1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ምርጫ ምን ይዞ ይመጣል?

ዓርብ፣ መስከረም 13 2009

ለሁለት አስርት ዓመታት መንግስት አልባ ሆና የቆየችው እና በእርስ በእርስ ጦርነት አሳር አበሳዋን ስታይ የባጀችው ሶማሊያ አንጻራዊ የሚባል መረጋጋት ከሰፈነባት ጥቂት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ የሽግግር መንግሥት አዋቅራ፣ ፓርላማ መስርታ፣ ጎረቤቶቿ በየጊዜው ከሚሰበሰቡበት ማህበር ዕድምተኛ መሆን ከጀመረች ከረመች፡፡

https://p.dw.com/p/1K77c
Afrika Somalia Bombenanschlag in Mogadischu Sicherheitskräfte
ምስል Reuters/I. Taxta

ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ መመለሷን ለማወጅ የምስራቅ አፍሪካ መሪዎችን ወደ መዲናዋ ሞቅዲሹ ጋብዛ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለምታካሂደው ምርጫ ይሁንታን ተቀብላለች፡፡
በመጪው ቅዳሜ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እና በበነጋታው የሚካሄደው የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ለሶማሊያ ያልጠና ፖለቲካ “ወሳኝ እርምጃ” ነው ተብሎለታል፡፡ ነገርየው ምርጫ ይባል እንጂ በሌላው ሀገር እንደተለመደው “የአንድ ሰው አንድ ድምጽ” አሰራርን የተከተለ አይደለምሚሀ፡፡ ይልቅስ በጎሳ መሪዎች የሚመረጡ ወደ 14 ሺህ ገደማ የሚሆኑ ሶማሊያውያን ድምጽ የሚሰጡበት “ቀጥተኛ ያልሆነ” የምርጫ አካሄድ ነው፡፡
ለጎሳ፣ ለንዑስ ጎሳ እና በተዋረድ ከዚያ በታች ላሉት የህብረተሰብ መዋቅሮች ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው የሶማሊያ ህዝብ በእንዲህ ዓይነቱ የምርጫ አካሄድ “በፍትሃዊነት መወከል ይችላል ወይ?” የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ግን አካሄዱ በፊት ከነበረው በተሻለ ሁሉን አካታች ነው፡፡
በአሜሪካ ኖርዝ ካሮላይና በሚገኘው ዳቪሰን ኮሌጅ የፖለቲካ ሳይንስ የሚያስተምሩት እና የሶማሊያን ጉዳይ ላለፉት 30 ዓመታት ያጠኑት ፕሮፌሰር ኬን ሜንክሀውስ በምርጫው “የጎሳዎች ውክልና ተጠብቋል” ይላሉ፡፡
“ምርጫው በጎሳው ውስጥ የሚደረግ እንጂ በጎሳዎች መካከል የሚደረግ አይደለም፡፡ ይህን የህብረተሰብ ቡድኖች ለአገር አቀፍ ምክር ቤት የሚሆኑ ተወካዮቻቸውን የሚመርጡበትን አካሄድ ፖለቲካል ሳይንቲስቶች የስምምነት ዴሞክራሲ እንለዋለን፡፡ ”
ሶማሊያዊው የፖለቲካ ተንታኝ አብዲሃኪም አየንቴ የፕሮፌሰሩን አስተያየት ይጋራሉ፡፡ እንደ ጎርጎርሳውያኑ አቆጣጠር በ2012 የተካሄደው የምክር ቤት አባላት ምርጫ በ135 ባህላዊ መሪዎች ብቻ መካሄዱን የሚያስታውሱት አብዱሃኪም የአሁኑ ከቀድሞው የተሻለ እና ቅቡልነት ያለው እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ምርጫ የሚሳተፉት መራጮች በቁጥር መብዛታቸውና በቀጥታ በጎሳ መሪዎች መሰየማቸው ሁሉም ጎሳዎች ቦታ እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል ይላሉ፡፡
“ሁሉም ጎሳ 50 ሲደመር አንድ ለሆነው የምርጫ ሂደት ተወካዮቹን ማምጣት አለበት፡፡ ይህ ሁሉንም የጎሳ ተዋረዶች፣ የተለያዩ ንዑስ ነገዶች እና ንዑስ ጎሳዎችን ይሸፍናል፡፡ አካሄዱ ጎሳዎቹ ተወካዮቻቸውን በመላክ፣ ድምጽ በመስጠት በሚቀጥለው መንግስት የሚካተቱ ባለስልጣናትን እና የምክር ቤት አባላትን እንዲመርጡ የማሳመኛ አንዱ መንገድ ነው፡፡”
