1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 1 2003

ሰንበቱን በርካታ የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ግጥሚያዎች ሲካሄዱ ለአንዳንዶቹ አገሮች ከወዲሁ ወሣኝነት የሚኖራቸው ቀጣይ ጨዋታዎችም በነገው ምሽት ይከተላሉ።

https://p.dw.com/p/PbT4
ምስል AP

በዘንድሮው የቺካጎ ማራቶን ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቶች ምንም እንኳ ለድል ባይበቁም ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ችለዋል። የፍርሙላ-አንድ አውቶሞሚል ሻምፒዮናም ሊገባደድ እየተቃረበ ሲሆን ትናንት ጃፓን-ሱዙካ ላይ የተካሄደው እሽቅድድም አሸናፊ ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል ሆኗል። ይህም ለሻምፒዮንነት የሚደረገውን ፉክክር ይበልጥ ማጠናከሩ አልቀረም።

BdT Hamburg Marathon 2010
ምስል AP

የቺካጎ ዓለምአቀፍ ማራቶን

በአትሌቲክስ እንጀምርና የትናንቱ የቺካጎ ማራቶን ሩጫ በወንዶች በኬንያና በሴቶች ደግሞ በሩሢያ ተወዳዳሪዎች ድል ተፈጽሟል። በወንዶች ያለፈውን ዓመት ድሉን በመድገም ለአሸናፊነት የበቃው የኦሎምፒኩ ሻምፒዮን ሣሚይ ዋንጂሩ ነበር። የኬንያው አትሌት ለዚህ ድል የበቃው በመጨረሻው ማይል ላይ የኢትዮጵያ ተፎካካሪውን ጸጋዬ ከበደን በማምለጥ ነው።
ዋንጂሩ ሩጫውን በሁለት ሰዓት ከስድሥት ደቂቃ 24 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም ጸጋዬ ደግሞ 18 ሤኮንዶች ዘግየት ብሎ ከግቡ ደርሷል። ሶሥተኛ የወጣውም የኢትዮጵያው ወጣት አትሌት ፈይሣ ሌሊሣ ነው። የሃያ ዓመቱ ፈይሣ ባለፈው ሚያዚያ ወር የሮተርዳም ማራቶን ሩጫውን ከሁለት ሰዓት ስድሥት ደቂቃ ጊዜ በታች በመፈጸም የመጀመሪያው ወጣት ማራቶን ሯጭ መሆኑ ይታወሣል።

በሴቶች የለንደኑ ማራቶን አሸናፊ ሩሢያዊት ሊሊያ ሾቡኮቫ አንደኛ ሆናለች። ሩጫውን በሁለተኝነት የፈጸመችው ደግሞ የሁለት ጊዜዋ የፓሪስ ማራቶን ባለድል አጸደ ባይሣ ነበረች። ጠንካራ ተፎካካሪዎች በተሰፉበት በዚሁ ሩጫ ማሚቱ ደስካም ስድሥተኛ ሆናለች። በጥቅሉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ውጤት አድናቆት ሊሰጠው የሚገባ ነው።

Miroslav Klose Deutschland Ungarn
ምስል AP

የአውሮፖ እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ

ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ በኡክራኒያና በፖላንድ የጋራ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር የሚካሄዱት የምድብ ግጥሚያዎች እንደ ሰንበቱ ሁሉ በነገው ምሽትም ይቀጥላሉ። ከብዙ በጥቂቱ በምድብ-አንድ ውስጥ ባለፈው አርብ ቱርክን በርሊን ላይ 3-0 የረታችው ጀርመን በሶሥት ግጥሚያዎች አንዲት ነጥብ ሳታስነካ በፍጹም የበላይነት ቀጥላለች። በአንጻሩ ለቱርክ መሽነፉ ሣይሆን ይበልጡንም በብዙ ጎል መሸኘቱና ለዚያውም ደግሞ ቱርካዊ ምንጭ ባለው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ኮከብ በሜሱት ኡዚል ጎል ጭምር መረታቱ የሚቆረቁር ሣይሆን አልቀረም።

