1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ መሪዎች ሽኩቻ

ሰኞ፣ ኅዳር 23 2006

ከአፍሪቃ ሕብረት-እስከ አረብ ሊግ፥ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ አዉሮጳ ሕብረት የሚገኙ አሐጉራዊ፥ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ያወደሱ፥ ያደነቁ፥የሚደግፉ፥ የሚረዱት መንግሥት ሹማምንታት ግን ከቀማዎቻቸዉ ብዙ የተለዩ አይመስሉም።

https://p.dw.com/p/1ARy1
President of Somalia Hassan Sheikh Mohamud (L) and Prime Minister Abdi Farah Shirdon Saaid confer during the appointment of Somalia's cabinet at the presidential palace in Mogadishu November 4, 2012. REUTERS/Omar Faruk (SOMALIA - Tags: POLITICS)
ወዳጅ ነበሩምስል Reuters

ሐያሉ ዓለም ሶሪያ-ኢራን፣ ጃፓን-ቻይና፣ ዩክሬይን-ታይላንድ ላይ እንዳነጣጠረ፥ ኢትዮጵያዊዉ ሳዑዲ አረቢያ በተሰደዱ ወገኖቹ ላይ የደረሰዉን በደል-ሲያብሰለስል፣ ሐያሉ ዓለም መረጋጋት መሻሻሏን የመሠከረላት፥ በርካታ ዶላር የሚያንቆረቁርላት፥ ኢትዮጵያ ሠለሟን ለማስከበር ጦር ያዘመተችላት ሶማሊያ ሐያ-ዓመት እንደለመደችዉ፥ ለተጨማሪ ጥፋት ፖለቲከኞችዋ ይሻኮቱባት ይዘዋል።ሌላዉን ለሌላ ጊዜ በይደር ይዘን የሶማሊያ ፖለቲከኞችን ሽኩቻ ላፍታ እንቃኛለን።አብራችሁን ቆዩ።


ነሐሴና ሶማሊያ።የሶማሊያ ደፈጣ ተዋጊዎች የቀድሞዉን የሐገሪቱን አምባገነን ገዢ መሐመድ ዚያድ ባሬን ሥርዓት በ1991 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከገረሰሱ ወዲሕ ከእልቂት፥ ትርምስ ተለይታ የማታዉቀዉ ሐገር ነሐሴ ጋር ልዩ ፍቅር የያዛት ትመስላለች።የፖለቲካ ፍቅር።የመጀመሪያዉ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት የተመሠረተዉ ነሐሴ ነበር።ሁለት ሺሕ።

ፕሬዝዳንት አብዲቃሲም ሳላድ ሐሰን የመሩት የሶማሊያ ብሔራዊ የሽግግር መንግሥት የተመሠረተዉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሪ፥አስተባባሪነት ጅቡቲ ላይ በተደረገ ጉባኤ፥ በሐያላኑ መንግሥታት ፍቃድና ግፊት ነበር።ይሁንና ከጅቡቲ ባለፍ የኢትዮጵያን ጨምሮ የአብዛኞቹን የአካባቢዉን መንግሥታት ድጋፍ በማጣቱ ከስም ባለፍ የመንግሥትነት ሥልጣኑን በገቢር ሳያስመሰክር ከሰመ።

ሳይኖር የከሰመዉን የብሔራዊ የሽግግር መንግሥት የተካዉ የሶማሊያ ፌደራላዊ የሽግግር መንግሥት ናይሮቢ-ኬንያ ላይ መመሥረቱ የታወጀዉም ነሐሴ ነበር።ሁለት ሺሕ አራት።የሽግግር መንግሥቱ መመስረቱ በታወጀ በአምስተኛዉ ሳምንት የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን የያዙት አብዱላሒ የሱፍ አሕመድ ተገፍተዉ ከሥልጣን ከለቀቁ በሕዋላ የተኳቸዉ ሌላዉ የሽግግር ፕሬዝዳት ሼሕ ሸሪፍ ሼሕ ሐሰን ሥልጣን የለቀቁት ነሐሴ ነበር።ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት።

