1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 22 2003

ካለፈው ሣምንት ታላላቅ የስፖርት ውድድሮች አንዱ ሮማ ላይ የተካሄደው የአትሌቲክስ ዳያመንድ ሊግ ውድድር ነበር።

https://p.dw.com/p/RQpt
ምስል AP

ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ በሮማ የተካሄደው በዘንድሮው የውድድር ወቅት ሶሥተኛው የአትሌቲክስ ዳያመንድ ሊግ ውድድር በጃሜይካው የኦሎምፒክ ሻምፒዮንና የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት በዩሤይን ቦልት የተሣካ መልስ ተፈጽሟል። ለመቶ ሜትሩ መንኮራኩር የሮማው ውድድር ከዘጠኝ ወራት በፊት በአሜሪካዊው አትሌት በታይሰን ጌይ ከተሸነፈ ወዲህ የመጀመሪያው ነበር። ቦልት ሩጫውን ግሩም በሆነ 9,91 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም ሁለተኛውም የአገሩ ልጅ አሣፋ ፓውል ነበር። ፈረንሣዊው ክሪስቶፍ ሌሜትር ደግሞ ሶሥተኛ ወጥቷል። በወንዶች 800 ሜትር አሜሪካዊው ካዴቪስ ሮቢንሰን ባልተጠበቀ ሆኔታ አሸናፊ ሲሆን ሁለተኛና ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን የፈጸሙት የደቡብ አፍሪቃና የኩዌይት ተወዳዳሪዎች ናቸው። ጠንካሮቹ የኬንያ አትሌቶች ከአራተኛው እስከ ሰባተኛው ቦታ በመከታተል መወሰኑ ግድ ነው የሆነባቸው።

በአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ድሉ የኢትዮጵያ ነበር። ኢማነ መርጋ ሁለት ኬንያውያንን ከኋላው አስከትሎ ሲያሸንፍ ደጀን ገ/መስቀልና ስለሺ ስሂነ ደግሞ አራተኛና አምሥተኛ መሆናቸው የቡድኑን ልዕልና የሚያሳይ ነው። ሌላው የኢትዮጵያ አትሌት አበራ ኩማም ሩጫውን በስምንተኝነት ፈጽሟል። በነገራችን ላይ ኢማነ መርጋ ያስመዘገበው ጊዜ በዚህ ዓመት ከታየው ሁሉ ፈጣኑ ነበር። በተቀረ የአሜሪካ ሴት አትሌቶች በሁለት መቶ፣ አራት መቶና 110 ሜትር መሰናክል ሲያሸንፉ በ 1,500 ሜትር የባህሬይኗ ማርያም-ዩሱፍ-ጀማል ለድል በቅታለች። በዚሁ ርቀት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች መስከረም ለገሰ ሁለተኛ ገለቴ ቡርቃም ሶሥተኛ ሆነዋል። በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ኬንያዊቱ ሚልካ ቼይዋ ስታሸንፍ ሶፊያ አሰፋ ሁለተኛ ወጥታለች። የተቀሩት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ብርቱካን አዳማ አራተኛ ስትሆን መቅደስ በቀለም ሩጫውን በ 11ኛነት ፈጽማለች።

ትናንት በኔዘርላንድ ሄንገሎ በተካሄደ ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ደግሞ በወንዶች 800 ሜትር የፖላንዱ አዳም ኪሽቾት ሲያሸንፍ በ 1,500 ሜትር የሳውዲ አረቢያው ሞሐመድ ሻዌን ለድል በቅቷል። በዚህ ርቀት ኬንያዊው ሃሮን ካይታኒይ ሁለተኛ ሲወጣ ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመው መኮንን ገ/መድህን ነው። በወንዶች አምሥት ሺህ ሜትር ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል ቀዳሚ ሲሆኑ በ 110 ሜትር መሰናክል ያሸነፈው የኩባው የዓለም ሻምፒዮን ዴይሮን ሮብልስ ነበር። ጀርመናውያን በምርኩዝ ዝላይና በዲስክ ውርወራ ሲያሸንፉ በሴቶች 1,500 ሜትር ማርያም ዩሱፍ ጀማል አንደኛ፤ እንዲሁም ቃልኪዳን ገዛኸኝ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽመዋል። ለኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ትልቁ ድል የኬንያ ወንዶች እንዳደረጉት ሁሉ በ 5000 ሜትር ከአንድ እስከ ሶሥት ተከታትሎ ማሸነፉ ነበር። መሠረት ደፋር አንደኛ፣ ስንታየሁ እጅጉ ሁለተኛ፣ ሱሌ ጌዶ ሶሥተኛ በመሆን ተከታትለው ገብተዋል።

