1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሪያው አመጽ 1ኛ ዓመት

ዓርብ፣ መጋቢት 7 2004

ከአንድ ዓመት በፊት በዛሬዋ ዕለት ነበረ፤ በሶሪያው ፈላጭ ቆራጭ መሪ ላይ ህዝብ ተቃውሞ ያነሣው። በቱኒሲያ የተቀሰቀሰው የዓረቡ ዓለም ህዝባዊ አመጽ፤ ግብፅንና ሊቢያን አዳርሶ ወደ ሶሪያ ቢሸጋገርም፤ የለውጡ እንቅሥቃሴ፣ ማለቂያ ወዳጣ የአርስ-

https://p.dw.com/p/14LHV
ፕሬዚዳንት በሺር ኧል አሰድና ባለቤታቸው ወ/ሮ አስማምስል picture-alliance/dpa

በርስ ጦርነት የተሸጋገረ ነው የመሰለው።በሺ የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ህይወታቸውን ገብረዋል። የኃይሉ እርምጃ የሚገታበት ምልክትም አይታይም። ኡልሪኽ ላይሆልት ስለዘግናኙ የአንድ ዓመት ብጥብጥ የጻፈውን ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል።

እ ጎ አ መጋቢት 15 ቀን 2011 ፤ ልክ የዛሬ ዓመት መሆኑ ነው፤ ተማሪዎች በአሰድ መንግሥት ላይ ተቃውሞ በማንሣት ደማስቆ ውስጥ አደባባይ ወጡ። የሶሪያው ህዝባዊ አመጽ በአንዲህ ሁኔታ ነበረ የተጀመረው። ፕሬዚዳንት በሺር አሰድ ያኔ እንዲህ የሚል ንግግር አሰሙ።

Syrien Protest
ህዝባዊ ተቃውሞምስል AP

«ታጥቀው፤ ሁከት ከሚያስፋፉ አሸባሪዎች ጋር አንዳች ግልግል አይደረግም፤ ከውጭው ዓለም ጋር አብረው በእኛ ላይ ለተነሱት አንዳች ትእግሥት አይኖረንም።»

ለፕሬዚዳንት አሰድ መንግሥት፣ ተማሪዎችም ናቸው ፤ የነጸነት መፈክሮች ግድግዳ ላይ በመጻፋቸው ፣ አሸባሪዎች እየተባሉ ታፍሰው የታሠሩት። በአሰድ ላይ የተቃውሞውን እሳት ያቀጣጠለው ፣በቁጣ ገንፍለው አደባባይ በመውጣት የተያዙ ልጆቻቸው እንዲለቀቁ የጠየቁ ወላጆች ናቸው።

«በሺር ይሠቀሉ!»

ተቃውሞው እያየለ መጣ ፤ አሰድ ቢንጠለጠልለት አጥብቆ የሚሻው በይበልጥ በገጠር ኑዋሪ የሆነው በድህነት የማቀቀው ህዝብ መሆኑ አልታበለም። ፈላጭ ቆራጩ አገዛዝ አጸፋዊ እርምጃ መወሰድ ጀመረ። በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥይት ማዝነሙን፤ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን እየያዘ ማሠሩንና ቁም ስቅል የሚያሳይ ይግፍ እርምጃ መውሰዱን ተያያዘው። በደማስቆ ኑዋሪ የሆኑት የድርጊቶች ተንታኝ፣ ታቤት ሳሌም እንዲህ ይላሉ።

«ሰዎች የሚያስቡትን በነጻ መናገር ከጀመሩ ፤ እንደሚመስለኝ አሰድ፤ በተለይ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ የብዙኀኑን ድጋፍ አያገኙም። እርግጥ ነው፤ ሳይንሳዊነት ያለው ምርጫና የመሳሰለው መካሄድ ይኖርበታል። አሰድ፤ ግፋ ቢል ከ 30 እስከ 35 ከመቶ ድጋፍ ቢያገኙ ነው።»

ፕሬዚዳንት በሺር ኧል አሰድ እንዲህ ብለውም ነበር።

«የተኀድሶ ለውጥ እርምጃችን ሁለት ገጾች አሉት። በአንድ በኩል የፖለቲካ ለውጥ ማድረግ ሁለተኛም ሽብርን መታገል ነው።»

በአንድ እጅ ዳቦ፣ በሌላው ጅራፍ የመያዝ ያህል ነው የአሰድ አዲሱ አመራር። አገዛዛቸውን እንደ ብረት አጠንክረው የተኀድሶ ለውጥ አራምዳለሁ ነው የሚሉት። ዐሠርተ-ዓመታት ጸንቶ የቆየውን የአስቸኳይ ሁኔታ አዋጅ እንዲሻር ከማድረጋቸውም፤ አዲስ ህገ መንግሥት እንደሚቀርብ ቃል ገብተዋል። ፓርቲዎች እንዲቋቋሙና ምርጫ እንዲካሄድ የሚደረግ ስለመሆኑም ተናግረዋል። የተቃውሞው እንቅሥቃሴ ሥር ከመስደዱ በፊት ቢያደርጉት ኖሮ ተሰሚነት ባገኙ ነበር። ይሁን እንጂ፤ የኃይል እርምጃ ከተወሰደ በኋላ በመሆኑ የህዝቡን ቁጣ ማብረድ አልተቻለም። ይሁንና የሶሪያ ተቃዋሚዎች ሁሉ ተባብረው የቆሙ አይመስሉም። ስለሀገሪቱ ጉዳዮች ጠለቅ ያለ ዕውቀት እንዳላቸው የሚነገርላቸው በቤይሩት የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ ሂላል ካሻን---

