1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማሊያ ጊዚያዊ ሁኔታ

ሐሙስ፣ መጋቢት 1 2008

በሶማልያ መንግሥት አንፃር የሚንቀሳቀሰው ያማፅያኑ ቡድን አሸባብ በተለይ ካለፉት ቀናት ወዲህ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች መጣሉን ቀጥሎዋል ። የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጓድ እና የዩኤስ አሜሪካ ጦር ኃይላት ከሶማልያ ጦር ጋር ባንድነት በመሆን፣ በአሸባብ ሚሊሺያዎች አንፃር ትግላቸውን አጠናክሮዋል።

https://p.dw.com/p/1IAcu
Bildergalerie Somalia Sicherheitslage Französischer Agent wird ermordet 2013
ምስል Mohamed Abdiwahab/AFP/Getty Images

[No title]

በዚሁ ጊዜ ግን ሶማልያ በዚህ ዓመት ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ለማካሄድ እቅድ ይዛለች። የፀጥታ ጠበብት ምርጫውን የሶማልያን ውዝግብ ለማብቃት እንደሚረዳ አንድ የፖለቲካ መፍትሔ ተመልክተውታል።

ወደሶማልያ ሲጓዝ የነበረ ሁለት ሚልዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ የጫነ የዓሳ አስጋሪ ጀልባ ባለፈው ሰኞ ኦማን ባህር ጠረፍ አቅራቢያ በአውስትሬሊያ ባህር ኃይል ተይዞዋል። እርግጥ፣ የጦር መሳሪያው ተቀባይ በግልጽ ባይታወቅም፣ ለአሸባብ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቶዋል። ከዚሁ ርምጃ ሁለት ቀን ቀደም ሲል ባለፈው ቅዳሜም በሶማልያ የሚገኙ የዩኤስ አሜሪካ ጦር ኃይላት ሰው አልባ የጦር አይሮፕላኖች ከመዲናይቱ ሞቃዲሾ 200 ኪሎሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ አንድ የአሸባብ ማሰልጠኛ ጣቢያን አጥቅተዋል፣ አሜሪካውያኑ በዚሁ ጥቃት ከ150 የሚበልጡ ሚሊሺያዎችን እንደገደሉ አስታውቀዋል። ይሁንና፣ የአሸባብ ዋና አዛዥ ሼክ ኢብራሂም አቡ አህመድ የተገደሉባችው ሚሊሺያዎች ጥቂት መሆናቸውን በማመልከት ቁጥሩ የተጋነነ ሲሉ አጣጥለውታል። የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጓድም ማክሰኞ ሌሊትም ሞቃዲሾ አቅራቢያ አንድ የአሸባብን ሰፈር አጥቅተው በርካታ ሚሊሺያዎችን መግደላቸውን ያይን እማኞች ገልጸዋል። ይህን ተከትሎ አሸባብ ትናንት በመዲናይቱ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ በጣለው ጥቃት ቢያንስ ሶስት ፖሊሶች እና ሁለት ሲቭሎችን ገድሎዋል።

