1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሪያ ጥፋትና የዲፕሎማሲዉ ምስቅልቅል

ሰኞ፣ ግንቦት 26 2005

ኒዮርክ ታይምስ የተሰኘዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጋዜጣ ባለፈዉ መጋቢት አዋቂዎችን ጠቅሶ እንደዘገበዉ በዩናይትድ ስቴትስ የስለላ ድርጅት ሲ አይ ኤ ድጋፍ፥ በሳዑዲ አረቢያና በቀጠር ገንዘብ እየተሸመተ በቱርክ በኩል ለሶሪያ አማፂያን የታደለዉ ጦር መሳሪያ ከሰወስት ሺሕ አምስት መቶ ቶን ይበልጣል

https://p.dw.com/p/18j8r
Forces loyal to Syria's President Bashar al-Assad walk while carrying their weapons during what they said was an operation to occupy Dahra Abd Rabbo village in Aleppo, May 26, 2013. REUTERS/George Ourfalian (SYRIA - Tags: CONFLICT)
ጥፋቱምስል Reuters
Former leader of the Syrian National Coalition (SNC) Moaz Alkhatib speaks during a meeting in Istanbul May 23, 2013. The meeting by members of the Syrian opposition was held to decide whether to attend the U.S.- and Russian-backed conference in Geneva aimed at ending the Syrian conflict. Alkhatib urged President Bashar al-Assad on Thursday to hand power to his deputy or his prime minister and then go abroad with 500 members of his entourage, without immunity from prosecution. REUTERS/Bulent Kilic/Pool (TURKEY - Tags: POLITICS CIVIL UNREST CONFLICT)
የተቃዋሚዎቹ መሪዎች አንዱ-ሞዓዝ አል ኻጢብምስል Reuters

የሶሪያ ፖለቲከኞች፥ መንግሥት፥ የሐገር ዉስጥ ወይም ሰላማዊ ተቃዋሚዎች፥ የዉጪ ወይም ስደተኛ ተቃዋሚ አለያም ሸማቂዎች እያሉ እብዙ ቦታ ተክፈለዉ እንደ ፖለቲከኛ እየተወዛገቡ እንደ ጠላት ይጋደላሉ። ሕዝብ፥ ሐገራቸዉን ያጠፋሉ።የዓረብ ቱጃር ነገሥታት ከቤኒዝን የሚዝቁትን ገንዘብ እንደ ቢንዝናቸዉ ሶሪያዎችን በሚያጠፋዉ እሳት ላይ ይረጫሉ።የእስራኤል ጄቶች፥ የኢራን ጠመንጃዎች፥ የሒዝቡላሕ ሚሊሺያዎች እሳቱን ያጋግማሉ።የዓለም ሐያል ሐብታም መንግሥታት የየሚደግፏቸዉን ሐያላት-እየረዱ፥ ደግሞ በተቃራኒዉ ድርድር ይላሉ።የእልቂት፥ ጥፋት ግመቱ ደረጃ፥ የተቃራኒዉ አቋም እንዴትነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።

ዛሬም እንደ አምና ሐቻምናዉ ሐይማኖተኛዉ ይፀልያል።

«ዉድ ወንድሞቼና እሕቶቼ፥ ሶሪያን ከሁለት ዓመታት በላይ የሚያጋየዉ ግጭት፥ በተለይም በሠላም ለመኖር በሚሻዉ ፍትሕና ርትዕት እንዲሰፍን በሚመኘዉ ሠላማዊ ሕዝብ ላይ የሚደርሰዉ ጉዳት ያሳደረብኝን ሕመም እና ሥጋት ሁሌም እንደተሸከምኩ ነዉ።ይሕ አጥፊ ጦርነት አሳዛኝ ድቀት አስከትሏል።ሞት፥ዉድመት፥ ከፍተኛ ምጣኔ ሐብታዊና አካባቢያዊ ጥፋት እና ሰዎችን የማገት ዘመቻን አድርሷል።ይሕን ከግምት በማስገባት ታጋቾችንና ቤተ-ሰቦችቸዉን በፀሎቴ እንደማረሳቸዉ ላረጋግጥ እወዳለሁ።(በመፈንስም) ከጎናቸዉ እንደቆምኩ ነዉ።አጋቶችም ታጋቾቻቸዉን እንዲለቁ አቤቱታዬን አቀርባለሁ።ለምንወዳት ሶሪያ እንፀልይ።»

