1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 9 2003

ሰንበቱ በዓለም እግር ኳስ መድረክ ላይ የከፍተኛ የፊፋ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዓባላት በጉቦ መጠርጠር ጥላ ቢያርፍበትም ከአውሮፓ እስከ አፍሪቃ በየቦታው የተለያዩ ውድድሮች መካሄዳቸው አልቀረም።

https://p.dw.com/p/Pgy5
ቡንደስሊጋ፤ ቦሩሢያ ዶርትሙንድምስል picture-alliance/dpa

የኮመንዌልዝ ጨዋታ ተጠቃለለ

የዘንድሮው የኒውዴልሂ የሞከንዌልዝ፤ ማለትም የጋራ ብልጽግናው መንግሥታት ጨዋታ በዋዜማውና በጅምሩ በዝግጅት ቀውስ ብዙ ካነጋገረ በኋላ በስኬት ተፈጽሟል። የዴልሂው ጨዋታ ምናልባትም በመጀመሪያው የተፈራውን ያህል አልከፋም። ግሩም የኮመንዌልስ ጨዋታ ሆኖ እንደሚታወስ ቢቀር የአዘጋጆቹ ዕምነት ነው። አንዳንዶች እንዲያውም ሕንድ የኦሎምፒክ ጨዋታን ለማስተናገድ ዕድል እንድታገኝ በር ከፋች ሆኗል ባዮች ናቸው። እርግጥ ጨዋታው በፌስታ ተከናውኗል። ይሁንና በጅምሩ የታዩት የዝግጅት ጉድለቶች ግን ለረጅም ጊዜ ባሉበት መቆየታቸው በሰፊው ነው የሚታመነው። በጅምሩ አትሌቶችን የገጠሙት የምግብና የጤና ችግሮች፤ የትራንስፖርትና የማረፊያ ቤቶች እክል፣ የተመልካች እጥረት፤ በአጠቃላይ የዝግጅትና የቅንብር ጉድለት የበለጠ ጥረትን ይጠይቃሉ።

ለማንኛውም ባለፈው ሐሙስ ከተጠናቀቀው ውድድር አንጻር አውስትራሊያ ከጠቅላላው 272 ወርቅ ሜዳሊያዎች 74ቱን በማሽነፍ እንደገና የጨዋታው ሃያል አገር ለመሆን በቅታለች። እርግጥ የጨዋታውን ፍጻሜ ይበልጥ የተሣካ ያደረገውና ግርማ ሞገስ የሰጠው አስተናጋጇ አገር ሕንድ 38 ሜዳሊያዎች በማሽነፍ በመጨረሻው ዕለት ክብረ-ወሰኗን ማሻሻሏ ነበር። ከ 71፤ በአብዛኛው የቀድሞ የብሪታኒያ ቅኝ’ ግዛት ከነበሩ ሃገራት የተጓዙት ስፖርተኞች በመጨረሻ መርካትም እንዲሁ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል። ከአፍሪቃ አገሮች ኬንያ በተለይ በሴቶችና በወንዶች የማራቶን አሸናፊ በመሆን የአትሌቶቿን የረጅም ርቀት ፍጹም ልዕልና አስመስክራለች።

ኬንያን ካነሣን በሣምንቱ በየቦታው በተካሄዱ የረጅም ርቀት ሩጫዎችም አትሌቶቿ ቀደምቱ ነበሩ። በቱርክ የኢስታምቡል ማራቶን ቪንሤንት ኪፕላጋት ለከተማይቱ እስካሁን ፈጣን በሆነ ጊዜ አሸንፏል። በሴቶች ግን ድሉ የኢትዮጵያዊቱ አትሌት የአሹ ካሢም ነበር። ኬንያውያን በቻይና-የናንኒንግ ግማሽ ማራቶን የዓለም ሻምፒዮና ደግሞ ድርብ ድል ተጎናጽፈዋል። በወንዶች ዊልሰን ኪፕሮፕ ኤርትራዊውን ዘረሰናይ ታደሰን አስከትሉ ሲያሽንፍ በሴቶችም የአገሩ ልጅ ፍሎሬንስ ኪፕላጋት አንደኛ ሆናለች። ሩጫውን በሁለተኝነት የፈጸመችው ድሬ ጡኔ ነበረች።

የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቼልሢይ ከኤስተን ቪላ ባዶ-ለባዶ ቢለያይም በሁለት ነጥቦች ብልጫ መምራቱን ቀጥሏል። በሁለተኝነት የሚከተለው ብላክፑልን 3-2 ያሸነፈው ማንቼስተር ሢቲይ ነው። የተቀሩት ቀደምት ክለቦች አርሰናል፣ ማንቼስተር ዩናይትድና ሆትስፐር እያንዳንዳቸው ከስምንት ግጥሚያዎች በኋላ እኩል 14 ነጥብ ሲኖራቸው የቼልሢይ የቅርብ ተፎካካሪ እንደሆኑ ይቀጥላሉ። በሌላ በኩል የአንዴው ድንቅ ክለብ ሊቨርፑል በአዲስ አሜሪካዊ ባለቤት አዲስ ጅማሮ ለማድረግ የያዘው ጥረት ቢቀር ሰንበቱን’ ሳይሰምርለት ቀርቷል። የአምሥት ጊዜው የአውሮፓ ሻምፒዮን ሊቨርፑል በኤቨርተን 2-0 ሲረታ በፕሬሚየር ሊጉ ታሪክ ውስጥ ከስልሣ ዓመታት ገደማ ወዲህ እንደዘንድሮው ደካማ ጅማሮ ያደረገበት ጊዜ የለም፤ በወቅቱ 19ኛ ነው።

Fußball Bundesliga 8. Spieltag : FC Bayern München - Hannover 96 Anatoli Timoschtschuk
ምስል picture-alliance/dpa

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር በሰባት ግጥሚያዎች ሰባት ጊዜም ለድል በቅቶ ተፎካካሪዎቹን ያስደነቀው ማይንስ በዚህ ሰንበት ለመጀመሪያ ሽንፈቱ በቅቷል። ክለቡ በሃምቡርግ በመጨረሻ ደቂቃ ላይ በተቆጠረች ጎል 1-0 ሲሽነፍ በዚሁ የሮኬትነት ጉዞው ማክተሙ ይሁን ወይም ሸርተቴው የአንድ ጊዜ ሣምንት ቀጣዩን ግጥሚያ ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው። የሃምቡርግ አሠልጣኝ አርሚን ፌህ በበኩሉ ማይንስን ከማወደስ አልተቆጠበም።

“እንደማስበው ጠንካራ ትግል የተመላበት ጨዋታ ነው ያየነው። ማይንስ ሰባት ግጥሚያዎቹን በሙሉ ያሽነፈው በአጋጣሚ እንዳልነበርም ለመታዘብ ችለናል። ቡድኑ ግሩም ጨዋታ ነው የሚጫወተው። እርግጥ ወሣኙ ነገር በመጨረሻ ተጋጣሚህ የማይሽራትን ጎል ማስገባት መቻል ነው”
ለማንኛውም የማይንስ ክስረት ኮሎኝን 2-1 ያሽነፈው ዶርትሙንድ በእኩል ነጥብም ቢሆን በጎል ብልጫ አመራሩን ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲጨብጥ ነው ያደረገው።

ሌቨርኩዝን ቮልፍስቡርግን አስደናቂ በሆነ ጨዋታ ከኋላ ተነስቶ 3-2 በመርታት ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ሲል አራተኛ ሆፈንሃይም፤ አምሥተኛ ደግሞ ሃምቡርግ ነው። ታላቁ ክለብ ባየርን ሙንሺን ማሪዮ ጎሜስ በብቸኝነት ባስቆጠራቸው ጎሎች ሃኖቨርን 3-0 ሲያሸንፍ ወደ አሥረኛው ቦታ ጥቂት ተሻሽሏል። ብሄራዊው ተጫዋች ጎሜስ ለወራት ባሳየው ድክመት መሳቂያና መሳለቂያ ሆኖ ሲቆይ የሰንበቱ ድሉ ምናልባት ዕፎይ የሚያሰኘው ነው። ስኬቱ ካርል-ሃይንስ-ሩመኒገን የመሳሰሉትን የክለቡን መሪዎችም ማረጋጋቱ አልቀረም።

