1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሐምሌ 18 2003

አርጄንቲና ውስጥ ሲካሄድ የሰነበተው የላቲን አሜሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ኮፓ-አሜሪካ ትናንት በኡሩጉዋይ አሸናፊነት ተፈጽሟል።

https://p.dw.com/p/Rc0v
ምስል dapd

ኡሩጉዋይ ለሬኮርድ 15ኛ የኮፓ-አሜሪካ ድሏ የበቃችው ፓራጉዋይን በፍጹም የበላይነት 3-0 ከረታች በኋላ ነው። ሉዊስ ሱዋሬስ በ 12ኛዋ ደቂቃ ላይ መክፈቻዋን ጎል ሲያስገባ የተቀሩትን ሁለት ጎሎች ያስቆጠረው ደግሞ በደቡብ አፍሪቃው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ወቅት ድንቅ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው ዲየጎ ፎርላን ነበር። ኡሩጉዋይ በዓለም ዋንጫው ውድድር አራተኛ በመውጣት ከብራዚልም ሆነ ከአርጄንቲና የተሻለችው የላቲን አሜሪካ ተወካይ እንደነበረች የሚታወስ ነው።
ከትናንቱ ድል በኋላ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የኡሩጉዋይ ዜጎች በሰማያዊ መለያ ቀለማቸው አሸብርቀው ዋና ከተማይቱ ሞንትቪዴዎ ውስጥ አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን በደመቀ ሆኔታ ገልጸዋል። ልዝብናን የመረጡት አሠልጣኙ ኦስካር ታባሬስ በበኩላቸው ኮፓ-አሜሪካን ማሸነፍ ግሩም ነገር ቢሆንም ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ግን ዋስትና አይደለም ሲሉ ነው የተናገሩት። ያም ሆነ ይህ ቡድኑን ትናንትም እንደ ዓለም ዋንጫው ሁሉ ለጥሩ ውጤት ያበቃው በተለይም አንድነቱና በጋራ የመታገል ስልቱ ነው። የሁለት ጊዜዋ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ኡሩጉዋይ በዚሁ ኮፓ-አሜሪካን ለ 15ኛ ጊዜ በማግኘት በቀደምትነት ትመራለች። አርጄንቲና ዋንጫውን 14 ጊዜ ስታገኝ ብራዚልም ስምንቴ ተሳክቶላታል። በተቀረ ፓራጉዋይና ፔሩ እያንዳንዳቸው ሁለቴ ለድል ሲበቁ ኮሉምቢያና ቦሊቪያም አንዳንድ ዕድል ደርሷቸዋል።

NO FLASH Fußball Supercup 2011 FC Schalke 04 - Borussia Dortmund
ምስል dapd

ቡንደስሊጋ

በዚህ በጀርመን ደግሞ የቡንደስሊጋው የ 2011/12 ውድድር ወቅት ሊከፈት ሁለት ሣምንታት ቀርተው ሳለ ሰንበቱን የመጀመሪያው የዋንጫ ጨዋታ ተካሂዶ ነበር። ይሄውም ባለፈው የውድድር ወቅት ሻምፒዮን በቦሩሢያ ዶርትሚንድና በፌደሬሺኑ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊ በሻልከ መካከል የተካሄደው የ Super Cup ግጥሚያ ሲሆን ጨዋታው የለየለት በፍጹም ቅጣት ምት ነው። ሁለቱ ቡድኖች በመደበኛው ዘጠና ደቂቃ ባዶ-ለባዶ ሲለያዩ ሻልከ የኋላ ኋላ በፍጹም ቅጣት ምት 4-3 ሊያሸንፍ በቅቷል። ለሻልከ ድል ትልቁ ዋስትና በተለይም የዶርትሙንድን ሁለት ፍጹም ቅጣት ምቶች ያከሸፈው በረኛው ራልፍ ፌህርማን ነበር። ለሻልከ ሱፐር-ካፑ የመጀመሪያው ሲሆን አሠልጣኙ ራልፍ ራንግኒክ እንዳለው ቡድኑ ባለፈው የውድድር ወቅት በሜዳው በዶርትሙንድ ለደረሰበት 3-1 ሽንፈት ማካካሻም ነው።

