1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 29 2003

በአትሌቲክሱ መድረክ የትናንቱ ሰንበት ሃይሌ ገብረ ሥላሴ ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ በለንደን ኦሎምፒክ ለመሳተፍ የነረበው ሕልም ሕልም ሆኖ የቀረበት ነበር።

https://p.dw.com/p/Q1jC
ምስል Alexander Göbel
Haile Gebrselassie Äthiopien gewinnt am Sonntag den 36. Berlin - Marathon
ምስል picture-alliance/ dpa

የኒውዮርክ ማራቶን፤ የሃይሌ ስንብት

በዓለምአቀፍ ደረጃ ሰፊ ዕውቅናና ዝናን ያተረፈው ድንቅ አትሌት የሃይሌ ገብረ ሥላሴ የስፖርተኝነት ዘመን ባለፈው ምሽት አክትሞለታል። የአሥር ሺህ ሜትር የኦሎምፒክ ባለድልና የማራቶን የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት የሆነው ሃይሌ ስንብት ማድረጉን ያስታወቀው ትናንት ጉልበቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት የኒውዮርክን ማራቶን አቋርጦ ከወጣ በኋላ ነው። የ 37 ዓመቱ ታላቅ አትሌት ለጋዜጠኞች ሲናገር ለወጣት አትሌቶች ዕድል ለመስጠት የመሰናበቱ ጊዜ አሁን ነው ብሏል።
ሃይሌ ገብረ-ሥላሴ ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ እ.ጎ.አ. በ 2012 ለንደን ላይ በሚካሄደው የኦሎምፒክ ጨዋታ ለመሳተፍ ዕቅድ እንደነበረው ይታወቃል። በመሆኑም ቀድሞ ባደረገው ስንብት ያዘኑት ስፖርተኞችም ሆኑ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አፍቃሪዎቹ እጅግ ብዙዎች ናቸው። እርግጥ ሃይሌ ትናንት ሩጫውን ባይፈጽምም ድሉ ግን ከኢትዮጵያ ዕጅ አልወጣም።
የ 26 ዓመቱ ገብሬ ገብረ ማርያም የዘንድሮው የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊ ሲሆን ሁኔታው ጥቂትም ቢሆን የሜክሢዮውን የአበበ ቢቂላንና የማሞ ወልዴን ታሪክ መልሶ የሚያስታውስ ነው። በጊዜው የሮማና የቶኪዮ ኦሎምፒክ አሽናፊ የነበረው አበበ ቢቂላ እግሩን አሞት ሩጫውን ሲያቋርጥ ማሞ ወልዴ ኢትዮጵያን ባዶ ዕጅ አላስቀረም ነበር። ሁለቱ አትሌቶች በሶሥት የኦሎምፒክ ውድድሮች በተከታታይ የማራቶን አሸናፊ በመሆን ለኢትዮጵያ ምንጊዜም የማይፋቅ ታሪክ አስመዝግበው ነው ያለፉት።

ከዚያን ወዲህ እርግጥ ኢትዮጵያ ከአርባ ዓመታት በላይ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ የማራቶን ድል አጥታ ነው የኖረችው። በመሆኑም ታዲያ ሃይሌ ገብረ ሥላሴ የነአቤን ክብር በማስመለስ የስፖርት ሕይወቱን በኦሎምፒክ ማራቶን ድል ለመፈጸም ማለሙ አልቀረም። ከመካከለኛ ርቀት ወደ ማራቶን ሻገር በማለትም ከሁለት ዓመታት በፊት በቤይጂንግ ኦሎምፒክ ለመወዳደር ተነሳስቶ ነበር።
ይሁንና በቤይጂንግ አየር መበከል ሳቢያ ባደረበት ትንፋሽ የማጣት ስጋት፤ በአስማ ሕመም ሳቢያ ከውድድሩ መራቁ ይታወሣል። አልሆነም፤ ከሁለት ዓመት በኋላም የለንደን ኦሎምፒክ ማራቶን ያለ ሃይሌ እንደሚካሄድ ከትናንት ወዲህ የለየለት ጉዳይ ነው። ሃይሌ እንዴት ሳይታሰብ ስንብት ሊያደርግ ቻለ፤ ለወጣት ስፖርተኞችስ ምን ቅርስ ነው ያስተላለፈው? በጉዳዩ የስፖርት ጋዜጠኛ የሆኑትን አቶ ሰለሞን በቀለን አነጋግረን ነበር።

