1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሪያ ጦርነትና የጣልቃ ገብነቱ ንረት

ሰኞ፣ ሐምሌ 23 2004

ሶሪያዊዉ እንደ ቱኒዚያና እንደ ግብፃዊዉ፥ አደባባይ የወጣዉ የአሰድ አገዛዝ እንደ ቤን ዓሊና እንደ ሙባረክ ብጤዎቹ በሠላማዊ ሕዝባዊ ግፊት እንዲወገድ ፈልጎ-እንጂ እንደሊቢያ በዉጪ ጣልቃ ገብ ሐይል፥ የቦምብ-ጥይት ማብረጃ መሆኑን ፈልጎ ሊሆን አይችልም

https://p.dw.com/p/15glG
Demonstranten verbrennen ein Plakat ihres Präsidenten Baschar al-Assad vor der Syrischen Botschaft in Nicosia. Auch in Syrien war der Karfreitag blutig. (Foto: dapd)
አሰድ-ሲያልቅምስል dapd


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ኮፊ አናን፥በሶሪያ ጉዳይ መግባባት ያልፈለጉት መንግሥታት የጋራ አቋም እንዲይዙ ይማፀናሉ።የዋሽግተን-ብራስልስ፣ የሞስኮ-ቤጂንግ ሐያላን ግን ይወቃቀሳሉ።ሪያድ፣ዶሐ፣ አንካራዎች አማፂያኑን ያስታጥቃሉ፣ ያደራጃሉ ያለመፀዉን ያሳምፃሉም ።አማን-ባግዳዶች በስደተኛ ሲተራመሱ ቤይሩቶች በወላፈኑ ይጠበሳሉ።የሶሪያ ጦርነት ግመትን ከአስተጋብኦቱ እንዴትነት፣የሐያላኑን ሽኩቻ ንረትን፣ ከጣልቃገብነቱ ስፋት ጋር እያጣቀስን ላፍታ እንቃኛለን አብራችሁኝ ቆዩ።

የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን የሶሪያ ተፋላሚዎችን እንዲሸመግሉ ባለፈዉ የካቲት ከተወከሉበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ጊዜ ብለዉት ነበር።በቀደም ደገሙት።

«ዳግም ከተባበርን፥ ምክር ቤቱ (የፀታዉ) ባንድ ድምፅ ከተናገረ፥ ያ አንድ ድምፅ ከተከፋፈለዉ ይበልጥ በጣም ጠንካራ ነዉ።»

አንጋፋዉ ዲፕሎማት የጋራ አቋም እንዲይዙ በተደጋጋሚ የሚጠይቋቸዉ የምዕራብ-ምሥራቅ ሐያላን አናንን ራሳቸዉን ለሸምጋይነት ለመምረጥ፣ የአናን የሠላም ዕቅድ ለማፅደቅ፣ ታዛቢ ሐይል ለማዝመት በጋራ መቆም-መወሰናቸዉ እርግጥ ነዉ።

የሶሪያ ሕዝብ ሠላማዊ አመፅ ወደ ነፍጥ ዉጊያ ከተቀየረበት ካለፈዉ ዓመት ግንቦት ጀምሮ የሶሪያዎች መጨቆን፣ መገደል፣ መቁሰል፣ መሠደድ፣ የሶሪያ ዉድመት ድቀት ብዙ እንደሚያሳስባቸዉ ከቋንቋ፣-መዝጊያ አንቀፅ ልዩነት ባለፍ እኩል ያልተናገሩበት፣ የሶሪያዎችን ችግር ለማስወገድ ከሶሪያዎች የሚቀድም እንደ ሌለ ያላስታወቁበት ጊዜ የለም።

ሐያላኑ ለሶሪያ ቀዉስ ሁነኛ ሠላማዊ መፍትሔ ለመፈለግ ግን እንደተራራቁ ነዉ።ታዛቢዎች እንደሚሉት-ሐያላኑ የመቃረናቸዉ ሥፋት፥ በጋራ የወሰኑት፥ተመሳሳይ ነገር ያሉና የሚሉት-ለየጥቅማቸዉ ስኬት ጊዜ ለመግዛት አልመዉ፥ የዲፕሎማሲ የበላይነትን አቅደዉ መሆኑን መስካሪ ነዉ።

