1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊላንድና የፑንትላንድ ግጭት መሠረታዊ ምክንያት፧

ማክሰኞ፣ ጥር 6 2000

አምባገነኑ መሪ ሲያድ ባሬ፧ በጥር ወር 1983 ዓ ም፧ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ አብዛኛው የሶማልያ ክፍል፧ በጎሣ የጦር አበጋዞች ቁጥር ሥር ውሎ፧ በእርስ በርስ ጦርነት ክፉኛ ሲጎዳ፧ ሰሜን ምዕራባዊው ክፍል ማለትም ሶማሊላንድ፧ የተረጋጋ አስተዳደር ከመሠረተች አሥር ሰባት ዓመት ገደማ ሆኗታል።

https://p.dw.com/p/E0Xt
ምስል AP
ከቀድሞዋ ቅኝ ገዥ ብሪታንያና ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ማለፊያ ግንኙነት እንዳላት የሚነገርላት ሶማሊላንድ፧ ተረጋግታ ኤኮኖሚዋን በመገንባት ላይ ብትሆንም ከምሥራቃዊቷ አጎራባች ከፊል ራስ ገዝ፧ ፑንትላንድ ጋር፧ አልፎ አልፎ በሚያገረሽ የግዛት ይገባኛል ጥያቄ፧ መጋጨቷ አልቀረም። ባለፈው እሁድ በተደረገ ግጭትም ቢያንስ 15 ሰዎች መሞታቸውና ከ 25በላይ መቁሰላቸውን የዜና አውታሮች ዘግበዋል። የዚህ ውዝግብ መሠረታዊ መንስዔ ምን ይሆን! በአካባቢው ሰፋ ያለ ምርምር ያደረጉትን ጀርመናዊ፧ በሃለ ከተማ የማክስ ፕላንክ ተቋም ለዶክተርነት የሚያበቃቸውን፧ ጽሑፍ በማዘጋጀት ላይ የሚገኙትን Herr Markus Hoehne ን ተክሌ የኋላ አነጋግሮ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።
«እንደ እኔ ግንዛቤ የግዛት ይገባኛል ጥያቄው፧ ዋናውና አንገብጋቢው ጉዳይ አይደለም። በዚሁ አከራካሪ ግዛት ሊገኝ የሚችል ማዕድንም አይደለም። ሶማሊላንድንና ፑንትላንድን የሚያጋጫቸውም ሆነ በየጊዜው የሚያዋጋቸው፧ ሁለቱ ወገኖች የሚፋለሙበት ቦታ፧ በሰሜን ምዕራብ፧ የቀድሞዋ የብሪታንያ የሞግዚት ግዛት፧ የሶማሊላንድ ድንበርና የኢጣልያ ቅኝ ግዛት የነበረው፧ ከሰሜን ምሥራቅ ሶማልያ፧ እስከ ደቡብ ሶማልያ ማለት ነው፧ እንግዲህ፧ እነዚህን ሁለቱን የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች የሚያዋስነው ድንበር ነው፧ የተብ መንስዔ የሆነው።
የሶማሊላንድ ዋና ትኩረትም ሆነ ፍላጎት፧ የቀድሞዋን የቅኝ ግዛት ድንበር ማስከበር ወይም ማረጋገጥና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማግኘት እንዲረዳት፧ በቁጥጥር ሥር አድርጎ መገኘት ነው።«
የሶማሊላንድ ፍላጎት እንደተብራራው ይህን ይመስላል። ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር የመሠረተችውና የሶማልያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት አብዲላሂ ዩሱፍ የትውልድ ክፍለ-ሀገር የሆነችው ፑንትላንድ የምትፋለምበት ዋና ምክንያት ምንይሆን!?
«የፑንትላንድ የዚህን የሶማሊላንድን የግዛት ይገባኛል ጥያቄም ሆነ እርምጃ ማጨናገፍና የሶማሊላንድን የነጻነት እወጃ ዝግጅት ማስቆም፧ ማሰናከል ነው። ምክንያቱም ፑንትላንድ፧ እንደቀድሞው አንድነትን ነው የምትደግፈው። ሶማልያ አንዲት የተባበረች ሀገር ሆና እንድትቀጥል ትሻለች። ስለሆነም የሶማሊላንድን የመገንጠል ሂደት በመግታት እውቅና እንድታገኝ ለማድረግ መጣር ነው።«
ታዲያ ይህን የመሰለ ፈተና የተጋረጠባት ግዛት፧ ነጻነት እወጃ ዓለም አቀፍ ዕውቅና የማግኘት ዕድል ይኖራታል ብለው ያስባሉ?
«ሶማሊላንድ ባለፉት 10 ዓመታት ያሳየችው ዕድገት፧ ከዴሞክራሲ ግንባታም ሆነ ከልማት አኳያ ሲታይ በጣሙን አዎንታዊ ነው። ሶማሊላንድ በአመዛኙ ሰላም የሠፈነባት ናት። ከደቡብ ሶማልያ ጋር ሲነጻጻር፧ ከፑንትላንድም ጋር ቢሆን ሌሎቹ የሶማሊላንድን ያህል መረጋጋት አይታይባቸውም። ደቡብ ሶማልያና ፑንትላንድ ውስጣዊ ውዝግብና የኃይል እርምጃ እንደተጠናወታቸው ይገኛሉ። ሶማሊላንድ በጣሙን ሰላም የሰፈነባት ናት። በማዕከላዊ የዝች ግዛት ከፊል፧ ለምሳሌ ያህል በሀርጌሣ፧ በቡርማና ቡርዖ፧ የኤኮኖሚና የማኅበራዊ ኑሮ ዕድገት አለ። አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎች ተገንብተዋል። በዛ ያሉ የልማት እርዳታ ፕሮጀክቶችም አሉ። በውጭ የሚኖሩ የሶማሊላንድ ተወላጆች(ዲያስፖራ) ትምህርት ቤቶችና ሀኪም ቤቶችን በማሠራት በትጋት ነው የሚሳተፉት። በአጠቃላይ መሠረተ-ልማቱ አስመሥጋኝ ነው። ባለፉት ዓመታት አንዳንድ ዴሞክራሲ-ቀመስ ምርጫዎች ተካሂደዋል። ከዚህ ሁኔታ በመነሣት፧ ሶማሊላንድ፧ ለዓለም-አቀፍ እውቅና ብቁ ናት ማለት ይችላል። በዴሞክራሲ የግንባታ ጥረቷም፧ መለኪያዎችን እያሟላች በመሆኗ እውቅና በመስጠት መካስ ባስፈለገ ነበር። በደቡብ ሶማልያ እንደታየው በጎሣ ጦር አበጋዞች አልተገዛችም፧ በውዝግብም ከመናጥ ተገላግላለች። ይሁንና ፖለቲካ፧ ተምኔታዊ አመለካከት ባላቸው ሳይሆን ገሀዳዊን ፈለግ በሚከተሉ የሚቀመር እንደመሆኑ መጠን፧ ከዚህም ገሀዳዊ ይዞታ አኳያ ሲመለከቱት፧ በዓለም ዙሪያ ሶማሊላንድን በመንግሥትነት ለማወቅ ፍላጎት ያሳየ የለም።«