1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶሪያ ጦርነት፥ ዲፕሎማሲዉና የዓለም እዉነታ

ሰኞ፣ መስከረም 7 2005

ካለፈዉ ሐሙስ ጀምሮ ከቤንጋዚ እስከ ካቡል፥ ከካይሮ እስከ ካራቺ፥ ከካርቱም እስከ ሲድኒ ከቱኒስ እስከ ሞንባሳ እንዳየን እንደሰማነዉ ግን ዓለም ሠላሙን ለማናጋት ማስጠንቀቂያ፥ ፀሎት ምሕላ አላገደዉም...የሰላም መቻቻል ምክር ፀሎት ስብከት የሚያስፈልገዉ በርግጥ ማን ነዉ?

https://p.dw.com/p/16AcB
++++ Alternativer Ausschnitt +++ epa03398423 A handout photo made available by Syria's Arab News Agency SANA shows Syrian President Bashar Assad (C-R) meeting with the U.N.-Arab League envoy, Lakhdar Brahimi (C-L), in Damascus, Syria on 15 September 2012 for talks that focused on the 18-month-old crisis in the country. Brahimi_s meeting with Assad is the first since he has replaced the former UN Secretary General Kofi Annan. Brahimi, who is on a three-day visit to Syria, held a series of meetings in Damascus with Syrian officials and opposition leaders in order to shape a clear perspective for his future initiative to end the crisis. EPA/SANA / HANDOUT HANDOUT EDITORIAL USE ONLY/NO SALES +++(c) dpa - Bildfunk+++
ብራሒሚና አሰድምስል picture-alliance/dpa


17 09 12


ለሶሪያ ጦርነት ሠላማዊ መፍትሔ ፍለጋ ላሕዳር ብራሒሚ ወደ ደማስቆ፣ ሐሰን አብድል አዚም ወደ ቤጂግ ሲያቀኑ፣የግብፅና የአዉሮጳ ሕብረት መሪዎች፣የደማስቆ ገዢዎችን የማስወገድ ዛቻ-ዉግዘታቸዉን ከብራስልስ ዳግም ያንቆረቁሩት ገቡ።አሌፖም ትጋያለች።ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት አሥራ-ሥድስተኛ በመካከለኛዉ ምሥራቅ ሠላም፣ መቻቻል እንዲፀና ቤይሩት ላይ ሲሰብኩ-ሲፀልዩ፣ የገሚስ ዓለም አደባባዮች አሜሪካ ሠራሹ ፊልም ሐይማኖቱን፣ ባንቋሸሸበት ሙስሊም ቁጣ ይንተከተኩ ነበር።የሩቅ-የቅርቡ ታዛቢ የሠላም ተልኮዉን እንዴትነት፥የፀሎት ስብከቱን ለማንነት እንዳጠያየቀ ዛሬ ሰኞ ባተ።ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ለቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታትና ለአረብ ሊግ ልዩ መልዕክተኛ ለኮፊ አናን የዓለም ሐያላንን፥ አረብ-ፋርስን ያነካካዉን የሶሪያን ጦርነት በሠላማዊ ድርድር የማስወገዱ ተልዕኮ የማይቻል ነበር (Mission Impossible) በሳቸዉ ቋንቋ።

«ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፥ የካባቢዉን ሐይላት ጨምሮ፥ ጠንካራ፥ በቅጡ የታሰበበትና ከልብ የመነጨ ግፊት እስካላደረጉ ድረስ፥ የሶሪያን መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚዎቹ የፖለቲካዊ መፍትሔ ሒደትን እንዲጀምሩ ማሳመን፥ ለኔም ሆነ ለማንኛዉም ሰዉ አይቻልም።»

አናን «የማይቻለዉ» የሚቻል መስሏቸዉ በሚጥሩበት ወራት እንኳን ከሞስኮ-ቤጂንግ፥ ከቴሕራን፥ ካራካስ ለደማስቆ ገዢዎች፥ ባንፃሩ ደግሞ ከሪያድ፥ ትሪፖሊ፥ ከዶሐ-አንካራ፥ ከዋሽግተን-ብራስልስ፥ ለሶሪያ አማፂያን የሚሰጠዉ ድጋፍ አላባራም ነበር።

አናን ወራት ያስቆጠረ ተልዕኳቸዉ የ«ማይቻል»ነቱን አረጋግጠዉ የልዩ መልዕክተኝነት ሥልጣናቸዉን በፍቃዳቸዉ መልቀቃቸዉን ባወጁ በሳምቱ-የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት መንግሥታቸዉ ለሶሪያ አማፂያን ይሰጥ ከነበረዉ «ገዳይ ያልሆነ» ከሚሉት መሳሪያ በተጨማሪ የመረጃና የማደራጀት ድጋፍ ለመስጠት ወሰኑ።b#b

