1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 23 2003

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ የሚካሄደው ውድድር በዚህ ሣምንትም አንዳንድ ማራኪ ግጥሚያዎች በታዩበት ሁኔታ ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/Qx2d
ሊዮኔል ሜሢምስል picture-alliance/ dpa

ያለፈው ሰንበት ሶሥት ታላላቅ ዓለምአቀፍና የአካባቢ ውድድሮች የተጠናቀቁበትም ነበር። የካታሩ የእሢያ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በጃፓን ድል ተፈጽሟል። አውስትሬሊያ ውስጥ ሲካሄድ የሰነበተው ታላቅ የቴኒስ ውድድር አውስትራሊያን-ኦፕን ደግሞ ትናንት ሲጠናቀቅ ዘንድሮ ለድል የበቁት ኮከቦች የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪችና የቤልጂጓ ኪም ክላይስተርስ ናቸው። ስዊድን ውስጥ የተካሄደው የዓለም ዕጅ ኳስ ሻምፒዮናም ትናንት እንደገና በፈረንሣይ አሸናፊነት ሲፈጸም የኢትዮጵያ አትሌቶችም በአሜሪካ ቀደምቱ ነበሩ።

በአውሮፓ እግር ኳስ እንጀምርና በስፓኝ ላ-ሊጋ የሬያል ማድሪድ መሰናከል ለባርሤሎና ሲበጅ በኢጣሊያ ሤሪያ-አ እና በጀርመን ቡንደስሊጋ ኤ,ሢ.ሚላንና ዶርትሙንድ በስኬት ጉዟቸው ቀጥለዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደግሞ ሣምንቱ የፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ነበር።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና ሄርኩለስን 3-0 በመርታት አመራሩን ወደ ሰባት ነጥቦች ሲያሰፋ ለዚሁ ምክንያት የሆነውም የቅርብ ተፎካካሪው ሬያል ማድሪድ ትናንት ከአንደኛው ዲቪዚዮን እንዳይወርድ በሚያሰጋው በኦሣሱና 1-0 መሸነፉ ነው። ለባርሣ የመጀመሪያዋን ጎል ፔድሮ ሲያስቆጥር የተቀሩትን ሁለት ጎሎች ያገባው ደግሞ ሊዮኔል ሜሢ ነበር። ለባርሤሎና የሰንበቱ ድል በተከታታይ 15ኛው ሲሆን በዚሁ ሬያል ማድሪድ እ.ጎ.አ. በ 1960-61 የጨዋታ ወቅት ካስመዘገበው ክብረ-ወሰን ላይ ሊደርስ በቅቷል።

ኤፍ.ሢ.ባርሤሎና አሁን ከፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ 21 ግጥሚያዎች በኋላ በ 58 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ሬያል ማድርድ በ 51 ይከተላል፤ ኤስፓኞልን 1-0 ያሸነፈው ቪላርሬያል ደግሞ በ 45 ነጥቦች ሶሥተኛ ነው። በጎል አግቢነት የሬያሉ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ 22 ጎሎች አስቆጥሮ የሚመራ ሲሆን ሊዮኔል ሜሢ በአንዲት ጎል ብቻ ዝቅ ብሎ በሁለተኝነት ይከተለዋል። የሁለቱ ከዋክብት ግሩም አጨዋወት ዘንድሮ በክለቦቻቸው የእስካሁን ዕርምጃ ላይ ታላቅ አስተዋጽኦ ነበረው፤ ሂደቱ ቀጣይ የሚሆንም ነው የሚመስለው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰንበቱ የፌደሬሺኑ ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች የተካሄዱበት ነበር። በሰንበቱ አምሥተኛ ዙር የመልስ ግጥሚያዎች የቀጣዩ ዙር 16 ተሳታፊ ክለቦች ማንነት ሲለይለት ዝቅተኛው የአምሥተኛ ዲቪዚዮን ቡድን ክሮውሊይ-ታውን ለምሳሌ ከነዚሁ አንዱ ሊሆን መብቃቱ ብዙዎችን ነው ያስደነቀው። ቡድኑ በሚቀጥለው ዙር በኦልድ-ትሬፎርድ ስታዲዮም የማንቼስተር ዩናይትድ ተጋጣሚ ሲሆን ለተጫዋቾቹ ታላቅ ሕልማቸው ዕውን ሊሆን በቅቷል። ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ ወደ ተከታዩ ዙር ያለፈው ሳውዝሃምፕተንን በትግል ከኋላ ተነስቶ 2-1 ካሸነፈ በኋላ ነበር።