በጀርመን የሚኖሩ ቱርካውያን በርከት ብለው ስታዲዮም መግባታቸው የበርሊኑ ጨዋታ ከደጋፊው ጩኸት አንጻር ለጀርመን ብሄራዊ ቡድን በውጭ ሜዳ የመጫወትን ያህል ሲመስል አሠልጣኙ ዮአኺም ሉቭም ቢሆን የዚሁ ግፊቱ እንደተሰማው ነው የገለጸው።

“ለማንኛውም የዛሬው ጨዋታ እጅግ ከባድ ነበር። በመጠኑም ቢሆን ግፊት ነበረብን ብዬ አስባለሁ። ሁኔታው ከሞላ-ጎደል በውጭ ሜዳ የመጫወትን ያህል ነው። እናም ቀላል አልነበረም። ነገር ግን ቡድኑ ጠንካራ የጨዋታና የትግል ፍላጎት በማሳየቱ በማያሻማ ሁኔታ ለማሸነፍ በቅተናል”

ጀርመን በነገው ምሽት ከካሳክስታን የምትጋጠም ሲሆን አሸንፋ መመለሷን የሚጠራጠር ብዙም የለም። ከሆነ አራት ጨዋታ አራት ድል ይሆናል ማለት ነው። ጀርመን እንግዲህ በአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜ ዙር አቅጣጫ እየገሰገሰች ሲሆን የቡድኑ አምበል ፊሊፕ ላም እንደሚለውም አጀማመሩ ተስፋን የሚያብር ነው።

“ግሩም ጅማሮ ነበር። ከዚህ የበለጠ ነገር የለም። የበለጠ ለማድረግ አይቻልም። ሶሥት ጨዋታ ዘጠኝ ነጥብ። በዚያ ላይ ያላንዳች ጥርጥር በምድቡ ውስጥ ጠንካራ የሆነችውን ቱርክን ማሽነፍ ቀላል ነገር አይደለም። ሆኖም ማክሰኞ ካላሽነፍን፤ ግን ማሽነፍ እንፈልጋለን፤ ካላሸነፍን ይሄ ሁሉ ዋጋ ቢስ ነው”

በዚሁ ምድብ ውስጥ የነገው ምሽት ሌሎች ተጋጣሚዎች አዘርባይጃን ከቱርክና ቤልጂል ከሁለተኛዋ ከአውስትሪያ ናቸው።

ምድብ-ሁለት ውስጥ ከሶሥት ግጥሚያዎች በኋላ አየርላንድ፣ ሩሢያና ስሎቫኪያ በእኩል ስድሥት ነጥብ የሚመሩ ሲሆን ስሎቫኪያና አየርላንድ በነገው ምሽት በቀጥታ ይገናኛሉ። በምድብ-ሶሥት ውስጥ ኢጣሊያ ከሰሜን አየርላንድ ባዶ-ለባዶ ብትለያይም በአንዲት ነጥብ ልዩነት ኤስቶኒያን አስከትላ ትመራለች። በምድብ-አራት ፈረንሣይ፤ በምድብ-አምሥት ኔዘርላንድ፤ እንዲሁም በምድብ-ስድሥት ደግሞ ክሮኤሺያ ቀደምቱ ናቸው።
በነዚህ ሶሥት ምድቦች ውስጥ በነገው ምሽት ከባድ እንደሚሆኑ ከሚጠበቁት ግጥሚያዎች መካከል ኔዘርላንድ ከስዊድን ዋነኛው ነው። በምድብ-ሰባት ውስጥ ሞንቴኔግሮ በአንድ’ ጨዋታ ብልጫ እንግሊዝን በሁለተኝነት አስከትላ የምትመራ ሲሆን በነገው ምሽት ሁለቱ እርስበርስ መገናኘታቸው አቅጣጫ አመልካችነት ይኖረዋል። በዜሮ ነጥብ የመጨረሻ የሆነችው የደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ስዊስም ከወደቀችበት አዘቅት ለመውጣት ዌልስን ማሸነፏ ግድ ነው። የምድብ-ዘጠኝ ቁንጮ ደግሞ የአውሮፓና የዓለም ሻምፒዮን ስፓኝ ናት።

