1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀኝ አክራሪዎች ጥቃትና ስደተኞች በጀርመን

ማክሰኞ፣ መጋቢት 2 2006

ጀርመን ውስጥ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያዎች ላይ በቀኝ አክራሪዎች የሚደርሱ ጥቃቶች መባባሳቸውን የጀርመን መንግሥት አስታውቋል ። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም የችግሩን አሳሳቢነት አጉልተው በማሳየት ላይ ናቸው ።

https://p.dw.com/p/1BNZP
Springerstiefel mit weißen Schnürsenkeln
ምስል imago/Rüdiger Wölk

በያዝነው የጎርጎሮሳውያኑ 2014 መባቻ ደቡብ ጀርመን በሚገኘው በባየርን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ስር ባለው ፊሽትልበርግ በተባለችው ከተማ በሚገኝ አንድ የስደተኞች መጠለያ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ገብተው ተቃውሞ አሰምተው ነበር ። እነዚሁ ጥቁር የለበሱና በከፊል ፊታቸውን የሸፈኑ ሰዎች መጠለያውን ጥሰው በመግባት ኮሪደሩ ላይ ቆመው ከጮሁ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ስፍራውን ለቀው ወጥተዋል ። በስፍራው ከነበሩት ስደተኞች አብዛኛዎቹ በቅርቡ ወደ ጀርመን የመጡና ጀርመንኛ የማይችሉ ነበርና ሰዎቹ በምን ምክንያት እንደሚጮሁ ምን ይሉም እንደነበር አልተረዱም ። መጠለያውን ጥሰው የገቡት ሰዎች ስደተኞቹ በዚያ መቀመጣቸውን የሚቃወሙ ሰዎች የተሰባሰቡበት ቡድን ነው ። እንደ እድል ሆኖ አነዚህ ሰዎች ተቃውሞአቸውን በጩኽት ከማሰማት ባለፈ በሰዎቹ ላይ ሌላ ጥቃት አላደረሱም ። በመላ ጀርመን የስደተኞች መጠለያዎችን፣ በእሳት መለኮስና መስኮቶቻቸውን መሰባበር የመሳሰሉ ጥቃቶች እንዲሁም በህንፃዎቹ ላይ ዘረኛ ስድቦችን መፃፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል ። የጀርመን የፌደራል የወንጀል መርማሪ መሥሪያ ቤት በምህፃሩ KBA በጎርጎሮሳውያኑ 2013 በሃገሪቱ ዓም በጀርመን እነዚህን መሰል 59 ጥቃቶች መፈፀማቸውን አረጋግጧል ። ይህ ደግሞ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከእጥፍ ይበልጣል ። እንደ መሥሪያ ቤቱ የጥቃቱ መጠን ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል ። በወንጀልነት ሳይመዘገቡ የቀሩባህርያቸው በግልፅ ከቀኝ አክራሪዎች ጥቃት ጋር ለመገናኘቱ በቂ ማስረጃ ያልተያዘባቸው ሌሎች ጥቃቶች ይደርሳሉና ። ለምሳሌ ፊሽትልበርግ ውስጥ የተፈፀመው ቀደም ሲል መንግሥት በስደተኖች ላይ ተፈፅመዋል ሲል ከመዘገባቸው ጥቃቶች ጋር የሚደመር አይደለም ። ወንጀሉ በውጭ ዜጎች ጥላቻ መንስኤ የተፈፀመ መሆኑን ለማረጋገጥ ፖሊስ ማስረጃ ይፈልጋል ። ስደተኞች በሚኖሩበት መጠለያ በማይረዱት ቋንቋ ኮሪደር ላይ መጮህን ፖሊስ እንደ ወንጀል ሊቆጠረው አልቻለም ።