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስካ።ትናንት።ሠብአዊ ርዳታ አቀባዮችም ግጭት ጦርነቱ ሲጀመር የጀመሩትን ተማፅዕኖ-አቤቱታ አሁንም እንደቀጠሉ ነዉ።ሆም፥ ሐማ፥ ኢድሊብ፥ ዳራዕ፥ አሌፖ፥ እና ሌሎችም ሲጋዩ ለየከተማዉ ሕዝብ ርዳታ እንዲደርስ አቤት ተብሎላቸዋል ነበር።ትናንት ተረኛዋ አል-ቁሳይር ናት።የምዕራባዊ ሶሪያ ከተማ።አቤት ባዩ-የዓለም ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ኮሚቴ።

«የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICC) የቁሳይሪዉ (ጦርነት) በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሰዉ ጉዳት በጣም አሳስቦታል።የምግብ፥ የዉሐ፥ የመድሐኒት እና የሌሎች ሸቀጦች እጥረት መከሰቱን ዘገቦች ይጠቁማሉ።በርካታ የቆሰሉ ሰዎች የሕክምና እርዳታ አያገኙም።አስቸኳይ ሕክምና ያስፈልጋቸዋል። ይሁንና ተደጋጋሚ ጥሪ ብናደርም አይ ሲ ሲ ቁሳይሪ ለመግባት እስካሁን አልተፈቀደለትም።»

የኮሚቴዉ ቃል-አቀባይ።

የሶሪያ ተፋላሚ ወገኖችን እንዲያደራድሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአሪብ ሊግ የካቲት-ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የወከላቸዉ የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን የሠላም ዕቅድ ነድፈዉ ነበር።

አናን ባለሥስድስት ነጥብ ዕቅድቸዉ ስድስት ወር ሳይሞላዉ መሞቱን ለሰላም ወዳዶች ሲያረዱ ወይም ለጦርነቱ ናፋቂዎች ሲያበስሩ ሁሉንም ብለዉት ነበር።

«ከልብ የመነጨ፥ ዓላማ ያለዉና የአካባቢዉን ሐይላት ጨምሮ የተባበረ ዓለም አቀፍ ግፊት በሌለበት የሶሪያ መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚዎቹ የፖለቲካዊ መፍትሔ ሒደትን እንዲጀምሩ ማሳማን ለኔም ሆነ ለማንም ሌላ ሰዉ አይቻልም።በዚሕም ምክንያት የሐላፊነት ዘመኔ ነሐሴ ማብቂያ ሲያበቃ ተልዕኮዬን መቀጠል እንደማልችል ለተመድ እና ለዓረብ ሊግ ዋና ፀሐፊዎች ዛሬ አሳዉቄያቸዋለሁ።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከኒዮርክ፣አረብ ሊግ ከካይሮ፥ ዲፕሎማት ቢሔድ ዲፕሎማት ይተካል አይነት ከማለት ባለፍ የተከሩት አልነበረም።አናን ሔዱ።ላሕዳር ብራሒሚ ተተኩ።ብራሒሚ ከኒዮርክ-ካይሮ፥ ከዶሐ-ደማስቆ፥ከቤይሩት-ቴሕራን መመላለሳቸዉ፥ አናን ያሉትን በየመገናኛ ዘዴዉ መድገማቸዉ ሐቅ ነዉ።የሠሩት ቀርቶ የሞከሩት ሳይታወቅ፥ የሚታወቀዉ የከርዕሥ-ከተማ፥ ርዕሠ ከተማ ጉዞ፥ የቴሌቪዥን መግለጫቸዉም በማይታወቅ ምክንያት ከቆመ፥ የማይታወቁ ወራት አለፉ።

