፒዮና

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውስጥ በጅምሩ ማንም ያላሰበው ክለብ ማይንስ ሰባተኛ ግጥሚያውንም በድል በመወጣት አመራሩን ጨብጦ እንደቀጠለ ነው። ማይንስ የጎል ፌስታ በተዋሃደው ግጥሚያ ሆፈንሃይምን 4-2 ሲረታ በቡንደስሊጋው ውድድር ታሪክ ውስጥ አከታትሎ በማሸነፍም እስካሁን ከነበረው ክብረ-ወሰን ላይ ደርሷል። ከዚህ ቀደም ይሄው የተሳካላቸው ቀደምቱ ባየርን ሙንሺንና ካይዘርስላውተርን ብቻ ነበሩ። ለነገሩ እንዳቸውም በዚያ በጥንካሬያቸው ወቅት ሻምፒዮን መሆኑ አልሰመረላቸውም። ይሁን እንጂ የማይንስ ጉዞ በቀላሉ የማይገታ መሆኑን ከወዲሁ መፈንጠዝ የያዙት የክለቡ ደጋፊዎችና ተጫዋቾች ያመኑ ነው የሚመስለው። አሠልጣኙ ቶማስ ቶሸልም በዚህ በኩል አንዳች ተቃውሞ የለውም።

"እርግጥ ነው መፈንጠዝ ይችላሉ። ወጣት ተጫዋቾቻችን በዚህ ወቅት ሊያምኑት የሚያዳግት ውጤት እያስመዘገቡ ነው። እናም በዚህ ሁኔታ አንዴ እንኳ መፈንደቅ ያስፈልጋል። ይህንንም ያላንዳች ገደብ ለማድረግ ይችላሉ"

ማይንስ በፌስታ ባሕር ውስጥ እየዋኘ ባለበት ሰዓት በሌላ በኩል የቡንደስሊጋው ሬኮርድ ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን በ 13 ነጥቦች ልዩነት ታች ወርዶ 12ኛ ይሆናል ብሎ በጅምሩ ያሰበ አልነበረም። ባየርን በዚህ ሰንበትም በጨዋታ በመበለጥ በማያሻማ ሁኔታ በዶርትሙንድ 2-0 ሲሽነፍ ዶርትሙንድ በአንጻሩ ከማይንስ ሶሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሁለተኛ ነው። የቡድኑ ጥንካሬ የአጋጣሚ አይመስልም፤ ዶርትሙንድ ዘንድሮ እንዲያውም ከማይንስ ይልቅ የሰከነው ነው የሚመስለው።

በጥቅሉ አነስተኛ የሚባሉት ክለቦች ማይንስ፣ ሃኖቭርና ፍራይቡርግ ከሣምንት ሣምንት አየጠነከሩ ሲሄዱ የዘንድሮው የቡንደስሊጋ ውድድር አሁንም በተለይ ለታላላቆቹ ለሻልከ፣ ለብሬመን ወይም ለሽቱታርት የክስረት እየሆነ ቀጥሏል። ሻልከ በኑርንበርግ 2-1 ተሸንፎ 17ኛ ሲሆን በፍራንፈርት በተመሳሳይ ውጤት የተረታው ሽቱትጋርት ደግሞ የመጨረሻ፤ 18ኛ ነው። ከባድ ፈተና ነው የተደቀነበት። ዳኛ ትክክለኛ ጎሌን አልቆጠረልኝም ሲል በጨዋታው ያማረረው የቡድኑ አጥቂ ካካዎ እንደሚለው ቡድኑ ከዚህ አዘቅት ለመውጣት የግድ መታገል አለበት።

"እንደማስበው በወቅቱ ሁሉም ነገር እየተጫነን ነው። ሁሉም ነገር አልሰምር ብሎናል። ሆኖም ግን ተሥፋ መቁረጥ የለብንም። አዕምሯችንን ነጻ በማድረግ ከዚህ ሁኔታ እንድንላቀቅ መጪዎቹን ቀናት በሚገባ መጠቀም ይኖርብናል"

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ በአንጻሩ ቀደምቱ ክለቦች ሬያል ማድሪድና ባርሤሎና አመራሩን አይያዙ እንጂ እንደ ቡንደስሊጋው ሃያላን አላቆለቆሉም። ሊጋውን አትሌቲኮ ቢልባዎን 2-1 ያሽነፈው ቫሌንሢያ በ 16 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ቪላርሬያል አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ በሁለተኝነት ይከተለዋል። ሬያል ማድሪድ ዴፖርቲቮ ላ ኮሩኛን 6-1 በመሸኘት በሶሥተኝነቱ ሲቀጥል ባርሤሎና በአንጻሩ ከማዮርካ አንድ-ለአንድ በመለያየቱ አራተኛ ነው። ሆኖም ከአንደኛው ከቫሌንሢያ የሚለዩት ሶሥት ነጥቦች ብቻ ናቸው። ሁኔታው በቀላሉ ሊለወጥ ይችላል ማለት ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኢንተር ሚላን ከብርቱ ተፎካካሪው ከጁቬንቱስ ባዶ-ለባዶ በመለያየቱ አመራሩን ለላሢዮ ማስረከቡ ግድ ሆኖበታል። ላሢዮ ለቁንጮነት የበቃው ብሬሺያን 1-0 ካሽነፈ በኋላ ነበር። ናፖሊ ክፉኛ ያቆለቆለውን ሮማን 2-0 በመርታት ሶሥተኛ ሲሆን ኤ.ሢ.ሚላን አራተኛ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሣምንቱ ታላቅ ግጥሚያ በሁለቱ የለንደን ክለቦች በቼልሢይና በአርሰናል መካከል የተካሄደው ነበር። በዚሁ ግጥሚያ ቼልሢይ 2-0በማሽነፍ አመራሩን በአራት ነጥቦች ሲያሰፋ አርሰናል ወደ አራተኝነት አቆልቁሏል። ውጤቱ የጠቀመው በተለይም ኒውካስል ዩናይትድን 2-1 ላሸነፈው ለማንቼስተር ሢቲይ ነው።

