1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ የሽግግር መንግሥትና የአዉሮጳ ሕብረት

ረቡዕ፣ ጥር 16 1999

«እንደ ሽግግር መንግሥት ሉአላዊ መንግሥት ነን።እንዲሕ አይነቱን መግለጫ ጨርሶ አንቀበልም።»

https://p.dw.com/p/E0Yt

የአዉሮጳ ሕብረት ለሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ለሚሰጠዉ ርዳታ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል መባሉን የሽግግር መንግሥቱ አጥብቆ ተቃወመዉ።የአዉሮጳ ሕብረት በፋንታዉ ቅደመ-ሁኔታዉ ለሽግግር መንግሥቱ ተቋማት የሚሰጠዉን ርዳታ ሳይሆን የአፍሪቃ ሕብረት ሠላም አስከባሪ ሠራዊትን የሚመለከት ነዉ ይላል።ነጋሽ መሐመድ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት እና የአዉሮጳ ሕብረትን የልማትና ተራድኦ ኮሚሽን ቃል አቀባዮች አነጋግሮ ነበር።


ባለፈዉ ሰኞ ብራስልስ-ቤልጅግ የተሰየመዉ የአዉሮጳ ሕብረት የሚንስትሮች ምክር ቤት ሥብሰባ ባወጣዉ መግለጫ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ከሌሎች የፖለቲካ ማሕበራት በተለይም በቅርቡ ከተሸነፉት ከሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ሕብረት ለዘብተኛ አባላት ጋር እንዲደራደር ጠይቆ ነበር።ሃያ ሰባቱ የሕብረቱ አባል ሐገራት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች የፈረሙበት መግለጫ እንደሚያትተዉ ሕብረቱ የሶማሊያን ሠላም ለማስከበር ለሚዘምተዉ የአፍሪቃ ሕብረት ሠራዊት ገንዘብ የሚረዳዉ የሽግግር መንግሥቱ ድርድርን ከፈቀደ ነዉ።

የሽግግር መንግሥቱ ቃል አቀባይ አብዱረሕማን መሐመድ ዲናሬ ይሕን የሕብረቱን አቋም እንደ ቅድመ ሁኔታ ነዉ ያዩት።በተለይ የሕብረቱ የልማትና ተራድዖ ኮሚሽነር ሉዊ ሚሼል ሁሉን አቀፍ መንግሥት እንዲመሠረት የሽግግር መንግሥቱ ካልፈቀደ ሶማሊያ ዳግም ከርስ በርስ ጦርነት ትገባለች ማለታቸዉ ቃል-አቀባይ ዲናሬ እንደሚሉት ሶማሊያን የሚያብጥ ነዉ።

«ሉዊ ሚሼል በሰጡት መግለጫ በጣም ነዉ ያዘንነዉ።እንደ መንግሥት እንደምታዉቀዉ ይረዱናል ብለን ነዉ የምንጠብቀዉ።ፀጥታ፣ሕግና ሥርዓት እንድናሰፍን ይደግፉናል ብለን ነዉ የምንጠብቀዉ። እንደ አለመታደል ሆኖ የሉዊ ሚሽል መግለጫ አዲስ ሁከት እና አለመረጋጋትን የሚፈጥርና የሚያበረታታ ነዉ።»

የሚሼል ቃል አቀባይ አሙዱ አልተፋጅ ግን ሕብረታቸዉ እስካሁንም የሽግግር መንግሥቱ ተቋማትን እየረዳ ነዉ ይላሉ።ለነዚሕ ተቋማት የሚሰጠዉን ርዳታ የማቋረጥ እቅድም የለዉም።ይሁንና ለሶማሊያ ሠላም ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ከማስፈር እኩል ድርድር አሥፈላጊ ነዉ ብሎ ሕብረቱ ያምናል። በዚሕም ምክንያት ይላሉ አልተፋጅ ሕብረቱ ለሠላም አስከባሪ ሠራዊት ሊሰጠዉ ያቀደዉን ርዳታ ፖለቲካዊ ድርድር ከመጀመሩ አስፈላጊነት ጋር አቆራኝቶታል።