«የሶማሊያ ፌደራላዊ» የተሰኘዉን የሽግግር መንግሥት «የሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ» ከሚል አዲስ ሥም ጋር አዲስ የተካዉ ቋሚ መንግሥት የተመሠረተዉ ነሐሴ-ነበር።ሁለት ሺሕ አስራ ሁለት።ሶማሊያና ነሐሴ-ይብቁን።

ጥር እንበል-ሁለት ሺሕ አራስራ-ሰወስት።

«ከአራት ዓመት በፊት የኦቦማ መስተዳድር በተጀመረበት ወቅት ሶማሊያ አሁን ካለችበት በብዙ መልኩ የተለየች ሐገር ነበረች።የሶማሊያ ሕዝብ እና መሪዎች በሐገራቸዉ የተሻለ መረጋጋት፥ ፀጥታ እና ሠላም ለማስፈን ታላቅ መስዋዕትነት ከፍለዋል።አሁንም ቢሆን ብዙ ርቀት መጓዝ እና በርካታ ፈተናዎችን መጋፈጥ ያስፈልጋል።ይሁንና አሁን ለተሻለ መፃኤ ዘመን አዲስ መሠረት መጣሉን አይተናል።ዛሬ ደግሞ ከዚያ በጎ ዘመን የሚያደርሰን ጠቃሚ እርምጃ ወስደናል።ከ1991ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ ለሶማሊያ መንግሥት እዉቅና መስጠቷን ሳዉጅ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል።»

የቀድሞዋ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን ናቸዉ።በዘመነ-ሥልጣናቸዉ የመጨረሻ ወር ካሉ ካደረጉት አንዱና ትልቁ ጉዳይ ለሶማሊያ እዉቅና መስጠት ነበር።ወትሮም በአሜሪካኖች የገንዘብ፥ የፖለቲካ፥ የጠመንጃም ድጋፍ ለተቋቋመዉ መንግሥት እዉቅና ለመስጠት ዋሽግተኖች በሩን ሲከፍቱ ሌሎች ምዕራባዉያን ሐገራትም እየተግተለተሉ ገቡ።

የቀድሞዋ ገሚስ ሶማሊያ፥ የዛሬዋ ሶማሊ ላንድ ቅኝ ገዢ ብሪታንያ ከብዙዎቹ ወዳጅ አቻዎቿ ቀድማ ካንዴም ሁለቴ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ የሚመክር ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለደን ላይ አስተናግዳልች። ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯን ሞቃዲሾ ድረስ ለመላክም ብሪታንያን የቀደመ ምዕራባዊ ሐገር አልነበረም።

«የቀድሞዉ ኤምባሲያችን ባልደረቦች ከሞቃዲሾ ከወጡና ባንዲራዉ ከወረደ ከሃያ-ሁለት ዓመት በኋላ ኤምባሲያችንን ዳግም ሥንከፍት እኛ የመጀመሪያዎቹ ምዕራባዉያን ሐገር ነን።ይሕ ለኛ፥ ሶማሊያ በዓለም አቀፍ ድጋፍ ችግሮችዋን መወጣት እንደምትችልም ምልክት ሰጪ ነዉ።ከዚሕም በተጨማሪ በርግጥ ተግባራዊ ትብብራችንንም ያጠናክርልናል።»

የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊሊያም ሔግ።የካቲት ሁለት-ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት።ሞቃዲሾ። የዚያድ ባሬ መንግሥት ከተወገደ ወዲሕ በተለያየ ሥምና ሥፍራ ከተቋቋሙት መንግሥታት ሁሉ እንደ ሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ መንግሥት ዓለም ተስፋ የጣለበት፥ ያደነቀ፥ ያወደሰ፥ የደገፈ፥ የረዳዉም መንግሥት የለም።

