1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሪያ የቱርክ ግጭት መቀጠሉ

ቅዳሜ፣ መስከረም 26 2005

ከአራት ቀናት በፊት በሶርያ እና ቱርክ ድንበር ላይ የጀመረዉ ግጭት አይሎ መቀጠሉ ተነገረ። ሶርያ እንደገና አዲስ ጥቃት በመሰንዘሯ የቱርክ ወታደራዊ ሃይል አጸፋዊ ርምጃ መዉሰዱን የቱርክ የብዙሃን መገናኛ አስታዉቆአል።

https://p.dw.com/p/16LkM
ምስል AFP/Getty Images

ከአራት ቀናት በፊት በሶርያ እና ቱርክ ድንበር ላይ የጀመረዉ ግጭት አይሎ መቀጠሉ ተነገረ። ሶርያ እንደገና አዲስ ጥቃት በመሰንዘሯ የቱርክ ወታደራዊ ሃይል አጸፋዊ ርምጃ መዉሰዱን የቱርክ የብዙሃን መገናኛ አስታዉቆአል። በጥቃቱ ከሁለቱም ወገን ሟች፤ አልያም ቁስለኛ መኖር አለመኖሩ ግን አልተገለጸም። በያዝነዉ ሳምንት ረቡዕ ከሶርያ በተተኮሰ የሞርታር ጥቃት የቱርክ አምስት ዜጎቿ በመገደላቸዉ፤ የምላሽ ጥቃት መሰንዘሯ ይታወሳል። የአንካራ ምክር ቤትም ድንበር ዘሎ ለሚደርስ ጥቃት ሁሉ ወታደራዊ ምላሽ እንዲሰጥ ዉሳኔ አስተላልፏል። የቱርክ ጠቅላይ ሚኒስቴር ረቺብ ጣይብ ኤርዶጋን ሶርያ የአገራቸዉን ድንበር ዘላ ጥቃት እንዳትሰነዝር አስጠንቅቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርዶጋን ከሶርያ ጋር ጦርነት መግጠም አንፈልግም፤ ደህንነታችንን የሚያናጋ ጥቃት ሲደርስ ግን እንከላከላለን ሲሉ ተናግረዋል። የጀርመንዋ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በሶርያ እና በቱርክ መካከል የተፈጠረዉን ዉጥረት እጅግ አሳሳቢ ብለዉታል። ቱርክ እና የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት «ኔቶ » በጋራ ችግሩ የሚፈታበትን ሁኔታ እንደሚያገኙ ተስፋ እንዳላቸዉም ተናግረዋል። ሜርክል የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት በሶርያ መንግስት ላይ ማዕቀብ እንዳይጥል ቻይና እና ሩስያ ድምፅን በድምፅ በመሻር መብታቸዉ በመጠቀም እሁንም ማዕቀቡን ማገድ መቀጠላቸዉን ነቅፈዋል።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዪ ለገሰ