“በጨዋታው መጨረሻ ማሸነፋችን ለቡድኑ ትልቅ ነገር እንደሆነ እርግጥ ጥያቄ የለውም። በበኩሌ ከሁሉም በላይ የምደሰተው ግን ለደጋፊዎቻችን ነው”

የዶርትሙንዱ አሠልጣን ዩርገን ክሎፕ ደግሞ ቡድኑ ከትናንቱ የተሻለ መጫወት እንደሚችል በመጥቀስ ዋንጫውን ባለማግኘቱ ጥቂት ማዘኑን አመልክቷል። ለማንኛውም የቡንደስሊጋው ውድድር ሊጀመር በር እያንኳኳ ሲሆን ሁለቱ ቡድኖች ዘንድሮ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆኑ እያደር የሚታይ ይሆናል።

በእግር ኳሱ መድረክ ላይ በዚሀ ሰንበት ሌላው ትልቁ ዜና የአንዴው የዓለም እግር ኳስ ፌደሪሺኖች ማሕበር ፕሬዚደንታዊ ዕጩ ሞሐመድ-ቢን-ሃማን ባለፈው ቅዳሜ ከፊፋ ለዕድሜ ልክ መታገዳቸው ነበር። የፊፋ የስነ-ምግባር ኮሚሢዮን ከዚህ ከባድ ውሣኔ ላይ የደረሰው ቢን-ሃማን ባለፈው ሰኔ ወር የፊፋ ፕሬዚደንትነት ምርጫ ለመመረጥ የካራይብን እግር ኳስ ማሕበር ባለሥልጣናት በጉቦ ለመግዛት መሞከራቸው መረጋገጡን በማመልከት ነው። ናሚቢያዊው የኮሚሢዮኑ ሊቀ-መንበር ፔትሩስ ዳማሤብ ሁለት ቀናት ከፈጀው ምርመራ በኋላ ውሣኔውን እንደሚከተለው ዘርዝረዋል።

“ቢን-ሃማንን የሚመለከተው ውሣኔ የሚከተለው ነው። አንደኛ፤ ባለሥልጣኑ ቢን-ሃማን የማሕበሩን ሕግጋት አንቀጽ 3 ቁጥር 1, 2 እና 3-ን በመጣስ፤ አንቀጽ 9 ታዛዥነትና ታማኝነትን፤ አንቀጽ 10 ቁጥር 2 መሸንገያ ስጦታን መስጠትና መቀበልን፤ እንዲሁም አንቀጽ 11 ቁጥር 2 ጉቦኝነትን የሚመለከት ደምብ በመርገጥ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል። በዚሁ መሠረትም ቢን-ሃማን በማንኛውም ዓይነት በብሄራዊም ሆነ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከአግር ኳስ የተዛመደ ተግባር፣ አስተዳደርና ሌላም ስፖርት ነክ ነገር ለዕድሜ ልክ ታግደዋል”

የካታሩ ተወላጅ የቀድሞ የእሢያ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን ፕሬዚደንት ቢን-ሃማን በበኩላቸው አንዳች ጥፋት እንደሌለባቸው በመጥቀስ ይግባኝ እንደሚሉ በዛሬው ዕለት አስታውቀዋል። ሃማን በተጨማሪ የፊፋ መረጃዎች በይፋ ለፕሬሱ ቀርበው እንዲደመጡ ሲጠይቁ የእግር ኳሱ ማሕበር ይህን መፍቀዱ ቢቀር በወቅቱ ገና ግልጽ አይደለም። በውዝግቡ የፊፋው ፕሬዚደንት የሤፕ ብላተር ሚናስ ምን ይሆን? ጉዳዩ አከራካሪ ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ነው የሚመስለው።

