1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 20 2004

ኬንያዊው ፓትሪክ ማካዉ በመስከረሙ የበርሊን ማራቶን የሃይሌ ገ/ሥላሴን ጊዜ በማሻሻል አዲስ ክብረ-ወሰን ሲያስመዘግብ ትናንት ደግሞ የአገሩ ልጅ ዊልሰን ኪፕሣንግ በፍራንክፈርት ማራቶን ከአራት ደቂቃ በታች በመሮጥ በታሪክ ሶሥተኛው ሰው ሊሆን በቅቷል።

https://p.dw.com/p/Ru3Z
ምስል AP

በሰላሣኛው የፍራንክፈርት ማራቶን ትናንት በመጀመሪያው አጋማሽ ስድሥት ሯጮች ከበርሊኑም የፈጠኑ ሆነው ሲታዩ ሁኔታው አዲስ ክብረ-ወሰን ይገኛል የሚል ተሥፋን ለአንድ አፍታም ቢሆን አሳድሮ ነበር። ይሁንና ሩጫው ከ 35ኛው ኪሎሜትር በኋላ መልሶ በረድ በማለቱ የታሰበው አልሆነም። ለማንኛውም ኪፕሣንግ የሮጠው ሁለተኛ ፈጣን ጊዜ ለራሱም ሆነ ለፍራንክፈርት ማራቶን አዲስ ክብረ-ወሰን ነው። በቅደም ተከተል ለማስቀመጥ ያህል ፓትሪክ ማካው በሁለት ሰዓት ከሶሥት ደቂቃ 38 ሤኮንድ ጊዜ የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ሲሆን ዊልሰን ኪፕሣንግ በሁለት ሰዓት ከሶሥት ደቂቃ ከ 42 ሤኮንድ ሁለተኛ ነው። ሃይሌ ገ/ሥላሴ ደግሞ በሶሥተኝነት ይከተላል።

ታዲያ የትናንቱ የፍራንክፈርት ማራቶንም ባለፉት ዓለምአቀፍ ውድድሮች ተደጋግሞ እንደታየው ሁሉ የኬንያ አትሌቶች ፍጹም ልዕልና የሰፈነበት መሆኑ አልቀረም። በወንዶቹ ማራቶን ለምሳሌ ኬንያውያኑ ከአንድ እስከ አሥር በመከታተል ቀደምት ሲሆኑ በስምንተኝነት መሃላቸው መግባት የቻለው የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ ሢራጅ ገና ብቻ ነበር። በሌላ በኩል በሴቶች የኢትዮጵያ አትሌቶች ግሩም ውጤት አስመዝግበዋል። ማሚቱ ዳስካ ሁለት ኬንያውያትን አስከትላ በአንደኝነት ከግቧ ስትደርስ ያስመዘገበችው ሁለት ሰዓት ከ 21 ደቂቃ 59 ሤኮንድ ጊዜም ለአርሷ የሁለት ደቂቃ መሻሻል ከመሆን ባሻገር ለፍራንክፈርትም ፈጣኑ ነበር። የተቀሩት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች መሪማ መሐመድ አራተኛ፣ ፋጤ ቶላ ሰባተኛና እንዲሁም ብሩክታይት ደገፋ ስምንተኛ በመሆን ከቀደምቱ አሥር ሯጮች መካከል ለመሰለፍ በቅተዋል።

ሜክሢኮ ውስጥ ላለፉት ሁለት ሣምንታት ሲካሄድ የቆየው የፓን-አሜሪካ ጨዋታ ደግሞ በትናንትናው ዕለት በጥሩ ውጤቶች ተፈጽሟል። አሜሪካ በ 92 የወርቅ ሜዳሊያዎች አንደኛ ስትሆን ኩባ በ 58 ሁለተኛ እንዲሁም ብራዚል በ 48 ወርቅ ሶሥተኛ ሆናለች። አስተናጋጇ ሜክሢኮም ካናዳን ከኋላዋ በማስቀረት ውድድሩን በአራተኝነት ለመፈጸም በቅታለች።

Fussball, 1. Bundesliga, 11. Spieltag, FC Bayern München - 1. FC Nürnberg
ምስል dapd

