1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሼል ኩባንያ የካሳ ክፍያ እና የተዳከመዉ ዩጋንዳዉ አማፂ ቡድን

ቅዳሜ፣ ጥር 2 2007

የሼል ኩባንያ በናይጄሪያ የነዳጅ ማስተላለፊያ ተሸንቁሮ ላደረሰው ጉዳት ለመጀመሪያ ጊዜ ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል። በዚሁ ሳምንት ራሱን የጌታ ተከላካይ ጦር (Lord's Resistance Army ) ብሎ ከሚጠራው የዩጋንዳ አማጺ ቡድን የጦር መሪዎች መካከል ዶሚኒክ ኦንግዌን እጁስ ሰጥቷል።

https://p.dw.com/p/1EIMX
Shell Öl Umweltverschmutzung in Nigeria
ምስል picture-alliance/dpa/EPA/Marten Van Dijl

ግዙፉ የነዳጅ ንግድ ኩባንያ ሼል ለናይጄሪያ የኒጀር ዴልታ ግዛት የኦጎኒላንድ አካባቢ ነዋሪዎች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም. ከነዳጅ ማስተላለፊያ መስፈር ፈሶ ለደረሰው ጉዳት 70 ሚሊዮን ዩሮ ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል። የግዛቲቱ ነዋሪዎችም ስምምነቱን በይሁንታ መቀበላቸው ነዉ የተሰማዉ።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2008 ዓ.ም. ግዛቲቱን አቋርጦ ከሚያልፈው ቱቦ የፈሰሰው ነዳጅ የነዋሪዎቹ ህይወት የተመሰረተበትን ሰፊ መሬት የሸፈነ ቁጥቋጦና የዓሳ ዝርያዎችን ማዉደሙ ይታወቃል።

በያዝነዉ ሳምንት ዕለተ ረቡዕ የተሰማው ዜና በናይጄሪያ የሼል እህት ኩባኒያ እና በናይጀርያዋ ቦዶ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ለሶስት ዓመታት በታላቋ ብሪታኒያ የተካሄደው ክርክር መቋጫ ሆኗል።

ሼል ኩባንያ ለ15,600 የቦዶ ዓሳ አስጋሪዎች እና ገበሬዎች 35 ሚሊዮን ፓውንድ ለማህበረሰቡ ደግሞ 20 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚከፍል አስታውቋል።

አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቨሌ የሰጡት ዲክ ሳሩ የተባሉ የግዛቲቱ ነዋሪ ስምምነቱ «የኦጎኒ ነዋሪዎች ቁጣ የተቀሰቀሰው የሼል ኩባንያን በመጥላት ሳይሆን በሰዎቹ ላይ ካደረሱት ጥፋት የሚመነጭ መሆኑን ይጠቁማል።» ሲሉ ተናግረዋል።

አሁን የተደረሰው ስምምነት እንደማንኛውም ናይጄሪያዊ፤ ዲክ ሳሩ ተጨማሪ ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።«በቦዶ ለደረሰው ጥፋት ሃላፊነቱን ከወሰዱ በሌሎች አካባቢዎች የፈሰሰውስ ጥፋት ያደረሰውስ?»

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International ) በየዓመቱ ከሼል የነዳጅ ማስተላለፊያዎች በመቶዎች የሚቆጠር የመፍሰስ አደጋ እንደሚከሰት አስታውቋል።

በቦዶ አቅራቢያ ለሚኖሩት ቤመን ታኔን የተባሉ ናይጄሪያዊ አሁን የተደረሰው ስምምነት መልካም ዜና ነው። «ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎች ሃላፊነታቸውን መቀበላቸው ለሰዎች መልካም ነው።»

55 በመቶ የመንግስት ድርሻ የሆነውን በናይጄሪያ የሼል እህት ኩባኒያ ሃላፊ ሙቲዩ ሱንሞኑ «ሁልጊዜም ለደረሰው ጥፋት በፍትኃዊነት ካሳ ለመክፈል እንፈልግ ነበር።» ሲሉ ከስምምነቱ በኋላ ተናግረዋል።

ነገር ግን በጥፋቱ የተጎዱት የኦጎኒነዋሪዎች ጠበቃ የሆኑት ሌግ ዴይ መጀመሪያ የሼል ኩባንያ ለመላው ማህበረሰብ 4,000 ፓውንድ ብቻ የመክፈል ሃሳብ እንደነበረው ተናግረዋል።

በናይጄሪያ ሌጎስ የዶይቼ ቨለ ወኪል የሆኑት ሳም ኦሉኮያ አሁን ከፍርድ ቤት ውጪ የተፈጸመው ስምምነት ከእስካሁኑ የተለየ እንደሆነ ነዉ የተናገሩት።