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እስካለፈዉ ነሐሴ ድረስ ለሶሪያ አማፂያን የሠጠዉ የጦር ሜዳ መነፅር፥ የመገናኛ፥ የዉጊያ ልዩ ባትሪና መሰል ቁሳቁሶች ሃያ አምስት ሚሊዮን ዶላር ወጥቶበታል።

የሪያድ፣ የዶሐ፣ የትሪፖሊ ገዢዎች ከየሕዝባቸዉ እየቀሙ በሚያንቆረቁሩት ገንዘብ የተገዛዉ ጠመጃ ሞልቶ የተረፋቸዉ፥ ሐብት የተንበሻበሹት፥ የቱርኮች ወታደራዊ ሥልት-ሥልጠና፥ የአሜሪካኖች «ገዳይ ያልሆነ» ትጥቅም ሆነ የአካባቢዉና የምዕራቡ ዓለም ፖለቲካዊ ድጋፍ የሶሪያን አማፂያን ለደማስቆ ቤተ-መንግሥት አላበቃም።

ሐቻምና በቀድሞዉ የሊቢያ ገዢ በኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ላይ እንደተደረገዉ ሁሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉሳኔ የአሰድን ሥርዓት ሲሆን በማቀብ አዳክሞ፣ካልሆነም በጦር ሐይል አጥፍቶ የደማስቆን ቤተ-መንግሥት ለአማፂያኑ ለማስረከብ ካንዴም፣ ሁለቴ የተደረገዉ ሙከራም በሩሲያና በቻይኖች እንቢተኝነት ከሽፏል።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የሐያሊቱ ሐገር ሐያል የስለላ ድርጅት CIA ለሶሪያ አማፂያን የመረጃ ድጋፍ እንዲሰጥ የወሰኑት አናን በድርድር «የማይቻል» ያሉትን፥ ሞስኮና ቤጂንጎች ያከሸፉትን፥ አማፂያኑ ያልሆነላቸዉን ተልዕኮ በሐይል እንደሚቻል ለማሳየት ነበር።እስካሁን ግን በርጥ አልተሳካም።

አንጋፋዉ ዲፕሎማት የተልዕኳቸዉ ተስፋ ነጥፎ-ከመድረቁ በፊት አስጠንቀዉ ነበር።

«ሁኔታዎች ካልተለወጡ፥ የሚከተለዉ ጭካኔ የተመላበት እመቃ፥ጭፍጨፋ፥የሐይማኖታዊ ሐራጥቃ ዉጊያ፥ ምናልባትም የርስ በርስ ጦርነት ሊሆን ይችላል።»

አናን በርግጥ በብራሒሚ ተለዉጠዋል።በአናን ሽምግልና ሰበብ ሶሪያ የዘመተዉ ሠላም አስከባሪ ተልዕኮ እንደ አናን ተልዕኮ ሁሉ የማይቻልነቱ ተረጋግጦ ተሰርዟል።የሶሪያዉ ጦርነትም አናን ይደርሳል ብለዉ ወደ አስጠነቀቁት ደረጃ ቀስበቀስ እያዘገመ ነዉ።የአሳድ መንግሥት ግን አልተለወጠም።

አናንን የተኩት አልጄሪያዊ ዲፕሎማት ላሕዳር ብራሒሚ ተልዕኳቸዉን እንደ ቀዳሚያቸዉ የማይቻል ባይሉትም ከባድነቱን ገና ከጅምሩ አልሸሸጉም ነበር።

«የማይቻል ነዉ ማለት አልችልም።ግን ምን ያሕል ከባድ እንደሆነ፥ ከማይቻል ደረጃ የሚደርስ እንደሆነ እናዉቃላን።»

የሶሪያዉን ጦርነት በድርድር ለማስወገድ የሚደረገዉ ጥረት ለአናን የማይቻል፥ ለብራሒሚ ከማይቻል ደረጃ የደረሰ የሆነበት ምክንያት፥ አናን በዲፕሎማሲዉ የግድምድሞሽ አገላለጥ የአካባቢዉ እና የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ግፊት ማነስ ከማለት ሌላ በግልፅ አይናገሩት እንጂ ትክክለኛዉ ምክንያት የተሠወረ አልነበረም።አይደለምም።

በልማዱ የፖለቲካዊ መርሕ፥ የርዕዮተ ዓለም፥ ያለፈ ዳራ፥ የታሪክ፥ የሐይማኖት መመሳሰል ለፖለቲካዊ አቋም አንድነት መሠረት በሆነ ነበር።በሶሪያዉ ጦርነት ግን ተቃራኒዉ ነዉ-የደመቀዉ።እርግጥ ነዉ ሕዝባቸዉን በብረት ጡንቻ ረግጠዉ የሚገዙት የሪያድ፥የዶሐ፥ የዮርዳኖስ፥ የራባትና የብጤዎቻቸዉ ነገስታት ለዲሞክራሲ ስርፀት እንዋጋለን ከሚሉት ከዋሽግተን ብራስልሶች ጋር መወዳጀታቸዉ አዲስ ነገር አይደለም።