Sebastian Vettel 10.10.2010
ምስል picture-alliance/dpa

የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም

ጀርመናዊው የሬድ-ቡል ሬኖ አውቶሞቢል ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል ትናንት ጃፓን፤ ሱዙካ ላይ የተካሄደው የፎርሙላ-አንድ ግራንድ-ፕሪ አሸናፊ ሆኗል። የ 23 ዓመቱ ወጣት ከ 140 ሺህ የሚበልጥ ተመልካች በተገኘበት በተደረገው እሽቅድድም ፍጹም ልዕልና ሲያሳይ ከግቡ የደረሰው አውስትራሊያዊውን የቡድኑን ዘዋሪ ማርክ ዌበርን በአንዲት ሤኮንድ በመቅደም ነው። ፌትል ትናንት በአነዳድ ታክቲክ ረገድም ጠንከር ብሎ ነበር የታየው።
“የኋላ ጎማችንን ለመቀየር ከማርክ ጋር ከቦክሳችን ገብተን የቆምንበት ጊዜ ትክክለኛው ነበር። ከዚያን በኋላ ሁለታችንም ቅድሚያ ለማግኘት እየተፎካከርን ነው የቀጠልነው። ማርክ በተጠጋ ቁጥር ሁሉ ጋዝ እየሰጠሁ ወደፊት ለማምለጥ ችያለሁ። በአጠቃላይ ሁኔታውን መቆጣጠሩና በአንደኝነት ከግብ መድረሱ ተሳክቶልኛል”

የፌራሪው ፌርናንዶ አሎንሶ ሶሥተኛ ሲወጣ የአንዴው የሰባት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ጀርመናዊው ሚሻኤል ሹማኸር ደግሞ እሽቅድድሙን ስድሥተኛ በመሆን ፈጽሟል። ከጠቅላላው 19 እሽቅድሞች 16ቱ ተካሂደው አሁንም ማርክ ዌበር በ 220 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን አሎንሶና ፌትል እያንዳንዳቸው እኩል 206 ነጥብ ይዘው ይከተላሉ። ሶሥቱም በመጨረሻ የዓለም ሻምፒዮን የመሆን ዕድላቸውን እንደጠበቁ ነው።

ሚሻኤል ሹማኸርን ካነሣን ታላቁ ዘዋሪ እስካሁን አንዴ እንኳ ለድል ሳይበቃ መቅረቱ በመልሱ ብዙ የጠበቁበትን አፍቃሪዎቹን ጭምር ማሳዘኑ አልቀረም። እንዳለፉት ሣምንታትና ወራት ሁሉ ታዲያ ከፎርሙላ-አንዱ መድረክ በክብር ከተሰናበተ በኋላ መመለሱ ተገቢ ነበር ወይ? የሚለው ጥያቄ አሁንም የሚነሣ ነው። የዶቼ ቬለ የስፖርት ፕሮግራም ክፍል ባልደረባ ሽቴፋን ኔስትለር እንደሚለው ሂደቱን ሹማኸር ራሱ የጠበቀው አልነበረም።

“እርሱ ራሱ በዘንድሮው ውድድር ሂደት በጣም ነው ያዘነው። መለስ ብለን ካስታወስን ሁለቴ ስድስተኛና ሁለቴ አራተኛ ነበር የአስካሁን የተሻለ ውጤቱ። ይህ ደግሞ አቻ ባልታየለት ሁኔታ ሰባት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ለነበረ ዘዋሪ በቂ ወይም አርኪ አይደለም። እርሱም አልጠበቀውም። ሹማኸርን ለሚያውቅ ሁሉ ለማሽነፍ የሚታገል እንጂ ከኋላ መከተል የማይወድ መሆኑ ግልጽ ነገር ነው። ሆኖም አንደኛ መውጣቱ እስካሁን አልተሳካለትም። እና በሚቀጥለው ዓመት ካልሆነለት መወዳደሩን የሚያቆም ይመስለኛል”