በጀርመን ለስደተኞች መብት የሚቆመው ፕሮ አዙል የተባለው ድርጅት ባለፉት ሁለት ወራት ተኩል ገደማ ማለትም በጎርጎሮሳውያኑ 2014 ዓም በስደተኞች ላይ 20 ጥቃቶች መድረሳቸውን መመዝገቡን አስታውቋል ። ከመካከላቸው 12 ቱ እሳት በመለኮስ የተፈፀሙ መሆናቸውን ድርጅቱ ገልጿል ። የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ጉንተር ቡርክሃርት እየተባባሱ የቀጠሉት እነዚህ ጥቃቶች ጀርመን ውስጥ እጎአ በ1990ዎቹ ቀኝ አክራሪዎች በስደተኞች ላይ ያደረሱትን ጥቃት የሚስታውሱ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት ።
« የቆዩ ትዝታዎችን ይቀሰቅሳል ። በዚያን ጊዜ ነበርኩኝ ። ይሁንና ያኔ በ1990ዎቹ ዓመታት እንደነበር ያለ በአሁኑ ጊዜ በስፋት በተገን ጠያቂዎች ላይ የሚካሄድ ዘመቻ የለም ። »
እጎአ በመስከረም 1991 በምስራቅ ጀርመኑ በዛክሰን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ውስጥ በምትገኘው በሆየርስቬርዳ የውጭ ዜጋ በሆኑ ጊዜያዊ ሠራተኞችና በተገን ጠያቂዎች መኖሪያዎች ላይ ቀኝ አክራሪዎች በለኮሱት እሳትና በወረወሩት ድንጋይ የውጭ ዜጎች ሞትን ጨምሮ ለተለያዩ ጉዳቶች የተጋለጡበት ጥቃት ምን ጊዜም የሚረሳ አይደለም ። ዓለም ዓቀፍ ትኩረትን የሳበው ይኽው ጥቃት ሲፈፀም የአካባቢው ነዋሪዎች ተመልካች መሆናቸው ይባስ ብሎም አንዳንዶቹ ድርጊቱን ሲደግፉ መሰማታቸው እስካሁንም ድረስ በአሳፋሪነቱ ይነሳል ። ቡርክሃርት እንደሚሉት ለነዚህ ጥቃቶች መባባስ ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ጀርመን ለጀርመኖች ብቻ የሚል አስተሳሰብ የሚያራምደው ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በምህፃሩ NPD እና አማራጭ ለጀርመን የተባለው ፓርቲ ህዝቡ በውጭ ዜጎች ላይ እንዲነሳ የሚያደርጉት ቅስቀሳ ነው ። ስለ ቀኝ አክራሪዎች ጥናት የሚያካሂዱት ተመራማሪው ሃዮ ፉንከ ከጀርመን ውህደት በኋላ እንደ ሰደድ እሳት ተስፋፋቶ የነበረውን በውጭ ዜጎች ላይ የተፈፀመ እስከ ሞት የሚያደርስ ጥቃት ለማስቀረት ተችሏል ይላሉ ። እጎአ በ1990 ዎቹ መጀመሪያ በቀኝ አክራሪዎች በተፈፀመው ጥቃት ብቻ 27 ሰዎች ተገድለዋል ። ፉንከ እንደሚሉት አሁንም ችግሩ አልተወገደም።
« እጎአ በ1990 ዎቹ መግቢያ ላይ እንደታየው የውጭ ዜጎችን አያሳየን ብሎ ለማጥፋት የታለመበት ዓይነት እርምጃ የለም ። ሆኖም በስደተኞች መኖሪያዎች ላይ የሚሰነዘር ጠብ ጫሪነትና ና ጥቃት በተፋጠነ ሁኔታ እየጨመረ ነው ። ይህም ቢሆን እስካሁን ልንወጣው ያልቻልን ተግዳሮት ነው ። »

Symbolfoto für Rechtextremismus
ምስል picture-alliance/dpa
Günter Burkhardt
ጉንተር ቡርክሃርትምስል picture-alliance/dpa