የሶሪያዉ ጦርነት ምዕራቦችንም፥ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን የያዙትን የአንካራ መሪዎችንም፥ በሕዝብ አመፅና ምርጫ ለስልጣን የበቁትን የካይሮና የቱኒዚያ አዳዲስ መሪዎችንም፥ በምዕራባዉያን ወታደራዊ እርምጃ ና በደፈጣ ዉጊያ የትሪፖሊን ቤተ-መንግሥት የተቆጣጠሩትንም ሕዝባዊ አመፅን ከደፈለቁና ከሚደፈልቁት ነገስታት ጎን ማቆሙ፥ በሸሪዓ ሕግ የሚገዙትን ቴሕራኖችን ከኮሚንስቶቹ ቤጂንጎች፥ ከመሐለኞቹ ሞስኮዎችም ጋር ማሰለፉ ነዉ እንቆቅልሹ።

ጥቅም ያቆላለፈዉ እንቆቅልሽ እስኪፈታ የሶሪያ ሕዝብ ማለቅ-መሰቃየቱ ደግሞ አሳዛኝ ሐቅ። ብራሒሚ የልዩ መልዕክተኛነቱን ሥልጣን ከያዙም በሕዋላ የእልቂት ፍጅቱን ንረት ለማቃለል ወጥ ዕቅድ አልነበራቸዉም።


«ጥቂት ሐሳቦች አሉኝ።እቅድ ግን የለኝም።»

ብራሒሚ ባለፈዉ አርብ ደማስቆ የገቡትም የሐያላኑን መንግሥታት ተወካዮች ኒዮርክ ላይ አነጋግረዉ፥ የአረብ ሊግ አባል ሐገራት ሹማምንታትን ለማነጋገር ካይሮ ሰነባብተዉ ነዉ።የአዛዉንቱ፥ ዲፕሎማት ሥልታዊ ጉዞ፥ ዉይይት አስራ-ሰባተኛ ወሩን ላስቆጠረዉ ጦርነት የመፍትሔ ጭላንጭል ማሳየት አለማሳየቱ ሲጠበቅ ግን የግብፅና የአዉሮጳ ሕብረት መሪዎች የአሰድ መንግሥት መወገድ አለበት የሚል ዛቻ-ማስጠንቀቂያቸዉን ደገሙት።

የሶሪያ ተፋላሚ ሐይላት ዉጊያም በተለይ የሐገሪቱን ትልቅ የንግድ ከተማ አሌፖን ያጋይ ነበር። በአሰድ ሥርዓት ላይ የሚሰነዘረዉ ዛቻ-ፉከራ ድግግሞሽና የጦርነቱ ግመት የብራሒሚን ተልዕኮ በጣሙን የደማስቆ ዉይይታቸዉን ዉጤት እንዴትነት መስካሪ ነበር።

እሳቸዉም የደማስቆ ዉይይታቸዉን እንዳጠናቀቁ አረጋገጡ።

«ከባድ ተልዕኮ እንደሆነ ተናግሬ ነበር።አሁንም በጣም ከባድ ነዉ።ከባድ እንደሆነም ይቀጥላል።ያም ሆኖ እንዲሕ አይነቱን ተልዕኮ ሊጋፈጡት ይገባል።የምጋፈጠዉ ለራሴ ፈጣን ዉጤት ለማምጣት ብዬ አይደለም።የምጋፈጠዉ ለሶሪያ ሕዝብ ትንሽም ቢሆን መርዳት እንደምችል ተስፋ በማድርጌ ነዉ።»

የብራሒሚ ቀጣይ እርምጃ በርግጥ አይታወቅም።ደማስቆ ላይ ብራሒሚን ያነጋገሩት የሶሪያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ለተመሳሳይ አላማ ግን ለሌላ ተልዕኮ ወደ ቤጂንግ ሔደዋል።ሐሰን አብዱል አዚምና ተባባሪዎቻቸዉ የሚመሩት ለዲሞክራሲያዊ ለዉጥ የሶሪያ ብሔራዊ አስተባባሪ አካል የተሰኘዉ ስብስብ የደማስቆ ገዢዎችን በሰላማዊ ትግል ለማስወገድ እንደሚታገል አስታዉቋል።የዉጪ ጦር ጣልቃ ገብነትንና ድጋፍን ይቃወማል።

