1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሪያ ተቃዋሚዎችና ድጋፉ፣

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 3 2005

ከ 130 አገሮችና ድርጅቶች የተውጣጡ ልዑካን ፣ 60 ያህል ሚንስትሮች ጭምር በዛሬው ዕለት ማራኬሽ ፤ ሞሮኮ ውስጥ በመሰብሰብ ፣ 21 ወር ስለሆነው የሶሪያው ውዝግብ በማንሳት በመምከር ላይ መሆቸውና ፤ ፈላጭ -ቆራጩን መሪ ፣ በሺር ኧል አሰድን

https://p.dw.com/p/170ah
ምስል picture-alliance/dpa

ከሥልጣን ለማስወገድ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኘው የተቃውሞው ወገን የሚደገፍበትን መላ በመሻት ላይ መሆናቸው ተነገረ።  በሞሮኮ፤ የሶሪያ ወዳጆች የተሰኘው ጉባዔ የተከፈተው፤ ዩናይትድ እስቴትስ፣ ለሶሪያ  ዋና የተቃውሞ ጉድኝት ዕውቅና በሰጠች ማግሥት ነው።

Assad / Syrien / Plakat
ምስል AP

ብሪታንያ ፤ ፈረንሳይ፤ ቱርክና የዐረብ ባህረሰላጤ አዋሳኝ አገሮች፣ የሶሪያ አብዮታዊና የተቃውሞ ኃይሎች ብሔራዊ ጥምረት ለተሰኘውን ቡድን  ቀደም አድርገው ነው ዕውቅና የሰጡት። በተባበረ ኃይል ፣ በአሰድ አገዛዝ ላይ  ለመነሣሣት ይኸው በሙዓዝ ኧል ከቲብ የሚመራው ጥምረት የተቋቋመው፣ ባለፈው ወር ነው። በማራኬሹ ጉባዔ፤ ብሔራዊ ም/ቤት ፣ የተሰኘው  የሶሪያ የተቃውሞው ወገን ኀላፊ ጂዎርጅ ሳብራ እንዳሉት፤በስደተኞች መበራከት  ሳቢያ ፣ ሰብአዊው ይዞታ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል።

የፈረንሳይ፤ የብሪታንያና የካናዳ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በማራኬሹ ጉባዔ የተገኙ ሲሆን፤ የዩናይትድ እስቴትስ ባልደረባቸው ወ/ሮ ሂልሪ ሮድሃም ክሊንተን በጤና እክል ሳቢያ አለመሳተፋቸው ተመልክቷል።  ከአውሮፓው ኅብረት ቀጥሎ ፣ ዩናይትድ እስቴትስ  የሶሪያ የተቃውሞ ወገን ጥምረት፤ ህጋዊው የሶሪያ ህዝብ ተወካይ ነው በማለት ትናንት ዕውቅና ሰጥታዋለች። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣--

«የሶሪያ የተቃውሞው ወገን ጥምረት፤ አሁን ፤ ሁሉንም ያጠቃለለ ፣ የሶሪያን ህዝብ የሚወክል በመሆኑ፣ የአሰድን  አገዛዝ በመቃወም በሚያደርገው ትግል  ህጋዊ  የህዝቡ ተወካይ ነው ብለን ለመቀበል ወስነናል።»

Syrien Free Syrian Army Rebellen Jubel 22.11.2012
ምስል Reuters

የአሳድ መንግሥት ዋና ተጓዳኝ ሆና የቆየችው ሩሲያ፣ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የዩናይትድ እስቴትስ እርምጃ አገራቸውን ያስገረማት መሆኑን ከመግለጻቸውም፣ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ፤ «አሜሪካ ፣ አሁን የሶሪያው ብሔራዊ ጥምረት፣ በጦር ኃይል  ድል እንዲቀዳጅ ለማብቃት ቆርጣ ተነስታለች» ብለዋል።

