1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜና የዓለም ሰላም

ሰኞ፣ መጋቢት 16 2005

የጀርመኑ የግጭት ጉዳይ ጥናት ተቋም እንደቆጠረዉ ግን ዓለም ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ እስከ ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት ድረስ ሰወስት መቶ ዘጠና ስድስት ጦርነቶችን ወይም ግጭቶችን አስተናግዳለች።ሚሊዮኖችን ተገድለዉባታል።ሚሊዮነ ሚሊዮናት ቆስለዋል፥ ተሰደዋል ወይም ተፈናቅለዋል። ዛሬም----

https://p.dw.com/p/1843F
A U.N. observer walks towards soldiers at a Syrian army checkpoint during a field visit in Douma city, near Damascus May 5, 2012, one of the locations where there are protests against the regime of Syrian President Bashar al-Assad. REUTERS/Khaled al- Hariri (SYRIA - Tags: POLITICS CIVIL UNREST MILITARY)
የተመድ ሰላም አሥከባሪምስል Reuters


የሶቬት ሕብረት ግዙፍ ጦር ሽንፈት፣ የምዕራብ ጠላቶችዋ ድል ካቡል ላይ ከተረጋገጠ ዘንድሮ የካቲት ሐያ-አራት አመቱን ደፈነ።ሰፊዋ ልዕለ ሐያሊቱ ሐገር መፈረካከስ፣ ኮሚንስታዊ ሥርዓትዋ ከምሥራቅ አጫፋሪዎቹ ጋር መናድ ከጀመረ-ደግሞ ዘንድሮ መጋቢት ሃያ-ሰወስት ዓመቱ። የኮሚንስቶቹ ዉድቀት፥ ኑክሌር ያማዘዘዉ፥ ከኮሪያ ልሳነ-ምድር እስከ ዛምቤዚ ሸለቆ፣ ከቬትናም ደኖች እስከ አማዞን ጫካ የሚሊዮኖችን የፈጀዉ የቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜን ማብሰሩ፥ ለዓለም የሰላም፣ ዲሞራሲ ተስፋን መፈንጠቁ አላነጋገረም።ዛሬም የሰላም ብልፅግና ተስፋ መንቆቆሩ አልቀረም።ከኢራቅ እስከ አፍቃኒስታን፣ ከሶሪያ እስከ ማሊ፣ ከሶማሊያ እስከ ማዕከላዊ አፍሪቃ፣ ከኢራን እስከ ኮሪያ የነበረና ያለዉ ሐቅ የቃል ተስፋዉን ቅጭት ማርዳቱ እንጂ ሕቅታዉ።ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሑኝ ቆዩ።


የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሐገራት ዲፕሎማቶች ሕብረታቸዉ የተመሠረተበትን ሐምሳኛ ዓመት ለመዘከር ልዩ ትኩረት ከሰጡት አንዱ ሥለ አፍሪቃ ግጭትና ጦርነቶች መነሻና መፍትሔያቸዉ አዲስ አበባ ላይ መምከር ነበር።

አፍሪቃዉያን ዲፕሎማቶች ከአዉሮጳ፥ አሜሪካ፥ ከእስያ አዎቻቸዉ ጋር ሆነዉ ግጭት ጦርነት ሥለሚወገድበት ሥልት አዲስ አበባ ላይ በመከሩ-ማግሥት ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፐብሊክ ነፃ የወጣችበትን ሐምሳ-ሰወስተኛ ዓመት ባዲስ መሪ፥ ባዲስ ሥርዓት ለማክበር፥ አዲስ ጦርነቷን አገባደደች።የሴሌካ አማፂያን ርዕሠ-ከተማ ባንጉይን ተቆጣጠሩ።ቅዳሜ።

«አማፂያኑ የርሠ-ከተማይቱን መንገዶች እየተቆጣጠሩ ነዉ።ሕዝቡ ሥጋት ላይ ነዉ።ዉሐና መብራት ተቋርጧል።የሕዝቡ ግን በጣም እየሠጋ ነዉ።»

