1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 7 2003

የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የእግር ኳስ ውድድር በዚህ ሰንበትም አስደናቂ ጨዋታዎችና ውጤቶች የታዩበት ሆኖ ነው ያለፈው።

https://p.dw.com/p/R0jp
ምስል dapd

ይሄው የቀደምቱ ሊጋዎች ውድድር፣ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋና ባለፈው ሣምንት አጋማሽ በዓለም ዙሪያ የተካሄዱት የወዳጅነት ግጥሚያዎች ዛሬ በእግር ኳሱ ዓለም በሰፊው የምናተኩርባቸው ጉዳዮች ናቸው።

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የእግር ኳስ ውድድር እንጀምርና በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሰንበቱ የባርሤሎና የድል ዕርምጃ ክለቡ በማከታተል 16 ጊዜ ካሸነፈ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገታበት ነበር። ባርሣ ከስፖርቲንግ ጊዮን 1-1 ሲለያይ አንዷን ነጥብም ለማዳን የቻለው ከኋላ ተነስቶ ከታገለ በኋላ ነው። በሌላ በኩል የቅርብ ተፎካካሪው ሬያል ማድሪድ በበኩሉ ግጥሚያ ኤስፓኞልን 1-0 በመርታት ባርሤሎናን እስከ አምሥት ነጥብ ሊቃረበው በቅቷል።
ሬያል በረኛው ኢከር ካሢያስ ገና ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ ላይ የኤስፓኞልን አጥቂ ሆሴ ካሌጆንን ጠልፎ በመጣል ቀይ ካርድ ተሰጥቶት ከሜዳ ሲወጣበት ለማሸነፍ መብቃቱ ራሱ የሚያስደንቅ ነው። ለማንኛውም ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ባርሣ በ 61 ነጥቦች ሊጋውን መምራቱን የቀጠለ ሲሆን ሬያል ማድሪድ በ 57 ነጥቦች በሁለተኝነት ይከተላል። ሶሥተኛው ቪላርሬያል በዴፖርቲቮ-ላ-ኮሩኛ 1-0 ሲሸነፍ ከሬያል ጋር ያለው ልዩነት ወደ አሥር ነጥብ ከፍ ብሏል። ከዚህ ውጤት በኋላ የስፓኝ ሻምፒዮና የሁለቱ ክለቦች የብቻ ፉክክር የሰፈነበት ሆኖ ለመቀጠሉ ብዙም ጥርጥር አይኖረውም።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሰንበቱ ታላቅ ግጥሚያ አመራሩን እንደያዘ በቀጠለው በማንቼስተር ዩናይትድና በከተማ ተፎካካሪው በማንቼስተር ሢቲይ መካከል የተካሄደው ነበር። ግጥሚያው በማንቼስተር ዩናይትድ አሸናፊነት 2-1 ሲፈጸም ማኒዩ ለድል እንዲበቃ ወሣኝ የሆነችው ዌይን ሩኒይ በ 78ኛው ደቂቃ ላይ ተገልብጦ ያገባት ግሩም ጎል ነበረች። ለማንቼስተር ሢቲይ የሰንበቱ ሽንፈት ከሻምፒዮነቱ ፉክክርም የስንብት ነው የሆነው። ክለቡ በወቅቱ ለዚያውም የአንድ ጨዋታ ብልጫ ኖሮት ከማንቼስተር ዩናይትድ በስምንት ነጥቦች ዝቅ ያለ ነው።

በሌላ በኩል ሁለተኛው አርሰናል ዎልቨርሃምፕተን ወንደረርስን ሆላንዳዊ አጥቂው ሮቢን-ፋን-ፐርሢ ባስቆጠራቸው ጎሎች 2-0 ሲረታ የማንቼስተር ዩናይትድ ብርቱ ተፎካካሪ ሆኖ ቀጥሏል። በወቅቱ ከማኒዩ የሚለዩት አራት ነጥቦች ብቻ ናቸው። በፕሬሚየር ሊጉ ውድድር ቶተንሃም ሆትስፐር ደግሞ ሰንደርላንድን 2-1 አሸንፎ አራተኛ ሲሆን ቼልሢይ ዛሬ ማምሻውን ፉልሃምን ከረታ ቢቀር በጎል ብልጫ በቦታው ሊተካ ይችላል። ሊቨርፑል ስድሥተኛ፤ ሰንደርላንድ ሰባተኛ!