ከቀደምቱ ክለቦች መካከል አርሰናልም ወደፊት ለመዝለቅ ብዙ መታገል ነበረበት። ቡድኑ ከሶሥተኛው ዲቪዚዮን ክለብ ከሃደርስፊልድ ጋር ባደረገው ግጥሚያ 2-1 በሆነች ጠባብ ውጤት ሲያሸንፍ ከውድቀት ያመለጠው ፋብሬጋስ ዘግይቶ ባስቆጠራት የፍጹም ቅጣት ምት ጎል ነበር። ሌላው ታላቅ ክለብ ማንቼስተር ሢቲይም ከሶሥተኛ ዲቪዚዮኑ ክለብ ከኖትስ-ካውንቲይ ጋር ባደረገው ግጥሚያ ለጥቂት ከውርደት ሊያመልጥ ችሏል። በተቀረ ፉልሃም፣ ኖቲንግሃም ፎሬስት፣ ስቶክ-ሢቲይ፣ ኤስተን ቪላና ቼልሢይም ወደ ቀጣዩ ዙር ከተሻገሩት ክለቦች መካከል ይገኛሉ።

Flash-Galerie Fussball Bundesliga Saison 10/11 20. Spieltag Vfl Wolfsburg Borussia Dortmund
ምስል dapd

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ባለፈው ሰንበትም ከ 11 ተከታታይ ግጥሚያዎቹ አሥረኛውን በማሸነፍ በድል ጉዞው ቀጥሏል። ቡድኑ ቮልፍስቡርግን በፍጹም ልዕልና 3-0 ሲረታ ሊጋውን የሚመራው ተዝናንቶ በ 11 ነጥቦች ልዩነት ነው። ቡድኑ በወቅቱ በቀላሉ ግሩም-ድንቅ ነው ለማለት ይቻላል። አሠልጣኙን ዩርገን ክሎፕን በዚህ ሰንበትም ይበልጥ ያረካው ይሄው የቡድኑ አጨዋወት ነበር።

“እርግጥ ነው በጨዋታው ውጤት፣ በተለይም ውጤቱ በተገኘበት ሁኔታና በቡድኑ አስተዋጽኦ በጣሙን ነው የተደሰትኩት። ቡድኑ ከኋላ እስከፊት በሙሉ ትኩረት ሲጫወት ከግቡ ለመድረስም ቁርጠኝነት አሳይቷል። በጨዋታው ሂደት አንዴም ሳይዳከም እስከመጨረሻው ነው የታገለው። እናም ትግል በተመላው ግጥሚያ በሚገባ ስናሽንፍ በዚሁ መሠረት ወደ ቤታችን ያመራነውም በደስታ ነው”

ሁለተኛው ሌቨርኩዝን ሃኖቨርን 2-0 ሲረታ ባለፉት ሣምንታት ጠቃሚ ዕርምጃ ያደረገው ባየርን ሙንሺንም ብሬመንን 3-1 በማሸነፍ በሶሥተኛው ቦታ ላይ ተቆናጧል። ሆኖም ዶርትሙንድ በእስካሁን ጥንካሬው ከቀጠለ የሚደረስበት መሆኑ በጣሙን የሚያጠራጥር ነው። ስለዚህም የሌቨርኩዝንና የባየርን ፉክክር ይበልጡን ለመጪው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ቀጥተኛ ተሳትፎ በሚያበቃው በሁለተኛ ቦታ ላይ የሚያተኩር ይመስላል። በዚሁ የተነሣ ከአካል ጉዳቱ በማገገም የተመለሰው የሌቨርኩዝን ተጫዋች ሚሻኤል ባላክም ለቡድኑ ድል ታላቅ ክብደት ነው የሰጠው።