አለ ጋዜጠኛዉ ትናንት።ጥር የተሰማዉ የሰላም ቃል፥ ዉል ተስፋዉ እንደገና በጠመንጃ አፈሙዝ ጩኸት ተደፈለቀ።ሥጋት፥ ጭንቀት፥ ሞት ሥደት-የትንሺቱ አፍሪቃዊት ሐገር የግማሽ ምዕተ-ዓመት ዑደት።ነሐሴ 1960 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ለተላቀቀችዉ ትንሺቱ አፍሪቃዊት ሐገር ሰላም እየተነገረላት፥ የሰላም ዉል እየተፈረመላት፥ በአምጋነኖች ጭቆና፥ በቅኝ ገዢዎች፥ በኮሚንስት ካፒታሊስቶች ጣልቃ ገብነት፥ በርስ በርስ ጦርነት መንገጫገጭ፥ ያሁኑ አዲሷ አይደለም።

ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፥ ማሊ፥ናጄሪያ፥ ሊቢያ፥ ሶማሊያ፥ሱዳን፥ ኢትዮጵያ፥ ኤርትራ፥ሌላዉም አፍሪቃ ድሮዉ እንዲያ ነበር።ዘንድሮም እንዲያ ነዉ።ዛሬ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊ የተሰኘችዉ ሐገር እንደ ነፃ አፍሪቃዊት ሐገር እነ-ኢትዮጵያን ሥትቀላቀል የኢትዮጵያ የጦር ጄኔራሎች የንጉሠ-ነገሥት ሐይለ ሥላሴን ዙፋናዊ አገዛዝ በይል ለማስወገድ ያሴሩ ነበር።

አፄ ሐይለ ሥላሴ መፈንቅለ መንግሥት የሞከሩ ታማኝ የጦር መኮንኖቻቸዉንና ተባባሪዎቻቸዉን አስለቅመዉ፣ አስገድለዉ፣ ወይም አሳስረዉ ሲያጠናቅቁ፣ ሞቅዲሾ ላይ የነፃ ሐገር አዲስ ባንዲራ ይዉልበለብ ያዘ።ንጉሱ ኢትዮጵያና ኤርትራ የተሳሰሩበትን ፌደራላዊ ሥርዓት አፍርሰዉ ኤርትራ የዘዉዳዊ ግዛታቸዉ አስራ-አራተኛ ክፍለ-ግዛት መሆኗን ሲያዉጁ፣ ፕሬዝዳንት አደን አብዱላሒ ዑስማን ዳዓርና ጠቅላይ ሚንስትር አብድረሽድ ዓሊ ሸርማርኬ ያዘመቱት የአዲሲቱ ነፃ ሐገር አዲስ ጦር ምሥራ ኢትዮጵያን ይተነኳኩስ ገባ።



ንጉሱ በመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ሰበብ የዉስጥ ተቃዋሚዎቻቸዉን ሠጥ-ለጥ አድርገዉ የሚገዙበትን ሥልት አጠናክረዉ፣ ጦራቸዉ ሰሜን ላይ ብረት ካነሱ የኤርትራ ተወላጆች፣ ምሥራቅ ጠረፍ ከሶማሌዎች ጋር ሲዋጋ፥ ለአፍሪቃ አንድነት፥ ለነፃነት፥ ሠላምና ብልፅግናዋ ይጥራል የተባለዉን የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት መሥራች ጉባኤን ያስተናግዱ ነበር።ግንቦት 1963።

ጦርነት እና ሠላም።ጭቆናና ነፃነት።አፍሪቃ።

አረብ፥ ዓለምን በግብፅ መስኮት፥-የያኔዉ የግብፅ መሪ ኮሎኔል ገማል አብድናስር አፄ ሐይለ ሥላሴ በሚያስተናግዱት ጉባኤ ላይ ለመካፈል ወደ አዲስ አበባ ከመዉረዳቸዉ በፊት በሰወስት ትላልቅ ጉዳዮች ላይ መወሰን ነበረባቸዉ።