ክለቡ በዚሁ በፕሬሚየር ሊጉ ውስጥ ሁለተኛውን ቦታ ለመያዝ በቅቷል። ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ ከሰንደርላንድ ባዶ-ለባዶ ሲለያይ አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ ሶሥተኛ ነው። በሌላ በኩል አንዴ በፕሬሚየር ሊጉና በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ሃያል የነበረው ሊቨርፑል ሰንበቱን በብላክፑል 2-1 ሲረታ ይባስ ብሎ ወደ 18ኛው ቦታ አቆልቁሏል። ማን አሰበው፤ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን እንዳይወርድ በጣሙን ነው የሚያሰጋው።

በተረፈ በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ስታድ ሬንስ ከሣንት ኤቲየን አመራሩን ሲነጥቅ በኔዘርላንድም አያክስ አምስተርዳም ቁንጮነቱን ለአይንድሆፈን አስረክቧል። በፖርቱጋል ሻምፒዮና በአንጻሩ ፖርቶ አንድ ጨዋታ ጎሎት እንኳ በአስተማማኝ ሁኔታ በስድሥት ነጥቦች ልዩነት እየመራ ነው።

ወደ አትሌቲክሱ ስፖርት እንመለስና በትናንትናው ዕለት በጀርመንና በስሎቫኪያ የተካሄዱት የከተማ ማራቶን ሩጫዎች በኬንያውያን ድል ተፈጽመዋል። በዚህ በጀርመን በኮሎኝ ከተማ ማራቶን በወንዶች ኬንያዊው ፍራንሲስ ኪፕኮክና በሴቶችም ጀርመናዊቱ ካታሪና ሃይኒግ ስያሸንፉ የሁለቱም ጊዜ ግን የሚገባውን ያህል ፈጣን አልነበረም። በሌላ በኩል በስሎቫኪያ 87ኛ የኮዚትሤ ማራቶን ጂልበርት ቼፕኮኒይ ሁለት የአገሩን ልጆች በማስከተል ሲያሽንፍ በሴቶች ደግሞ ኢትዮጵያዊቱ አልማዝ አለሙ ለእደኝነት በቅታለች። የሁለቱም ጊዜ ከኮሎኙ የተሻለ ነበር።

የስፓኙ የቴኒስ ዓለምአቀፍ ኮከብ ራፋኤል ናዳል ባለፈው ቅዳሜ ከታይላንድ-ኦፕን ውድድር በግማሽ ፍያሜው ተሸንፎ ከወጣ በኋላ በጃፓን-ኦፕን ለመጀመሪያ ጊዜ በመሳተፍ ወደተለመደ የድል ጉዞው ለመመለስ እያለመ ነው። ናዳል ዛሬ ለዚሁ ተልዕኮ ቶኪዮ ገብቷል። ቀደምቱ ኮከብ ከታይላንድ-ኦፕን ተሸንፎ የወጣው በአገሩ ልጅ በጂላርሞ-ጋርሢያ-ሎፔዝ በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 በመረታት ነበር። የ 24 ዓመቱ ናዳል በፊታችን ማክሰኞ የሚጋጠመው ከኮሉምቢያው ተወላጅ ከሣንቲያጎ ጂራልዶ ጋር ነው።

በተቀረ መጪው የቤዝቦል ኢንተር-ኮንቲኔንታል፤ የክፍለ-ዓለማት ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ከፊታችን ጥቅምት 13 አንስቶ በታይዋን አስተናጋጅነት ይካሄዳል። 17ኛው ፍጻሜ ውድድር የታይፔይ የቤዝቦል ማሕበር እንዳስታወቀው የሚጠቃለለው ጥቅምት 21 ቀን ነው። ውድድሩ ስዊትዘርላንድ-ሉዛን ላይ ተቀማጭ በሆነው ዓለምአቀፍ ፌደሬሺን እንደሚዘጋጅ ይታወቃል። ምድብ-አንድ ውስጥ ኩባ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቼክ ሬፑብሊክ፣ ሆንግ ኮንግና የቻይና ታይፔይ የተደለደሉ ሲሆን ምድብ-ሁለት ደግሞ ጃፓንን፣ ኔዘርላንድን፣ ኒካራጉዋን፣ ኢጣሊያንና ታይላንድን የሚጠቀልል ነው። በውድድሩ ሂደት ከያንዳንዱ ምድብ ሶሥት አገሮች ወደ ሜዳሊያው ዙር ያልፋሉ።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