«በኒጀር ዴልታ ግዛት ነዳጅ ከማስተላለፊያ ቱቦ ፈሶ አደጋ ሲያደርስ ካሳ መክፈል ሁሌም የተለመደ አይደለም። ነዳጅ ከማስተላለፊያ ቱቦ ተሸንቁሮ ጥፋት ሲያስከትል ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎችን ኩባንያዎቹ በፖሊስ በማሳሰር በአሻጥር ይከሷቸዋል። ይህ የአሁኑ ግን በጣም የተለየ ጉዳይ ነው።»

የሼል ኩባንያ እንዲህ አይነቶቹ የነዳጅ ዘይት መፍሰስ እና የአካባቢ መበከል ችግሮች የሚፈጠሩት በማስተላለፊያ ቱቦዎች ብልሽት መሆኑን ያምናል። ይሁንና ኩባንያው ብዙዎቹ በኒጀር ዴልታ የሚከሰቱ መሰል ችግሮች በአሻጥር፤በህገ-ወጥ መንገድ ነዳጅ ለማጣራት በሚደረግ ሙከራ እና ስርቆት ነው የሚል መከራከሪያ ያቀርባል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International) የአካባቢ፤ ሰብዓዊ መብት እና ልማት ማዕከል (Center for Environment, Human Rights and Development) የተሰኙት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የሼል ኩባንያ በፈሰሰው ነዳጅ የተበከለውን አካባቢ እንዲያጸዳ እና ካሳ እንዲከፍል የቦዶ ነዋሪዎችን በመወከል ላለፉት ስድስት አመታት ሲከራከሩ ቆይተዋል።

Öl in Nigeria
ምስል picture-alliance/dpa

ሼል ኩባንያ በአካባቢው የፈሰሰው ነዳጅ 4,000 በርሜል ብቻ ነው ቢልም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባቀረበዉ ጥናት ከ100,000 በርሜል በላይ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደ ሼል ያሉ ኩባንያዎች ለሚያደርሱት ጥፋት ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚደረገውን ዘመቻ በሃላፊነት የሚመሩት ጆ ዌስትቢ በቦዶ የተከሰተው እና በአካባቢው ላይ ብክለት የፈጠረው ችግር ሼል ኩባንያ እንደሚለው በግዛቲቱ ከፍተኛ ችግሮች በሆኑት አሻጥር እና ስርቆት የተከሰተ አይደለም በማለት ለዶይቼ ቨሌ ተናግረዋል።

በቦዶ የአለቆችና ያገር ሽማግሌዎች መማክርት መሪ የሆኑት ሲልቬስተር ኮግባራ «አሁን ሼል በሚሰራባቸው አካባቢዎች ያሉ ማህበረሰቦችን ያከብራል።» በማለት የተበከለውን የኦጎኒላንድ አካባቢ ማጽዳት መጀመር እንዳለበት ለፈረንሳዩ ኤ.ፒ. የዜና ወኪል ተናግረዋል።

አከባቢውን መልሶ የማጽዳቱ ሥራ 30 ዓመት እንደሚወስድና እስከ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስወጣ፣ ከዓመት በፊት በተባበሩት መንግስታት የተሰራ አንድ ጥናት ያመለክታል።

የዶይቼ ቨሌው ዘጋቢ አሁን ከቦዶ ነዋሪዎች ጋር የተደረሰው ስምምነት «የነዳጅ ንግድ ኩባንያዎች የመኖሪያ አካባቢዎችን በክለው ዝም ብለው መሄድ እንደማይችሉ ይጠቁማል።» ሲል ያስረዳል።

በናይጄሪያ የሼል እህት ኩባኒያ ሃላፊ ሙቲዩ ሱንሞኑ ድርጅታቸው የተበከለውን አካባቢ ለማጽዳት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለሙያ የሆኑት ዌስትቢ በበኩላቸው ከማስተላለፊያ ቱቦ በፈሰሰው ነዳጅ የተበከለውን አካባቢ ስፋት ለማወቅ የሼል ኩባንያ በእጁ የሚገኙ ማስረጃዎችን ይፋ ማድረግ እንደሚኖርበት ያሳስባሉ።

ሼል ኩባንያ የፈሰሰውን ነዳጅ መጠን ዝቅ አድርጎ መመልከቱን በታላቋ ብሪታኒያ በነበረው የክርክር ሂደት ማመኑን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ አድርጓል።