እግር ኳስ፤ አውሮፓና ቡንደስሊጋ

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ በሚካሄደው ውድድር ታላላቆቹ ክለቦች ቀስ በቀስ አመራራቸውን እያጠነከሩ በመሄድ ላይ ናቸው። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ባለፈው ሰንበት የዝቅተኛው ክለብ የሌቫንቴ አስደናቂ ግንባር ቀደም ጉዞ ለጊዜውም ቢሆን ተገትቶ ሬያል ማድሪድ አመራሩን ተረክቧል። ለዚህም ምክንያት የሆነው ሌቫንቴ በኦሣሱና 2-0 በመረታት ለዘንድሮው ውድድር ወቅት የመጀመሪያ ሽንፈቱ መብቃቱ ነው። ሬያል ማድሪድ በበኩሉ ግጥሚያ ሬያል ሶሲየዳድን 1-0 ሲያሸንፍ ሊጋውን በ 25 ነጥቦች ይመራል። ለማድሪድ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው አርጄንቲናዊው አጥቂ ጎንዛሎ ሂጉዌይን ነበር። ባርሤሎናም በድንቅ ተጫዋቹ በሊዮኔል ሜሢ እየተመራ ሬያል ማዮርካን 5-0 ሲሸኝ በ 24 ነጥቦች ሁለተኛ ነው። እስካለፈው ሣምንት ይመራ የነበረው ሌቫንቴ በበኩሉ ከአንድ ወደ ሶሥተኛው ቦታ አቆልቁሏል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር ቀደምቱ ማንቼስተር ሢቲይ ሰንበቱን ዎልቨርሃምፕተን ዎንደረርስን 3-1 በማሸነፍ የከተማ ተፎካካሪውን ማንቼስተር ዩናይትድን በአምሥት ነጥቦች ልዩነት አስከትሎ እየመራ ነው። ማንቼስተር ዩናይትድም በበኩሉ ግጥሚያ ኤቨርተንን 1-0 ረትቷል። ማንቼስተር ሢቲይ አሁን ከአሥር ግጥሚያዎች በኋላ 28 ነጥቦች አሉት። በሌላ በኩል በሣምንቱ ትልቁ ክስረት የደረሰበት በገዛ ሜዳው በአርሰናል 5-2 የተረታው ሶሥተኛው ቼልሢይ ነው። ክለቡ በዚህ አያያዙ ከአመራሩ ጨርሶ እየራቀ እንዳይሄድ በጣሙን ያሰጋዋል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ባየርን ሙንሺን ባለፈው ሣምንት ደርሶበት ከነበረው ሽንፈት በማገገም በግሩም ጨዋታ አመራሩን ወደ አራት ነጥቦች ልዩነት ከፍ ማድረጉ ተሳክቶለታል። በ 25 ነጥቦች አሁንም የሊጋው ቁንጮ ነው። ባየርን በሰንበቱ ግጥሚያ ኑርንበርግን 4-0 ሲረታ የመሃል ሜዳ ተጫዋቹ ቶኒይ ክሮስ እንዳለው የበላይነቱ እጅግ ጎልቶ የታየ ነበር።
“ውጤቱ ጥንካሬያችንን በሚገባ የሚያንጸባርቅ ነው። በዚህም ግጥሚያ ገና ከጅምሩ ቀድመን ነው የመራነው። ይህ ደግሞ በራስ መተማመንን የሚያዳብር ነገር ነው። በጥቅሉ ቡድናችን በማያሻማ ሁኔታ የተሻለው ነበር። የተጋጣሚያችንን ስህተቶች በመጠቀም ጎሎች ማስቆጠሩ ተሳክቶልናል”

የጎል ነገር ከተነሣ ጎል አግቢው ማሪዮ ጎሜስም ከአራት ሁለቱን ጎሎች በማስቆጠር ዘንድሮ አቻ እንደሌለው በሚገባ ነው ያስመሰከረው። እስካሁን በተካሄዱት አሥር ግጥሚያዎች 12 በማስቆጠር የሊጋው ቁንጮ ነው። ያለፈው ጊዜ ሻምፒዮን ዶርትሙንድ በአንጻሩ ከሽቱትጋርት ጋር ባደረገው ግጥሚያ በ 1-1 ውጤት በመወሰኑ ከሁለት ወደ ሶሥተኛው ቦታ ሲያቆለቁል ሆፈንሃይምን የረታው ሻልከ በቦታው ተተክቷል። ቨርደር ብሬመንና መንሸንግላድባህ ደግሞ የየበኩላቸውን ግጥሚያዎች ሲያሸንፉ ከዶርትሙንድ ጋር በነጥብ እኩል ናቸው። አራተኛና አምሥተኛ በመሆን ይከተሉታል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጁቬንቱስ ኢንተር ሚላንን 2-1 በማሸነፍ በአመራሩ ሲቀጥል ፓሌርሞን 1-0 የረታው ኡዲኔዘም አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ ሁለተኛ ነው። ላሢዮና ኤ.ሢ.ሚላን ደግሞ ሶሥተኛና አራተኛ ሆነው ይከተላሉ። በሌላ በኩል ማቆልቆሉን የቀጠለው ታላቁ ክለብ ኢንተር ሚላን በወደፊት ዕጣው በጣሙን ሊሰጋ የሚገባው ነው። ከለፉት ዘጠኝ ግጥሚያዎቹ በአምሥቱ የተሽነፈው ሚላን በሤሪያው አሰላለፍ በውቅቱ በ 17ኛው ቦታ ላይ ነው የሚገኘው። ይህን በውድድሩ መጀመሪያ የጠበቀው ቀርቶ ያለመው እንኳ አልነበረም። በተቀረ በፈረንሣይ ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን፣ በኔዘርላንድ አልክማርና በፖርቱጋል ደግሞ ፖርቶ በዚህ ሣምንትም አመራራቸውን ይዘው እንደቀጠሉ ነው።

