1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 29 2003

የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያ፤ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ሁለት-ለሁለት ተለያዩ።

https://p.dw.com/p/RS08
ምስል AP

በሰንበቱ የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ዘንድሮ ያን ያህል ያልተጠበቀ ባይሆንም አስደናቂው ነገር ያለፈው ውድድር ወቅት አሸናፊ ግብጽ ከአራት ግጥሚያዎች በኋላ በሁለት ነጥቦች ብቻ በመወሰን ከወዲሁ መሰናበቷ ነው። ግብጽ ትናንት ካይሮ ላይ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ባካሄደችው ግጥሚያ ባዶ-ለባዶ ነበር የተለያየችው። ይበልጥ ደግሞ የሚያሳዝነው ግብጽ እስካሁን በምድቧ ውስጥ አንድ ግጥሚያ እንኳ ለማሸነፍ ሳትችል መቅረቷም ጭምር ነው። ጠንካራ ተብዬ ቡድኖችን ካነሣን አልጄሪያም ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በጎረቤቷ በሞሮኮ 4-0 በመቀጣት የምድብ አራት መጨረሻ ስትሆን ከምድብ አምሥት መሪ ከሤኔጋል ባዶ-ለባዶ ከተለያየችው ከካሜሩን ጋር በመንገዳገድ ላይ ናቸው። የግብጽ ዕጣ እንዳይገጥማቸው በጣሙን ያሰጋቸዋል።
የአልጄሪያ እግር ኳስ ፌደሬሺን በበኩሉ የብሄራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ አብደልሃክ ቤንቺካ ሥራቸውን መልቀቃቸውን ይፋ ለማድረግ ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም። በነገራችን ላይ የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ባለፈው ዓመት በአሕጉራዊው ውድድር ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰና ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ተሳታፊም እንደነበር አይዘነጋም። ካሜሩን ውስጥ ደግሞ ብሄራዊዉ ቡድን ያውንዴ ላይ ከሤኔጋል ባዶ-ለባዶ በመውጣቱ ቁጣ ያደረባቸው ደጋፊዎቹ በአውቶሞቢሎችና በመደብሮች ላይ የድንጋይ ናዳ ሲያወርዱ ጸጥታ አስከባሪዎች ውዥምብሩን ለማብረድ ውሃ መርጫ መሣሪያዎችን መጠቀም ነበረባቸው። በዓመጹ ሳቢያ ብዙ ሰዎች እስከመቁሰልም ደርሰዋል። እርግጥ ታዋቂው አጥቂ ሣሙዔል ኤቶ በ 87 ኛዋ ደቂቃ ላይ ያገኛትን ፍጹም ቅጣት ምት ባይስት ኖሮ ምናልባት ከዚህ ሁሉ ባልተደረሰም ነበር።

በምድብ ሁለት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ትናንት አዲስ አበባ ላይ ከናይጄሪያ ጋር ባደረገው ግጥሚያ 2-2 ሲለያይ ጨዋታው ሊያበቃ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ውጤቱን ያስተካከለው የናይጄሪያ ቡድን በዕድሉ ሊደሰት ይገባዋል። የናይጄሪያ ቡድን በኡቼ አማካይነት በ 25ኛዋ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ጎል ቀድሞ ቢመራም የኢትዮጵያ ተጫዎቾች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ወኔ አልከዳቸውም። ሣላዲን ሰይድ በ 41ኛና ከእረፍት በኋላም በ 50ኛዋ ደቂቃ አከታትሎ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር እስከዚያው ድሉ ከዕጅ የገባ ነበር የመሰለው። ሆኖም ጆዜፍ ዮቦ በ 86ኛዋ ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ሁለተኛ ግብ ለናይጄሪያ ዕፎይታ ለኢትዮጵያ መቆጫ ሆናለች።
ከትናንቱ አራተኛ ግጥሚያ በኋላ ምድቡን ጊኒ በአሥር ነጥብ የምትመራ ሲሆን ናይጄሪያ በሰባት ሁለተኛ፣ ኢትዮጵያ በአራት ነጥቦች ሶሥተኛ፤ እንዲሁም ማዳጋስካር በአንዲት ነጥብ አራተኛ ናት። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ትናንት ዕድል ቢከዳውም ወደ ፍጻሜው ለማለፍ የቀረችውን ጥቂት ዕድል ለመጠቀም የተቻለውን ሁሉ እንደሚጥር አምበሉ ደጉ ደበበ ዛሬ ቀትር ላይ በስልክ ሳነጋግረው ገልጾልኝ ነበር።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አምበል ደጉ ደበበ ነበር፤ የፌደሬሺኑ የግንኙነት ሃላፊ አቶ መላኩ አየለም ቢሆን ቡድኑ ትናንት ባመለጠው ዕድል በመቆጨት በአያያዙ ከቀጠለ ተሥፋ እንዳለው ነው የሚያምኑት።

የተቀሩትን ምድቦች በአጭሩ ለመዳሰስ ምድብ አንድን ካፕ ቨርዴ ማሊን አስከትላ የምትመራ ሲሆን ምድብ ሶሥት ውስጥ አንደኛዋ ዛምቢያ ናት። ምድብ አራትን ሞሮኮ፣ ምድብ አምሥትን ሤኔጋል፣ ምድብ ስድሥትን ቡርኪና ፋሶ፤ እንዲሁም ምድብ ሰባትን አይቮሪ ኮስት ይመራሉ። በነገራችን ላይ አይቮሪ ኮስት በ 12 ነጥቦች ከወዲሁ ለፍጻሜው ማለፏን አረጋግጣለች። ጋና፣ ሱዳንና ኡጋንዳም በየምድባቸው ቀደምት ሲሆኑ የሚያስደንቅ ሆኖ ቦትሱዋናም አምሥት ሃገራትን ባቀፈው በመጨረሻው ምድብ ቱኒዚያን በሰባት ነጥብ ብልጫ በማስከተል ለፍጻሜ አልፋለች። ለግንዛቤ ያህል ወደ ፍጻሜው ዙር የሚያልፉት የየምድቡ አንደኞች፣ የመጨረሻው ምድብና የተቀሩት አሥር ምድቦች ሶሥት ጠንካራ ሁለተኞች ይሆናሉ።

መሥፍን መኮንን

መሳይ መኮንን

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