አፍሪቃዉያን ኢትዮጵያን ጨምሮ ገንዘብ ቢያጡ ደም፥ አካል፥ ሲከፋም ሕይወቱን የሚገብር ሠራዊት አዝምተዋል።ቱርክ፥ አረብ፥ ፋርስ፥ ቻይና ገንዘብ፥ ባለሙያ፥ ኩባንያዉን ልኳል።
ሐያሉ ምዕራቡ ዓለም ከፖለቲካዊ ተፅዕኖ-እስከ ጦር ጡንቻዉ፥ ከእሕል እርዳታዉ እስከ ዶላር ድጎማዉ ለሶማሊያ ያንቆረቁራል።


ከአፍሪቃ ሕብረት-እስከ አረብ ሊግ፥ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ አዉሮጳ ሕብረት የሚገኙ አሐጉራዊ፥ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ያወደሱ፥ ያደነቁ፥የሚደግፉ፥ የሚረዱት መንግሥት ሹማምንታት ግን ከቀማዎቻቸዉ ብዙ የተለዩ አይመስሉም።በሞቃዲሾ የዶቸ ቬለ ተባባሪ ዘጋቢ መሐመድ ዑመር ሁሴይንም ሌላ የሚለዉ የለም።

«እዉነቱን ለመናገር የቀድሞዉ የሶማሊያ (የዚያድ ባሬ) ሥርዓት ከፈረሰ ወዲሕ ሶማሊያ ዉስጥ በርካታ የሽግግር መንግሥታት ተመሥርተዉ ነበር።ሁል ጊዜ ግን በፕሬዝዳንቱ እና በጠቅላይ ሚንስትሩ መካካል የሥልጣን ሽኩቻ አለ።ያሁንም ከቀድሞዎቹ የተለየ አይደለም።እኛ፥ ሶማሊያዉያን ይሕ መንግሥት የዚያድ ባሬ መንግሥት ከተወገደ በኋላ ከተመሠረቱት መንግሥታት ሁሉ የተረጋጋ እና የተሻለ ነዉ የሚል ተስፋ ነበረን።አሁን በጠቅላይ ሚንስትሩ እና በፕሬዝዳንቱ መካካል ያለዉ ሽኩቻ ግን መንግሥቱ ከቀዳሚዎቹ አለመለየቱን እየጠቆመ ነዉ።»

ፕሬዝዳት ሐሰን ሼኽ መሐሙድ ሥልጣን ከያዙ በሕዋላ የምዕራባዉን ድጋፍ፥ እዉቅና እና ዉዳሴን በአካል ተገኝተዉ ለማየት፥ ለመስማት እና በፊርማቸዉ ለማረጋገጥ ወራት አልፈጀባቸዉም ነበር። መስከረም ቪላ መቋዲሾ ገቡ። ጥር ዋይትሐዉስን አዩ።አሜሪካን፥ አዉሮጳን ጎበኙ።ዓመት ሳይደፍኑ ዘንድሮ ግን እራሳቸዉ ከሾሟቸዉ ጠቅላይ ሚንስትር ከአብዲ ፋራሕ ሺርዶን ሰዓድ ጋር ይወዛገቡ ያዙ።

የዉዝግቡ ሰበብ ምክንያት በርግጥ ግልፅ አይደለም።አዲሱ የሶማሊያ ሕገ-መንግሥት በሚያዘዉ መሠረት የመንግሥቱን ሰወስት ትላልቅ ሥልጣኖች ማለት የፕሬዝዳንትነቱን፥ የምክር ቤት አፈ-ጉባኤነቱን እና የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን የሚከፋፈሉት ከአራቱ ትላልቅ ጎሳ የወጡ ፖለቲከኞች ናቸዉ።