ሶማልያ ከአሚሶም እና ከዩኤስ አሜሪካ ፀጥታ ኃይላት ድጋፍ ብታገኝም እስካሁን የአሸባብን ሽብር ማብቃት አልቻለችም፣ በመሆኑም ፣ ይላሉ የሶማልያ መንግሥት አክራሪነት እንዳይስፋፋ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው መንበሩን ለንደን ያደረገው «ቻተም ሀውስ» የተባለው የፖለቲካ ጥናት ተቋም፣ ባልደረባ አህመድ ሶሊማን አስረድተዋል።
« በመጀመሪያ ደረጃ የአፍሪቃ ህብርት ሰላም አስከባሪ ጓድ በሶማልያ ባይሰማራ ኖሮ ሀገሪቱ ከርስበርሱ ጦርነት ባልተላቀቀች ነበር፣ የድህረ ጦርነት መልሶ ግንባታም ባልጀመረች ነበር፣ ማዕከላይ ፌዴራዊ መንግሥትም ባልኖራት እና ለሀገር አመራር የሚያስፈልጉትን ተቋማትም መገንባት ባልቻለች ነበር። »
ይሁንና፣ አሚሶም ምንም እንኳን አንድ ጓድ ቢሆንም፣ የእዙ ሠንሠለት አንድ ወጥ ያልሆነበት ድርጊት ክፍተት እንደፈጠረ «ክራይስስ ግሩፕ» የተባለው ለውዝግቦች መፍትሔ የሚሻው ቡድን የአፍሪቃ ቀንድ ክፍል ባልደረባ ሴድሪክ ባርንስ አስረድተዋል።
« የእዝ ማዕከሉ አሁንም የተከፋፈለ ነው። እና ብዙው የአሚሶም ቡድኖች በአሚሶም ስር ቢሆኑም፣ ትዕዛዝ የሚቀበሉት በጓዱ ከተጠቃለሉት ሀገራት መዲናዎች ነው። የተለያየ ደንበኛ እና ግንኙነት ነው ያላቸው። በተለይ ኬንያ እና ኢትዮጵያ በሀገሪቱ ካሉ ሶማልያውያን ፖለቲከኞች ጋር የተለያየ ግንኙነት ነው ያላቸው። ይህም አንዳንዴ የማስተባበር እና የእቅድ ችግር ይፈጥራል። »
በአሚሶም ስር የተሰማሩት ወታደሮች ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከዩጋንዳ፣ ከቡሩንዲ፣ ጅቡቲ እና ሲየራ ልዮን የተውጣጡ ሲሆን፣ በባርንስ አስተያየት አስፈላጊው ትብብር እና የጋራ የሚሉት ጥቅም ተጓድሎ ይገኛል።
« የአሚሶምን ዘመቻ በተመለከተ የሚታየው አንዱ ትልቁ ችግር፣ ጓዱ እጎአ ከ2012 ዓም ወዲህ ከአሸባብ ብዙ አካባቢ አስለቅቆዋል። ከዚያ በኋላ ግን ባይዶዋን ከመሳሰሉ ጥቂት አካባቢዎች በስተቀር፣ ሌሎቹን በዘላቂነት ለማረጋጋት፣ ማለትም፣ መልሶ ለመገንባትም ሆነ ዘላቂ አስተዳዳራዊ መዋቅር ለመትከል አንዳችም ጥረት አልተደረገም። »
ለዚህም የሶማልያ የወደፊት የፖለቲካ ስርዓት ምን መሆን አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ አሁንም ልዩነቱ ሰፊ መሆኑ፣ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥትም ገና ያልተሟላበት ድርጊት ተጠያቂ ነው። ሀገሪቱ ከ2012 ዓም ወዲህ በጊዚያዊ ሕገ መንግሥት ነው የምትተዳደረው። ይህ ግን ባርንስ እንዳስረዱት፣ ፖለቲካዊው በጎ ፈቃደኝነት ስላለ፣ ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟላል ተብሎ ባይጠበቅም፣ ፕሬዚደንታዊውን ምርጫ በሚቀጥለው ክረምት ከመደረግ አያግደውም። በባርንስ አንፃር የ«ቻተም ሀውስ» ባልደረባ አህመድ ሶሊማን የሶማልያ መንግሥት በሀገሩ ትክክለኛውን የምርጫ ሂደት ለማስከበር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
« እንደሚመስለኝ፣ ጥሩ መሻሻል ተደርጓል። መንግሥት ያወጣውን እቅድ የካቲት መጀመሪያ ላይ እንደተመለከትነው እጎአ እስከ 2020 ድረስ «አንድ ሰው፣ አንድ ድምፅ» የሚሰኘውን መርህ ተግባራዊ ለማድረገ አስቦዋል። »
እስከዚያው ግን የየአካባቢው ተወካዮች፣ የጎሳ ተጠሪዎች እና የፖለቲካ መሪዎች የሁለቱን ምክር ቤቶች እንደራሴዎች እና ተወካዮች ይመርጣሉ፣ እነዚህ ደግሞ የሀገሪቱን ፕሬዚደንት ይመርጣሉ።

Somalia AU Truppen bei der Stadt Merka
ምስል Getty Images/AFP/M. Abdiwahab
Waffenlieferung Somalia Beschlagnahmung Australien Navy
ምስል Reuters/S.Ebsworth/Australian Defence Force

ለቴሬዛ ክሪኒንር/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