Flash-Galerie Fußball Bundesliga - 1. FC Kaiserslautern gegen Borussia Dortmund
ምስል dapd

በጀርመን ቡንደስሊጋ ዶርትሙንድ ለሁለተኛ ሣምንት በተከታታይ በእኩል ለእኩል ውጤት ቢወሰንም ሊጋውን በአሥር ነጥቦች ልዩናት መምራቱን ቀጥሏል። ቡድኑ በካይዘርስላውተርን ሜዳ ላይ ባደረገው የውጭ ግጥሚያ እስከ ዘጠናኛዋ ደቂቃ ድረስ ሲመራ ቆይቶ በመጨረሻ 1-1 ሲለያይ ውጤቱ እንደ ስቬን ቤንደር ሁሉ ተጫዋቾቹን በጣሙን ነው ያስቆጨው።

“ድላችንን በመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ መነጠቃችን እርግጥ መሪርና የሚያሳዝን ነገር ነው። በዚህ ግሩም ስታዲዮም ውስጥ የጋለ የደጋፊዎች ጩኸትና ብርቱ ተጋጣሚም እንደሚጠብቀን ከወዲሁ እናውቅ ነበር። ሆኖም ጨዋታው ሊያበቃ ሲል ጎል መቀበላችን መሪር ነው”

ሁለተኛው ሌቨርኩዝን በአንጻሩ በግሩም ጨዋታ ፍራንክፉርትን 3-0 ሲረታ ሶሥተኛው ባየርን ሙንሺንም እንዲሁ ሆፈንሃይምን 4-0 በመቅጣት መልሶ መጠናከሩን አሳይቷል። በኔዘርላንዱ ኮከብ በአርየን ሮበንና በፈረንሣዩ ብሄራዊ ተጫዋች በፍራንክ ሪቤሪይ መመለስ ያየለው ባየርን ሙንሺን ዶርትሙንድ አንድ ሁለቴ ከተሰናከለ ለሻምፒዮንነቱ ሊያሰጋውም የሚችል ነው።
በሌላ በኩል የቀድሞው ሃያል ክለብ ብሬመን በዚህ ሰንበትም በሜዳው በማሽነፍ አቆልቋይ ሂደቱን ለመግታት ሳይችል ቀርቷል። ቡድኑ ከሃኖቨር ጋር 1-1 ሲለያይ በወቅቱ በቡንደስሊጋው ተዋረድ ላይ 14ኛ ነው። በአንጻሩ ኤፍ-ሢ.ኮሎኝ ትናንትም ጠንካራ ሆኖ ታይቷል። ቡድኑ ማይንስን 4-2 ሲያሸንፍ ተጫዋቹ ማርቲን ላኒግ እንደሚለው ባለፈው ሣምንት በባየርን ላይ የተጎናጸፈው ድሉ ሳያበረታታው አልቀረም።

“የማስበው በባየርን ሙንሺን ላይ ያገኘነው 3-2 ውጤት ታላቅ ግፊት ሆኖናል ብዬ ነው። ዛሬ ሜዳ የገባነው ይህንኑ ስሜት ይዘን ነበር። እናም በጠቅላላው በውድድሩ ሂደት ግሩም ጨዋታችንን ዛሬ እንዳሳየን ነው የማምነው”

