1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ዉጊያና የሰላማዊዉ ሕዝብ ችግር

ሐሙስ፣ ሰኔ 11 2001

የሽግግር መንግሥቱ የአራት ሺሕ ሰወስት መቶዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጦርና የአለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ አልተለየዉም። ግራ-ቀኝ ፈጥርቀዉ በያዙት እስላማዊ ደፈጣ ተዋጊዎች ጨርሶ ከመደፍለቅ ለመዳን የሚያደርገዉ ጥረት-ጥቃት ግን ከመፈራገጥ የተሻለ አይነት አልሆነለነም

https://p.dw.com/p/ISos
ደፈጣ ተዋጊዉምስል AP

18 06 09

በሶማሊያ የሽግግር መንግሥትና በእስላማዊ ደፈጣ ተዋጊዎች መካካል የሚደረገዉ ዉጊያ ተባብሶ እንደቀጠለ ነዉ።ማዕከላዊ ሶማሊያ በለድወይኔ በተባለች ከተማ አጥፍቶ ጠፊዎች ዛሬ ባፈነዱት ቦምብ የሽግግር መንግሥቱ የፀጥታ ሚንስትር ተገደሉ።ርዕሠ-ከተማ መቅዲሾ ዉስጥ ትናንት በደፈጣ ተዋጊዎችና በመንግሥት ወታደሮች መካካል በተደረገ ዉጊያ የከተማይቱን ፖሊስ አዘዥ ተገድለዉ ነበር።ትናንት እና ዛሬ ሌሎች በርካታ ሰዎችም ተገደለዋል።እዚያዉ መቅዲሾ ዉስጥ የሚሰራ የጀርመን የሕፃናት መርጃ ድርጅት ባልደረባ ዛሬ ታግቷል።ነጋሽ መሐመድ የዜና መልዕክቶችን አሰባስቧል።

ለሶማሊያና ለሶማሌዎች ነገሩ-ከድጡ ወደ ማጡ አይነት ነዉ።ርዕሥ-ከተማ መቅዲሾ በርግጥ ግጭት፥ ዉጊያ፥ ግድያ ተለይቷት አያዉቅም።ከትናንት በስቲያ ጀምሮ-እስከ ትናንት ዉድቅ የቀጠለዉ ግን እዚያዉ መቅዲሾ የሚገኘዉ ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ሐጂ አብዲኑር እንደሚለዉ በቅርብ ወራት ከተደረጉት ሁሉ እጅግ ከባዱ ነዉ።

«ትናንትና ከትናንት ወዲያ በርዕሠ-ከተማይቱ ደቡባዊና ሰሜናዊ ክፍል በጣም ከፍተኛ ዉጊያ ሲደረግ ነበር።በዉጊያዉ የአፍሪቃ ሕብረት ሠላም አስከባሪ ወታደሮችም ተካፍለዋል።ምክንያቱም ተልዕኳቸዉ ለደካማዉ የሶማሊያ መንግሥት ድጋፍ መስጠት በመሆኑ በቅርቡ በሚደረጉት ዉጊያዎች በደቡብና ሰሜን (መቅዲሾ) የሚገኙ የአማፂያኑን ጠንካራ ይዞታዎች በከባድ መሳሪያዎች መደብደብ ይካፈላሉ።»

የሽግግር መንግሥቱ የአራት ሺሕ ሰወስት መቶዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጦርና የአለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ አልተለየዉም። ግራ-ቀኝ ፈጥርቀዉ በያዙት እስላማዊ ደፈጣ ተዋጊዎች ጨርሶ ከመደፍለቅ ለመዳን የሚያደርገዉ ጥረት-ጥቃት ግን ከመፈራገጥ የተሻለ አይነት አልሆነለነም።በትናንቱ ዉጊያ የመቅዲሾ ፖሊስ አዛዡን አጥቷል።ኮሎኔል አሊ ሰኤድን።ከኮሎኔሉ ጋር ከሰላሳ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።ከአንድ መቶ በላይ ቆስለዋል።

