1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሪያ ጊዚያዊ ሁኔታ

ረቡዕ፣ ጥር 30 2004
https://p.dw.com/p/13xMr
ምስል dapd

የሩሲያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌይ ላቭሮቭ ከሶርያዉ ፕሬዝደንት ባሽር አልአሰድ ጋ ለመነጋገር ደማስቆ ገቡ። የላቭሮቭ የጉብኝት ዓላማ ፕሬዝደንቱ ስልጣን እንዲለቁ ለማግባባት ነዉ የሚል ጭምጭምታ ቢኖርም፤ አሰድ ግን በአገራቸዉ ህገመንግስት ላይ ህዝበ ዉሳኔ ሊጠሩ መዘጋጀታቸዉን አመልክተዋል። ከፕሬዝደንቱ ጋ ባደረጉት ንግግርም እያንዳንዱ የአገር መሪ ያለበትን ኃላፊነት ይገነዘባል ማለታቸዉ ተጠቅሷል። ላቭሮቭ አገራቸዉ የሶርያን አገዛዝ በሚመለከት ለያዘችዉ አቋምም በአሰድ ደጋፊዎች የሞቀ አቀባበል እንደተቸራቸዉ ተዘግቧል። እንዲያም ሆኖ ዛሬም የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተቃዉሞ ባየለባት ሆምስ ከተማ ህዝብ በርከት ብሎ ይኖርባቸዋል የተባሉ አካባቢዎችን በተኩስ መደብደናቸዉ ተነግሯል። በጥቃቱ ቢያንስ የ50 ሰዎች ህይወት ማለፉን፤ በርካቶችም መጎዳታቸዉን፤ የህክምና ርዳታም ማግኘት አለመቻሉንም ነዉ አንድ የከተማዋ ኗሪ የሚያስረዱት፤
«በርካታ ሰዎች ጎዳና ላይ ወድቀዋል፤ ከባድ መሳሪያ ተኩሱ በየቦታዉ ቀጥሏል፤ የህክምና ርዳታዉ አዳጋች ነዉ፤ የተጎዱትን በየቤቱ ለማከምና ህይወት ለማትረፍ እየጣርን ነዉ፤ ሁኔታዉ ግን አስቸጋሪ እኛንም ጥይት እንዳይመታን እንሰጋለን። ከተማዋ ተነጥላለች ማንም መግባትም ሆነ መዉጣት አይችልም፤ ምን እንደምናደርግ አናዉቅም።»
ይህ በእንዲህ እንዳለም ፈረንሳይ ዲፕሎማቷን በጥቂት ቀናት ዉስጥ ከሶርያ ለማዉጣት መወሰኗን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዛሬ አመለከቱ። በርናርድ ቫሌሮ አገራቸዉ ከብሪታንያ ጋ በመነጋገርም በራሱ ህዝብ ላይ የኃይል ተግባሩን በቀጠለዉ የደማስቆ አገዛዝ ላይ ማዕቀብ ለማጥበቅ መዘጋጀቷንም ገልጸዋል። ፓሪስ ይህን ዉሳኔ ከማሳለፏ አስቀድሞ ጣሊያን፤ ብሪታንያ፤ እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስ ልዑካኖቻቸዉን ከሶርያ ማንሳታቸዉ ተዘግቧል።

ሸዋዬ ለገሰ

ነጋሽ መሀመድ