የስፖርት ጋዜጠኛው አቶ ሰለሞን በቀለ ነበሩ፤ አቶ ሰለሞንን ለሰጡን አስተያየት ከልብ እናመሰግናለን።

የኢትዮጵያ ወጣት አትሌቶች ከሃይሌ ገብረ ሥላሴ ብዙ ተምረዋል። እርሱን አረአያ በማድረግ ባለፉት አሥር ዓመታት የተነሱትና ዓለምአቀፍ ከዋክብት ለመሆን የበቁትም ብዙዎች ናቸው። እንደ ስዊስ ሰዓት በትክክል በሚሰራ አይምሮው የተሰላ ሩጫ መሮጥ የሚችለው አትሌት ሃይሌ ከአሠርተ-ዓመት በላይ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍቃሪዎችና አድናቂዎችን ለማፍራት ችሏል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም ታላላቅ የአትሌቲክስ መድረኮች ብዙ ጊዜ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረገ ታላቅ አትሌት ነው።
ስለዚህም ለታላቅ የስፖርት አስተዋጽኦው በዚህ አጋጣሚ ልናመሰግነው እንወዳለን። በተረፈ የሃይሌን ስንብት ተሥፋ አስቆራጭ የማያደርገው ኢትዮጵያ ብዙ ድንቅ ወጣት አትሌቶችን ማፍራቷ፤ የምታፈራም መሆኑ ነው። በትናንቱ የኒውዮርክ ከተማ ማራቶን በጠቅላላው 43 ሺህ ሯጮች ሲሳተፉ በሴቶች ኬንያዊቱ ኤድና ኪፕላጋት አሸንፋለች።

Fußball Bundesliga Hannover 96 gegen Borussia Dortmund Flash-Galerie
ምስል dapd

የአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጋዎች ሻምፒዮና

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የእግር ኳስ ሻምፒዮና በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሬያል ማድሪድ ከአሥር ግጥሚያዎች በኋላም ለአንዴ እንኳ ሳይሸነፍ ሊጋውን በ 26 ነጥቦች በበላይነት መምራቱን ቀጥሏል። ባርሤሎናም ጌታፌን 3-1 ሲያሸነፍ አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው። ሶሥተኛ ቪላርሬያል!

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቀደምቱ ቼልሢይ በሊቨርፑል 2-0 ሲረታ በዘንድሮው ውድድር በደረሰበት ሁለተኛ ሽንፈት አመራሩ ወደ ሁለት ነጥብ ዝቅ ብሏል። ሁለተኛው ወንደረርስን 2-1 ያሸነፈው ማንቼስተር ዩናይትድ ሲሆን ሶሥተኛው አርሰናል ነው። በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ላሢዮ ምንም እንኳ በሮማ 2-0 ቢረታም በሁለት ነጥቦች መምራቱን ሲቀጥል ኢንተር ሚላን ከብሬሺያ 1-1 በመለያየቱ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ተንሸራቷል። ውጤቱ የጠቀመው ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ላለው ለኤ.ሢ.ሚላን ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ዶርትሙንድ አመራሩን በአራት ነጥቦች ሲያሰፋ በጅምሩ የማይበገር መስሎ የታየው ክለብ ማይንስ በማቆልቆል አቅጣጫው ቀጥሏል። በወቅቱ ሁለተኛ ነው። ባየርን ሙንሺን በእኩል ለእኩል ውጤት ከስምንት ወደ ዘጠኝ ሲንሸራተት የብሬመን ቡድን ደግሞ ለዚያውም በመጨረሻው በሽቱትጋርት 6-0 ተቀጥቶ ከሜዳ ወጥቷል።

Sebastian Vettel Großer Preis von Brasilien Formel 1
ምስል AP

የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም የዘንድሮው ሻምፒዮና ሊጠናቀቅ አንድ ሣምንት ብቻ ቀርቶት ሳለ በተለይ የሶሥት ዘዋሪዎች ፉክክር የጦፈበት እየሆነ ነው። በትናንቱ 18ኛ ውድድር በብራዚሉ ግራንድ-ፕሪ የጀርመኑ ዜባስቲያን ፌትል ሲያሸንፍ የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር ሁለተኛ እንዲሁም የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ሶሥተኛ ወጥተዋል። በአጠቃላይ ነጥብ በወቅቱ አሎንሶ የሚመራ ሲሆን ሻምፒዮናው የሚለይለት በፊታችን ሰንበት የአቡ-ድሃቢ የመጨረሻ እሽቅድድም ነው።

በሴቶች የቴኒስ ፌደሬሺን ዋንጫ ፍጻሜ የኢጣሊያ ቡድን ትናንት ሣን-ዲየጎ ላይ በተካሄደ ግጥሚያ አሜሪካን በማሸነፍ በአምሥት ዓመታት ውስጥ ሶሥተኛ የሆነ ድሉን አስመዝግቧል። ድሉ የተረጋገጠው ፕላቪያ ፔኔታ ከአምሥቱ ግጥሚያዎች የመጨረሻውን 6-1, 6-2 በሆነ በለየለት ውጤት ካሸነፈች በኋላ ነበር። በተቀረ ሮጀር ፌደረር በስዊትዘርላንድ-ባዝል ፍጻሜ ግጥሚያ ኖቫክ ጆኮቪችን 2-1 ሲያሽንፍ በስፓኝ-ቫሌንሢያም ዴቪድ ፌሬር ለዓመቱ ሁለተኛ ድሉ በቅቷል።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