1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሺሞን ፔሪዝ ስርዓተ ቀብር

ዓርብ፣ መስከረም 20 2009

ከተለያዩ የዓለም ሃገራት የመጡ መንግሥታትና የመንግሥታት ተጠሪዎች እንዲሁም ታዋቂ ፖለቲከኞች በተገኙበት የቀድሞዉ የእስራኤል ፕሬዚደንትና የታዋቂዉ ፖለቲከኛ የሺሞን ፔሪዝ ስርዓተ ቀብር ዛሬ ተፈፀመ ።

https://p.dw.com/p/2QmnO
Israel Jerusalem  Shimon Peres Beisetzung
ምስል picture-alliance/AP Photo/S.Scheiner

ወደ 3000 ሰዎች በተገኙበት በዚሁ ቀብር ሥነ-ስርዓት ላይ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሟቹን የኖቤል ተሸላሚ ሺሞን ፔሪዝን « ታላቁ የሕዝባችን መሪ» ሲሉ አወድሰዋል። አንድ ትልቅ ሰዉ አጣን በእስራኤል ላይ የደረሰ ብሔራዊ ጉዳት ሲሉ የእስራኤል ፕሬዚዳንት ሬዩቪን ሪቭሊን፤ በሺሞን ፔሪዝ  ሞት ኃዘናቸዉን ገልፀዋል። በቀብር ሥነ-ስርዓቱ ላይ ከተገኙት መንግሥታት መካከል የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ዩአሂም ጋዉክ፤ የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ፤ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦላንድ፤ የብሪታንያዉ ልዑል ቻርልስ እንዲሁም የፍልስጤሙ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አባስ ይገኙበታል።  
የእስራኤል ሕዝብ በቀድሞ ፕሬዝደንቱ በሺሞን ፔሪዝ ሞት የተሰማዉ ሐዘን ሲገልፅ ነዉ የዋለዉ። ከአንድ ሳምንት በፊት ጭንቅላታቸዉ ዉስጥ ደም በመፍሰሱ በሕክምና ሲረዱ የቆዩት ፔሪዝ ትናንት ለዛሬ አጥቢያ ነዉ ያረፉት። 93 ዓመታቸዉ ነበር። የፔሪዝ ልጅ ቻሚ ፔርስ የአባታቸዉን ሞት ሲያዉጁ ዛሬ እንዳሉት፤ አንጋፋዉ ፖለቲከኛ እስራኤል እንደ ሐገር ከመመሥረቷ አስቀድሞ የአይሁዶች ፍላጎትና ጥያቄ እንዲሳካ ዕድሜ ልካቸዉን የታገሉ ፖለቲከኛ ናቸዉ።«አባቴ ከእስራኤል መሥራች አባቶች አንዱ ነበር። የእስራኤል መንግሥት ከመመሥረቱ በፊት ጀምሮ ለሕዝቡ ሲታገል ፤ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላም እስከ መጨረሻዉ ዕለት ድረስ ሲያገለግል ነበር። ሰባ ዓመታት ባስቆጠረ አገልግሎቱ የሐገሪቱ ዘጠነኛ ፕሬዝደንት፤ ጠቅላይ ሚንስትር፤ መከላከያ ሚንስትር እና በሌሎችም የኃላፊነት ሥፍራዎች ሐገሩን በታማኝነት አገልግሏል። አባቴ፤«የአንተ ትልቅነት እንደቆምክለት ዓለማ ትልቅነት የሚወሰን ነዉ» ይል ነበር። እስከ መጨረሻዉ እስትንፋሱ ድረስ የሚያምንበትን እና የሚያፈቅረዉን የእስራኤልን ሕዝብ ከማገልገል ሌላ፤ ሌላ ፍላጎት አልነበረዉም።»

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