የማህበረሰቡ ባህላዊ መሪ ሲልቬስተር ኮግባራ በበኩላቸዉ ለማህበረሰቡ ሊከፈል ቃል የተገባው 20 ሚሊዮን ዶላር መሰረታዊ ግልጋሎቶችን ለማቅረብ እንደሚውል ተናግረዋል።

«የጤና አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችሉ ተቋማት የሉንም።ትምህርት ቤቶቻችን መሰረታዊ ናቸው። የንጹህ ውሃ አቅርቦት የለም»

የተዳከመዉ ዩጋንዳዉ አማፂ ቡድን

ዶሚኒክ ኦንግዌን በዩጋንዳ፤በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፤ደቡብ ሱዳን እና ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የተፈጸሙ ዘግናኝ ወንጀሎችን የመራ አስፈሪ የጦር መሪ ነው። የዛሬውን የዩጋንዳ መሪ ለ27 ዓመታት ሲዋጋ የኖረውን ራሱን የጌታ ተከላካይ ጦር(Lord's Resistance Army)ብሎ የሚጠራው አማፂ ቡድን የተቀላቀለው ታፍኖ ተወስዶ በልጅነቱ ነበር። በፅንፈኛው የክርስትና አቀንቃኝ አማፂ ቡድን ውስጥ ገኖ መሪ ከሆነ በኋላ ዶሚኒክ ኦንግዌን ለመያዝ መረጃ ለሚሰጥአሜሪካ የ5 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ አዘጋጅታ ነበር።

Infografik LRA The Lord’s Resistance Army Englisch

ዶሚኒክ ኦንግዌን እጁን ለአሜሪካን ጦር ከሰጠ በኋላ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው ሂዉማን ራይትስ ዋች ለፈጸማቸው ወንጀሎች ይጠየቅ ዘንድ መቀመጫው ሄግ ላደረገው ለዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ተላልፎ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርቧል።

የዩጋንዳ መንግስት ዋና አቃቤ ሕግ ፒተር ኒዮምቢ ግን ሃገራቸው ዶሚኒክ ኦንግዌን የተከሰሰባቸውን ወንጀሎች የመዳኘት አቅም እንዳላት ያምናሉ። የዩጋንዳ መከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር ክሪስፐስ ኪዮንጋ ግን ጉዳዩ የሃገሪቱን ከፍተና ሹማምንት ውሳኔ እንደሚጠብቅ ለዶይቼ ቨሌ ተናግረዋል።

«ውሳኔ እንሰጣለን። ጉዳዩ በዩጋንዳ ይታይ ወይስ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት የሚለውን ጉዳይ ገና እየተማከርን ነው። ጉዳዩ ግን የሕግ ጉዳይ ነው።»

በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ መስጠል ቀላል ነገር አይደለም። ዩጋንዳ በፈቃደኝነት እጃቸውን ለሚሰጡ አማፂዎች ይቅርታ ታደርጋለች። ይሁንና ዶሚኒክ ኦንግዌን በጥብቅ የሚፈለግ ወንጀለኛ ነው።

በአፍሪቃ ሕብረት ፓርላማ የፍትህና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ሊቀመንበር የሆኑት ኦንያንጎ ካኮባ ውሳኔ አሰጣጡ በጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ያሳስባሉ።

«በፈቃደኝነት ከሆነ እጁን የሰጠው እንደ ግለሰብ ትክክለኛ ውሳኔ ወስኗል። የአማጺውን ቡድን ለመግታትም ከፍ ያለ ጥቅም ያበረክታል። ሰውየው በጥብቅ የሚፈለግ መሆኑ ጉዳዩን ውስብስብ ያደርገዋል። ዶሚኒክ ኦንግዌን በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት በጥብቅ ይፈለጋል።በሌላ በኩል በዩጋንዳ እጃቸውን በፈቃደኝነት ለሚሰጡ አማፂዎች ይቅርታ የመስጠት አሰራር አለ። ስለዚህ ፍትህ ለማግኘት ሁሉም ነገር በጥንቃቄ መፈታት ይኖርበታል።»

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሁማን ራይትስ ዎች የዩጋንዳ መንግስት ራሱን የጌታ ተከላካይ ጦር (LRA)ብሎ የሚጠራው አማፂ ቡድን አባላትን ጉዳይ በሙሉ ወደ ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ሲልክ የቆየ በመሆኑ ይህ የተለየ መሆን የለበትም የሚል አቋም አለው።

Joseph Kony Rebellenführer LRA Uganda Archivbild
ምስል Stuart Price/AFP/Getty Images