በርሳቸው አስተያየት ይህን መሰሉ ችግር ወደፊትም እየተባባሰ ሊቀጥል ይችላል
«ትልቁ አደጋ እሳት በመለኮስ በሚነሳው ተዛማች ቃጠሎ ሳቢያ የሚቆስሉና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከአሁኑ በበለጠ ሊጨምር መቻሉ ነው ። »
በ2013 ቀኝ አክራሪዎች በግልፅ ተገን ጠያቂዎችን ተቃውመው መነሳታቸውን የጀርመን መንግሥት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፓመላ ሙለር ኒስ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል ። መንግሥት ፣አሁን የተመዘገበው በስደተኞች ላይ የሚፈፀም የጥቃት መጠን እንዳሳሰበው ሳይገልፅ አላለፈም ። ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ 2013 ጀርመን የገቡት ስደተኞች ቁጥር ከጎርጎሮሳውያኑ 1999 ወዲህ እጅግ ከፍተኛው ነው ። ሃገሪቱ በ 2013 ወደ ጀርመን የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር 127 ሺህ ሲሆን የመጡትም ከሶሪያ ከአፍጋኒስታንና ከሌሎችም ጦርነት ከሚካሄድባቸው አደገኛ አካባቢዎች ነው ። ስደተኞቹም በተለያዩ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ወደ መኖሪያነት በተቀየሩ የቀድሞ ትምህርት ቤቶችና ወታደራዊ ጦር ሰፈሮች ውስጥ ነው የተጠለሉት ። መጠለያዎቹ የሚገኙባቸው የአንዳንድ ከተሞች ነዋሪዎች ትኩረት እንደተነፈጋቸው መቁጠራቸውን ቀኝ አክራሪዎች እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም በየአካባቢው ስደተኞቹ መጠለላቸውን እንዲቃወሙ ይገፋፋሉ ። ይህን መሰሉ ተቃውሞ በርሊን ውስጥ ከወራት በፊት ሄለርስዶርፍ በተባለው አካባቢ ተካሂዷል ። ተባብሶ በቀጠለ በዚሁ ተቃውሞ ሰበብ ስደተኞች ወደ መጠለያቸው ያለ ፖሊስ ጥበቃ ወደ መጠለያቸው መግባት አይችሉም ነበር ። ፉንከ እንደሚሉት ከጀመርመናውያን ገሚሱ ጀርመን በጣም ብዙ የውጭ ዜጎች የሚኖሩባት ሃገር ናት ባይ ናቸው ። ይህን ደግሞ ተመራማሪው ለውጭ ዜጎች ያላቸው ፍርሃት አድርገው ነው የተረጎሙት

እስካሁን ልንወጣው ያልቻልን ተግዳሮት ነው ። »

« ግማሽ ያህል የጀርመን ህዝብ የውጭ ዜጎች በዙብን ሲል ያማርራል ። ይህም ማለት በውጭ ዜጎች ላይ ያለው ስጋት የተዛመተ ነው ማለት ነው »
ለስደተኞች መብት መጠበቅ የሚታገለው የፕሮ አዙሉ ቡርክሃርት ለዚህ ምክንያት የሚሉት ጀርመን ውስጥ ቀኝ አክራሪዎች የሚያካሂዱትን ፀረ የውጭ ዜጎች ፕሮፓጋንዳ ነው ። ተበርሳቸው አስተያየት ይህን የመታገል ሃላፊነቱ ፖለቲከኞች ላይ ነው የሚወድቀው ። ከዚሁ ጋርም ለጥቃት የሚያጋልጣቸውን የመኖሪያ አካባቢዎቻቸውን መለወጥም ያስፈልጋል ይላሉ ።
«ስደተኞቹ ለቀኝ አክራሪዎች ጥቃት እንዳይጋለጡ በትላልቅ የማቆያ ስፍራዎች ሳይሆን ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ ማድረግ ይገባል ። ከዚህ ሌላ የውህደት መርሃ ግብር ያስፈልጋል ። ህብረተሰቡ ስደተኞቹ እንደ ማንኛውም ሰው ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ የሚችሉ መሆናቸውን የሚረዳበት ሰርተው ራሳቸውን የሚችሉበት ፣ በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ፣ መርሃ ግብር መቅረፅ ያስፈልጋል ። »
የውህደት መርሃ ግብሩ በቡክሃርት አስተያየት በሌላ መልኩም መከናወን ይኖርበታል ።
« ተቀራርቦ ለመኖር የሚያስችለውን ፅንሰ ሃሳብ መቀበል ያስፈልገናል ። ይህንንም ለማከናወን በነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ወገኖች የሚያቀርቧቸውን ጠቃሚ ሃሳቦች መደገፍ ይጠበቅብናል ። እየተባባሰ በመሄድ ላይ ያለው የቀኝ አክራሪዎች የኃይል እርምጃ ብቻ ሳይሆን ተገን ለሚጠይቁ ሰዎች በሚያስገርም ሁኔታ እየጨመረ የመጣ የድጋፍ ንቅናቄም አለ ። »
በጀርመን ዘረኝነትና ያለመቻቻል ስሜት እየተባባሰ መሄድ በአውሮፓ ምክር ቤት ፀረ ዘረኝነት ኮሚሽን ሳይቀር ዘንድሮ ማሳሰቢያ የተሰጠበት ጉዳይ ነው ። መንግሥት በዚህ ረገድ ከተወቀሰችባቸው መካከል በተለይ ወንጀለኞችን በመያዝና ተከታትሎም በአጥፊው ላይ ተገቢው ቅጣት ባለመስጠት ረገድ አሳይቷል የተባለው ድክመት ነው ።

Berliner Rechtsextremismus-Forscher Hajo Funke
ሃዮ ፉንክምስል picture-alliance/dpa

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