“እርግጥ ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ በማጠናቀቄ ደስተኛ ነኝ። ይበልጡን ግን የቡድኑ ማሸነፍና ሁለተኛ ቦታውን ማረጋገጡ ነው ትልቁ ነገር። ግጥሚያው እርግጥ በጣም ከባድ ነበር። እናም በዚህ ሁኔታ ሶሥቱን ነጥቦች ለመውሰድ በመቻላችን ደስታችን ታላቅ ነው”

በተረፈ ዘንድሮ ዕድል የከዳቸው የቀድሞ ጠንካራ ክለቦች ብሬመንና ሻልከ በሰንበቱ ሽንፈታቸው መልሰው ሲያቆለቁሉ በተለይም ቬርደር ብሬመን ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን እንዳይወርድ በጣሙን ያሰጋዋል። በወቅቱ 15ኛ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኤሢ.ሚላን ካታኛን 2-0 በማሸነፍ በአራት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። ሁለተኛው ናፖሊም ሣምፕዶሪያን 4-0 ሲሸኝ ሶሥተኛው ላሢዮ ደግሞ ፊዮሬንቲናን 2-0 አሸንፏል። ከዚሁ ሌላ በፈረንሣይ ሻምፒዮና ሊልና በፖርቱጋልም ፖርቶ ሊጋቸውን በየፊናቸው ይመራሉ።

ካታር ውስጥ ሲካሄድ የሰነበተው የእሢያ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በጃፓን አሸናፊነት ተፈጽሟል። የጃፓን ብሄራዊ ቡድን ለዚህ ክብር የበቃው የፍጻሜ ተጋጣሚውን አውስትራሊያን በተጨማሪ ጊዜ 1-0 ከረታ በኋላ ነው። “ወርቃማዋን ጎል” ጨዋታው ሊያበቃ 11 ደቂቃዎች ቀርተው ሳለ ያስቆጠረው ሊ-ታዳናሪ ነበር። ጃፓን የእሢያን ዋንጫ ስታገኝ ከ 1992 ወዲህ በጠቅላላው ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።

የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን ሞሮኮ እ.ጎ.አ. በ 2015 ዓ.ም. የአፍሪቃን ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ከ 1988 ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ እንድታስተናግድ መረጠ። የፌደሬሺኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኪንሻሣ ላይ ባደረገው ስብሰባ የዓለም ዋንጫን በአስደናቂ ሁኔታ ያስተናገደችው ደቡብ አፍሪቃ ደግሞ የ 2017-ን ፍጻሜ እንድታዘጋጅ ሰይሟል። አፍሪቃን ካነሣን ለንደን ላይ ለሚካሄደው የ 2012 ኦሎምፒክ ጨዋታ በሚደረገው የሴቶች የእግር ኳስ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎን በመልስ ግጥሚያው 3-0 በመርታት ወደ ሁለተኛው ዙር አልፏል። የመጀመሪያ ግጥሚያ 0-0 መፈጸሙ ይታወሣል። የኢትዮጵያ ሴቶች በሁለተኛው ዙር የሚጋጠሙት ጊኒን 7-1 አሸንፎ ካስወጣው የጋና ቡድን ጋር ነው።