የሶሪያ ተቀናቃኞች ይገዳደሉ።ሕዝብ ይፈጃሉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ እስካለፈዉ ሳምንት ድረስ ብቻ አስራ-ስምንት ሺሕ ሰላማዊ ሰዉ ተገድሏል።የቆሰለዉን ቤቱ ይቁጥረዉ።በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ቤት-ንብረት ሐገሩን ጥሎ ተሰዷል።

የዓለም ዘዋሪዎች ግን ገና ይወነጃጀላሉ።


«የእርምጃቸዉ ዉጤት (የሩሲያና የቻይና) አረመኔዉን ሥርዓት መደገፍ ነዉ።ከሚሊዮን ሶሪያዉያን ሕይወት ይልቅ ጥቅማቸዉን ማስቀደሙን መርጠዋል።»

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የብሪታንያዉ አምባሳደር ልያል ግራንት።ከሳምንት በፊት።የሩሲያዉ አምባሳደር የቪታሊ ቹርኪን የመልስ ምት ጠንካራ ነበር።

«የመልከዓ-ምድር ፖለቲካዊ ጥቅም ታላቅ ፍልሚያ ሶሪያ ምድር እየተካሔደ ነዉ።ይሕ ከሶሪያ ሕዝብ ፍላጎት ጋር ምንም ግንኙነት የለዉም።»

የመልከዓ-ምድር፥ ፖለቲካዊ ጥቅም።ሞስኮ ቤጂንጎች የባግዳድና የትሪፖሊ የጦር መሳሪና የሌሎች ሸቀጦች ሸማች-ሺያጭ ደንበኞቻቸዉን በተከታታይ አጥተዋል።ሰወስተኛዉን፥ደማስቆን በቀላሉ ማጣት አይሹም።በተለይ ሩሲያ ደማስቆን አጣች ማለት በመካከለኛዉ ምሥራቅ ያላትን ብቸኛ የጦር ሠፈር ለምዕራቦች አስረከበች ማለት ነዉ።

ቱርኮች ወደ የኋላ ታሪክን ካገላበጡ በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት ከብሪታንያና ከፈረንሳይ ጋር ያበሩት ሶሪያዎች ያደረሱባቸዉን ሽንፈት መበቀል ይመኙ ይሆናል።እዚያም በይደርሱ እንኳ ለቱርክ ኩርዶች ድጋፍ የሚሰጠዉን የደመስቆ ሥርዓት ለማስወገድ ከዚሕ «የተሻለ አጋጣሚ የለም» ይሉ ይሆናል።

የሳዑዲ አረቢያ፥ የቀጠረና የአማን ነገስታት ዙፋናቸዉ አጠገብ የደረሰዉን ሕዝባዊ አመፅ ደማስቆ ዉጊያ መቅበር ይሻሉ።የአሜሪካኖችን ፍላጎት ማስፈፀምም አለባቸዉ።አሜሪካኖች እስራኤልን የሚያሰጋዉ፥ የሊባኖስን ፖለቲካ የሚጫነዉ፥ ከኢራን ጋር የሚተባበረዉን የደማስቆ ሥርዓትን ለማስወገድ መዛት መፎከር የጀመሩት ባግዳድን በተቆጣጠሩ ማግሥት ነበር።

ያም ሆኖ የአሰድን መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅጣት ለማንበርከክ ምዕራባዉያን ለሰወስተኛ ጊዜ ያደረጉት ሙከራ በሩሲያና በቻይና ተቃዉሞ በቀደም ከሸፈ።የምዕራቡ ጎራ መሪና አስተባባሪ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ግን ባለፉት አስራ-አራት ወራት በተደጋጋሚ ያሉትን ባለፈዉ ማክሰኞ ደገሙት።

«የሶሪያ ሕዝብ ከአሰድ ሥርዓት ነፃ ወጥቶ-የተሻለ እንዲኖር ለማድረግ ዛሬም ጭምር እየሠራን ነዉ።»

በአሰድ መንግሥት ላይ የተነሳዉ ተቃዉሞ ሕዝባዊና ሠላማዊ በነበረበት ባለፈዉ ዓመት መጋቢት በየአደባባዩ እንደታየዉ የዚያን ሥርዓት መወገድ አብዛሐዉ ሶሪያዊ እንደሚደግፈዉ መገመት አይገድም።