አብዛኞቹ ቁስለኞች የሚታከሙበት የመዲና ሆስፒታል ዳይሬክተር መሐመድ የሱፍ እንደሚሉት ታካሚዎቻቸዉ በሁሉም የጦር-መሳሪያ አይነት የቆሰሉ ናቸዉ።

«በጠመንጃ ጥይት፥ በሞርታርና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች አረሮች፥በእጅ ቦምብና በመሳሰሉት ፈንጂዎች የቆሰሉ ናቸዉ።መሳሪዎቹ ባለፈዉ አመት፥-አመት ከመንፈቅ ተፋላሚዎቹ የሚያዘወትሯቸዉ ናቸዉ።»

Somalia Präsident Sheik Sharif Achmed
የመንግሥታቸዉ ሕልዉና አጠያያቂ ነዉምስል ap

ቁስለኛዉን ፈጥኖ ሐኪም ቤት የሚያደርሰዉ የለም።የደረሰዉም በቂ ሕክምና አያገኝም።ሌላዉ የመቅዲሾ ነዋሪ ይሰደዳል።ምግብ መጠለያ ግን የለዉም።የአለም ምግብ ድርጅት ቃል አቀባይ ፔተር ስመርደን እንደሚሉት እርዳታዉ ቢገኝ እንኳን ማከፋፈሉ አደጋች ነዉ።

«ባለፈዉ ወር ከ120 ሺሕ በላይ ሰዎች ከከተማይቱ ሸሽተዋል።ባለፉት ጥቂት አመታት ባጠቃላይ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጥ ነዋሪ ከከተይቱ ተሰዷል።ሁኔታዉ ሲበዛ አሳሳቢ ነዉ።በዉጊያ መሐል እርዳታ ማከፋፈል አደጋች ነዉ።በተለይ ጭርቃቸዉን ብቻ አንጠልጥለዉ የሚሸሹ ብዙ ሰዎች ማረፊያ እስኪያገኙ ድረስ መርዳት ከባድ ነዉ።የርዳታ ሠራተኞች ማድረግ የሚችሉት ተፈናቃዮቹ አስተማማኝ መጠለያ አግኝተዉ ሲሰፍሩ የሰፈሩበትን አካባቢ ፈልገዉ መርዳት ነዉ።ይሕ እሲኮሆን ደግሞ ሒደቱ ረጅም ከባድም ነዉ።»

በዚያ ላይ የርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ይገደላሉ-አለያም ይታገታሉ።ዛሬ ርዕሠ-መንበሩን ሙንሽን-ጀርመን ያደረገዉ ኪንደር ዶርፍ የተሰኘዉ የጀርመን የሕፃናት መርጃ ድርጅት የሶማሊያ ቅርንጫፍ ሶማሊያዊ ሐላፊ ታግቷል።ያም ሆኖ ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ሐጂ ዛሬ እንዳለዉ መቅዲሾ ማረፈጃዋን የተረጋጋች መስላለች።

«ዛሬ ጠዋት ሁኔታዉ የተረጋጋ መስሏል።ይሁንና ሁለቱም ወገኖች ግራ-ቀኝ መሽገዉ እንደተፋጠጡ ነዉ።የሆነ-ጊዜ ዉጊያ መጫሩ አይቀርም።በተፋላሚ ሐይላት መካከል የተኩስ አቁም አልተደረገም።»

ዛሬ ተራዉ የበለድወይኔ ሳይሆን አልቀረም።ማርፈጃዉ ላይ የከተማይቱ ትልቅ ሆቴል በአጥፍቶ ጠፊዎች ቦምብ ጋየ።የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ኦመር ሐሺ አደን ተገደሉ።ሌሎች አስራ-ሁለት ሰዎችም እንዲሁ።ኮሎኔል አሊ ትናንት ሲሞቱ የፕሬዝዳት ሽሪፍ አሕመድ መንግሥት ከተመሠረተ ካለፈዉ ሚያዚያ ወዲሕ ከፍተኛዉ ባለሥልጣን ተገደሉ ተብሎ ነበር።ዛሬ ደግሞ እጅግ ከፍተኛዉ ባለሥልጣን «ተገደሉ»-ይባል ይዟል።

dw.ቃ.መ/ነጋሽ መሐመድ/አርያም ተክሌ

►◄