1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ቀዉስና አለም አቀፉ ማሕበረሰብ

ሰኞ፣ ግንቦት 10 2001

በ1960ዎቹ አደን አብዱሌ ኡስማን ዳሬ እና አብዱረሺድ አሊ ሸርማርኬ እንደዲሞክራሲዉ ወግ በሕዝብ ተመርጠዉ ስልጣን ሲይዙባት ከብዙዎቹ የአፍሪቃ፥ የሙስሊም ሐገራት የተሻለች መስላ ነበር።

https://p.dw.com/p/HsnS
ደፈጣ ተዋጊዎቹ-መቅዲሾ ዉስጥምስል AP


18 05 09

በካፒታሊስት-ኮሚንስቱ ተፃራሪ ሐይል ግፊት-ጀርመኖች እሁለት ሲገመሱ፣ ኮሪያዎች፣ ቬትናሞች፣ የመኖች ሁለት ባንዲራ ስቅለዉ-ሲተላለቁ፣-አንድነትን መምረጣቸዉ-ለብዙዎቹ ጥሩ አብነት፣ ሌሎቹን ለሁለት-ብዙነት የሚያዋጋዉ ሐያል አለም ደግነት-ምልክት፣ሐራምቤን ለዘመረዉ አፍሪቃዊ ብርታት መስለዉ ነበር።ሶማሌዎች።የብዙ ሁለት-ብዙዎች አንድነት በፀናበት ዘመን ግን ብዙዎችን ተቃርና እንደተፈረካከሰችዉ ሶቬት ሕብረት ብዙ፣ ካምቦዲያ፤ ሊባኖስ፤ ላቤሪያዎች ተከትለዉ የጥፋት ማዕከልም ሆኑ።ዘንድሮ ደግሞ ከቃል በላፍ ማንም-የማያያቸዉ-ምንም ናቸዉ።ሶማሌዎች።ግን ለምን? ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።የሶማሊያን ሁኔታ እያነሳን እንደገና ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን ለሶማሊያ ገንዘብ ለማዋጣት ባለፈዉ ሚያዚያ ብራሥልስ-ቤልጅግ ለተሰየመዉ ጉባኤ እንደነገሩት የሶማሊያ የባሕር ወንበዴዎች-የሶማሊያ ሁከት ትርምስ እንጂ-መርከብ የሚያጠቁ፤ የሚያግቱበት ባሕር አልወለዳቸዉም።

መልዕክቱ የሐብታሙ አለም የሶማሊያን ሰላምና ደሕንነት ቢያስከብር የሸቀጥ-ዝዉዉሩን የሚያዉኩትን ወንበዴዎች ማጥፋት እንደሚችል-የማረጋገጡን ያክል-ጉባኤተኞች ሶማሊያን ያስታወሷት ንግዳቸዉ በመታወኩ-ወንበዴዎቹን ለመዉጋት ያዘመቱት ጦር ዉጤት በማጣቱ እንጂ ለዚያች ሐገር ሰላምና ደሕንነት አለመጨነቃቸዉን ጠቋሚ ነዉ።

ከምንምና ከማንም በላይ ጥቅምና ደሕነቱን ለማስከበር ፈርጣማ-ጉልበቱን፤ ክምር ሐብቱን፤ ረቂቅ ብልሐቱን፤ በሳል እዉቀቱን ለመዘርገፍ የማይሰስተዉ፣ አለምን ለማሰለፍ የማያመነታዉ አለም-ካለፍ አገደም ባለፍ ሶማሊያን ከረሳት-በሶማሊያ ከተረሳም አስራ-ዘጠኝ ዘመናት ተቆጠሯል።

የሚሊዮኖችን ከሞት፤ ከአካለ ጎደሎነት፤ ከረሐብ-እርዛት፤ ከስደት-እንግልት ለማዳንም በርግጥ መሽቷል።ግን አልጨለመም።ሐያሉ አለም የሸቀጥ ዝዉዉሩን ለማስከበር-ይሁን በሌላ ምክንያት ሶማሊያን ማስታወሱ ለሶማሌዎች የሩቅ-ተስፋ፣ ለሰላም ወዳዶች፤ ለሰዉ ልጅ ደሕንነት ተጨናቂዎች በርግጥ ታላቅ ደስታ ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትስን፥ በዉጤቱም የአለምን የስምንት ዘመን የተበላሸ ጉዞ እንደሚቀይሩ-ቃል የገቡ-እንደሚቀይሩት ተስፋ የተደረገባቸዉ፥ ከኬንያዊ አባት የሚወለዱት ባራክ ኦባማ የሚመሩት መስተዳድር እንኳን የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባልደረባ ጆን ኤልተን ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ከባሕር ወንበዴዎቿ ባለፍ-ሶማሊያን አለማስታወሱ-ነዉ ለመሸበት ሕዝብ የመጨለሙ ቀቢፀ-ተስፋ።