ራሱን የጌታ ተከላካይ ጦር (LRA)ብሎ ራሱን የሚጠራው አማፂ ቡድን ሽንፈቶች የአማፂ ቡድኑ ዳግም እንደ ማያንሰራራ ማረጋገጥ ለሚፈልጉት ለሰሜን ዩጋንዳ ነዋሪዎች የምሥራች ነው። በሰሜን ዩጋንዳ የሚገኙ አንዳንድ መሪዎች የዶሚኒክ ኦንግዌን እጅ መስጠት በእርግጥም ለዘመናት የሃገራቸው ራስ ምታት ሆኖ የቆየውን አማፂ ቡድን ያዳክመዋል።

በአቾሊ ግዛት ሕግ አውጪዎች የተቋቋመው የአቾሊ ፓርላማ አባላት ቡድን (Acholi Parliamentary group)ምክትል ሊቀ-መንበር የሆኑት ሎዊላ ኦቴካዮት ዶሚኒክ ኦንግዌን እጅ መስጠት የአማፂውን ዋና መሪ የጆሴፍ ኮኒ መውደቅ ምልክት ያደርጉታል።

«ዶሚኒክ ኦንግዌን ከአማፂ ቡድኑ መሪዎች አንዱ የነበረ በመሆኑ ከጆሴፍ ኮኒ እና ከቡድኑ ጋር የሚደረገው ትግል በጥሩ ሂደት ላይ ለመሆኑ ምልክት ነው። በእያንዳንዷ ቀን ጆሴፍ ኮኒ እየተዳከመ ለመሆኑ ግልፅ ምልክት ነው።»

የአሜሪካ ፤የአፍሪቃ ሕብረት እና የዩጋንዳ ጦር ራሱን የጌታ ተከላካይ ጦር (LRA)ብሎ ራሱን የሚጠራውን አማፂ ቡድን ለማጥፋት በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ በጋራ ይሰራሉ።

የዩጋንዳ የመከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር ክሪስፐስ ኪዮንጋ ዶሚኒክ ኦንግዌን የሚዳኘው የትም ይሁን የት የሃገሪቱ ብሄራዊ ጦር አማፂ ቡድኑን ማደኑን ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።

«የዩጋንዳ ብሄራዊ ጦር የጌታ ተከላካይ ጦርን እያጠቃ ነው። ዶሚኒክ ኦንግዌን የሚያክል የጦር መሪ እጅ መስጠት አማፂ ቡድኑ ያለበትን አጣብቂኝ ያሳያል።»

የ10 ዓመት ልጅ ሳለ ታግቶ የተወሰደው ዶሚኒክ ኦንግዌን በአማፂ ቡድኑ ውስጥ ብርጋዴየር ጄኔራል የሆነው ገና በ20 ዓመቱ ነበር።

ራሱን የጌታ ተከላካይ ጦር (LRA)ብሎ የሚጠራው አማፂ ቡድን በአቾሊ ህዝቦች ስም የፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒን መንግስት መታገል የጀመረው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1986 ዓ.ም. ነበር። ይሁንና አማፂ ቡድኑ በደፈጣ ውጊያ ድንበር ተሻግሮ የአካባቢውን ሃገሮች ለማተራመስ የወሰደበት ጥቂት ዓመታት ብቻ ነው።

ቡድኑ መቀመጫውን በዩጋንዳ፤ደቡብ ሱዳን፤የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክና በስተመጨረሻም በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ በመቀያየር ህጻናትን በግዳጅ ለውትድርና ሲዳርግና ጥቃት ሲፈፅም ቆይቷል። በጆሴፍ ኮኒ የሚመራው ይህ አማፂ ቡድን የቀጣናው ሃገራትን የርስ በርስ ግንኙነት እስከ ማሻከርም ድርሶ ነበር።

የመፅሐፍ ቅዱስ አስርቱ ትዕዛዛትን የሚከተል መንግስት ለመመስረት እታገላለሁ የሚሉት የአማፂ ቡድኑ መሪ ጆሴፍ ኮኒ በአፍሪቃ ሕብረት፤ ዩጋንዳ እና የአሜሪካ ጦር ይፈለጋሉ።

ኮኒ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ1987 ዓም ጀምሮ በዩጋንዳ፤ ደቡብ ሱዳን፣ በምሥራቅ ኮንጎ እና በማዕከላዊአፍሪቃ ሬፓብሊክ ዉስጥ ዓመፅና ግጭት በመቀስቀሳቸው፣ በጦር እና በስብዕና አንፃር በፈፀሙት ወንጀል በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ እንደተቆረጠላቸዉ ይታወቃል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