የሶሪያ ወዳጆች የተሰኘው ስብስብ፣ ባወጣው የጋራ መግለጫ፣ ፕሬዚዳንት በሺር ኧል አሰድ፣ ሥልጣን እንዲለቁ ከማሳሰቡም፤ መንግሥታቸው ዓለም አቀፍ ህግጋትን በመጣስ ከቅጣት አያመልጥም ሲል አስገንዝቧል። አሰድ ህጋዊ ሥልጣን ያጡ መሪ በመሆናቸው ዘላቂነት ያለው የፖለቲካ ሽግግር እንዲደረግ ገለል ቢሉ ይበጃልም ብሏል።የሶሪያ መንግሥት በጅምላ ጨራሽ መርዘኛ የቅመማ ጦር መሣሪያ ቢጠቀም ብርቱ ዓለም አቀፍ እርምጃ እንደሚጠብቀውም ነው የተነገረው።

የሶሪያ የተቃውሞ ወገን እንዲተባበር በተደረገበት ግፊት፤ ባለፈው ኅዳር ወር መግቢያ ገደማ ፣ ዶሃ፣ ቐጠር ላይ ብሔራዊ ጥምረት የተሰኘው  ጉድኝት መመሥረቱ  የሚታወስ ነው። ይሁንና ራሳቸውን ጂሃዲስቶች እያሉ የሚጠሩት፤ በሰሜናዊው ሶሪያ፣  በአሌፖ ከመንግሥት ወታደሮች ጋር የሚፋለሙት ኃይሎች፤ በሶሪያ ወደፊት እስላማዊ መንግሥት የመመሥረት እቅድ እንዳላቸው ነው ያስታወቁት። ከጂሃዲስቶቹ መካከል፤ጀብሃት  ኧል ኑሥራ የተሰኘው ግንባር  ይገኝበታል። ዩናይትድ እስቴትስ የተጠቀሰው ግንባር ፣ ኢራቅ ውስጥ ከኧል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው አሸባሪ ቡድን ነው  ባይ ናት።

Damaskus Syrien 30.11.2012
ምስል Reuters

የብሔራዊው ጥምረት መሪ ሙዓዝ ኧልካቲብ ግን ፣ በአሁኑ ወቅት የማንኛውም አማጺ ጠብመንጃ፤ በፈለጭ -ቆራጩና ወንጀለኛው አገዛዝ ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ፣ ዩናይትድ እስቴትስ ፣ ጀብሃት ኧል ኑሥራን  በአሸባሪነት የፈረጀበትን ውሳኔ እንደገና ትመረምረው ዘንድ ጠይቀዋል። የሶሪያው የሙስሊም ወንድማማች ማኅበር በበኩሉ፤ በሶሪያ ፤  አሸባሪው፣   በሺር ኧል አሰድ ብቻ ናቸው ብሏል።

21 ወር  በሆነው የሶሪያው የእርስ-በርስ ጦርነት፣ ከ 42 ሺ በላይ ህዝብ መሞቱን፤ ወደ አጎራባች ሃገራት የተሰደዱት ሶሪያውያን አኀዝም ከግማሽ ሚሊዮን መብለጡን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ተመልካች ቡድን አስታውቋል። የሶሪያ የተቃውሞው ጉድኝት፤ ይበልጥ ታዋቂነት እያገኘ ቢሄድም፤ አንዳንድ የአውሮፓው ኅብረት ሚንስትሮች፣ ቡድኑ የቱን ያህል የሶሪያን ህዝብ እንደሚወክልና ለዴሞክራሲም በመቆም ረገድ ያለውን አቋም  በጥርጣሬ ዓይን ሆኗል የሚመለከቱት።

በሶሪያ  ውጊያውም ስደቱም እንደቀጠለ ሲሆን፤ በሰሜናዊው የአገሪቱ ከፊል፤ በሃማ አውራጃ፤ አቕራብ በተሰኘ የአላውያን መንደር  125 ሰዎች ሳይገደሉ አልቀሩም ሲል የሶሪያ የሰብአዊ መብት ተይዞ ተከከታታይ ድርጅት ጠቁሞአል። የአካባቢው የተቃውሞ ቡድኖች በበኩላቸው 200 ያህል ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ነው የተናገሩት።  አያይዘውም፤ ጥቃት የፈጸሙት የአሰድ ጦር ሠራዊት አባላት ናቸው ይላሉ። ወታደሮቹ፤ አላውያኑን እንደ ጋሻ ሳይጠቀሙባቸው እንዳልቀሩ ጠቁመዋል። አሳድ፣  የአላውያን ወገን መሆናቸው የታወቀ ነው።

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