Syrien Rebellen mit Waffen
የታጠቁ አማጽያንምስል picture-alliance/dpa

«የሶሪያ የተቃውሞው ወገን በቡድንና በጎሳ የተከፋፈለ ነው። አሰድን የሚቃወሙት ወገኖች በማዘጋጃ ቤቶችና በምክር ቤቶች የተወከሉት ሁሉም አንድ ዓይነት አቋም የላቸውም። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የተከፋፈለ ነው። ምዕራባውያን አገሮች፤ የሚያሳዩት አቋም ሞቅም ቀዝቀዝም ያለ አይደለም። በሶሪያ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን አይፈቅዱትም፤ ይህ ከዐረብ አገሮች በኩል ቢሠነዘር እንደሚመረጥ ነው የሚገልጹት። ሩሲያና ቻይና የሶሪያ ወዳጆች ነን ብለው ከዓለም ተነጥለው ከአሰድ ጎን ቆመዋል። ዐረቦችም ቢሆኑ አንድ ዓይነት አቋም የላቸውም። አንዳንዶች አሰድ ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል ባዮች ናቸው። አልጀሪያና ሊባኖስ ደግሞ በግልጽ ከአሰድ ጎን ነው የቆሙት። ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው የማያውቁም አሉ። የአሰድ ጥንካሬ፤ የተቃዋሚዎቻቸው መከፋፈልና የህዝቡ በተለያየ የፖለቲካ አቋም መተራመስ ነው።»

ይህም በመሆኑ ፤ የደማስቆ መንግሥት የዴሞክራሲ ጥያቄ ባነሱት ላይ ሁሉ የኃይል እርምጃ መውሰዱን እንደቀጠለ ነው። በተለይ ሆምስ የተባለችው እንቅሥቃሴው የተጀመረባት ከተማ ህዝብ በተደጋጋሚ የጸጥታ አስከባሪዎች ዒላማ መሆኗ አልቀረም።

አንድ የሆምስ ከተማ ኑዋሪ የሆነ የዓይን ምሥክር እንዲህ ማለቱ ይታወሳል።

«ለኛ የቆመ ማንም እንደሌለ ነው የሚሰማን። ለእኛ የሚቆረቆር የለም። የተባበሩት መንግሥታት፣ አሰድ በሮኬት ሲደበድበን ዝም ብሎ ነው የሚመለከተው። በሩሲያ T-72 ታንክ እንደበደባለን። ስለሆነም ራሳችንን በተቻለን አቅም ሁሉ እንከላከላለን። ከማዕድ ቤት ቢላዋ እየወሰድን በዚሁ ራሳችንን እንከላከላለን። ይህ ደግሞ መብታችን ነው። »

Proteste in Homs
የድረሱልን ጥሪ ከሆምስ ከተማምስል Reuters

በሶሪያ በአንድ ዓመት የህዝብ አመጽ፤ 6 ሺ 7 ሺ ወይም 8ሺ ያህል ሰዎች ሳይገደሉ አልቀሩም፤ ፕሬዚዳንት አሰድ ግን፣ይህን ነበረ ያሉት።

«ህዝብችንን አንገድልም። በዓለም ውስጥ የራሱን ህዝብ የሚገድል አንድም አይገኝም። እንዲህ ዓይነቱን ተግባር የሚፈጽሙ ዕብዶች ብቻ ናቸው።»

ይህን አባባል የማይቀበለው ህዝብ ፣ በሰላማዊ መንገድ መፍትኄ ይገኛል ብሎ ለማመን ሳይቸገር አልቀረም። የሶሪያ ጉዳዮች ተመራማሪ ሻዲ ሐሚድ---

«እንደሚመስለኝ ሶሪያውያን በሰላማዊ መንገድ ለውጥ የሚገኝበት ዕድል እንደተሰናከለ ነው የሚሰማቸው። ለዚህም ነው ራሳቸውን በግልጽ እስከማስታጠቅ የደረሱት። በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት፣ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ተግባራዊ መሆን፤ ከሶሪያ መከላከያ ኃይል ወጥተው ነጻ የሶሪያ ጦር ኃይል ለሚመሰርቱት እጅግ በጣም ጥሩ ማስታወቂያ ነው የሆነላቸው።»

Kofi Annan in Damascus in Syrien
ሸምጋዩ ዲፕሎማት ኮፊ አናንምስል picture-alliance/dpa

ለሶሪያ ታዲያ ምንድን ነው የሚበጃት፤? ስለ አማራጩና ብቸኛው መፍትኄ፣ የዐረቡ ዓለም ህዝባዊ አመጽ የተጀመረባት ሀገር ፤ የቱኒሲያ ጠ/ሚንስትር፣ ሞንሴፍ ማርዙኪ እንዲህ ይላሉ።

«በፖለቲካው መስክ፤ ችግሩ፣ በፈላጭ ቆራጩ አገዛዝ ላይ ተጨማሪ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም። ነገር ግን ፤ አሰድና ቤተሰባቸው ቅጣት ሳያገኛቸው አገር ለቀው እንዲወጡ ቃል መግባቱ ይበጃል። መላው፤ የየመኑን ዓይነት መፍትኄው መፈለግ ብቻ ነው።»

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