1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 4 2003

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የእግር ኳስ ሻምፒዮና በዚህ ሰንበትም አንዳንድ ድንቅ ጨዋታዎች ታይተዋል።

https://p.dw.com/p/QX9K
ምስል AP

ታንዛኒያ ውስጥ የተካሄደው የማዕከላዊና ምሥራቅ አፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ትናንት በአስተናጋጇ አገር ድል ተፈጽሟል። ታንዛኒያ ለዚህ ክብር የበቃችው ዳር-ኤስ-ሳላም ላይ በተካሄደው ፍጻሜ ግጥሚያ አይቮሪ ኮስትን 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነው። ለነገሩ ምዕራብ አፍሪቃይቱ አይቮሪ ኮስት አሸንፋ ቢሆን ኖሮ እንኳ ዋንጫውን የምትወስደው ከፍጻሜ በመድረስ በአካባቢው ቀደምት ለመሆን የበቃችው ታንዛኒያ ነበረች።

ያም ሆነ ይህ ቀደም ሲል በዕለቱ ለሶሥተኝነት በተካሄደው ግጥሚያ ደግሞ ኡጋንዳ ኢትዮጵያን 4-3 አሸንፋለች። እስከ እረፍት ድረስ እንዲያውም ኢትዮጵያ 2-1 ትመራ ነበር። በግጥሚያው ሰባት ጎሎች መቆጠራቸው እርግጥ በአብዛኛው የበረኞችና የተከላካዮች ስህተት መፈራረቅ ያስከተለው ሆኖ ታይቷል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተለይም በመከላከል ስህተትና በአካል ጥንካሬ ጉድለት በአራተኝነት ቢወሰንም በተለይ በተጫዋቾቹ የቴክኒክ ጥበብና ግሩም የቅብብል ብስለት ብዙ አድናቆትን ነው ያተረፈው።
ቡድኑ የመጀመሪያውን የምድብ ዙር ኬንያን 2-1 በማሸነፍና ከማላዊ 1-1 በመለያየት ሲወጣ በተለይም በሩብ ፍጻሜው ዛምቢያን 1-0 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ ማለፉ የተጠበቀ አልነበረም። በግማሽ ፍጻሜውም ምንም እንኳ በአይቮሪ ኮስት 1-0 ይረታ እንጂ በጥቅሉ ግሩም ውጤት ለማስመዝገብ ችሏል። የቡድኑ አሰልጣኝ አይፊም ኦኑኦራም ከዚህ በመነሣት የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደ ቀድሞ ጥንካሬው ለመመለስ ተሥፋ እንደሚያደርግ ነው የገለጸው።

“በካፍ በአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን መስራቾች ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ ከመጀመሪያዎቹ አንዷና ከጠንካሮቹ መካከል የምትገኝ ነበረች። ግን አሁን ያ ጊዜ አልፏል። እናም ቀላል ባይሆንም የተጫዋቾቹን የግል ችሎታና ተሰጥኦ በመጠቀም የኢትዮጵያን እግር ኳስ ለማደስ ነው የምንጥረው”

ቡድኑ በታንዛኒያው ውድድር የተሳተፈው በተለይም አቅምን ለመፈተሽ ነበር። ይሁንና ውጤቱ በመጨረሻ ከታሰበው በላይ ነው የሆነው። ይህም ኦኑራ እንደጠቀሰው እርግጥ ያለ ምክንያት አይደለም።

“አዎን ቀድሞ የነበሩትን ስህተቶች እያረምን ነው የምንሄደው። የሥልጠና ዘዴያችንንም በዚሁ መስመር ማራመድ ይዘናል። አሁን የአጨራወት ዲሲፕሊን አለን። ይህ ነው የስኬቱ ምክንያት”

ብዙዎቹን የአፍሪቃ ቡድኖች ከኢትዮጵያ ይልቅ ጠንካራ የሚያደርጋቸው በተለይም ተጫዋቾቻቸው በአውሮፓ ሊጋዎች ውስጥ የሚጫወቱና ልምድ የቀሰሙ መሆናቸው ነው። በቴክኒክ ,ረገድ ግን ኢትዮጵያ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች ማፍራቷን ዛሬም አላቆመችም። ታዲያ ወደፊት የኢትዮጵያ ተጫዋቾችም በአውሮፓ በርከት ብለው ይታዩ ይሆን? ይህ በተለይም የአሠልጣኙ የአይፊም ኦኑኦራ ፍላጎት ነው።