«የአዉሮጳ ሕብረት ያለዉና በሃያ-ሰባቱ የሕብረቱ አባል ሐገራት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች በሙሉ የፀደቀዉ ለአለም አቀፉ ሠላም አስከባሪ ሐይል ለመስጠት ያቀድነዉ ገንዘብ ሁሉም የሚሳተፍበት የፖለቲካ ዉይይትን ከመጀመር ጋር እንዲያያዝ ነዉ።የሽግግር ተቋማቱ በተለይ የሽግግር መንግሥቱ ፖለቲካዊ ድርድር ለመጀመር ሲፈቅድ ገንዘቡን እንደምንፈቅድ መጠየቃችን ብቻ ነዉ-ባለፈዉ ሰኞ በአዉሮጳ ምክር ቤት ሥብሰባ ማብቂያ የተደረሰበት ማጠቃለያ።»

ይሁንና ቃል አቀባይ አል-ተፋጅ እንዳሉት የሽግግር መንግሥቱ እስካሁን የሚወስዳቸዉ እርምጃዎች ዘላዊ ሠላም ለማስፈን ተስፋ ሰጪ አይደሉም።ተስፋ አስቆራጩ ሁኔታ ከቀጠለ የአዉሮጳ ሕብረት እስካሁን የሚሰጠዉን እርዳታ የሚቀጥልበት ተስፋ አይኖርም-ማለት ይሆን?።አልተፋጅ።

«የለም እዚሕ ነጥብ ላይ አልደረስንም።ዉይይቱ የተደረገዉ በዚሕ መልኩ አልነበረም።ይልቅዬ በተቃራኒዉ እኛ የምናደርገዉ ፌደራላዊዉ የሽግግር መንግሥት ፖለቲካዊዉን ድርድር እንዲከፍት ማበረታታት ነዉ።እኔ እስከማዉቀዉ ድረስ ዩናይትድ ስቴትስም፣ የአረብ ሊግም ተመሳሳይ መልዕክት ነዉ-ያላቸዉ።»

የአዉሮጳ ሕብረት ድርድር ማለቱን ቃል አቀባይ ዲናሬ እንዳሉት የሽግግር መንግሥታቸዉም ይቀበለዋል።መንግሥታቸዉ አሁንም ቢሆን ከጎሳ መሪዎችና ከቀድሞ የጦር አበጋዞች ጋር እየተደራደረ ነዉ።ከዚሕ ባለፍ ግን አሉ ዲናሬ «የአዉሮጳ ሕብረት ይሕን ካላደረጋችሁ-ያን አናደርግም አይነት መመሪያና ትዕዛዝ ሊሰጠን አይችልም።» እንዲሕ አይነቱ የሕብረቱ መግለጫ በዲናሬ እምነት የመንግሥታቸዉን ሉአላዊነት የሚጋፋ ነዉ።
«እንደ ሽግግር መንግሥት ሉአላዊ መንግሥት ነን።እንዲሕ አይነቱን መግለጫ ጨርሶ አንቀበልም።»

በቅርቡ አዲስ አበባ የሚሰየመዉ የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ትልቅ ርዕሥ የሶማሊያ ጉዳይ ይሆናል ተብሎ ነዉ-የሚጠበቅ።የአዉሮጳ ሕብረት የልማት ተራድኦ ኮሚሽነር ሉዊ ሚሼል በዚሁ ጉባኤ ላይ ይገኛሉ።ሚሼል ከሌሎቹ የአፍሪቃ መሪዎች እና ከሶማሊያዉ የሽግግር ፕሬዝዳት አብዱላፊ የሱፍ ጋር ለመወያየት ቀጠሮ አላቸዉ።ዉይይቱ ዉዝግቡን ለማርገብ ይረዳል-ነዉ የሁለቱ ወገኖች ቃል አቀባዮች ተስፋ።