FIFA Logo

የፊፋ ፕሬዚደንት ከሙስና ነጻ ተደረጉ

የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የፊፋ ስነ ምግባር ኮሚቴ ትናንት ባካሄደው ስብሰባ የድርጅቱን ፕሬዚደንት ሤፕ ብላተርን ከሙስና ክስ ነጻ ሲያደርግ የተቀሩትን ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ደግሞ በጊዜያዊነት አግዷል። ሁለቱ የታገዱት ባለሥልጣናት ብላተርን በፕሬዚደንት የመፎካከር ዕጩነታቸውን ጥቂት ሰዓታት ቀደም ሲል የሳቡት የእሢያው እግር ኳስ ኮን-ፌደሬሺን ፕሬዚደንት የካታሩ ቢን-ሃማንና የኮንካካፍ፤ የሰሜን፣ ማዕከላዊና ካራይብ አካባቢ ፌደሬሺን ባለሥልጣን የፊፋ ምክትል ፕሬዚደንት ጃክ ዋርነር ናቸው። ሁለቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተከሰሱት የካራይብ አካባቢ ልዑካን በፊፋ ፕሬዚደንትነት ምርጫ ለብላተር ብቸኛ ተፎካካሪ ለሃማን ድምጽ እንዲሰጡ 40 ሺህ ዶላር ጉቦ ለማሸግ ተስማምተዋል በመባል ነው። የስዊሱ ተወላጅ የዜፍ ብላተር አሁን ከማንኛውም ክስ ነጻ በመሆናቸው በፊታችን ረቡዕ ለአራተኛ የሥልጣን ዘመን የፊፋ ፕሬዚደንት ሆነው እንደሚመረጡ የሚጠራጠር የለም። የስነ-ምግባር ኮሚቴው ምክትል ሊቀ-መንበር ፔትሩስ ዳማሤብ ባለፈው ምሽት ዙሪክ ላይ ውሣኔውን ሲያብራሩ እንዳመለከቱት በብላተር ላይ ከእንግዲህ የሚቀጥል ምርመራ አይኖርም።

“ኮሚቴው የፊፋን ፕሬዚደንት ሤፕ ብላተርን በተመለከተ እርካታ ነው የሚሰማው። በማሕበሩ ደምብ አንቀጽ 129 መሠረት ስነ ምግባር መጣሱን የሚያመለክት አንዳች ነገር የለም። እናም ኮሚቴው በብላተር ላይ ምርመራ እንዲከፈት ወይም እንዲቀጥል አይደረግም”
ቢሆንም የሙስናው ጥርጣሬ በማሕበሩ ላይ እንድዣበበ መቀጠሉ የማይቀር ነገር ነው። የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ በየጊዜው ለተመሳሳይ ነቀፌታ ሲጋለጥ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው 24 ዓባላት አሥሩ ባለፈው ዓመት በሙስና መከሰሳቸውና እስከመታገድ የደረሱ መኖራቸውም የሚዘነጋ አይደለም። የቀድሞው የፈረንሣይ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋችና የዛሬው የአውሮፓ እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የዩኤፋ ፕሬዚደንት ሚሼል ፕላቲኒ ፊፋ ከገባበት አዘቅት እንዲወጣ የእግር ኳስ ሙያ በሚገባቸው ሰዎች መተዳደር የሚኖርበት ጊዜ አሁን መሆኑን አስገንዝቧል።

“ፊፋ ዓለምአቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ IOC ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በነበረበት ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው። የአሥራር ስልቱ ጊዜው ያለፈበት ይመስለኛል። ይህ ታላቅ የስፖርት ተቋም ወደፊት በእግር ኳስ አዋቂዎች እንጂ የኦሎምፒኩን ኮሚቴ ፕሬዚደንት ሣማራንዥን በመሳሰሉ ሰዎች መመራት የለበትም። ብላተርም እንደ አቫላንዥ ሁሉ ከፖለቲካው ዘርፍ የመጡ ናቸው። እናም ፊፋ ወደ እግር ኳስ ሊመለስ ይገባል እላለሁ”

Champions League Finale 2011 Barcelona vs. Manchester United Flash-Galerie
ምስል AP

