1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሽብር ጥቃት በኮት ዲ ቯር

ሰኞ፣ መጋቢት 5 2008

የኮት ዲ ቯር ባለስልጣናት በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሸባሪዎች ጥቃት ከደረሰ በኋላ አስቸኳይ የፀጥታ ጉዳይ ስብሰባ እያካሄዱ ነዉ። ትናንት የዉጭ ዜጎች በሚያዘዉትሩት የባህር ዳርቻ መዝናኛ ስፍራ አሸባሪዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ22 በላይ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል።

https://p.dw.com/p/1ID1J
Elfenbeinküste Anschlag Grand Bassam in Abidjan
ምስል Reuters/J. Penney

[No title]

«ከታጣቂዎቹ መካከል አንደኛው ገና ልጅ ነው። ስልክ በማነጋገር ላይ ወደ ነበረች አንዲት ሴት በመሄድ «አላሁ አክበር» እያለ በመጮህ ጭንቅላቷ ላይ ተኩሶ መታት።»

ይህ በትናንትናው ዕለት በኮት ዴቩዋሯ የአቢጃን ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ቅንጡ የመዝናኛ ሆቴል የነበሩ እንግዶች ከታዘቧቸው አሰቃቂ ትዕይንቶች መካከል አንዱ ነው።

የኮትዲቯር እና የውጭ አገር ጎብኚዎች በሚያዘወትሩት የባህር ዳርቻ አቅራቢያ በሚገኙ ሶስት ሆቴሎች ላይ ባነጣጠረ የሽብርተኞች ጥቃት ቢያንስ 22 ሰዎች ተገድለዋል። ታጣቂዎቹ በግራንድ-ባሳም የባህር ዳርቻ የመዝናኛ ሥፍራ ከገደሏቸው ሰዎች መካከል አራት አውሮጳውያንም ይገኙበታል።

Elfenbeinküste Anschlag Grand Bassam in Abidjan
ምስል Reuters/J. Penney

የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ከኮት ዲ ቯር አቢጃን ከተማ ደቡብ ምሥራቅ በ25 .. ርቀት ላይ በሚገኘው ሆቴል ላይ በተፈጸመው ጥቃት አንዲት ጀርመናዊት ህይወታቸው ማለፉን አረጋግጠዋል። ጀርመናዊቱ በናይጄሪያ አቢጃን ከተማ የሚገኘው የጎይተ የጀርመን የባህል ተቋም ኃላፊ መሆናቸውንም መቀመጫውን በሌጎስ ያደረገው የዶይቼ ቬለ ወኪል ዣን ፊሊፕ ሾልዝ ዘግቧል። የኮት ዲ ቯር የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሐመድ ባካዮኮ የፈረንሳይ፤ ቡርኪና ፋሶ፤ ማሊ እና ካሜሩን ዜጎችም የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የእጅ ቦምቦች እና የነፍስ ወከፍ ጦር መሳሪያዎች የታጠቁት ግለሰቦች ወደ ሶስት ሆቴሎች በመግባት የእሩምታ ተኩስ መክፈታቸው ነዉ የተነገረዉ። ታጣቂዎቹ በመዋኘት፤ ፀሐይ በመሞቅ፤ በመመገብ እና በመጠጣት ላይ የነበሩ እንግዶችን ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል። ሜሪ ክሌር በቦታው የተፈጸመውን ጥቃት ከተመለከቱት መካከል አንዷ ናቸው።

«አንዲት ልጅ እና አንድ ወጣት ከፊት ለፊታችን በጥይት ተመተዋል። ወደ ውኃ ውስጥ ሁሉ ሲተኩሱ ነበር። እኛም የተረፍንው በዕድል ነው።»

የኮት ዲ ቯር የጸጥታ ኃሎች ከጥቃቱ ፈጻሚዎች መካከል ስድስት መግደላቸውን ያስታወቁ ሲሆን የአገሪቱ መንግስት ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጠዋል። የጀርመን ዜና አገልግሎት (DPA) እንደዘገበዉ በሰሜን አፍሪቃ ማግሬብ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የአልቃዒዳ ክንፍ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል። ታጣቂ ቡድኑ በአገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች ሶስት አባላቱ መገደላቸውንም ጨምሮ አስታውቋል። የዓይን እማኞች ጥቃት ፈጻሚዎቹ የሚወክሉትን ቡድን ማንነት በትክክል ባያውቁም ፊታቸውን ግን መመልከት ችለዋል።

«ከቀኑ ሰባት ሰዓት ሲሆን ሁለት የታጠቁ ሰዎች ሲገቡ ተመለከትን። ወዲያው ወደ ሁሉም አቅጣጫ መተኮስ ጀመሩ። እነዚህ ወድቀው የምትመለከታቸው ሰዎች ደንበኞች ናቸው። አሸባሪዎቹ የቱዓረግ ሰዎችን ይመስላሉ።»

Elfenbeinküste Anschlag Grand Bassam in Abidjan
ምስል Reuters/J. Penney

የተ... ዋና ጸሐፊ ባንኪ ሙን ጥቃቱን አውግዘው ወንጀለኞቹን ከፍርድ ለማቅረብ ለኮት ዲ ቯር መንግሥት እገዛ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። በፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ በኩል ጥቃቱን ያወገዘችው ፈረንሳይ ታጣቂዎቹን ለመያዝ እርዳታ እንደምታደርግ አስታውቃለች። ፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ማርክ አይራዑልትን ጨምሮ ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣኖቿን ወደ ኮት ዲ ቯር ልካለች። ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ የምዕራብ አፍሪቃ አገራትን ዒላማ ያደረጉ ሽብርተኞችን እዋጋለሁ ብላለች።

በሰሜን አፍሪቃ ማግሬብ አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የአልቃዒዳ ክንፍ ይህ በቀጣናው የፈጸመው ሶስተኛ ጥቃት ነው። ከዚህ ቀደም ቡርኪና ፋሶ እና ማሊም የአክራሪ ቡድኑ የጥቃት ዒላማዎች ነበሩ። የጸጥታ እና ደህንነት ተንታኞች በሳህል ቀጠና የሚገኙት ኮት ዲ ቯር እና ሴኔጋልን የመሳሰሉ አገራት መሰል የሽብር ጥቃት ሊፈጸምባቸው እንደሚችል ቅድመ-ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው እንደነበር አስታውሰዋል። የፈረንሳይ የደህንነት ተቋማት ኮት ዲ ቯር በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የአልቃዒዳ ክንፍ በመኪና ላይ በተጠመዱ ቦንቦች የውጭ አገር ዜጎች በሚያዘወትሩባቸው አደባባዮች እና ቅንጡ የመዝናኛ ቦታዎች ጥቃት ሊሰነዝሩ ማቀዳቸውን የሚጠቁም ማስረጃ አቀብለው እንደነበር አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