ይሁንና ሶሪያዊዉ እንደ ቱኒዚያና እንደ ግብፃዊዉ፥ አደባባይ የወጣዉ የአሰድ አገዛዝ እንደ ቤን ዓሊና እንደ ሙባረክ ብጤዎቹ በሠላማዊ ሕዝባዊ ግፊት ወይም በትንሽ መስዋዕትነት እንዲወገድ ፈልጎ-እንጂ እንደሊቢያ በዉጪ ጣልቃ ገብ ሐይል፥ የቦምብ-ጥይት ማብረጃ መሆኑን ፈልጎ ሊሆን አይችልም።ጦርነት መግጠም የፈለገ ታጥቆ ጫካ-ይገባል እንጂ ባዶ እጁን ባደባባይ አይሰለፍም።

ሶሪያ አሁን ጦርነት ላይ ናት።ፕሬዝዳንት ኦባማ እንዳሉት ልዕለ ሐያል ሐገራቸዉ የአሳድን ሥርዓት ለማስወገድ እየሰራች ከሆነ ብዙዎች እንደጠረጠሩት፥ የሩሲያዉ አምባሳደር በግልፅ እንዳሉት ዋሽግተን የጦርነቱ ተካፋይ ናት ማለት ይሆን?።

ሆነም አልሆነ፥ ከፕሬዝዳት ኦባማ እስከ አምባሳደር ራይስ ያሉ የዋሽግተን ባለሥልጣናት ላለፉት አስራ-አራት ወራት ያሉትን፥ ጦርነቱ አሌፖን ሲያነድ በቀደም የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ቪክቶሪያ ነላንድ ባጭሩ ደገሙት።ሐሙስ።

«አሌፖ ላይ ጨፍጨፋ እናያለን።ሥርዓቱ የሚደረጃዉ ለዚሕ ሳይሆን አይቀርም።ይሕ ያሰጋል።»

የአሜሪካኖች የአትላንቲክ ወዲሕ ማዶ ወዳጆች እንደ ብዙዉ የዓለም ጉዳዮች ሁሉ በሶሪያም ቀዉስ ከዋሽግተኖች የተለየ አቋም የላቸዉም።ከጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን እስከ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል፣ ከፕሬዝዳት ኒካላ ሳርኮዚ፣ ሳርኮዚን እስከተኩት ፍራንሷ ኦሎንድ የነበሩና ያሉት የአዉሮጳ መሪዎች ባለፉት አስራ-አምስት ወራት ያሉና የሚሉትን የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ ባለፈዉ አርብ ደገሙት።

«በሌላ በኩል ከሶሪያ የሚወጡ ዜናዎች እንደሚጠቁሙት የአሠድ ሥርዓት ተፃራሪዎቹን ከአየር ጨምሮ በከባድ መሳሪያዎች መደብደቡ በጣም አሳሳቢ ነዉ።በዚሕም ምክንያት ቻይና እና ሩሲያ የአሳድን ሥርዓት የሚደግፍ እጃቸዉን እንዲሰበስቡ እጠይቃለሁ።»

የሶሪያ የሕዝብ እልቂት ቬስተር ቬለ እንዳሉት በርግጥ ማንንም ሰብአዊ ፍጥር ያሳዝናል።ያሰጋልም። ጦርነት ግን የሁለት ወይም የከዚያ በላይ ወገኖች ፍልሚያ ነዉ።በዚሕ ፍልሚያ የሚያልቀዉን ሕዝብ ለማዳን አብነቱ ጦርነቱን ማቆም ወይም ማስቆም ነዉ።የአሜሪካና የአዉሮጳ መሪዎች አምባገነናዊ አገዝን እንቃወማለት የማለታቸዉ ሰናይ፥ ሕዝብ የሚፈጀዉ ጦርነት ባስቸኳይ እንዲቆም ተፋላሚ ወገኖችን እኩል ካለመጠየቃቸዉ እኩይ ጋር የመላተሙ ሐቅ-ነዉ ግራ አጋቢዉ።