EM Leichtathletik in Spanien
ምስል AP

አትሌቲክስ

ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ሞናኮ ውስጥ በተካሄደው የዳያመንድ-ሊግ አትሌቲክስ ውድድር የአጭር ርቀቱ የጃማይካ መንኮራኩር ዩሤይን ቦልት በአንድ መቶ ሜትር ሩጫ በጠባብ ልዩነት ለማሽነፍ በቅቷል። ቦልት በአጀማመሩ ዘግየት ብልም በ 9,88 ሤኮንድ ጊዜ የአገሩን ልጅ ኔስታ ካርተርን በሁለት-መቶኛ ሤኮንድ ልዩነት ሊቀድም ችሏል። ሶሥተኛ የሆነው አሜሪካዊው ማይክል ሮጀርስ ነበር። ሶሥቱም አትሌቶች ከአሥር ሤኮንድ በታች መሮጡ ተሳክቶላቸዋል። ዩሤይን ቦልት ፉክክሩ ጠንካራ ቢሆንም በፊታችን ነሐሴ ወር ደቡብ ኮሪያ ዴጉ ላይ ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አንዳች ስጋት እንደሌለው ነው የተናገረው።

በወንዶች ስምንት መቶ ሜትር ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ የአገሩን ልጅ አስቤል ኪፕሮፕን አስከትሎ ሲያሸንፍ አሜሪካዉዊው ኒክ ሣይመንድስ ሶሥተኛ ሆኗል። በ 1,500 ሜትር ሩጫም ኬንያውያኑ ሢላስ ኪፕላጋትና ኒክሰን ኪፕሊሞ ቀዳሚ ሲሆኑ የሱዳኑ አቡባከር ካኪ ሶሥተኛ ወጥቷል። በአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ የሶማሊያው ተወላጅ የብሪታኒያ ተወዳዳሪ ሞ ፋራህ ሲያሸንፍ የኬንያንና የኢትዮጵያን አትሌቶች ከኋላው ማስቀረቱ ሰምሮለታል። ከኬንያ የመነጨው አሜሪካዊ በርናርድ ላጋት ሁለተኛ ሲወጣ ኬንያዊው ኢሢያህ ኮች ሶሥተኛ አንዲሁም ኢትዮጵያዊው ኢማነ መርጋ ሩጫውን በአራተኝነት ፈጽሟል። ታሪኩ በቀለና የኔው አላምረው ደግሞ ሰባተኛና ስምንተኛ ሆነዋል።

በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል ሲያሸንፉ ሩጫውን በአንደኝነት የፈጸመው ብሪሚን ኪፕሮቶ ነበር። የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ ሮባ ጋሪ ኬንያውያን ባመዘኑበት ሩጫ ስምንተኛ ሆኗል። በሴቶች ሁለት መቶ ሜትር አራት አሜሪካውያት በቀደምትነት ተከታትለው ሲገቡ ካሜሊታ ጄተር አንደኛ፤ እንዲሁም አሊሰን ፌሊክስ ሁለተኛ ሆነዋል። በአራት መቶ ሜትር የቦትሱዋና ተወዳዳሪ አማንትሌ ሞንቾ ስታሸንፍ በ 1,500 ሜትር ደግሞ የባሕሬይኗ ማርያም-ዩሱፍ-ጀማል ቀዳሚ ሆናለች። መስከረም አሰፋ ሰባተኛ!
በመቶ ሜትር መሰናክል አውስትራሊያዊቱ አትሌት ሤሊይ ፒርሰን ቀዳሚ ስትሆን በከፍታ ዝላይ ደግሞ የክሮኤሺያዋ የዓለም ሻምፒዮን ብላንካ ቭላዚች አሸንፋለች። በነገራችን ላይ ሩሢያዊቱ አና ቺቼሮቫ ባለፈው አርብ በሩሢያ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለት ሜትር ከሰባት በመዝለል በዓለም ላይ ሶሥተኛውን ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ በቅታለች። ቺቼሮቫ በመጪው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከባድ የሜዳሊያ ተፎካካሪ እንደምትሆን የሚጠበቅ ነው። በተረፈ በሞናኮው ዳያመንድ ሊግ በርዝመት ዝላይ አሜሪካዊቱ ብሪትኒይ ሪስ፤ እንዲሁም በዲስክ ውርወራ የጀርመኗ ናዲን ሙለር አሸናፊዎች ሆነዋል።