የባርሤሎና የሻምፒዮና ሊጋ ድል

ሰንበቱን ጭጋግ በጋረደው የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር አድማስ ላይ በጎ የብርሃን ጮራ የፈነጠቀው በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ ግጥሚያ ድንቁ ክለብ ባርሤሎና ያሳየው ግሩም ጨዋታ ነበር ለማለት ይቻላል። የስፓኙ ታላቅ ክለብ በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲዮም በተካሄደው ግጥሚያ ኳስን በመቆጣጠር የተለየ ጥበቡ ማንቼስተር ዩናይትድን የሜዳ ውስጥ ተመልካች ሲያደርግ በወቅቱ በዓለም ላይ አቻ እንደማይገኝለት በውል ነው ያስመሰከረው። ባርሣ ሜሢን፣ ሻቪን፣ ኢኒየስታንና ፒኬን በመሳሰሉት ኮከቦቹ ረቂቅ አጨዋወት፤ የአጭር ቅብብል ስልትና ተጋጣሚን የመበታተን ዘይቤ የማንቼስተርን ተጫዋቾች አፍ ሲያስከፍት የእንግሊዙ ሻምፒዮን በ 3-1 ውጤት ብቻ በመሸነፉ እፎይ ሊል ይገባዋል። የዓለም ጋዜጦችም ባርሣን እጅጉን ሲያወድሱ የማንቼስተር ዩናይትድ አንጋፋ አሠልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጊሰንም ለካታሎኒያው የተውኔት ክለብ ልዩ አክብሮታቸውን ነው የገለጹት።

“በአሠልጣኝነት ዘመኔ ያጋጠመን ምርጥ ቡድን ይሄ ነው ለማለት እወዳለሁ። ይሄን ሁሉም የሚቀበለው ነው፤ እኔም እቀበለዋለሁ። በዚህ ዓይነት መንገድ ከተሸነፉ በኋላ ሌላ ነገር ለማለት ያዳግታል። በዕውነቱ እንዲህ ዓይነት ልዕልና ያለው ቡድን ገጥሞን አያውቅም። እናም ባርሣዎች ታላቅ ናቸው። እግር ኳስን በደስታ የሚጫወቱ በመሆኑ ድሉም ይገባቸዋል”

የባርሣን ጎሎች ፔድሮ፣ ሜሢና ቪያ ሲያስቆጥሩ ለማኒዩ ብቸኛዋን ጎል ያገባው ዌይን ሩኔይ ነበር። ለባርሣ የቅዳሜው ምሽት የሻምፒዮና ሊጋ ድል ባለፉት ስድሥት ዓመታት ውስጥ ሶሥተኛው መሆኑ ነው። ግጥሚያውን በዓለም ዙሪያ 300 ሚሊዮን ሕዝብ በቴሌቪዥን ሲከታተል የከዋክብቱ ኮከብ በተለይም ሁለተኛዋን ድንቅ ጎል ያስቆጠረው አርጄንቲናዊ ሊዮኔል ሜሢ ነበር። ሜሢ የትውልዱ ማራዶና መሆኑን በዌምብሌይ ስታዲዮም እንደገና በውል ነው ያስመሰከረው።

ከዚሁ ሌላ ባለፈው ምሽት በዚሀ በጀርመን አንድ የወዳጅነት ግጥሚያ ተካሂዶ ነበር። ተጋጣሚዎቹ ያለፈውን የደቡብ አፍሪቃን የዓለም ዋንጫ ውድድር ከግማሽ ፍጻሜ በመድረስ በስኬት በሶሥተኝነትና በአራተኝነት የፈጸሙት ጀርመንና ኡሩጉዋይ ሲሆኑ ጨዋታው በጀርመን አሸናፊነት 2-1 ተፈጽሟል። በጨዋታው የተመልካችን ቀልብ የሳበችው በተለይም በወጣቱ የማይንስ አጥቂ በአንድሬ ሹርለ የተቆጠረችው ሁለተኛዋ ግብ ነበረች። በተቀረ በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ከሰባት ዓመታት በኋላ ዘንድሮ የሊጋ ሻምፒዮንነቱን ለከተማ ተፎካካሪው ለኤ.ሢ.ሚላን ያስረከበው ቀደምት ክለብ ኢንተር ሚላን ትናንት በሊጋው የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ግሩም በሆነ ጨዋታ ፓሌርሞን 3-1 በመርታት የውድድሩን ወቅት በስኬት አጠቃሏል። ከሶሥት ሁለቱን ጎሎች የካሜሩኑ ኮከብ ሣሙዔል ኤቶ ሲያስቆጥር ሌላው የኢንተር ጎል አግቢ ደግሞ ዲየጎ ሚሊቶ ነበር።

በአውቶሞቢል ስፖርት ለማጠቃለል ሞናኮ ላይ ትናንት በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም ጀርመናዊው የሬድ-ቡል ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል በአስደናቂ ሁኔታ አሸናፊ ሆኗል። የ 23 ዓመቱ ወጣት በዘንድሮው ውድድር ከስድሥት አምሥቱን ማሸነፉ ነው። ፌትል ከትናንቱ ድሉ በኋላ በ 58 ነጥቦች ልዩነት የብሪታኒያውን ዘዋሪ ሉዊስ ሃሚልተንን አስከትሎ ይመራል። የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ሁለተኛ ሲወጣ እሽቅድሙን በሶሥተኝነት የፈጸመው ደግሞ የብሪታኒያው ጄሰን ባተን ነበር።

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