ጥቅምን ለማስከበር፥ ክብርን ለማስጠበቅ፥ የገዘብ ሐይልን፥ የጦር ሐይል ጡንቻን ለማሳየት የሚጣደፍ እንጂ የአናንን ምክር ማስጠንቀቂያ የሠማ፥ ሠላም ለማስፈን ከልቡ የተጨነቀ የተባበረ-ዓለም እስካሁን የለም።አናን የአካባቢዉ ሐይላት ካሏቸዉ ሐገራት ትንሺቱ ቀጠር ናት።የፖለቲካ አዋቂዎች እንደገመቱት የዶሐ-ነገስታት የሶሪያ ሸማቂዎችን ለማስታጠቅ እና የመንግሥት ወታደሮችን ለማስኮብለል በትንሽ ግምት ሰወስት ቢሊዮን ዶላር ዘርታለች።የሪያድ ነገስታት ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ በትነዋል።

ኒዮርክ ታይምስ የተሰኘዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጋዜጣ ባለፈዉ መጋቢት አዋቂዎችን ጠቅሶ እንደዘገበዉ በዩናይትድ ስቴትስ የስለላ ድርጅት ሲ አይ ኤ ድጋፍ፥ በሳዑዲ አረቢያና በቀጠር ገንዘብ እየተሸመተ በቱርክ በኩል ለሶሪያ አማፂያን የታደለዉ ጦር መሳሪያ ከሰወስት ሺሕ አምስት መቶ ቶን ይበልጣል።ኢራን ባንፃሩ ብዛት መጠኑ በዉል አይጠቀስ እንጂ ለደማስቆ መንግሥት የጦርና የሥለላ መሳሪያ ታቀብላለች።

አናን የማይቻል ተልዕኳቸዉ እንደማይቻል ሲያስታዉቁ የአካባቢዉ ሐገራት ጣልቃ ገብነት ከገንዘብ፥ ከጦር መሳሪያ፥ ከመረጃና ዲፕሎማሲ ያለፈ አልነበረም።ከነሐሴ-እስካሁን በተቆጠሩት አስር ወራት ዉስጥ ግን የእስራኤል የጦር ጄቶች ካንዴም ሁለቴ ሶሪያን ደብድበዋል።የፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ ዛቻ፥ ፉከራም «አሸባሪ» ከሚሏቸዉ ሶሪያዊ ጠላቶቻቸዉ ተሻግሮ- በእስራኤልም ላይ አነጣጥሯል።

«እስራኤል ሌላ ጥቃት ከፈፀመችብን እንድንበቀል ላሳሰቡን ለዉጪና ለአረብ ወገኖች በሙሉ ካንድ በላይ ብቀላ መኖሩን አሳዉቀናል።እስራኤል ብቀላችንን ለመቀልበስ ሞክራነበር ግን በቀጥታ ተበቅለናል። እስራኤልን መበቀል ሥንፈልግ ጊዚያዊ ብቀላ ዋጋ የለዉም።ብቀላችን ሥልታዊ መሆን አለበት።»

የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቡላሕ በይፋ ከጦርነቱ መግባቱ አሳድ እንዳሉት የብቀላዉ አንዱ ገፅታ ሊሆን ይችላል።ለሊባኖስ፥ ለሶሪያ፥ ምናልባትም የሶሪያን ጦርነት ከሩቅ ለሚቆሰቁስት ሐይላት የሚኖረዉ ፋይዳ ግን በርግጥ ግልፅ አይደለም።ሶሪያን የሚያጋየዉ ጦርነት ሊባኖስን መለብለብ መጀመሩ ግን ሐቅ ነዉ።ቤይሩት።ሳምንት ዕሁድ