በዚህ የምርጫ አካሄድ መሰረት 275 መቀመጫዎች የሚኖሩት የሶማሊያ የሕግ መምሪያ በ4.5 የስልጣን ክፍፍል ቀመር መሰረት ለእያንዳንዱ ጎሳ ይከፋፈላል፡፡ ይህ ሂደት በጎሳዎች ዘንድ የሚነሳውን የመወከል ችግር ይቀርፋል ቢባልም በሀገሪቱ አሁን በተቋቋሙት የፌደራል አስተዳደሮች ዘንድ ግን ተቃውሞ አስነስቷል፡፡ የፌደራል አስተዳደሮቹ 58 የሚሆኑትን የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት በቀጥታ የመሰየም ስልጣን ቢሰጣቸውም በምርጫው አካሄድ ላይ ተቃውሞ ያሰማሉ፡፡
ፕሮፌሰር ኬን በዚህ የምርጫ ሂደት ውስጥ “የፌደራል አስተዳደሮቹ ሚና በጣም ወሳኝ ነው” ይላሉ፡፡
“በሶማሊያ ያለው ምክር ቤት የተሽመደመደ ነው፡፡ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የፌዴራል አስተዳዳሮች ፕሬዝዳንቶችን በመሰብሰብ አገር አቀፍ የአመራር መድረክ የሚባል ይፋዊ ያልሆነ ቡድን ፈጥረዋል፡፡ ቡድኑ ከምክር ቤቱ ዕውቅና ውጭ ምርጫው እንዴት መካሄድ እንዳለበት ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ ቆይቷል፡፡ አንዳንድ ሶማሊያውያን ይህ ህገመንግስታዊ አይደለም ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ ”
እንደ ፕሮፌሰሩ አባባል ይህ ለፌደራል አስተዳደሮቹ “ከፍተኛ የሆነ ስልጣን” አጎናጽፏል፡፡ ይህ ስልጣን እነርሱ ያልተስማሙበት ማንኛውንም ሂደት ውድቅ እስከ ማድረግ ድረስ የተለጠጠ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት በምርጫው ሂደት ደስተኛ ያልነበሩ የፌደራል አስተዳደሮች ጥለው ለመውጣት መዛታቸውን የሚያስታውሱት ፕሮፌሰር ኬን “ይህ ከሆነ ሁሉም ነገር ይፈራርሳል” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ አብዲሃኪም ግን የፌደራል አስተዳደሮቹ ጉዳይ ሊያሳስብ አይገባም ባይ ናቸው፡፡ አስተዳደሮቹ ያነሱት ጥያቄ እንደ የጊዜ ሰሌዳ እና ሎጀስቲክ የመሳሰሉ ቴክኒካዊ ጉዳዩች ናቸው እንጂ መሰረታዊ አይደሉም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
በዚህም አለ በዚያ ሶማሊያ ዳግም ወደ ምርጫ እየተንደረደረች ነው፡፡ ባለፈው ምርጫ በጎሳ መሪዎች የተመረጡት የፓርላማ አባላት ባለፈው ሳምንት ስልጣናቸው ያበቃውን ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ መርጠው ነበር፡፡ በመጪው ጥቅምት የምክር ቤት አባልነቱን ስልጣ የሚይዙት አዲሱን ፕሬዝዳንት ይመርጣሉ፡፡
“ምርጫው ሶማሊያን አንድ እርምጃ ወደፊት ያራምዳታል ወይስ በእስካሁን ጉዞዋ እንድትቀጥል ያደርጋል?” የሚለው ጥያቄ ገና አልለየለትም፡፡ ለፕሮፌሰር ኬን ግን ምርጫው በሶማሊያ ላይ የሚያመጣው መሰረታዊ ለውጥ የለም፡፡
“ብዙዎች እንደሚጠብቁት ምርጫው በወሳኝ የሶማሊያ ፖለቲካዊ ለውጦች ላይ የረጅም ጊዜ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብዬ አልገምትም፡፡”
ሶማሊያዊው የፖለቲካ ተንታኝ አብዲሃኪም ግን ከፕሮፌሰሩ በተቃራኒ ይቆማሉ፡፡ ሶማሊያ በ“ወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች” የሚሉት አብዲሃኪም ይህን ግን “ስጋት ውስጥ ሊከት አይገባም” ይላሉ፡፡
“ምርጫው መቶ በመቶ ነጻ እና ፍትሃዊ ይሆናል ብዬ አልጠብቅም። ነገር ግን ሰላማዊ የሚሆን ይመስለኛል፡፡”

Somalia Angriff auf Restaurant in Mogadischu
ምስል Reuters/F. Omar
Somalia Mogadischu Sicherheitskräfte
ምስል Getty Images/Bongarts/C. Koepsel
Somalia Soldat Lido Beach in Mogadischu
ምስል Getty Images/AFP/M. Abdiwahab


ተስፋለም ወልደየስ


ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