ከምራቦቹ በተቃራኒ ጎራ የታደሙት የሞስኮ-ቤጂንግ ሐያላን እንደ ምዕራብ አንጣዎቻቸዉ ሁሉ ሰዉ መገደል፣ መቁሰል መሰደዱ፣ሐብት ንብረት መጥፋት መዉደሙ እንደሚያሳዝናቸዉ ያልገለጡበት ጊዜ የለም።ለሶሪያ ቀዉስ ዘላቂዉ መፍትሔ የሶሪያዎች ብቻ ነዉ እንዳሉም ነዉ።

«ማንም ለሌላዉ ሕዝብ የመወሰን፥ ማን ሥልጣን መያዝ እንዳለበት እና ማን ሥልጣኑን መልቀቅ እንዳለበት የፍረድ መብት የለዉም።ሁለተኛ አስፈላጊዉ ነገር የሥልጣን ሽግግርን በቀላሉ ማሟላት አይቻልም።እንዲሕ አይነቱን ሁኔታ ለማሳካት በሐገሪቱ ሠላም ማስፈንና ደም መፋሰሱን ማቆም አስፈላጊ ነዉ።ይሕ ሁኔታ ደግሞ በሕገ-መንግሥታዊዉ መንገድ ከግብ መድረስ አለበት።»

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን።የዚያኑ ያክል ዋሽግተኖች ለእልቂት ጥፋቱ የደማስቆ ገዢዎችን ብቻ ነጥለዉ ተጠያቂ ከማድረጋቸዉ እኩል ሞስኮ-ቤጂንጎች የሶሪያ አማፂያንንና ምዕራቦቹን ጨምሮ የአማፂያኑን ደጋፊዎች መወንጀል መክሰሳቸዉ ነዉ-የተቃርኖዉ ርቀት።

ከፕሬዝዳንት ሜድቬዴቭ እስከ ፕሬዝዳንት ፑቲን፣ እስከ አምባሳደር ቹርኪን፥ ከፕሬዝዳንት ሁ ጂንታኦ እስከ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ያንግ ጂቺ በተደጋጋሚ ያሉትን የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ባለፈዉ ቅዳሜ ደገሙት።ላቭሮቭ ከጃፓኑ አቻቸዉ ጋር ሆነዉ በሰጡት መግለጫ፥-


«እንዳለመታደል ሆኖ የምዕራብ ሸሪኮቻችንና ትንሽ የተለየ ነገር ማድረግ ነዉ የሚፈልጉት።ከአንዳድ የሶሪያ አጎራባች ሐገራት ጋር ሆነዉ በሶሪያ ሥርዓት ላይ የተከፈተዉን የትጥቅ ዉጊያ ያበረታታሉ፥ ይደግፋሉ፥ ይመራሉም----የዚሕ ሁሉ ዋጋ ተጨማሪ ደም ነዉ» ነበር ያሉት የሩሲያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር።

አምና መጋቢትና ሚዚያ በሰላማዊ ሕዝባዊ ትግል ሰላማዊ ለዉጥ ለማምጣት አልሞ አደባባይ ወጥቶ ከነበረዉ ሕዝብ የሞተ፣የቆሰለ፣ የተሰደደዉን ሕዝብ ብዛት በትክክል የቆጠረዉ የለም።የንፁሐን ደም ግን ላቭሮቭ እንዳሉት አሁንም ይንዠቀዠቃል።

በሐያላኑ ሽኩቻ፣ ለተፋሚዎች በሚሰጡት ድጋፍ፣ የሳዑዲ አረቢያና የቃጣር ነገስታት ከየሕዝባቸዉ ቀምተዉ በሚያፈሱት ገንዘብ፣ በቱርክ ማን አለብኝነት የሚዘወረዉ ጦርነትና ሽብር ሆምስን፣ ኢድሊብን፣ ዴር-አዞ ዞርን አዉድሞ የጥንታዊቷን ሐገር ትልቅ ከተማ አሌፖን እያንቀረቀባት፥ ታሪካዎቷን ርዕሠ ከተማ ደማስቆን እያነደዳት ነዉ።

ቅዳሜ። ቅዳሜዉኑ የቱርኩ ጠቅላይ ሚንስትር ሬሴፕ ተይብ ኤርዶኻን የአሰድ ሥርዓት ለማስወገድ ሥለሚወሰደዉ ተጨሪ እርምጃ ከብሪታንያዉ አቻቸዉ ከዴቪድ ካሜሩን ጋር ለንደን ዉስጥ መክረዉ ነበር።ቅዳሜዉኑ የትሪፖሊ-ሊባኖስ ነዋሪዎች በሶሪያዉ ዉጊያ ሰበብ ተጋጭተዉ ስምንት ሰዉ ተገደለ።