«ማለዳ አስራ-ሁለት ሠዓት ከአርባ ላይ በመኪና ማቆሚያዉ አካባቢ ፍንዳታ ሠማን።ከጥቂት ደቂቃዎች በሕዋላ ሌላ ሥፍራ ሌላ ሮኬት አረፈ።ሁለተኛዉ ሰወስት ሰዉ አቁስሏል።ጥፋትም አድርሷል።»

ይላሉ-የአይን ምሥክሩ።የሒዝቡላሕ ደጋፊዎች የሚኖሩበትን አካባቢ ለመምታት ያለመዉና የሶሪያ ደፈጣ ተዋጊዎች የተኮሱት የመጀመሪያዉ ሮኬት ሁለት ሰዉ ገድሏል።ባለፈዉ አርብም ሔርሜል የተባለች ከተማም በከባድ መሳሪያ ተደብድባለች። የሶሪያዉ ጦርነት አካባቢዉን እንዳያዳርስ ያላስጠነቀቀ ዲፕሎማት፥ የፖለቲካ አዋቂ አልነበረም።ሐያላን መንግሥታት ጦርነቱን በሠላማዊ መንገድ እንዲያቆሙ ያልተማፀነም ጥቂት ነዉ።

«እኛ (እርምጃ) በምንፈልግበት፥ የሶሪያ ሕዝብ ፈጣን እርምጃ እንዲወሰድ አጥብቆ በሚመኝበት ወቅት በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት መወቃቀሱና መተቻቸቱ እንደቀጠለ ነዉ።»

ብለዉ ነበር፥-የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ-አምና ነሐሴ።

ሞስኮ፥ ቤጂንጎች ከደማስቆ ገዢዎች ጎን፥ ዋሽግተንና የምዕራብ አዉሮጳ ተባባሪዎቻቸዉ ከሶሪያ ተቃዋሚዎች ጎን ቆመዉ መወቃቀስ፥ መወጋገዝ፥ መሻኮታቸዉ ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።የየሚደግፉትን ሐይል ማስታጠቅ፥ መርዳታቸዉም ቀጥሏል።የሚያልቀዉ ሶሪያዊ ቁጥርም በትንሽ ግምት መቶ ሺሕ ደርሷል።ዘግናኙ ጦርነት ሰዉ በቁሙ እየተተለተለበት፥አስከሬኑ እንደ ቅርጫ ሥጋ እየተመተረበትም ነዉ።አስር ሺዎች ቆስለዋል።ሚሊኖች ተሰደዋል።

እልቂት ፍጅቱን ለማስቆም መፍትሔዉን የማያዉቅ፥ የማይናገረዉም የለም።

«በጋራ እንደሚታመነዉ የሶሪያዉ ጦርነት ከቀጠለ ሶሪያንም ሆነ አካባቢዉን የሚያወድም መዘዝ ያስከትላል።ይሕን አሉታዊ ገፅታ መለወጥ የሚቻለዉ የጠመንጃዉ ዉጊያ ሲቆም ብቻ ነዉ።ይሕ ፖለቲካዉ መፍትሔንም ይጨምራል።»

የሩሲያዉ ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቲን።ግንቦት አጋማሽ።ትናንት ሶሪያ ዉስጥ ብቻ የነበረዉ ዉጊያ ዛሬ የእስራልን ጡንቻ ገብዟል።ሊባኖስን መጎነጫጨፍ ጀምሯል።አሳድን ለማስወገድ ወይም ተቃዋሚዎቻቸዉን በማጥፋት ሠላም ለማስፈን የዋሽግተንና የሞስኮ መንግሥታትና ተከታዮቻቸዉ እስካሁን የወሰዱት እርምጃ፥ ፈጣንም ይባል ቀርፋ የተከረዉ የለም።የዋሽግተንና የሞስኮ መሪዎች ተፋላሚ ወገኖችን ወደ ማደራደሩ ፊታቸዉን መመለሳቸዉ አዲስ ተስፋ መጫሩ አልቀረም።ግራ ቀኝ የቆሙትን የዓለም መንግሥታት ድጋፍ ያገኘዉን የድርድር ሐሳብ የሶሪያ መንግሥት፥ ተቃዋሚዎቹም ተቀብለዉታል።