አራት ለአምስት ተብሎ በተፈረጀዉ ደንብ መሠረት የአራቱ ትላልቅ ጎሳዎች አባላት ሰወስቱን ትላልቅ ሥልጣን ሲከፋፈሉ ከተቀሩት አምስት አነስተኛ ጎሳዎች የሚወለዱ ፖለቲከኞች ደግሞ ከተቀሩት ሥልጣኖች ይጋራሉ።በዚሕ ክፍፍል መሠረት የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን የያዙት ሐሰን ሼኽ መሐሙድ የሐዉያ ጎሳ ተወላጅ ሲሆኑ፥ ጠቅላይ ሚንስትር አብዲ ፋራሕ ሺርዶን ሰዓድ የዳሮድ ጎሳ ተወላጅ ናቸዉ።

ይሕ ልዩነት ለጠቡ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል።ሶማሊያዊዉ ጋዜጠኛ እንደሚለዉ ግን የጠቡ መነሻ በጎሳ ልዩነት ላይ የተመሠረተ አይመስልም።

«እስካሁን ድረስ ይሕን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ነገር አልታየም።ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣን እዲለቁ የጠየቁት ሐላፊነታቸዉን በአግባቡ አልተወጡም በሚል ምክንያት ነዉ።የሞቃዲሾ ነዋሪዎችም የፕሬዝዳንቱን አቋም የሚጋሩ ይመስላሉ።አንዳዶቹ እንደሚሉት ሺርዶን የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ቢሮ ይዘዉ ከመቀመጥ ሌላ የዉጪ ዲፕሎማቶችን ማነጋገሩን፥የሐገሪቱን ካቢኔ ሥራ መቆጣጠሩን ጭራሽ ትተዉታል።ከዲፕሎማቶች ጋር የሚገናኙት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯ ወይዘሮ ፎዚያ ናቸዉ።»

አብዛኛዉ የሞቃዲሾ እና የአካባቢዋ ነዋሪ ፕሬዝዳንቱ ጎሳ አባል ነዉ።ሐዉያ።ሐዉያዉ ሕዝብ ከሐዉያ ጎሳ የሚወለዱትን ፕሬዝዳት አቋም የማይደግፍበት ምክንያት መኖሩ አጠራጣሪ ነዉ።እና የጎሳ ልዩነት ከሃያ-ዓመት በላይ ደም በሚያራጨዉ ሶማሊያ የሁለቱ ሹማምንት ሽኩቻ ከጎሳ ልዩነት የፀዳ ነዉ ማለት ሲበዛ ከባድ ነዉ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣን እንዲለቁ ፕሬዝዳንቱ ያቀረቡትን ጥያቄ በቀጥታ ዉድቅ አላደረጉትም። የጠቡን መነሻ ለሐገሪቱ ምክር ቤት (ብሔራዊ ሸንጎ) ማስረዳት አለብኝ ባይ ናቸዉ።የምክር ቤቱ አባላት ጠቅላይ ሚንስትሩ ያቀረቡን ጥያቄ እስከ ትናንት ድረስ አልተቀበሏቸዉም።ጠቅላይ ሚንስትሩ የፕሬዝዳንቱን ትዕዛዝ አክብረዉ ወይም ተቀብለዉ ሥልጣናቸዉን ይልቀቁ-አይልቀቁ በሚለዉ ሐሳብ ላይ ቅዳሜ የጀመረዉን ዉይይት ግን ዛሬ ለመቀጠል ቀጠሮ አለዉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ሻርዶን ትናንት ማታ በጠሩት ጋዜጣዊ ጉባኤ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ መነጋገሩን እንደሚደግፉት አስታዉቀዋል።ለጋዜጠኞች በተደጋጋሚ የነገሩት ግን ጉዳዬን ወይም ቅሬታዬን ለምክር ቤቱ ለማሰማት ያቀረብኩትን ጥያቄ ምክር ቤቱ የመቀበል ሕገ-መንግሥታዊ ሐላፊነት አለበት እያሉ ነበር።