Petra Kvitova Wimbledon Siegerin
ምስል dapd

ዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድሮች

የቼክ ሬፑብሊኳ ኮከብ ፔትራ ክቪቶቫ ከታላቁ የዊንብልደን ድሏ ወዲህ በዓለም የሴቶች ቴኒስ መድረክ እንደ ሮኬት ወደ ላይ መተኮሷን ቀጥላለች። የ 21 ዓመቷ ወጣት ትናንት ኢስታምቡል ላይ በዓለም ቴኒስ ማሕበር ፍጻሜ የቤላሩስ ተጋጣሚዋን ቪክቶሪያ አዛሬንካን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 7-5, 4-6, 6-3 በሆነ ውጤት 2-1 በማሸነፍ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ለማለት በቅታለች። ግራኝነት መለያዋ የሆነው ክቪቶቫ በመጪው ጥር የአውስትራሊያ-ኦፕን አንደኛዋን ካሮሊል ቮዝኒያችኪን ከዙፋኗ ብታስወርድ ብዙ የሚደነቅ እንደማይኖር ነው የሚታመነው።

በሌሎች የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያዎች በቫሌንሢያ-ኦፕን የስፓኙ ፓብሎ አንዱሃር የአርጄንቲና ተጋጣሚውን ሁዋን-ኢግናሢዮ-ቼላን በሁለት ምድብ ጨዋታ ሲረታ በአውስትሪያ-ኦፕን የፈረንሣዩ ጆ-ዊልፍሪድ-ሶንጋ የአርጄንቲናውን ሁዋን-ማርቲን-ዴል-ፖትሮን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 አሸንፏል። በሩሢያ የሣንት-ፒተርስቡርግ ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ የክሮኤሺያው ማሪን ቺሊች የሰርቢያውን ያንኮ ቲፕሣሬቪችን በተመሳሳይ ውጤት ለማሽነፍ በቅቷል።

Formel1-Rennen Sebastian Vettel Lewis Hamilton Mark Webber
ምስል dapd

የአውቶሞቢል እሽቅድድም

ሕንድ ውስጥ ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የተሳካ የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ወጣቱ ጀርመናዊ የዓለም ሻምፒዮን ዜባስቲያን ፌትል አሸናፊ ሆኗል። የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ሁለተኛ ሲወጣ እሽቅድድሙን በሶሥተኝነት የፈጸመው የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር ነበር። አዘጋጆቹ በታላቅ ኩራት እንደተናገሩት በኒው ዴልሂ መዳረሻ ላይ ባለው የእሽቅድድም ስፍራ 95 ሺህ ተመልካቾች ተገኝተው ውድድሩን ተከታትለዋል። ይህም ውድድሩ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱ ሲታሰብ የሚያስደንቅ ቁጥር ነው። የአገሪቱ ጋዜጦችም ዛሬ በታላቅ ኩራት ሕንድን በአሸናፊነት አወድሰዋል።

ዘገባችንን በእግር ኳስ ለማጠቃለል በዚህ በአውሮፓ ነገና ከነገ በስቲያ የሻምፒዮና ሊጋ የምድብ ዙር ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። 16 ክለቦችን ወደሚያቅፈው ወደ ተከታዩ የጥሎ ማለፍ ዙር ለማለፍ በሚደረገው ትግል በነገው ዕለት ለምሳሌ የኢጣሊያው ኤ.ሢ.ሚላንና የስፓኙ ባርሤሎና ካሸነፉ ሁለት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ቀድመው ስኬታቸውን ሊያረጋግጡ ይ’ችላሉ። ለነገሩም ተጋጣሚዎቻቸው ያን ያህል ጠንካሮች ባለመሆናቸው ሂደቱ የሚጠበቅ ነው። ቤንፊካ ሊዝበን፣ ሬያል ማድሪድና አርሰናልም የሣምንቱን ግጥሚያቸውን ካሸነፉ ወደፊት የሚዘልቁ ሲሆን ቼልሢይ ሕያው ሆኖ ለመቀጠል ሶሥቱንም ነጥቦች ለመያዝ መቻለ አለበት።
የጀርመኑ ባየርን ሙንሺንም ከናፖሊ ባካሄደው የመጀመሪያ ግጥሚያ 1-1 በመለያየቱ የነገው የመልስ ግጥሚያ ሰፊ ትኩረትን የሚስብ ነው የሚሆነው። የእንግሊዙ ሻምፒዮን ማንቼስተር ዩናይትድም በምድብ ሶሥት ውስጥ ምንም እንኳ በመጀመሪያ ሁለት ግጥሚያዎቹ ከእኩል ለእኩል ውጤት ባያልፍም ነገ ካሸነፈ ተዝናንቶ ማለፉ የሚገደው አይሆንም። በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል ጠንካራ ከሚባሉት ዋና ዋና ግጥሚያዎች መካከል ነገ አርሰናል ከኦላምፒክ ማርሤይና ዶርሙንድ ከኦሊምፒያኮስ ፒሬውስ፤ እንዲሁም ረቡዕ ምሽት ባየርን ሙንሺን ከናፖሊ፣ ኢንተር ሚላን ከፈረንሣዩ ሻምፒዮን ከሊልና ኦላምፒክ ሊዮን ከሬያል ማድሪድ ይገኙበታል።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ


ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