በማግሥቱ እሁድ ቴሕራን ዉስጥ ከኢራኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጋር የተወያዩት የሶሪያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ወሊድ ሙዓሊም በዉጪ ሐይላት ይደገፋሉ ያሏቸዉ አማፂያን ይደመሰሳሉ አሉ።

ደማስቆ-ሐሙስ፣-«ወደዚሕ እንድን መጣ የጋበዙን ነዋሪዎቹ ናቸዉ፥ሐገሪቱን ከአሸባሪዎችና ከታጣቂ ሽፍታዎች ነፃ እንድናወጣ።»
የመንግሥት ወታደር።ደማስቆ።
ከሃያ-አራት ዓመታቸዉ ጀምረዉ በዲፕሎማሲዉ ጎርምሰዉ፣ በዲፕሎማሲዉ ጎልምሰዉ፣ በዲፕሎማሲዉ ተክነዉ ግዙፍን ድርጅት ለሥምንት አመታት የመሩት ኮፊ አናን የሶሪያን ጦርነት ሰበብ-ምክንያት፥ አስተጋብኦቱን እስከየትነት መገመት፥ የጣልቃ ገቦቹን አላማ ፍላጎት አያዉቁትም ማለት ጅልነት ነዉ።ግን ያዉ በጋራ እንቁም እንዳሉ የሠላም ዕቅዳቸዉ ብልጭ ብሎ ድርግም አለ።ቀጥሎስ? ነጋሽ መሐመድ ሲሆን ለመስማት ያብቃን።

In this image from amateur video made available by the Ugarit News group on Tuesday Nov. 15, 2011 shows a a burning Syrian tank in Daraa, Syria on Monday Nov. 14, 2011. (Foto:Ugarit vai APTN/AP/dapd) TV OUT THE ASSOCIATED PRESS CANNOT INDEPENDENTLY VERIFY THE CONTENT, DATE, LOCATION OR AUTHENTICITY OF THIS MATERIAL. TV OUT
የዉጊያዉ ዉጤትምስል dapd
Syrien01: Mädchen in Syrischen Flüchtlingslager Autor: Marine Olivesi Ort: Boynuyogun Flüchtlingslager Datum: 06/02/2012 ### Unser Autor hat uns die Bilder geschickt und uns die Erlaubnis gegeben die zu publizieren in Zusammenhang mit ihrer Geschichte über ein Flüchtlingslager an der Syrien/Türkei Grenze. ###
አምና ቤት ነበራቸዉምስል Marine Olivesi
A Free Syrian Army soldier walks next to a burned tractor in Sarmin, north of Syria, Tuesday, Feb. 28, 2012. According to the residents of the city at least fourteen people were killed yesterday during clashes between the Free Syrian Army and President Assad's forces. (Foto:Rodrigo Abd/AP/dapd) Die Freie Syrische Armee (arabisch ‏الجيش السوري الحر‎ al-Dschaisch as-Suri al-Hurr, französisch Armée syrienne libre, Kürzel ASL) ist die größte bewaffnete Oppositionsgruppe in Syrien.[2] Sie ist mit dem Syrischen Nationalrat verbunden.[
አምና ትራክተር-ሕንጻ ነበርምስል AP
Members of the Free Syrian Army hold their rifles as they stand in al-Bayada,Homs, February 29, 2012. Syrian troops launched a ground attack in Homs on Wednesday in an apparent attempt to overrun the rebel-held Baba Amro neighborhood that has endured 25 days of siege and fierce bombardment, opposition sources said. REUTERS/Stringer (SYRIA - Tags: POLITICS CIVIL UNREST) Die Freie Syrische Armee (arabisch ‏الجيش السوري الحر‎ al-Dschaisch as-Suri al-Hurr, französisch Armée syrienne libre, Kürzel ASL) ist die größte bewaffnete Oppositionsgruppe in Syrien.[2] Sie ist mit dem Syrischen Nationalrat verbunden.[
አማፅያኑምስል Reuters

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ






ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