በዚሕም ምክንያት ርዕሠ መንበሩን ቱርክ ያደረገዉ የሶሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰኘዉ የአማፂዎች ስብስብ የእነ ሐሰንን ቡድን አቋም አይደግፉትም።እንደ ብራሒሚ የወደፊት ዕቅድ ሁሉ የነሐሰን የቤጂንግ ጉዞ ዉጤት ቢያንስ ለዛሬ አልታወቀም።

የታወቀዉ ጦርነቱ ብሶ መቀጠሉ ነዉ።የታወቀዉ፥ የተባበሩት መንግሥታት የሠብአዊ መብት ምክር ቤት፥ የሶሪያ መንግሥት ጦርም፥ አማፂያኑም በሕዝቡ ላይ የሚፈፅሙት ጅምላ ግድያ፥ ዘረፋ፥ ሽብርም ማየሉን ማረጋገጡ ነዉ።የታወቀዉ፥ ብራሒሚ እዚያዉ ደማስቆ ላይ ልክ እንደ ኮፊ አናን ሁሉ የሶሪያዉ ዉጊያ ለአካባቢዉ ለመላዉ ዓለምም ሠላም አደገኛ መሆኑን ማስጠንቀቃቸዉ ነዉ።

«ሥለዚሕ ሥለ ሶሪያዉ ግጭት ተነጋግረናል።ይሕ በጣም አደገኛ ነዉ።እየከፋ የሚሔድ ነዉ።የሶሪያ ሕዝብን፥ አካባቢዉን ምናልባትም የመላዉ ዓለምን ሠላም የሚያሰጋ ነዉ።»

ብራሒሚ እንደ ዲፕሎማት ደማስቆ ላይ ዓለምን ሲያስጠነቅቁ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት አስራ-ስድስተኛ እንደ ሐይማኖት አባት፥ የሶሪያና የመካካለኛዉ ምሥራቅ ሙስሊም ክርስቲያኖች ተቻችለዉ እንዲኖሩ ቤይሩት ላይ ሲፀልዩ፥ ሲሰብኩ፥ ሲመክሩም ነበር።

«እንደተረዳሁት እዚሕ ከሶሪያ የመጣችሁ ወጣቶችም አላችሁ።ፅናታችሁ ምን ያሕል እንዳስደነቀኝ ልነግራችሁ እወዳለሁ።ለወላጆቻችሁና ለወዳጆቻችሁ ጳጳሱ አይረሷችሁም ብላችሁ ንገሯቸዉ።ሁከትና ጦርነትን ለማስቆም ሙስሊሞችና ክሪስቲያኖች በጋራ የሚወስኑበት ወቅት ነዉ አሁን።»

ካለፈዉ ሐሙስ ጀምሮ ከቤንጋዚ እስከ ካቡል፥ ከካይሮ እስከ ካራቺ፥ ከካርቱም እስከ ሲድኒ ከቱኒስ እስከ ሞንባሳ እንዳየን እንደሰማነዉ ግን ዓለም ሠላሙን ለማናጋት የብራሒሚ ማስጠንቀቂያ፥ የርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳቱ ፀሎት ምሕላ አላገደዉም።የሶሪያን ጦርነት ግመት መጠበቅም አላስፈለገዉም። ከዩናይትድ ስቴትስ የወጣዉ እስልምናን የሚያንቋሽሽ ፊልም-ያጫራዉ ቁጣ የመጀመሪያ ሰለቦች የራሷ የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማትና ወታደሮቻ መሆናቸዉ ነዉ-ዚቁ።እና የሰላም መቻቻል ምክር ፀሎት ስብከት የሚያስፈልገዉ በርግጥ ማን ነዉ? ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ
























Hundreds of Afghans demonstrate against the film of "Innocence of Muslims" on 17 Sept 2012 in Kabul, Afghanistan. Photo: Hussain Sirat/DW
ካቡል ፀረ-አሜሪካ ተቃዉሞምስል DW
+++ ALTERNATIVER AUSSCHNITT +++ Pope Benedict XVI attends an open-air mass in Beirut's waterfront on September 16, 2012, on the final day of his visit to Lebanon. Pope prayed that leaders in the Middle East work toward peace and reconciliation, in his homily at an open-air mass where an estimated 350,000 people attend. AFP PHOTO/FILIPPO MONTEFORTE (Photo credit should read FILIPPO MONTEFORTE/AFP/GettyImages)
ቤኔዲክት XXVIምስል AFP/Getty Images
In this image from amateur video made available by the Ugarit News group on Tuesday Nov. 15, 2011 shows a a burning Syrian tank in Daraa, Syria on Monday Nov. 14, 2011. (Foto:Ugarit vai APTN/AP/dapd) TV OUT THE ASSOCIATED PRESS CANNOT INDEPENDENTLY VERIFY THE CONTENT, DATE, LOCATION OR AUTHENTICITY OF THIS MATERIAL. TV OUT
የሶሪያዉ ጦርነትምስል dapd
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