NO FLASH Formel 1 Lewis Hamilton
ምስል dapd

ፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም በጀርመን

የትናንቱ የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል የጀርመን ግራንድ-ፕሪ እሽቅድድም ለአስተናጋጇ አገር የዓለም ሻምፒዮን ለዜባስቲያን ፌትልም ሆነ ለብዙዎች ተመልካቾቹ ገዳም ሣይሆን አልፋል። በውድድሩ የብሪታኒያው ዘዋሪ ሉዊስ ሃሚልተን ሰያሸንፍ የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ተከትሎት ገብቷል። ሉዊስ ሃሚልተን ለጋዜጠኞች ሲናገር እንደተደመጠው ድሉን ለማመን ያቃተው ነበር የመሰለው።
“በጣም ትልቅ ደስታ ነው የሚሰማኝ። ሞተሬ ዛሬ በጣም ግሩም ነበር። የቴክኒክ ረዳቶቼ ግሩም ስራ ነው የሰሩት። ይህን ያህል ፈጣን ነን ብዬ አላሰብሉም። በሕይወቴ እስካሁን ያደረግኩት ድንቅ እሽቅድድም ነበር”

አውስትራሊያው ማርክ ዌበር ሶሥተኛ ሲወጣ ፌትል ውድድሩን የፈጸመው በአራተኝነት ነው። እስካሁን ከተካሄዱት ዘጠኝ እሽቅድድሞች በኋላ ዜባስቲያን ፌትል በአጠቃላይ ዌበርን በሰማኒያ ነጥቦች ብልጫ አስከትሎ የሚመራ ቢሆንም ፉክክሩ እየጠነከረበት የሚሄድ ነው የሚመስለው። ገና አሥር እሽቅድሞች ይቀራሉ።

Flash-Galerie Tour de France 2011 - Cadel Evans
)ምስል dapd

ቱውር ዴ ፍራንስ / ቴኒስ

በታላቁ የፈረንሣይ ዓለምአቀፍ አገር-አቋረጭ የቢስክሌት ውድድር ቱውር ዴ ፍራንስ በአጠቃላይ ነጥብ የዘንድሮው አሸናፊ የአውስትራሊያው ካዴል ኤቫንስ ሆኗል። ድሉ ለአውስትራሊያ በ 108 ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው ሲሆን ያስከተለው ደስታና ብሄራዊ ኩራትም እጅግ ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል። ኤቫንስ ራሱ “ምን ልበል፤ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ፤ ገና በ 14 ዓመት ዕድሜዬ ጀምሬ በቱውር ዴ ፍራንስ ለማሸነፍ ሳልም ነበር የኖርኩት” በማለት ነው የድሉን ታሪካዊነት ያንጸባረቀው። የአገሪቱ ጋዜጦች በዚሁ ዜና ዓምዶቻቸውን ሲያጨናንቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሊያ ጊላርድ ሳይቀሩ ስልክ ደውለው ባለድሉን ስፖርተኛ እንኳን ደስ ያለህ ብለውታል።

ዘገባችንን በቴኒስ ለማጠቃለል በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ በዘጠነኛው ቦታ የሚገኘው አሜሪካዊ ማርዲይ ፊሽ ትናንት በአትላንታ ሻምፒዮና የአገሩን ተወዳዳሪ ጆን ኢስነርን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 በማሸነፍ ያለፈውን ዓመት የፍጻሜ ድሉን ደግሞታል። በዚህ በጀርመን በሃምቡርግ ከተማ ዓለምአቀፍ ውድድር ደግሞ ፈረንሣዊው ዢል ሢሞን የስፓኝ ተጋጣሚውን ኒኮላስ አልማግሮን እንዲሁ 2-1 በማሸነፍ ለዘጠነኛ የውድድር ድሉ በቅቷል። በነገራችን ላይ ሢሞን ከሄንሪ ሌ ኮንት ድል ከ 25 ዓመታት በኋላ በሃምቡርግ ሲያሸንፍ የመጀመሪያው ፈረንሣዊ መሆኑ ነው። በመጨረሻ ሩሢያዊቱ ኮከብ ተጫዋች ቬራ ዝቮናሬቫም በባኩ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ሻምፒዮና የአገሯን ልጅ ክሤኒያ ፔርባክን 6-1, 6-4 በማሸፍ የ 220 ሺህ ዶላር ተሽላሚ ሆናለች።

መሥፍን መኮንን

ሒሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