1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሻምበል አበበ ቢቂላ የሮም ድል 50ኛ ዓመት

ሰኞ፣ መስከረም 3 2003

«አበበ ድል ያደረገው አትሌቲክስን ብቻ አይደለም።ጥቁሮች ማሸነፍ እንደሚችሉም ለዓለም አስተምሯል።» ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ «ለቅኝ ግዛት ማክተም አስተዋጽኦ ያደረገ ድል! የአበበ ድል አፍሪካውያን እኩል መሆናቸውን አሳይቷል።» ፖል ራምባኒ--የአበበ ቢቂላ መጽሀፍ አዘጋጅ

https://p.dw.com/p/PB5B
ምስል dpa

ባለፈው ዓርብ ዻጉሜን 5/2002 ሻምበል አበበ ቢቂላ በሮም በባዶ እግሩ ሮጦ ድል ያደረገበት 50ኛ ዓመት ተዘክሯል። ሻምበል አበበ ቢቂላ ወደ ሮም ያመራው በተጠባባቂነት ነበር። ዋሚ ቢራቱ በጉልበቱ ላይ በደረሰበት አደጋ መሮጥ ባለመቻሉ ሲውዲናዊው አሰልጣኝ አበበ ተክቶ እንዲሮጥ ያደርጋሉ። ትንሹ አበበ በሮም ጎዳና ባዶ እግሩን ሲሮጥ ሲታይ ተመልካቹ ተደናገጠ። 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ 11 ሰከንድ በኋላ ግን ያልተጠበቀ እንግዳ የሆነ ክስተት በሮም የኦሎምፒክ መንደር ላይ ታየ። በባዶ እግሩ የሚሮጥ፤ ጥቁር ሯጭ ከኦሎምፒክ መንደሩ በአንደኝነት ሲገባ ዓለም ባልተጠበቀው ክስተት ታዓምር አለ።

ይህ ታላቅ ድል ከተከሰተ 50 ዓመት ሞላው። ሻምበል አበበ ቢቂላ ግን በሞት ከተለየ 37 ዓመት ሆኖታል። ዛሬም ድረስ የሮሙ ድሉ ዓለምን አንዳስደነቀ አለ። ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ «አሁን አትሌቲክሱን ለተቆጣጠርነው አፍሪካውያን አትሌቶች ፈር የቀደደ፤ በር የከፈተ ድል» ብሎታል-የሮሙን ድል። አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ «ህልም እንጂ በእውነት የተከሰተ የማይመስል ተአምረኛ ድል» ሲል ገልጾታል። ቤር ፉት ረነር የተሰኘ በሻምበል አበበ ቢቂላ ላይ የተዘጋጀውን መጽሀፍ በቅርቡ ለንባብ ያበቁት እንግሊዛዊው ፓል ራምባኒ«ድንቅ ድል ነበር። በጥቁር አፍሪካዊ የተገኘ የመጀመሪያው የወርቅ ድል! በእርግጥ በዚያን ወቅት ሌሎች ጥቁር አፍሪካውያን ሯጮችም ነበሩ።ግን የሚሮጡት ቅኝ ለገዟቸው የአውሮፓ ሀገራት ነበር። የአበበ ድል ታላቅ የሆነው ለዚያም ጭምር ነው። አዎን!አበበ ለዓለም አዲስ ነገር አሳየ። የአፍሪካ ህዝብ በእኩል መወዳደርና ማሸነፍ እንደሚችል አረጋገጠ።

የመጀመሪያው ምክንያቴ ማንም ያንን ስላላደረገው ነው። በእርግጥ እንደሚመስለኝ ኢትዮዽያውያን ይህን ማድረግ ነበረባቸው። ግን ሊያደርጉ አልቻሉም። ልጅ እያለሁ አበበ ቢቂላ ሲሮጥ በቴሌቪዥን ካየሁት ጊዜ ጀምሮ ለእሱ ያለኝ አክብሮትና አድናቆት ከፍተኛ ነው። የአበበ ድል ከታላላቅ ስፖርታዊ ክስተቶች ጎልቶ የሚጠቀስ ስለሆነ በሚገባ አውቀዋለሁ። ለእሱ ያለኝ ስሜት እየጨመረ ሲመጣ ስለእሱ ማጥናት፤ እሱን የተመለከቱ ነገሮችን መሰብሰብ ጀመርኩ። ያም ስለእሱ በጣም እንድማረክ አድርጎኛል።» ብለዋል።

መሳይ መኮንን

ነጋሽ መሐመድ