“በግልጽና በሃቅ ልናገር፤ በማሪዮ ጎሜስ ላይ ሆሌም ዕምነት ነበረኝ። በሁሉም ነገር የተሟላ አጥቂያችን አድርጌ ስለምመለከተው! እናም ይሄ፤ በተለይም የእኛ ትዕግሥት ዛሬ ከሚጠበቀው በላይ ነው ፍሬ የሰጠው”

በቡንደስሊጋው ማዕረግ ተዋረድ ላይ 11ኛውም ዘንድሮ እንደ ባየርን ሁሉ የሊጋው ውድድር ያልሰመረለት ቤርደር ብሬመን ነው። በተረፈ ሻልከ፣ ኮሎኝና ሽቱትጋርት ደግሞ የመጨረሻዎቹ ናቸው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን የፖልቱጋሉ ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በግሩም ጨዋታ ክለቡ ሬያል ማድሪድ አመራሩን እንዲይዝ ለማድረግ በቅቷል። ሬያል ማላጋን 4-1 ሲረታ ሮናልዶ ሁለቱን ጎሎች ራሱ በማስገባትና ሁለቱን ደግሞ ለአርጄንቲናዊው አጥቂ ለጎንዛሎ ሂጉዌይን በማዘጋጀት የቡድኑ መንኮራኩር ነበር። እስካሁን አንዴም ያልተሽነፈው ሬያል ማድሪድ ከሰባት ግጥሚያዎች በኋላ በ 17 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ባርሤሎናና ቫሌንሢያ ደግሞ አንዲት ነጥብ ወረድ ብለው ይከተላሉ። ቫሌንሢያ አመራሩን የተነጠቀው በባርሣ 2-1 በመሸነፉ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ እስከቅርቡ ማንም ያልጠበቀው ላሢዮ ባሪን 2-0 በማሽነፍ በ 16 ነጥቦች በቁንጮነቱ እንደጸና ነው። ኤ.ሢ.ሚላን ቺየቮ ቬሮናን 3-1 በመርታት በሁለተኝነቱ ሲቀጥል ኢንተር ሚላንም ካልጋሪን 1-0 በማሸነፍ ሶሥተኛ ነው። ሁለቱም ክለቦች በነጥብ እያንዳንዳቸው 14 በመያዝ እኩል ናቸው። በፈረንሣይ ሻምፒዮና ስታድ ሬንስ ከሌንስ ባዶ-ለባዶ ቢለያይም ሣንት ኤቲየንን በሁለት ነጥቦች ልዩነት አስከትሎ መምራቱን ቀጥሏል። በኔዘርላንድ ሊጋም አይንድሆቨን አያክስንና ኤንሼዴን አስከትሎ ይመራል።

Vitali Klitschko vs. Shannon Briggs FLASH-Galerie
ምስል picture alliance/dpa

ቡጡ ስፖርት ወይስ ወሰን ያጣ ድብደባ

በዚህ በጀርመን ነዋሪ በሆነው በኡክራኒያው ተወላጅ በቪታሊ ክሊችኮና በአሜሪካዊው በሻኖን ብሪግስ መካከል ሰንበቱን ሃምቡርግ ውስጥ በተካሄደው የዓለም ቡጡ ሻምፒዮና የከባድ ሚዛን ግጥሚያ የቡጡ ስፖርትነት እንደገና አጠያያቂ ሆኗል። ብሪግስ እየተደበደበ 12ቱን ዙር ቢፈጽምም ለገንዘብ ሲል በከፈለው መስዋዕት በመጨረሻ ድንገተኛ ክትትል ወደሚደረግበት ሆስፒታል መወሰዱ ግድ ነው የሆነበት። የሆስፒታሉ ሃኪም ብሪግስ ማውራቱን ባያቆምም ከራስ ምታት እስከ ራስ ማዞርና ድካም አሳሳቢ ሁኔታ እንደታየበት ነው የተናገረው።

