1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማልያ የፀጥታ ኀላፊዎች ሹም -ሽር

ሐሙስ፣ ሐምሌ 3 2006

የሶማልያ ጠ/ሚንስትር አብዲዋሊ ሼክ አህመድ ሙሐመድ፣የብሔራዊ ደኅንነት ድርጅት ሹም የነበሩትን በሺር ጉቤንና የፖሊሱን ኃይል አዛዥ አብዲከሪም ዳሒርን በመሻር በምትካቸው፤ በብሪታንያ የሶማልያ አምባሰደር የነበሩት

https://p.dw.com/p/1CaPQ
ምስል picture-alliance/AP Photo

አብዱላሒ ሳንባሉልሽ ፣ አዲሱ የስለላው ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ ሙሐመድ ሼክ ሐሰን ደግሞ ጥብቅ የፖሊሱ ኃይል ኀላፊ ይሆኑ ዘንድ ሾመዋል።በተጨማሪም አብዲከሪን ሑሴን ጉሌድን በመተካት ፣ ጀኔራል ካሊፍ አህመድ ኤሪግ የፀጥታ ጉዳዮች ሚንስትር እንዲሆኑ አድርገዋል።

የሶማልያን የፀጥታ ይዞታ የመረመሩ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ ሹም-ሽሩን ያስከተለው፤ ከትናንት በስቲያ ኃይለኛ የፈንጂ መንጎድና አማጽያኑ ወደ ቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ዘልቀው በመግባት ፤ በውስጥና ውጭ ተሠማርተው ከነበሩት ወታደሮች ጋር በፈንጂ ውርወራና የጠብመንጃ የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው ነው። የማስታወቂያ ሚንስትሩ ሙስጠፋ ዱሑሑሎው እንዳስታወቁትም፤ የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ከአደጋ ጣዮች መካከል አንደኛውን ሲይዙ ቢያንስ 2 ተገድለዋል። ሹም ሽር በማድረግ 2 አዳዲስ የፀጥታ ጉዳይ ተሿሚዎችን ማሳወቁ ለመቅዲሹና ባጠቃላይ ለሀገሪቱ ፀጥታ የሚያስገኘው ፋይዳ እንዴት ነው የሚገመገመው? የመቅዲሾው የዶይቸ ቬለ ተባባሪ ዘጋቢ ሙሐመድ ዖማር ሁሴን---

« እነዚህ ሰዎች (አሸባቦች) የአገሪቱን ሰፊ ክፍል በቁጥጥር ሥር እንዳደረጉ ናቸው። በመቅዲሹና በቀሪውም የአገሪቱ ክፍል፣ በተከታታይ ጥቃት ያደረሱበት ፤ አደጋ የጣሉበት ሁኔታ አለ። በዚህ በረመዳን ጾም ወቅት፣ ጠ/ሚንስትሩ ለሙስሊሙ ማሕበረሰብ፣ ሰላም እንደሚመኙ መግለጻቸው ቢታወቅም፤ ከአንድ ሌሊት ቀደም ሲል መሣሪያ ያልጫነ ተሽከርካሪ ወደ ሶማልያ ፓርላማ፣ (ቪላ ሶማልያ) ቅጥር ግቢ ዘልቆ እንደገባ ተኩስ ተከፍቶ ነበር። ከ 2 ቀናት በፊትም ተመሳሳይ ድርጊት ነበረ የተፈጸመው። ስለሆነም ጠ/ሚንስትሩ አዲስ የፀጥታ ሚንስትር ለመሾም የተገደዱበት ይህ ምክንያት ስለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ።»

Anschlag in Mogadischu Somalia 09.07.2014
ምስል picture-alliance/dpa

ከፖለቲካ ድርጅት ፤ ከተቋማትና ከመሳሰለው ይልቅ የተዓማኒነት ጉዳይ በአመዛኙ በጎሣ የተመሠረተ መሆኑ በሚነገርላት ሀገር በሶማልያ፤ ጠ/ሚንስትሩ የደህነነትና የፖሊስ ኃይል ሹማንንት ሲሾሙ መለኪያቸው ምንድን ነው?

«መንግሥት፤ በተጠቀሱት 2 ሰዎች ላይ የራሱ የሆነ። ጥርጣሬ አለው። እናም፤ ሌሎችን መርጧል ፤ሾሟል።። ይህ የፀጥታውን ይዞታ እንዳያናጋ ታስቦበት የተከናወነ ጉዳይ ነው። ይህ ነው ሌላ መመዘኛ እንዳላስቀመጡ አስባለሁ። ተስፋ የማደርገው፣ በአዲሶቹ ተሿሚዎች አማካኝነት የፀጥታውን ይዞታ በተለመደ አሠራር መቆጣጠር ይቻላል ብለው ነው የሚያስቡት።»

እርግጥ ነው አሸባሪው አክራሪ ድርጅት፣ አሸባብ፣ ከሚንቀሳቀስባቸው የገጠር አውራጃዎች አልፎ በመዲናይቱ በመቅዲሹ በድፍረት ብርቱ አደጋ የጣለባቸው ሁኔታዎች ነበሩ። በአሁኑ ጊዜም አልተገቱም። አሸባብ ምን ያህል ደካም ነው ጥንካሬውስ? ፕሬዚዳንቱን ፣ የፓርላማውን አፈ-ጉባዔና ጠ/ሚንስትሩን የሚጠብቀው የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይel የመከላከል ፣ የማክሸፍ አቅምስ እስከምን ድረስ ነው?

«አሸባብ ተዳክሞ አይታይም። እርግጥ በሺ የሚቆጠር ሠራዊት አያዘምትም። ግን ወሳኝነት ያለው ርምጃ የው የሚወስዱት። ቀንም፣ ሌትም ነው የማጥቃት ርምጃ የሚወስዱት። ስልታዊ አቀማመጥ ባላቸው ቦታዎች፣ በጠራራ ፀሐይ ርምጃ መውሰድ ይችላሉ። ይህል እንዳልተዳከመ የሚያሳይ ይመስለኛል። የአፍሪቃ ኅብረት፤ ሰላም አስከባሪዎች፤ ከጦር ሠፈራቸው አይወጡም፤ ከሰሞኑ ፣ አሸባብን ለመውጋት ወደ ውጭ ሲወጡ አልታዩም።

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