የጠብ ሽኩቻዉ ምክንያት ጎሳዊ ከመሆን ይልቅ ጋዜጠኛ መሐመድ ዑመር ሁሴይን እንዳለዉ ሐላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ሊሆን ይችላል።ወይም የሥልጣን ሽሚያ፥ ወይም ጠቅላይ ሚንስትሩ እናገረዋለሁ ያሉት ሌላ ሚስጥር ሊሆንም ይችላል።ልዩነቱ መፍጠጡ፥ የጠቅላይ ሚንስትር አብዲ ፋራሕ ሺርዶን ዘመነ-ሥልጣን በዓመት እድሜ ከፍፃሜዉ መጀመሪያ ላይ መድረሱ እርግጥ ነዉ።ይሕ ደግሞ አይ ኤስ ኤስ በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ አታ አሳ ሞዋ እንደሚሉት የሶማሊያ መንግሥት መዋቅር እንደታሰበዉ ጠንካራ አለመሆኑን አመልካች ነዉ።

«(ሽኩቻዉ) በሽግግሩ ወቅት የተመሠረቱ መንግሥታትን በሙሉ ማለት ይቻላል ካደከሙዋቸዉ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ነዉ።አሁን የሚያሳስበዉ ይሕ ነዉ።የዉስጣዊ ሽኩቻዉ ማየል የመንግሥቱን መዋቅር ደካማነት የሚያረጋግጥ ነዉ።ይሕ መንግሥት በተለይ ብዙ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።በፕሬዝዳንቱ እና በጠቅላይ ሚንስትሩ መካካል አሁን ያለዉ ሽኩቻ ግን ሁሉም ጥሩ እንዳልሆነ አመልካች ነዉ።»

ሶማሊያ በፖለቲካዉ ጥሩ መስሎ የሚታይ እንጂ ጥሩ ሆኖባት አይያዉቅ።በተለይ ከ1991 ወዲሕ። የመጀመሪያዉ የሽግግር መንግሥት በሁለት ሺሕ መቃቋሙ ተነግሮ፥ መኖሩ ሳይታወቅ መክሰሙ እስከታወጀበት እስከ ሁለት አራት ድረስ አራት ጠቅላይ ሚንስትሮች ተፈራርቀዉበታል።

በሁለት ሺሕ አራት የተመሠረተዉ የሽግግር መንግሥት በሁለት ሺሕ ዘጠኝ በሌላ መንግሥት እስከተተካበት ጊዜ ድረስ በተቆጠረዉ አራት ዓመት ከመንፈቅ ሰወስት ጠቅላይ ሚንስትሮች ተለዋዉጠዋል።ከሁለት ሺሕ ዘጠኝ ያሁኑ መንግሥት ሥልጣን እስከ ያዘበት እስከ ነሐሴ ሁለት ሺሕ አሥራ-ሁለት ድረስ ሠወስት ዓመታት ነበሩ።በሰወስት ዓመት ሶማሊያ አምስት ጠቅላይ ሚንስትር እየተሾመ ተሽሮባታል።

አሁንም ጠቅላይ ሚንስትር ሽሮ መሾሙ በርግጥ አይግድም።ሒደት፥ ዉጤት መዘዙ ግን አታ አሳ ሞዋ እንደሚሉት ለሶማሊያ አሳሳቢ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል።ለአክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ለአሸባብማ ደግሞ ግልፅ ነዉ።ሠርግ እና ምላሽ።

