1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀዘቀዘዉ የአሜሪካ -ሳዉዲ ግንኙነት

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 13 2008

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ለሥራ ጉብኝት ስዑድ አረቢያ ገብተዋል። ኦባማ በዚህ ጉብኝታቸዉ ሪያድ በምታስተናግደዉ ስድስት የፋርስ ባህረ ሰላጤዉን ሃገራት ያካተተ በአካባቢዉ ፀጥታ እና በፅንፈኛ ቡድኖች ላይ ስለሚያካሂዱት ዘመቻ በሚነጋገሩበት ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል።

https://p.dw.com/p/1IaUX
Saudi-Arabien König Salman empängt Barack Obama
ምስል Reuters/K. Lamarque

[No title]

ምንም እንኳን ሳዉዲ በመካከለኛዉ ምሥራቅ ከአሜሪካን ጋር ጥብቅ ተጓዳኝ አረብ ሀገር ብትሆንም ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ የሁለቱ ወገኖች ግንኙነት እየቀዘቀዘ መሄዱ ይነገራል። ለመቃቃራቸዉ የኢራን ጉዳይ መንስኤ እንደሆነ ነዉ የሚነገረዉ።

ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ተበሳጭተዋል። ይህንንም ለፖለቲካ ወዳጃቸዉ ለአዉስትራሊያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ማልኮም ተርንቡል ይነግራሉ። ያካፈሏቸዉ ምሥጢር በንጉሥ የምትተዳደረዉ ስዑድ አረቢያ እና ሌሎች የባህረ ሰላጤዉ አረብ ሃገራት የሚከተሉትን ጥብቅ የኢስላም አስተምህሮ እንደነኢንዶኔዢያ ባሉ ሃገራትም ለማስረጽ እንደሚሞክሩ ነዉ። ተርንቡል «ሳዉዲዎች ግን ወዳጆቻችሁ አይደሉም እንዴ?» በማለት ጠየቁ። የኦባማ ምላሽ« ዉስብስብ ነዉ» የሚል ነዉ። የአሜሪካዉ ጋዜጣ «ዘ አትላንቲክ» ቀንጭቦ ለአደባባይ ያበቃት ይህች መጠነኛ ታሪክ፤ የሳዉዲ እና የአሜሪካ ግንኙነት የቀድሞ ሙቀትና ጥብቀቱን እንዳጣ ያመለክታል። ለበርካታ አስርት ዓመታትም በሁለቱ ሃገራት መካከል በዝምታ ዉስጥ የነበረዉ የመግባባት መንፈስም አክትሞ ባለመተማመን እና ቁጥብነት ተተክቷል እየተባለ ነዉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2001 መስከረም 11 ቀን ኒዉዮርክ እና ዋሽንግተን ላይ በደረሰዉ የሽብር ጥቃት ከተሳተፉት 19 አሸባሪዎች፤ 15ቱ የሳዉዲ ዜጎች ነበሩ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም የሳዉዲ መንግሥት ሃይማኖት የሆነዉ ዋሀቢዝምን ዋሽንግተን ቢያንስ በጥርጣሬ ትመለከታለች። እንዲያም ሆኖ ይህን በተመለከተ የወቅቱ የሳዉዲ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከወዳጃቸዉ ከአሜሪካን በግልጽ የቀረበ ክስም ሆነ ዝርዝር ነገር እንደሌለ እና ያንንም እንደማያዉቁ ገልጸዉ ነበር። በሌላ በኩል ሳዉዲ በበኩሏ ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራን ጋር የጀመረችዉን መቀራረብ ከመቃወሟ ሌላ የሶሪያን ጉዳያ ለመፍታት የምትሄድበት መንገድ አላስደሰታትም። የጀርመን የዉጭ ግንኙነት ምርምር ተቋም የመካከለኛዉ ምሥራቅ ፖለቲካ ተንታኝ ሴባስቲያን ዞንስ የሁለቱ ወዳጅ ሃገራት ትስስር ለመላላቱ የሚከተሉትን በመንስኤነት ይዘረዝራሉ።

Saudi-Arabien Barack Obama Gipfelkonferenz des Golf-Kooperationsrates in Riad
ምስል Reuters/K. Lamarque

« ስዑድ አረቢያ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የነበራትን ግንኙነት ያላላዉ፤ በተለይ ከዋነኛ ተቀናቃኟ ከኢራን ጋር በኒኩሊየር መርሃግብሯ ላይ የተደረሰዉ ስምምነት ነዉ። በዚያም ላይ ዩናይትድ ስቴትስ ሳዉዲ የመን ዉስጥ የምታካሂደዉን ወታደራዊ ዘመቻ እምብዛም አለመደገፏም ነዉ። በተጨማሪም በሶርያ ጉዳይ ተመሳሳይ ፍላጎት የላቸዉም። ስዑድ አረቢያ በሽር አል አሰድ ከስልጣን እንዲወዱ ትፈልጋለች፣ ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ እስካሁን በዚህ ጉዳይ ቁጥብነትን መርጣለች። በዚያም ላይ በንጉሥ ሳልማን የምትመራዉ ሳዉዲ አሜሪካን እንደበፊቱ በሀገሯ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራት ትሻለች። ዩናይትድ ስቴትስ በፋንታዋ በነዳጅ ዘይቱ ዘርፍ የሳዉዲ ተፅዕኖ ገበያዉን ምን ያህል እንዳዛባዉ ባለመዘንጋቷ በራሷ ምድር የጀመረችዉ የነዳጅ እና ጋዝ ፍለጋ ሂደትም አንድ ነገር ነዉ።»