«በአሐጉሪቱ (በአፍሪቃ) ያሉ ዋና ዋና ችግሮችን ለመፍታት በአስቸኳይ ትኩረት ሲሰጠዉ ማየት እንፈልጋለን።ሥለ ሶማሊያ ከዚሕ በፊትም ተናግረናል።ይሁንና አሁንም ብዙዎቹ የዋሽንግተን ባለሥልጣናት የሶማሊያን ችግር የባሕር ወንበዴዎች የሚፈጥሩት ችግር ብቻ አድርገዉ ነዉ-የሚያዩት።በዚያች ሐገር ግዛት ዉስጥ ያለዉን ከፍተኛ ሰብአዊ ድቀትና የሰብአዊ መብት ድቀትን አይመለከቱትም»

የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ቡትሩስ ቡትሩስ ጋሊ የሶማሊያን ሕዝብ ከባሰ እልቂት ለማዳን የአሜሪካ ጦር ፈጥኖ ካልዘመተ ሁከት ትርምሱ አለም አቀፍ ሠራዊት እስኪዋጣ-እስኪዘምት ድረስ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም ብለዉ ነበር።ታሕሳስ 1991 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።)

UN-Gebertreffen in Brüssel - Somalia
ፕሬዝዳንት ሸሪፍ ከለጋሽ ሐገራት ጉባኤተኞ ጋራምስል AP

የፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ቀዳማዊ መስተዳድር «ተስፋ መልስ» ላለዉ ዘመቻ የአሜሪካ ባሕር ሐይል ጦርን ያዘመተዉ በርግጥ ከእርስ በርስ ጦርነቱ ጋር ረሐብ-ድርቅ የሚፈጀዉን ሕዝብ ሕይወት ለማዳን እግረ መንገዱንም የኢራቅን ጦር ከኩዌት ለማስጣት በተደረገዉ ዉጊያ የተባበሩ የሙስሊም አረብ ሐገሮችን ዉለታ ለመመለስ፥ በጦርነቱ የተከፉትን ለማስደሰት ወይም ምክንያት ለማሳጣት-አልነበረም ማለት ያጃጅላል።

ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን የአሜሪካ ጦር-ቀድሞ፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራዊት ተከትሎ ሶማሊያ መግባቱ አለም አቀፍ የሚባለዉ ማሕበረሰብ ለዚያች ሐገር፥ለአካባቢዉም ሠላም-የማሰብ መቆርቀሩ ተስፋ ነበር።ተስፋ ሊመልስ የዘመተዉ ሠራዊት እንደ ደቡብ ሊባኖስ ሃያ-ሃያ አምስት ሊቀመጥ ቀርቶ በአሁለት አመት እድሜ የራሱንም የሁሉንም ተስፋ ቀጭቶ-ጓዙን ጠቅልሎ መዉጣቱ እንጂ የእስካሁኑ ድቀት።

የቡትሩስ ቡትሩስ ጋሊ ቃል ያጫራዉ ተስፋ በበነነ በ15ኛ አመቱ ዘንድሮ በሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ አሕመዱ ኡሉድ አብደላሕ አለም አቀፍ ማሕበረሰብ ሶማሊያን ለመርዳት ሐይሉን ማስተባበር አለበት ይላሉ።

«አለም አቀፉ ማሕበረሰብ የሚወስደዉን እርምጃ ማቀናጀት አለበት።አለም አቀፉ ማሕበረሰብ እርምጃዉን በሙሉ ባንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ማድረግ የለበትም።የተለያዩ ጉዳዮችን ለመፍታት ባንድ ጊዜ እኩል እርምጃ መዉሰድ አለብን።»

የርዕሠ-ከተማ መቅዲሾ መደብሮች፥ ትምሕር ቤቶች፣ሐኪም ቤቶች አመዳቸዉን አራግፈዉ ሳይጨርሱ ክሳያቸዉ ዳግም ሲነድ፥ነዋሪዉ ዘመድ-ወዳጆቹን ቀብሮ-አስታሞ ሳያርፍ-እራሱ ሲሞት፥ አካሉን ሲያጣ ዳግም ሲሰደድ አለም አቀፍ የሚባለዉ ማሕበረሰብ ገና ሐይሉን እንዲያቀናጅ መጠየቁ ነዉ-ቅጭቱ።ሐምሌ-2000 አርተ-ጅቡቲ ላይ የተሰየመዉ የሶማሊያ የጎሳ መሪዎችና የጦር አበጋዞች ጉባኤ አብዲቃሲም ሳላድ ሐሰን የሚመሩት ጊዚያዊ መንግሥት መስርቶ ነበር።