በተቀረ መንሸን ግላድባህ በዚህ ሣምንትም በሣንት ፓውሊ 3-1 በመሸነፍ የመጨረሻ እንደሆነ ሲቀጥል ውጤቱ ክለቡ ከአሠልጣኙ ከሚሻኤል ፍሮንሤክ እንዲለያይ ነው ያደረገው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ የውድድር ሂደት ቢቀር አመራሩን በተመለከተ የተለወጠ ነገር የለም። ቀደምቱ ኤ.ሢ.ሚላን ፓርማን 4-0 ሲሽኝ በሁለተኝነት የሚከተለው ናፖሊም ሮማን 2-0 አሸንፏል። ሶሥተኛው ላሢዮም ብሬሻን እንዲሁ 2-0 ሲረታ በጁቬንቱስ 1-0 በመሸነፍ በረድ ያለው ኢንተር ሚላን ነው። ያለፉት ዓመታት የኢጣሊያ ሻምፒዮን በዚሁ ሶሥተኝነቱ አምልጦታል። በተቀረ በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ሊል፤ በኔዘርላንድ ሊጋ አይንድሆፈንና በፖርቱጋል ሻምፒዮናም ፖርቶ አመራራቸውን እንደያዙ ቀጥለዋል።

Flash-Galerie Joachim Löw
አሠልጣኝ ዮአኺም ሉቭምስል AP

ያለፈው ሣምንት በብሄራዊ ቡድኖች ደረጃ በዓለም ዙሪያ ከ 25 የሚበልጡ በርካታ የወዳጅነት ግጥሚያዎች የተካሄዱበትም ነበር። ከነዚሁ ጠንካራ የነበሩትን ለማንሣት ጀርመን ከኢጣሊያ 1-1፤ አርጄንቲና ከፖርቱጋል 2-1፤ ፈረንሣይ ከብራዚል 1-0፤ ስፓኝ ከኮሉምቢያ 1-0፤ እንዲሁም ኔዘርላንድ ከአውስሪያ 3-1 ተለያይተዋል። ይሄው የአቅም ፍተሻ ሙከራ ከደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ውድድር በኋላ ሁለተኛው ሲሆን በዚህ በጀርመን ብሄራዊው ቡድን ጥሩ ቢጫወትም በ 2006 የዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ በኢጣሊያ ደርሶበት የነበረውን ሽንፈቱን ማካካሱ አልሆነለትም። ይህም ያልተሳካው አሠልጣኙ ዮአኺም ሉቭ እንደሚለው ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ጠንክሮ ባለመቀጠሉ ነው።

“የኢጣሊያን ቡድን ለማሽነፍ ዘጠናውን ደቂቃ ሙሉ በፍጥነት መጫወት እንደነበረብን ቀደም ብለን የምናውቀው ጉዳይ ነው። ይህን እነሱ አይወዱትም። ሆኖም በሁለተኛው አጋማሽ ቀልጥፈን በመጫወት 2-0 መምራቱ አልተሳካልንም። አንድ ለዜሮውን ውጤት ይዘን ለማቆየት ነው የሞከርነው። ግን ይህን ከና የበለጠ የሚያውቁበት የኢጣሊያ ተጫዋቾች ናቸው”

በሌሎቹ ታላቅ ግጥሚያዎች የብራዚል ብሄራዊ ቡድን አሁንም የፓሪስ ምድር አልቀናውም። በአንጻሩ በአርጄንቲናና በፖርቱጋል የስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ኮከቦች በሊዮኔል ሜሢና በክሪስቲያኖ ሮናልዶ መካከል በተካሄደው ቀጥተኛ ፉክክር የላቲን አሜሪካ ልዕልና ጎልቶ ታይቷል። በሌሎች ተጨማሪ ጠንካራ በነበሩ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ደግሞ ክሮኤሺያ ከቼክ ሬፑብሊክ 4-2፤ ዴንማርክ ከእንግሊዝ 1-2፤ እንዲሁም ቱርክ ከደቡብ ኮሪያ ባዶ-ለባዶ ተለያይተዋል።