Saudi-Arabien Barack Obama Gipfelkonferenz des Golf-Kooperationsrates in Riad
ምስል Reuters/K. Lamarque

በዚህና በተያያዥ ምክንያቶች ሁለቱ ሃገራት ሆድና ጀርባ መሆናቸዉ ቢነገርም ስድስት የባህረ ሰላጤዉ ሃገራት ማኅበረሰብ የትብብር ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ለመገኘት ፕሬዝደንት ኦባማ ትናንት ሪያድ ገብተዋል። ከሳዉዲ በተጨማሪ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፤ ቀጠር፣ ኩየት፣ ኦማን እና ባህሬን በሚገኝበት በዚህ ጉባኤ ዋሽንግተን በተለይ የአካባቢዉ መረጋጋት ላይ በትኩረት መወያየት እንደምትሻ አመልክታለች።

«እራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለዉ ቡድን ላይ የተከፈተዉ ጦርነት አንዱና ሁሉቱም የሚፈልጉት እና የሚከታተሉት ጉዳይ ነዉ። ቤተ መንግሥቱ IS የፀጥታ ስጋት ብቻ ሳይሆን የሃይማኖታዊ ፍልስፍናም ፈተና መሆኑን በይፋ አሳዉቋል። ባለፉት ወራት በሳዉዲ ግዛት ዉስጥ በIS ተዋጊዎች ጠንከር ያለ ጥቃት ደርሷል። ይህ ሳዑድ አረቢያን በጣም ያሳስባታል። ያም ቢሆን ግን እስካሁን ለቡድን ከለጋሽ ድርጅቶችና ተቋማት የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ ማስቆም አልቻለችም። ይህ የተጀመረዉ ከመስከረም 11ዱ ጥቃት ወዲህ ቢሆንም አሁንም ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል። እንዲያም ሆኖ ግን የIS ጉዳይ በአሁኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ እና ሳዉዲን አንድ የሚያደርግ ነዉ። በመሠረታዊነትም የአካባቢዉ መረጋጋት ሁለቱ ተጓዳኞች የሚፈልጉት ጉዳይ ነዉ።»

ኦባማ ከአረብ ሃገራቱ ጋር በሚያደርጉት ዉይይት ከፍተኛ ትችት የሚቀርብበትን የሰብዓዊ መብቶች አያያዛቸዉን ወደጎን ብለዉ በወቅቱ አሳሳቢ ጉዳያቸዉ ማለትም እራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለዉ ቡድን ላይ የተጠናከረ ዘመቻ ማካሄድ የሚለዉ አጀንዳቸዉ ላይ ሳያተኩሩ አይቀርም በሚል ከጉዟቸዉ አስቀድሞ ነዉ ትችት ሲሰነዘርባቸዉ የነበረዉ። በፕሬዝደንትነት ስልጣናቸዉ የመጨረሻ ሊሆን እንደሚችል በሚገለጸዉ የመካከለኛዉ ምሥራቅ የአሜሪካን አጋር ሳዉዲ ጉብኝታቸዉም ከፋርስ ባህረ ሰላጤዉ ሃገራት ጋር በሳዉዲዉ ንጉሥ ቤተ መንግሥት የሚያካሂዱት ስብሰባም ወሳኝ እንደሆነ ነዉ የሚገለጸዉ። ሴባስቲያን ዞንስ አጋጣሚዉ ለሳዉዲም ጠቃሚ ሚና ይጫወታል ባይ ናቸዉ።

Saudi-Arabien Barack Obama Gipfelkonferenz des Golf-Kooperationsrates in Riad
ምስል Reuters/K. Lamarque

«በመጀመሪያ ደረጃ ስዑድ አረቢያ በፋርስ ባህረ ሰላጤዉ አካባቢ ያላትን የበላይነት ማረጋገጫ ነዉ። በንጉሥ ምትተዳደረዉ ሀገር ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ከኢራን በኩል ቀጥታ ስጋት ተፈጥሮባታል፤ በተለይም ወደ ኢራቅ እና ባህሪን ተፅዕኖዋ መስፋፋቱ በዚያም ላይ ወደየመን መሻገሩ ያሳስባታል። በዚያም ላይ ኢራንን በሚመለከት ከዩናይትድ ስቴትስ በኩል በቂ ከለላ አላገኘሁም የሚል ስጋት አላት።»

ይህን እና ተያያዥ የሳዉዲን ስጋት ቅሬታዎች ለማስታመምም ኦባማ ሪያድ ዉስጥ ለ24 ሰዓታት በሚያደርጉት ቆይታ ከንጉሥ ሳልማን ጋር በግል የብቻቸዉን ስብሰባ ያካሂዳሉ። ከኋይት ኃዉስ የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱትም ከባህረ ሰላጤዉ ሃገራት ጋር በሚካሄደዉ ስብሰባ የሚነሱት ነጥቦት የአካባቢዉን ፀጥታ እና ፅንፈኛ ቡድኖችን መዋጋት ላይ ቢያተኩርም ሳዉዲን ጨምሮ ሌሎቹ ተሰብሳቢ ሃገራት በስጋት የሚመለከቷት ኢራን ጉዳይም መነጋገሪያቸዉ ነዉ። በስብሰባዉ ላይ ከኦባማ በተጨማሪ የመከላከያ ሚኒስትሩ አሽ ካርተር፤ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆን ኬሪ፤ የአሜሪካን ብሔራዊ የፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ሱዛን ራይስ እና የCIA ዳይሬክተር ጆን ብሬነን ይገኛሉ።

ሸዋዬ ለገሠ/ከርስተን ክኒፕን

ነጋሽ መሐመድ