“ይሄ አንዱ ወደፊት የምናተኩርበት ነገር ነው። ብዙ ተጫዋቾች በአንግሊዝና መሰል ሊጋዎች ልምድ እንዲቀስሙ ለማድረግ እንፈልጋለን። አንዳንዶቹ ደግሞ በዚህ አቅጣጫ ጠቃሚ ዕርምጃ እንደሚያደርጉ ተሥፋዬ ነው”

ኢትዮጵያ ለ 2012 ዓ.ም. በሚካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ከባድ ምድብ ውስጥ መሆኗ ይታወቃል። በወቅቱ ማዳጋስካርን አሸንፋ በምድቧ ውስጥ ሶሥተኛ ስትሆን የተሳካ ዕርምጃ ለማድረግ ናይጄሪያንና ጊኒን የመሳሰሉትን ሃያል አገሮች ለመፈታተን መብቃቷ ግድ ነው። ለዚሁ የታንዛኒያው ውድድር ውጤት ተሥፋ ሰጭ ሣይሆን አልቀረም።

“እርግጥ ምድቡ ከባድ እንደሆነ እናውቃለን። ማዳጋስካርን አሸንፈናል። ጊኒንና ናይጄሪያን በተመለከተ ደግሞ በራሳችን ሜዳ ለማሸነፍ መጣር አለብን። አሁን ታንዛኒያ ውስጥ ያልተጠበቀ ነገር ነው ያየነው። እናም ስኬት ላይ ልንደርስ እንችላለን ብዬ ነው የማምነው”

ለማንኛውም ከባዱን ማጣሪያ ለማለፍ በተለይም የታክቲክ ስህተቶችን ከወዲሁ ማረሙ ግድ የሚሆን ነው የሚመስለው።

በአትሌቲክስ ላይ እናተኩርና ኬንያዊው ኒኮላስ ቼሊሞ ትናንት ሆኖሉሉ ላይ የተካሄደው የማራቶን ሩጫ አሸናፊ ሆኗል። በዚሁ ውድድር ይበልጥ አስደናቂው ውጤት በሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ማራቶን የሮጠችው ኢትዮጵያዊት በላይነሽ ገብሬ ለድል መብቃቷ ነበር። የቀድሞዋ ሻምፒዮን ሩሢያዊቱ ስቬትላና ዛካሮቫ ሁለተኛ ስትወጣ በላይነሽ ያሸነፈችው ከጓደኛዋ ውሃ በመቀበል ያላግባብ ነው ስትል ለውድድሩ ኮሚቴ አቤቱታ አሰምለች። ሆኖም ኮሚቴው ድርጊቱን ሕገ-ወጥ አድርጎ አላገኘውም።

ሰንበቱን ፖርቱጋል ውስጥ በተካሄደው የአውሮፓ አገር አቋራጭ ሩጫ ውድድር ደግሞ የኡክራኒያው አትሌት ሤርጂ ሌቤድ ለዘጠነኛ ጊዜ አሸናፊ ሆኗል። የ 35 ዓመቱ ሌቤድ የመጀመሪያ ድሉን የተቀዳጀው ከ 12 ዓመታት በፊት በዚያው በፖርቱጋል ነበር። የስፓኙ አያል ላምዳሰም ሁለተኛ ሲወጣ የፖርቱጋሉ ዩሱፍ-ኤል-ካላይ ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል። በሴቶች ንጽጽር የፖርቱጋሏ ጄሲካ አጉስቶ የቱርክ ተፎካካሪዋን በማስከተል አሸናፊ ሆናለች።