የፖለቲካ ፍልስፍናቸዉን የሚጋሯቸዉ የሶሪያ፣ የኢራቅ፣ የሱዳንና የየመን የጦር መኮንኖች የየሐገራቸዉን ገዢዎች አስወግደዉ ሥልጣን የሚይዙበት ሥልት የደረሰበትን ደረጃ መገምገም-አንድ። የመን ያዘመቱት ጦር በሳዑዲ አረቢያ ከሚደገፉት የሐገሪቱ ንጉሳዊ ሐላይት ጋር የገጠመዉን ዉጊያ እንዲቀጥል ማዘዝ-ሁለት።በአስራ-አምስት ዓመት ለሰወስተኛ ጊዜ ከእስራኤል ጠላቱ ጋር ለመዋጋት የተፋጠጠዉን ጦራቸዉን ብቃት ዝግጅት መቃኘት-ሰወስት ምናልባትም ዋናዉ ነበር።

በሐምሳኛ ዓመቱ ዘንድሮ የግብፅን አጎራባቾች እስራኤልን፥ የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድርንና የዮርዳኖስን የጎበኙት የብቸኛይቱ ልዕለ-ሐያል ሐገር ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ እስራኤል ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ እንደነበሩት የሐገራቸዉ መሪዎች ሁሉ ለእስራኤል የማይናወጥ ድጋፋቸዉን እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።የዚያኑ ያሕል ከሥልሳ-ዘመን በላይ ያስቆጠረዉ የእስራኤል ፍልስጤሞች ግጭትን በሰላም ለማስወገድ እንደሚጥሩ አስታዉቀዋል።ደግሞ በተቃራኒዉ የደማስቆ ገዢዎችን አዉግዘዋል።

«አሠድ እስከድ ሚሳዬልን ጨምሮ በሁሉም ዓይነት ሊባል በሚችል መደበኛ ጦር መሳሪያ የሶሪያ ሕዝብን በመዉጋት ለመግዛት ያደረጉት ሙከራ ሕጋዊነትን አጥቷል።አሁን ደግሞ በሶሪያ ሕዝብ ላይ ኬሚካዊ የጦር መሳሪያን ለመተኮስ መሞከር ከፍተኛ እና አሳዛኝ ጥፋት ነዉ-የሆን።»

ቴሕራኖችንም አስጠንቅቀዋል።

«ሁሉም አማራጮች ጠረጴዛ ላይ ናቸዉ።ኢራን የዓለምን እጅግ መጥፎ የጦር መሳሪያ እንዳትታጠቅ ለማገድ አስፈላጊዉን ሁሉ እናደርጋለን።»

የአሜሪካ ፕሬዝዳት የባራክ ኦባማ የሠላም ቃል፥ የዉጊያ ዛቻ ማስጠንቀቂያ ሲንቆረቆር ኢራቆች በአሜሪካኖች የተወረሩበትን አስረኛ ዓመት፥ በአሜሪካና በተባባሪዎችዋ፥ በቦምብ፥ ሚሳዬል፥ በአሸባሪዎች ቦምብ ያለቁባቸዉን ወገኖቻቸዉን ይቆጥሩ ነበር።ከመቶ ሐምሳ ሺሕ በላይ።

አረብ፥ ፋርስ፥ ዓለም። ሠላምና ጦርነት።

ፕሬዝዳት ጆን ኤፍ ኬኔዲ የጋና አቻቸዉን አሳግዬፎ ዶክተር ክዋሚ ንክሩማን ዋሽግተን ድረስ የጋበዙት፣ንኩሩማ የአፍሪቃ ሶሻሊዝም የሚል ፍልስፍናቸዉ ከሞስኮዎች ጉያ እንዳይወሽቃቸዉ ለመመከላከል ነበር።ንኩሩማ መጋቢት 1961 ዋሽግተንን ጎብኝተዉ እንደተመለሱ ግን የእሳቸዉን ፍልስፍና የሚቀናቀን ፖለቲከኛ እንቅስቃሴ የሚታገድበትን ሥልት ቀየሱ።