ስኬት እየጠፋ ከሄደ ሜርሤደስ ቡድኑም በዚህ መልክ መቀጠሉ ሲበዛ ያጠራጥራል።
ሽቴፋን ኔስትለር ሹማኸር በተቀሩት የዘንድሮው ሶሥት እሽቅድድሞችም አንዴ እንኳ ባለ ድል ለመሆን መብቃቱን ሊያምኑት የሚያዳግት ነገር አድርጎ ነው የሚመለከተው።

“እርግጥ ገና ሶሥት እሽ’ቅድድሞች ይቀራሉ። ሆኖም ግን የማሸነፍ ጭብጥ ዕድል አለው ብዬ አላምንም። በአሁኑ ጊዜ ይልቁንም ሌሎቹ ቡድኖች ጠንካሮች ናቸው። የርሱ ሜርሤደስ ግን በጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለም። የሬድ ቡል ዘዋሪዎች ማርክ ዌበርና ዜባስቲያን ፌትል በመጨረሻዎቹ ሶሥት እሽቅድዶች ላይ ወሣኝ ተጽዕኖ የሚኖራቸው ነው የሚመስለኝ”

የዜባስቲያን ፌትል ነገር ከተነሣ ወጣቱ ጀርመናዊ ዘንድሮና ባለፈው ዓመት ሻምፒዮና ያሳየው ዕርምጃ በጣሙን የሚደነቅ ነው። በሌላ በኩል ይሁንና ብዙ ያለቀላቸው ድሎቹን አሳልፎ በመስጠት ድክመት ማሳየቱም አልቀረም። እናም በሽቴፋን ኔትስለር ዕምነት ፌትል በአጠቃላይ ነጥብ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን መብቃቱ ብዙ የሚያጠያይቅ ይሆናል።

“የምጠራጠረው ነገር ነው። ባለፈው ዓመት ሁለተኛ የዓለም ሻምፒዮን በመሆን ብዙዎችን ነበር ያስደነቀው። አሁንም ሊያሸንፍ ይችል ይሆናል። ለነገሩ እስካሁን ቁንጮ የመሆን ብዙ ዕድል ነበረው። ግን ዕድሉን በማይረቡ የአነዳድ ስህተቶች ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል። አሁን ሱዙካ ላይ መልሶ ለማሸነፍ በቅቷል። እና በመሠረቱ ሶሥት ቀሪ ዕድሎች አሉት። ግን ጥያቄው በቂ ነርቭ ኖሮት ይቀጥላል ወይ ነው። እዚህ ላይ በጣም እጠራጠራለሁ”

ዘገባችንን በቴኒስ ለማጠቃለል በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ከስፓኙ ኮከብ ከራፋኤል ናዳል ቀጥሎ ሁለተኛ የሆነው ኖቫክ ጆኮቪች ባለፈው ሌሊት የቻይና-ኦፕን አሸናፊ ሆኗል። የሰርቢያው ተወላጅ ለዓመቱ ሁለተኛ የኤቲፒ ድል የበቃው የስፓኙን ዴቪድ ፌሬርን በዝናብ ሳቢያ በተጓተተ ጨዋታ 6-2, 6-4 በማሽነፍ ነው። ራፋኤል ናዳልም በቶኪዮ ዓለምአቀፍ ፍጻሜ የፈረንሣይ ተጋጣሚውን ጌል ሚንፊልስን 6-1, 7-5 በመሸኘት ፍጹም የበላይነቱን እንደገና አስመስክሯል።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