ይገርማል የፊቱ አጥንቶች ስብራት ሳይበግረው በድምጽ ማጉያ አሸናፊውን ለማወደስ መግተርተሩ ላየው አሳፋሪ ነበር። ዳኛውና የሪንጉ ሃኪምም ጨዋታው ቀድሞ እንዲቋረጥ አለማድረጋቸው በቡጢው ግጥሚያ ገንዘብ ወሣኙ ነገር እንደሆነ እንደገና አስመስክሯል። ብሪግስ በወዶ ፈቃደኝነት ገጽታውን ለድብደባ ማቅረቡና ክሊችኮም አመታቱን ቢያበርድም በድብደባው እስከመጨረሻው መዝለቁ እጅግ የሚያሳፍር ነገር ነው።

Fifa Präsident Joseph Blatter weiht das zukünftige FIFA Haus in Zürich ein
ምስል AP

የፊፋ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጉቦ መጠርጠር

የብሪታኒያው ሰንዴይ-ታይምስ ጋዜጣ ሁለት ቀደምት የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የፊፋ ስራ አስፈጻሚ አካል ዓባላት የ 2018 እና 2022 የዓለም ዋንጫ አስተናጋጆች ማንነት ከመወሰኑ በፊት ድምጻቸውን ለመሸጥ እንደሞከሩ መዘገቡ ለማሕበሩ ዝና ጉድፍ እየሆነ ነው። ጋዜጣው የናይጄሪያው አሞስ አዳሙ ለግል ፕሮዤ ገንዘብ ሲጠይቁ በፊልም መቀረጻቸውን ሲዘግብ የኦሺኒያው ኮንፌደሬሺን ፕሬዚደንት ሬይናልድ ቴማሪም ለስፖርት አካዳሚ ገንዘብ መሻታቸውን አትቷል። የናይጄሪያው አሠልጣኝ ኡስማን ላንጋሪ ክሱን አስደንጋጭ ነው ያለው።

“እንደ ዕውነቱ አሞስ አዳሙን በመሰለ በናይጄሪያ እግር ኳስ ውስጥ ለዓመታት ጥሩ ስም ባለው ሰው ላይ ይህ ክስ መሰንዘሩ የሚያስደነግጥ ነው። በጣም አስደንግጦኛል”

የፊፋ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዓባላት የሁለቱን የዓለም ዋንጫ አዘጋጆች ማንነት በድምጽ ብልጫ የሚወስኑት በፊታችን ሕዳር 23 ቀን. ዙሪክ ውስጥ በሚያካሂዱት ስብሰባ ነው። የፊፋ ፕሬዚደንት ሤፕ ብላተር በጉዳዩ አስቸኳይ ምርመራ እንዲካሄድ ሲያዙ የኮሚቴው ዓባላት ለመገናኛው አውታር ገለጻ ከመስጠት እንዲቆጠቡም ጠይቀዋል።

በዓለምአቀፉ ቴኒስ ላይ እናተኩርና የብሪታኒያው ተወላጅ ኤንዲይ መሪይ ትናንት የስዊዙን ተጋጣሚውን ሮጀር ፌደረርን በሁለት ምድብ ጨዋታ በማሸነፍ የሻንግሃይ ማስተርስ ባለድል ሆኗል። በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አራተኛ የሆነው የ 23 ዓመቱ መሪይ ለዘንድሮው ሁለተኛ የማስተርስ ድሉ የበቃው በለየለት ውጤት 6-3, 6-2 በማሸነፍ ነበር። አውስትሪያ-ሊንስ ላይ በተካሄደ የሴቶች የዓለም ቴኒስ ማሕበር ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ ሰርቢያዊቱ አና ኢቫኖቫ የስዊሷን ፓቲይ ሽናይደርን 6-1, 6-2 በማሸነፍ ፍጹም የበላይነት አሳይታለች።

ዘገባችን በእግር ኳስ ለማጠቃለል ሰንበቱን በተካሄዱ የአፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያዎች የቱኒዚያ ኤስፔራንስ አል-አህሊ-ካይሮን 1-0 ሲረታ የአልጄሪያው ካቢሊና የኮንጎው ማዜምቤ ደግሞ ባዶ-ለባዶ ተለያይተዋል። በዚሁ ውጤት መሠረት ኤስፔራንስ በውጭ በተቆጠረ ጎል ብልጫ ወደ ፍጻሜው ሲያልፍ የመጨረሻ ተጋጣሚው የሚሆነውም ማዜምቤ ነው።

መሥፍን መኮንን