የአፍሪቃ ሶሻሊዝም መርሐቸዉን የሚያሰራጭና የሚያስተምር ተቋም ከፍተዉ የመንግሥት ሠራተኛ እና የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሁሉ የፍልስፍናዉን ይዘት እንዲማር ደነገጉ።ንኩሩማ አዲስ አበባ የሔዱት ደግሞ ሶቬየት ሕብረት ለታላቅ ኮሚንስታዊ ወዳጅዋ የምትጠዉን የሌኒን የሰላም ኒሻን በተሸለሙ ማግሥት ነበር።

እና አፄ ሐይለ ሥላሴ፥ ገማል አብድናስር፥ ክዋሚ ንክሩማ የመሯቸዉ የአፍሪቃ መሪዎች አዲስ አበባ ላይ ለአፍሪቃዉያን ነፃነት፥ ሠላምና ብልፅግና የሚጥር ማሕበር አቋቋሙ ።ግንቦት 1963


ከሐይለ ሥላሴ-እስከ መለስ ዜናዊ፥ ከናስር እስከ ሆስኒ ሙባራክ፥ ከንኩሩማ እስከ ጄሪ ሮሊንግስ የተፈራረቁት የአፍሪቃ መሪዎች በየአዳራሹ፥ በየአደባባዩ ሠላም፥ ነፃነት፥ ፍትሕ እኩልነት ያላሉበት ዘመን የለም።ጦርነት ሳይዋጉ፥ ሕዝብ ሳያፍኑ የገዘቡበት ጊዜም አይታወቅም።

የካቲት አስራ-አምስት 1989። አፍቃኒስታን ዉስጥ ለዘጠኝ ዓመታት የተዋጋዉ የሶቬት ሕብረት ጦር የመጨረሻ አዛዥ ኮሎኔል ጄኔራል ቦሪስ ግሮሞቭ እንደ መጨረሻዉ የሶቬት ሕብረት ወታደር ካቡልን ለቅቀዉ ወጡ።


የጄኔራሉ ሥንብት፥ የሶቬት ሕብረት ሽንፈት፥ የምዕራብ ጠላቶችዋ ድልን ያረጋገጠ፥ ለአፍቃኒስታኖች ሠላም ጅምርነቱ ያስነገረ ነበር። በምዕራቡ ዓለምና በደጋፊዎቻቸዉ ተወድሶ፥ ካቡል፥ ኢስላማድ ላይ ብዙ ተጨፍሮለት ነበር።ዘንድሮ ሃያ-አራት ዓመቱ።

ተዋጊ፥ አዋጊዎቹ፥ አላማ ፍላጎታቸዉ በርግጥ ተለዋዉጧል።አፍቃኒስታን ግን ያኔም፥ ከያኔ እስከ ዛሬም፥ ዛሬም ከጦርነት፥ጥፋት፥ ሕዝቧ ከእልቂት ፍጅት አልተላቀቀም።

1990 መጋቢት ማብቂያ። የዎርሶ፥ የቡዳፔስት፥ የበርሊን ኮሚንስታዊ መንግሥታት አንድም ተጠራርገዋል አለያም የመጨረሻ እስትንፋሳቸዉ እየለበቃቸዉ ነዉ።የበርሊን ግንብ ተደርምሷል።ሚኻኤል ጎርቫቾቭ ኮሚንስታዊዉን ሥርዓት አጣዳፈዉ ለመቅበር የሚረዳቸዉን አንድ የመረጫ ጠንካራ እርምጃ ጨመሩበት።የሶቬት ሕብረት ሪፐብሎኮች በኮሚንታዊዉ ሕገ-መንግሥት በተደነገገዉ መሠረት በሕዝበ ዉሳኔ የየራሳቸዉን ነፃነት ማወጅ የሚችሉበትን ሕግ አስፀደቁ።