ወደ እግር ኳሱ ስፖርት እንመለስና በአውሮፓ ቀደምት ክለቦች ሻምፒዮና ባለፈው ሣምንትም ብዙ አስደናቂ ግጥሚያዎች ተካሂደዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ሢቲይ ዌስት-ሃም-ዩናይትድን 3-1 በማሸነፍ ለጊዜውም ቢሆን አመራሩን ከያዘው ከአርሰናል ጋር በነጥብ ሲመሳሰል ቼልሢይ በአንጻሩ ከቶተንሃም ሆትስፐር ጋር ባደረገው ግጥሚያ 1-1 በሆነ ውጤት በመወሰን ወደ አራተኛው ቦታ ተንሸራቷል። አርሰናልና ማንቼስተር ዩናይትድ ዛሬ ማምሻውን የሚጋጠሙ ሲሆን የሁለቱ አሸናፊ አመራሩን ሊይዝ የሚችል ነው።

1. Bundesliga Hamburger SV - Bayer 04 Leverkusen
ምስል dapd

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ዶርትሙንድ ብሬመንን 2-0 በማሸነፍ አመራሩን ወደ 11 ነጥቦች ከፍ ሲያደርግ በፍጹም ልዕልና ወደፊት መገስገሱን እንደቀጠለ ነው። ሆኖም ሻምፒዮን ስለመሆን አሁንም ደፍሮ ለመናገር የሚፈልግ የቡድኑ ባልደረባ የለም። እንዲያውም እንደ ብሄራዊው ተጫዋች እንደ ማትስ ሁመልስ አባባል ቁጥብነት ነው የተመረጠው።

“ዛሬ ጥሩ ጨዋታ አላሳየንም። ይልቁንም ውጤቱ ብዙ ትግልን የጠየቀ ነበር። ዋናው ነገር እርግጥ ግጥሚያዎቻችንን ማሸነፋችን ነው። ይህ ከተሣካ በየሣምንቱ ደስተኛ እንደሆንን እንቀጥላለን”
ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ሃምቡርግን 4-2 ያሸነፈው ሌቨርኩዝን ሁለተኛ ሲሆን ሶሥተኛው ደግሞ ሽቱትጋርትን 2-1 የሸኘው ሃኖቨር 96 ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሁለቱም ቀደምት ክለቦች ሰንበቱን በድል ሲያሳልፉ በተለይም ቀደምቱ ባርሤሎና ሬያል ሶሲየዳድን 5-0 በማሸነፍ ልዕልናውን አስመስክሯል። ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው ድንቁ ሊዮኔል ሜሢ ነበር። ሁለተኛው ሬያል ማድሪድም ሣራጎሣን 3-1 ሲረታ ከባርሤሎና የሚያንሰው በሁለት ነጥቦች ብቻ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኤ.ሢ.ሚላን ቦሎኛን 3-0 ሲረታ ሁለተኛው ላሢዮ በጁቬንቱስ በመሸነፉ የተነሣ አመራሩን ወደ ስድሥት ነጥቦች ከፍ ሊያደርግ በቅቷል። ኢንተር ሚላን በአንጻሩ አንድ ጨዋታ ጎሎት ሰባተኛ ነው። በተረፈ በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ሊል አመራሩን መልሶ ሲይዝ በኔዘርላንድ ሻምፒዮናም አይንድሆፈን ምንም እንኳ እኩል ለእኩል ቢወጣም ቀደምቱ እንደሆነ ቀጥሏል።

በአውሮፓ የ 2010 የሴቶች የዕጅ ኳስ ውድድር ትናንት በተካሄደ ግጥሚያ ስዊድን የኖርዌይን ሻምፒዮን ቡድን ባልተጠበቀ ሁኔታ ለመጀመሪያው ሽንፈት አብቅታለች። የስዊድኑ ቡድን ያሸነፈው 24-19 በሆነ ውጤት ነበር። ከዴንማርክ ጋር የጋራ አስተናጋጅ የሆነችው ኖርዌይ ውድድሩን የጀመረችው ለተከታታይ አራተኛ ድል ለመብቃት ነበር። በተቀሩት የትናንት ግጥሚያዎች ፈረንሣይ ከኔዘርላንድ 23-21፤ እንዲሁም ሁንጋሪያ ከኡክራኒያ 26-25 ተለያይተዋል። በዛሬው ዕለት ደግሞ ስፓኝ ከሞንቴኔግሮ፣ ሩሜኒያ ከክሮኤሺያና ዴንማርክ ከሩሢያ ይጋጠማሉ።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