በጉባኤዉ ዉጤት የረኩት የያኔዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ከኢጋድ እስከ አፍሪቃ አንድነት፥ ከአረብ ሊግ እስከ አዉሮጳ ሕብረት፥ከሙስሊም ሐገራት ማሕበር እስከ ገለልተኛ ሐገራት ንቅናቄ የሚገኙ ድርጅቶና ተቋማት የፕሬዝዳት አብዲቃሲም መንግሥትን እንደሚደግፉ አስታዉቀዉ ነበር።

ይህ ሁሉ የቃል ድጋፍ የተንቆረቆረለት መንግሥት ሶማሊያን አይደለም ገሚስ መቅዲሾን እንኳን ሳይቆጣጠር በሰወስተኛ አመቱ ፈረሰ። በአስራ-ዘጠነኛ አመቱ ዘንድሮ ልዩ መልዕክተኛ ኡሉድ አብደላሕ የፕሬዝዳት ሼሕ ሸሪፍ ሼሕ አሕመድ መንግሥት ከፍተኛ አለም አቀፍ ድጋፍ አለዉ ይሉናል።
«መንግሥቱን ለማጠናከር አሁንም አልዘገየም።መንግሥቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጠንካራ ድጋፍ እያገኘ ነዉ።አለም አቀፉ ማሕበረሰብ መንግሥቱን የሚወጉት ሶማሊያን፥ ኢጋድን የአፍሪቃ ቀንድን አካባቢ እንደማይጠቅሙ በስተመጨረሻዉ መረዳቱ በጣም ጥሩ ነዉ።»

የዛሬ ሰወስት አመት በሐይል-ተቆጣጥረዉት የነበረዉን ቪላ መቅዲሾን በሐይል የተቀሙት ሼክ ሸሪፍ አሕመድ በቅርቡ ዳግም ግን በሰለም ከተመለሱበት ወዲሕ ተረጋግተዉ ተቀምጠዉበት አያዉቁም።ሙሉ ድጋፍ ይሰጣል የተባለዉ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ አል-ሸባብና አክራሪ ተባበሪዎቹ የሼክ ሼሪፍ መንግሥትን ለማስወገድ መቅዲሾን ሲቀጠቅጡ-ከሩቅ እየተዛበ ነዉ።

ዩናይትድ ስቴትስ፥ተባባሪዎችና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሸባሪ እያሉ ከፖለቲካዉ ሒደት የገፏቸዉ፥ ይበልጥ አክራሪ፥ ይባስ ነዉጠኛ ያደረጓቸዉ የቀድሞዉ ኮሎኔል ሼኽ ዳሒር አዌስ የቀድሞ ባልደረባቸዉን ሼኽ ሸሪፍን ለሥልጣናቸዉ አይደለም ለሕወታቸዉም እየዛቱባቸዉ ነዉ።አረቦች፥ ሐበሾች፥ ደርቪሾች፥ ቱርኮች ሲፈራረቁባት፥ እንግሊዞች፥ ጣሊያኖች እሁለት ሲገምሷት፥ ሕዝብ ሲረግጡ-ሲገዟት ዘመነ-ዘመናት ያስቆጠረችዉ ሐገር በ1960 አንድነቷንም፥ ነፃነቷንም ሥታስከብር ጀርመን፥ ኮሪያ፥ ቬትናም እንዳልሆነች አስመስክራ ነበር።
----------------

በ1960ዎቹ አደን አብዱሌ ኡስማን ዳሬ እና አብዱረሺድ አሊ ሸርማርኬ እንደዲሞክራሲዉ ወግ በሕዝብ ተመርጠዉ ስልጣን ሲይዙባት ከብዙዎቹ የአፍሪቃ፥ የሙስሊም ሐገራት የተሻለች መስላ ነበር።ሶማሊያ።ጄኔራል ዚያድ ባሬ በ1969 በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ሲይዙባት በጎዋ ሁሉ ቀረባት።ከ1990 ወዲሕ እሁለት-እሰወስትም ተገምሳ በእልቂት ፍጅት ካምቦዲያ፥ ሊባኖስ ላይበሪያን ተቀይጣለች።ሌሎቹ በሙሉ ከዉድመት በሚያገግሙበት ዘመን-አሁንም የሚደርስላት-የምትደርስበትም አጥታ-ትተረማመሳለች።ሶማሊያ።የነገን-የሚያቅ የለም።ላሁኑ ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

dw

ነጋሽ መሐመድ

ሂሩት መለሰ