ሶቬት ሕብረት ትፈረካከስ ያዘች።ኮሚንስታዊዉ ሥርዓት አለቀ-ደቀቀ።የቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ፥ የዓለም ሠላም፥ የሕዝቦች ልዕልና፥ የፍትሕ እኩልነት መሠረት ተጣለ።በትክክለኛዉ አላለፅ ትክክለኛዉ መሠረት ተጣለ ተባለ።ከዎርሶ፥ እስከ አዲስ አበባ ኮሚንስታዊ ምልክቶችን እየሰባበረ ያልጣለ፥ ያላቃጠለ፥ ያልቦረቀ-ያልጨፈረ አልነበረም።ዓለም ግን ሰላም በርግጥ ናት? ከሳርየቮ እስከ ኪጋሊ፥ ከባድሜ፥ እስከ ሞቃዲሾ፥ ከባግዳድ እስከ ካቡል፥ ከትሪፖሊ እስከ ባማኮ፥ ከጋዛ እስከ ቤይሩት፥ ከደማስቆ እስከ ጁባ---ከምሥራቅ ቲሞር እስከ ፊሊፒንስ፥ ከፍሪታዉን እስከ ቦጎታ----፧ ጊዜ ካለዎት ይቁጥሩ።

የጀርመኑ የግጭት ጉዳይ ጥናት ተቋም እንደቆጠረዉ ግን ዓለም ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ እስከ ሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት ድረስ ሰወስት መቶ ዘጠና ስድስት ጦርነቶችን ወይም ግጭቶችን አስተናግዳለች።ሚሊዮኖችን ተገድለዉባታል።ሚሊዮነ ሚሊዮናት ቆስለዋል፥ ተሰደዋል ወይም ተፈናቅለዋል። ዛሬም ማሊ፥ ሶማሊያ፥ ሶሪያ፥ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፥ ኢራቅ፥ አንድም በጦርነት፥ አለያም በግጭት ይነዳሉ።በጀርመኑ ተቋም ጥናት መሠረት በድፍን ዓለም አስራ-ስምንት ሙሉ ጦርነቶች፥ ሃያ አምስት መለሰተኛ ጦርነቶች፥ አርባ ሰወስት ግጭቶች ይደረጋሉ።የኮሪያ ልሳነ ምድር፥ መካከለኛዉ ምሥራቅ፥ ፋርስ ለሌላ ጦርነት ይዛት ይፎከርባቸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠላም ለማስከበር በዓመት ሰባት ነጥብ ሁለት ሰወስት ቢሊዮን ዶላር ይከሰክሳል።ሠላም ግን የለም።ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ
















Afghan firefighters wash debris off the road at the site of a suicide attack in Kabul, February 27, 2013. At least seven Afghan National Army personnel were wounded in the attack, police officials said. REUTERS/Omar Sobhani (AFGHANISTAN - Tags: CIVIL UNREST DISASTER)
አፍቃኒስታን ድሮም-ዘንድሮም እልቂትምስል Reuters
Residents gather at the site of a car bomb attack in the AL-Mashtal district in Baghdad March 19, 2013. A series of coordinated car bombs and blasts hit Shi'ite districts across Baghdad and south of the Iraqi capital on Tuesday, killing at least 25 people on the tenth anniversary of the U.S.-led invasion. REUTERS/Mohammed Ameen (IRAQ - Tags: CONFLICT CIVIL UNREST)
ኢራቅ የጥፋት አብነትምስል Reuters
Congolese flee the eastern Congolese town of Sake , 27kms west of Goma, Friday Nov. 23 2012. Thousands fled the M23 controlled town as platoons of rebels were making their way across the hills from Sake to the next major town of Minova, where the Congolese army was believed to be regrouping. The militants seeking to overthrow the government vowed to push forward despite mounting international pressure.(Foto:Jerome Delay/AP/dapd)
ኮንጎ-ከሞት ለማምለጥምስል AP
Haitians react to the recent flood in Vertieres, suburb of Cap-Haitian (274 Km from Port-au-Prince) November 11, 2012. Flood waters inundated impoverished areas of Cap Haitien, Haiti's second largest city, killing as many as 16 people, including three children, city officials said November 9, 2012. AFP PHOTO / THONY BELIZAIRE (Photo credit should read THONY BELIZAIRE/AFP/Getty Images)
ሔይቲ ስዉም-ተፍጥሮም ነዉ የጨከነባትምስል AFP/Getty Images