ከሐምሳ የሚበልጡ ተቃዋሚዎችን የሚወክለዉ ሐይል ማንነት ግን እስካሁን በዉል አልታወቀም። የድርድሩን ቀንም-የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊሙን እንኳን አያዉቁትም። የድርድሩ ዕለት፥ ይዘትና ሒደቱ፥ የተሳታፊዎቹ ማንነት በሚያነጋግርበት መሐል እኒያዉ ድርድር እንዲደረግ መስማማታቸዉን ያስታወቁት ሐያላን እንደገና ይወቃቀሱ እንዲያዉም በቃላት ይበቃቀሉ ገቡ።የሜሪካዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ።

«የሶሪያ ሥርዓት ከሩሲያም ሆነ ከሌላ ከማንኛቸዉም ወገን የጦር መሳሪያ ማግኘቱ ለእኛ አሳሳቢ ጉዳይ ነዉ።ለዚሕም ነዉ እኛ እና ተባባሪዎቻችን ተቃዋሚዎቹን ለመርዳት አበክረን የምንጥረዉ።»

ከአሜሪካ ተባባሪዎች መሐል በተለይ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ከመጪዉ ነሐሴ ጀምሮ ተቃዋሚዎቹን በግልፅ ለማስታጠቅ ተዘጋጅተዋል።ለዚሕ እንዲመቻቸዉ የአዉሮጳ ሕብረት በሶሪያ ተፋላሚዎች ላይ ጥሎት የነበረዉ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ቀነ-ገደብ እንዳይራዘም ባለፈዉ ሳምንት አስወስነዋል።የሩሲያ ምክትል ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ለመልስ ምት አልሰነፉም።

«ዉሳኔዉ የአዉሮጳ ወዳጆቻችን የሚከተሉትን ተቃራኒ መርሕ በግልፅ የሚያሳይ ነዉ።ባንድ በኩል ወደ ሶሪያ የጦር መሳሪያ የሚጎርፍበትን መንገድ እየተከተልክ፥ በሌላ በኩል ደም መፋሰሱን አስቆማለሁ ልትል አትችልም።»

ግን ተችሏል።ለዲፕሎማሲዉ ወግ፥ የሕዝብን ዋይታ፥ የመብት ተማጋቾችን፥ የፍትሕ ጠያቂዎችን ጫጫታ ለማስተንፈስ-በቃል ድርድር እየተባለ፥ ጥቅምን ለማስከበር ታማኝ ጠቃሚን ማስታጠቁ በገቢር ቀጥሏል።እልቂት፥ስደት፥ ዉድመት ጥፋቱም።እንዲሁ።ለዛሬ ይብቃን።

ARCHIV - Der syrische Staatspräsident Baschar al-Assad (Archivfoto vom 12.02.2013) befürchtet eine militärische Intervention des Westens in seinem Land. «Die Vorwürfe gegen Syrien bezüglich Chemiewaffen und die Forderungen nach meinem Rücktritt ändern sich jeden Tag», sagte Al-Assad in einem am 18.05.2013 veröffentlichten Interview der staatlichen argentinischen Nachrichtenagentur Télam. EPA/SANA / HANDOUT EDITORIAL USE ONLY/NO SALES dpa +++(c) dpa - Bildfunk+++
ፕሬዝዳንት አሰድምስል picture alliance/dpa
A Free Syrian Army fighter takes position by pointing an artillery weapon towards the sky in Idlib, May 18, 2013. Picture taken May 18, 2013. REUTERS/Abdalghne Karoof (SYRIA - Tags: POLITICS CIVIL UNREST CONFLICT) // eingestellt se
አማፂያኑምስል Reuters
Forces loyal to Syria's President Bashar al-Assad are seen on a tank during what they said was an operation to occupy Dahra Abd Rabbo village in Aleppo, May 26, 2013. REUTERS/George Ourfalian (SYRIA - Tags: CONFLICT)
የመንግሥት ጦርምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ














ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