በዚህ በጀርመን ሰንበቱን በካርልስሩኸና በዱስልዶርፍ ከተሞች በተካሄዱ ዓለምአቀፍ የአዳራሽ ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች የቻይናው የመሰናክል ሩጫ የኦሎምፒክ ሻምፒዮንና የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ሊዩ ሢያንግ ከሶሥት ዓመታት በኋላ በአውሮፓ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረገው ውድድር በ 60 ሜትር ሶሥተኛ ለመሆን ችሏል። በመካከለኛ ርቀት ሩጫ አይለው የታዩት ከሞላ ጎደል በሙሉ ኬንያውያን አትሌቶች ነበሩ። በነገራችን ላይ ሊዩ ሢያንግን በተመለከተ ትልቁ ዜና አትሌቱ ወደፊት በሃይሌ ገብረ ሥላሴ ሆላንዳዊ ማኔጀር በጆስ ሄርመንስ የሚመራ መሆኑ ነው።

ቤይጂንግ በ 2015 ዓ.ም. በምታስተናግደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሌሎች ሴት የመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫ ስፖርተኞቿ ጭምር ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማድረግ የሄርመንስን ድጋፍ ሳትፈልግ አልቀረችም። በሌላ ጃፓን-ቺባ ላይ በተካሄደ አገር-አቋረጭ ሩጫ ውድድር በወንዶች የኬንያ አትሌቶች በ 12 ኪሎሜትር ከአንድ እስከ ሶሥት ተከታትለው ሲገቡ በሴቶች 8 ኪሎሜትር ደግሞ የአስተናጋጇ አገር አትሌቶች ተመሳሳይ ውጤት አስመዝግበዋል።

Aravane Rezai Tennis Frankreich Iran NO FLASH
ምስል AP

በዓለምአቀፉ የቴኒስ መድረክ ትናንት በአሜሪካ-ሣን ሆሴ የኤቲፒ ፍጻሜ ግጥሚያ ወጣቱ የካናዳ ተጫዋች ሚሎሽ ራኦኒች ታዋቂውን የስፓኝ ተጋጣሚውን ፌርናንዶ ቫርዳስኮን በአስደናቂ ሁኔታ 7-6, 7-6 በማሸነፍ ለመጀመሪያ የውድድር ድሉ በቅቷል። ቫርዳስኮ ያለፈው የሣን ሆሤ ኦፕን አሸናፊ እንደነበር የሚታወስ ነው። የሃያ ዓመቱ ወጣት ካናዳዊ ራኦኒች በትናንት ድሉ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ከ 84 ወደ 59 ከፍ እንደሚል ይጠበቃል።

በፓሪስ ኦፕን የሴቶች ፍጻሜ ደግሞ የቼክ ሬፑብሊኳ ፔትራ ክቪቶቫ የቅርቧን የአውስትራሊያን ኦፕን አሸናፊ የቤልጊጓን ቀደምት ተጫዋች ኪም ክላይስተርስን 6-4, 6-3 በመርታት ዓለምን አስደንቃለች። የሃያ ዓመቷ ክቪቶቫ እስካሁን በዓለም የማዕረድ ተዋረድ ላይ ከሁለተኛዋ ከክላይስተርስ አንጻር ብዙ ርቃ 18ኛዋ ነበረች። በሮተርዳም የቴኒስ ውድድርም የስዊድኑ ኮከብ ሮቢን ሶደርሊንግ ፈረንሣዊ ተጋጣሚውን ጆ-ዊልፍሪድ-ትሶንጋን 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ዘገባችንን በእግር ኳስ ለማጠቃለል በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ነገና ከነገ በስቲያ በቀሪዎቹ 16 ክለቦች መካከል የመጀመሪያው ዙር ጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ከነዚሁ በተለይ ጠንካራና ማራኪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ግጥሚያዎችም እርሰናል ከባርሤሎናና ኤ.ሢ.ሚላን ከቶተንሃም ሆትስፐር ናቸው። በተቀረ ብራዚልን ለሁለት የዓለም ዋንጫ ድሎች ያበቃው ድንቅ አጥቂ ሮናልዶ በዛሬው ምሽት ስንብቱን እንደሚያስታውቅ እየተጠበቀ ነው። የ 34 ዓመቱ የብራዚክ ኮከብ የሚያበቃው የቀድሞ ቅልጥፍናው እየከዳው በመሄዱ እንደሆነ ቀደም ሲል አመልክቶ ነበር።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