«የሶማሊያን ሁኔታ ስታይ ግጭትና ልዩነት ያለባት ሐገር ናት።እንዲሕ አይነቱ ሽኩቻም በቀላሉ የጎሳ ልዩነት መስመርን ሊከተል ይችላል።ሥለዚሕ አንደኛ ሽኩቻዉ ወደ ሌላ አቅጣጫ አምርቶ መንግሥቱን ያዳክማል።ሁለተኛ መሪዎቹ እርስ በርስ ሲጠላለፉ ለሶማሊያ ሕዝብ መስራት የሚገባቸዉን መሠረታዊ ነገር እንዳይሰሩ፥ ሐላፊነታቸዉንም በአግባቡ እንዳይወጡ ያናጥባቸዋል። በሰወስተኛ ደረጃ ሽኩቻዉ ለአሸባብ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ጥሩ ግብዓት ነዉ።አሸባብ ወትሮም በሥልጣን ላይ ያለዉ መንግሥት የዓለም አቀፉን ፍላጎት ለመጠበቅ እንጂ የሶማሊያን ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት በራሱ የሚንቀሳቀስ አይደለም እያለ ነዉ።»

ሶማሊያ እና መንግሥቶቿ።ከ1960 እስከ 1969 ሶማሊያ፥ የሶማሊ ሪፐብሊክ መንግሥት ነበረች።ወይም ነበራት። በ1969 ጄኔራል መሐመድ ዚያድ ባሬ ሶሻሊስ አደረጓት እና መንግሥቷን የሶማሊ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ አሉት።ከ2000 እስከ 2004 ።የሶማሊ ብሔራዊ የሽግግር መንግሥት።ከ2004 እስከ 2012 የሶማሊያ ፌደራላዊ የሽግግር መንግሥት።ከ2012 በኋላ የሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ሆናለች።

እነሆ ፌደራላዊ ሪፐብሊካዊ መንግሥት እንደቀዳሚዎቹ ሁሉ መሪዎቹን ሊቀያይር በጠቅላይ ሚንስትሩ አንድ ሊል ነዉ።ዝግጅታችችን በተመለከተ አስተያየትና ጥቆማ የሰጣችሁንን አመሰግናለሁ። አንዳዶቻቸሁ ያቀረባችሁትን ጥቆማ ማሕደረ ዜና ወደፊት ይቃኛዋል።አሁንም ያላችሁን አስተያየት በደብዳቤ፥ ኢሜይል፥ በፌስቡክ፥ በኤስ ኤምስ እና በስልክ ላኩልን።ለዛሬዉ ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

Newly appointed members of Somalia's cabinet stand during the ceremony held at the presidential palace in capital Mogadishu November 4, 2012. REUTERS/Omar Faruk (SOMALIA - Tags: POLITICS)
ካቢኔዉምስል Reuters
Newly appointed Somalia's Prime Minister Abdi Farah Shirdon Saaid addresses the media in Somalia's capital Mogadishu October 6, 2012. Somali President Hassan Sheikh Mohamud has named Saaid as the country's new prime minister, diplomats and a government source said, the first major decision by an administration installed after over 20 years of conflict. REUTERS/Feisal Omar (SOMALIA - Tags: SOCIETY POLITICS)
ጠ.ሚ ሺርዶንምስል Reuters
Residents walk past the campaign billboard of Somalia's presidential candidate Hassan Sheikh Mohamud in Somalia's capital Mogadishu, September 9, 2012. Somalia's lawmakers voted overwhelmingly on Monday for Mohamud as the country's next president, with the streets of the capital erupting into celebratory gunfire, Reuters witnesses said. Two of the four candidates who made it to the second round of voting opted out, leaving the incumbent President Sheikh Sharif Ahmed and Mohamud.Picture taken September 9, 2012. REUTERS/Feisal Omar (SOMALIA - Tags: POLITICS ELECTIONS)
ፕሬዝዳንት ሐሰንምስል picture-alliance/dpa
A woman holds up election campaign posters of Somalia's President Sheikh Sharif Ahmed in Mogadishu, September 9, 2012. The presidential election will be held on September 10. REUTERS/Feisal Omar (SOMALIA - Tags: ELECTIONS POLITICS TPX IMAGES OF THE DAY)
ምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ




ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