Flash-Galerie Handball WM Schweden
ምስል AP

ስዊድን ውስጥ የተካሄደው የዓለም ዕጅ ኳስ ሻምፒዮና ትናንት በፈረንሣይ ድል ተፈጽሟል። ፈረንሣይ ማልመ ላይ በተካሄደው የፍጻሜ ግጥሚያ ዴንማርክን 37-35 ስታሸንፍ ይህም በተከታታይ አራተኛው የዓለም ሻምፒዮና ድሏ መሆኑ ነበር። በተጨማሪ ሰዓት በለየለት ፍጻሜ ጨዋታ የፈረንሣይ ቡድን ልዕልና በሚገባ ሲንጸባረቅ አንዳንዶቹን ተጫዋቾች በቅርብ የሚያውቃቸው በዚህ በጀርመን የሃምቡርግ የዕጅ ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ማርቲን ሽቫልብ እንዳለው ቡድኑ በወቅቱ አቻ የማይገኝለት ነው።

“በቀላሉ ልምድ ያላቸው ናቸው። ችሎታቸው ከፍተኛ እንደሆነም ያውቃሉ። በጨዋታ ላይ ብዙ ስህተት አይሰሩም። የተረጋገጉ ናቸው። እናም የዓለም ሻምፒዮን መሆናቸው ተገቢ ነው”

ስፓኝ በውድድሩ ሶሥተኛ ስትወጣ ከፍተኛ ውጤት የማስመዝገብ ታላቅ ተሥፋ ጥሎ ወደ ወድድሩ የሄደው የጀርመን ቡድን በአንጻሩ በ 11ኝነት መገታቱ ግድ ሆኖበታል።

Flash-Galerie Australian Open Djokovic
ምስል AP

በዓለም ላይ ታላላቅ ከሚባሉት የቴኒስ ውድድሮች አንዱ በሆነው በአውስትራሊያን-ኦፕን ደግሞ በወንዶች የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪች የብሪታኒያ ተጋጣሚውን ኤንዲይ መሪይን በማሽነፍ የዓመቱን ግሩም ጅማሮ አድርጓል። ጆኮቪች 6-4, 6-2, 6-3 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ለድል የበቃው በፍጹም ልዕልና ነበር። ታዲያ ተጋጣሚው ኤንዲይ መሪይም ለአሸናፊው ዕውቅና መስጠቱ አልቀረም።

“ኖቫክን ለድሉ እንኳን ደስ ያለህ ለማለት እወዳለሁ። በበኩሌ ወደፊት ነው የምመለከተው። ለመመለስ ብዙ ዕድል ነው ያለኝ

በሴቶች ፍጻሜ ደግሞ የቤልጂጓ ኪም ክላይስተርስ የቻይና ተጋጣሚዋን ሊ-ናን በማሸነፍ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ልትል በቅታለች። ተዋረዱን አሁንም በአንደኝነት የምትመራው የዴንማርኳ ካሮሊን ቮዝኒያችኪ ናት።

በመጨረሻም በአትሌቲክስ ላይ እናተኩርና ሰንበቱን አሜሪካ ውስጥ በተካሄደው የሂዩስተን ማራቶን ድሉ በሴቶችና በወንዶች በጠቅላላው የኢትዮጵያ አትሌቶች ሆኗል። በካና ዳባ የአገሩን ልጅ ተሾመ ገላናን አስከትሎ ሲያሸንፍ በሴቶች ደግሞ ማሚቱ ዳስካ ቀዳሚ ሆናለች። ባለፈው አርብ የኒውዮርክ ሜልሮዝ የማይል ሩጫም አሸናፊው ኢትዮጵያዊ ነበር። ከሰባት ዓመታት ወዲህ በስፍራው ተሸንፎ የማያውቀው ከኬንያ የመነጨ አሜሪካዊ አትሌት ቤርናርድ ላጋት ድሉን ለመጀመሪያ ጊዜ ለደረሰ መኮንን ማስረከቡ ግድ ሆኖበታል። ሌላው የአትሌቲክስ አዲስ ዜና ሃይሌ ገብረሥላሴ በሚቀጥለው ወር የቶኪዮ ማራቶን የሚወዳደር መሆኑ ነው። አዘጋጆቹ ከወዲሁ እንዳስታወቁት በሩጫው ላይ በርካታ ጠንካራ አትሌቶች ይሳተፋሉ።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